ዘመን፡- በየአመቱ ህዳር ሃያ ዘጠኝ ቀን እየተከበረ የሚገኘው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ፋይዳ ምንድነው ʔ
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ህዳር ሃያ ዘጠኝ የሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ፋይዳዎች አጠቃላይ የሆኑ ነገሮችን በመዘርዘር መግለፅ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ ጥናቱ በየአመቱ የሚከበረው ህዳር ሃያ ዘጠኝ ቀን ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ምንድነው፣ ቀኑ በመከበሩ እስካሁን የተገኙት ፋይዳዎች ምንድን ናቸው፣ቀኑ በመከበሩ ምን ተገኘ፣ተግዳሮቶችስ ምንድን ናቸው፣በቀጣይ በምን መንገድ ማስኬድ አለብን፣ምን ቢሆን ይሻላል የሚለውን የመፍትሄ ሀሳብ ለመጠቆም የተደረገ ነው፡፡ ይህ ሳይንሳዊ ጥናት የአስራ አንድ አመታት የተከበሩ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አከባበሮችን የዳሰሰ፣ ሁሉንም ክልሎች፣የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ጥናት ነው፡፡ የዳሰሳ ጥናቱ የቀኑን መከበር ፋይዳዎች በዝርዝር ለይቷል፡፡
ዘመን፡- በጥናት የተለዩት የበአሉ ፋይዳዎች ምንድን ናቸውʔ
ወይዘሮ ኬሪያ፡- የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል አከባበር ከአመት አመት ከስፋት አንፃር እየጨመረ መምጣቱን ሁላችንም እናውቀዋለን፡፡ በዚህ ረገድ ያስገኛቸው ፋይዳዎች አሉ፡፡ አንደኛ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከርና እርስበርስ መተማመንን እንዲፈጠር በማድረግ ዙሪያ ላይ የተሻለ ስራ እንዲሰራ ማድረጉን የጥናቱ ግኝት ያሳያል፡፡ በእርግጥ ይህ ግኝት አሁን በአገራችን እየታዩ ያሉ ችግሮችን በማየት ትክክል እንዳልሆነ የሚያስቡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የተደረገው ጥናት በ2009 አመተ ምህረት አካባቢ በመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ ሚዛኑን ሊያዛባው ይችላል፡፡ በወቅቱ ህዝቡ የሰጠውን አስተያየት መሰረት ተደርጎ የተሰራ ጥናት ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ግጭቶች ቢኖሩም ህዝብ ከህዝብ የሚደረግ ግጭት አይደለም፡፡ መሀል ላይ ሆኖ ህዝብ ከህዝብ እንዲጋጭ እያደረገ ያለ ሌላ አካል አለ፡፡ ህዝብ ለህዝብ ቢጋጭ ኖሮ እስካሁን እንደ አገር አንድ ሆነን አንቀጥልም ነበር፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ህዝብ ለህዝብ ትስስርን እንዲጠናከርና በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነበር፡፡
ከዚህ አንፃር ባይሰራ ኖሮ አገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ችግሮች ከፉ ይሆኑ ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የጥናቱ ግኝት ብዝሀነት በአግባቡ ካልተያዘ፣ በአግባቡ ካልተስተናገደ ለአንድነት የስጋት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ነገር ግን ብዝሀነት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በአግባቡ ከተያዘና ከተስተናገደ የበለጠ በውበትና በጥንካሬ የተመሰረተ አንድነት ሊመሰርት እንደሚችል የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በአል አሳይቶናል፡፡ ስለዚህ ብዝሀነታችን ለኢትዮጵያ አንድነታችን ስጋት እንዳልሆነ፣ በአግባቡ ከተሰራ በህዝቦች መካከል መልካም ግንኙነት ከተጠናከረ፣ ትስስር ከተፈጠረ ይህም ስር እንዲሰድ ከተደረገ ብዝሀነት ውበት፣ብዝሀነት የኢትዮጵያ ጥንካሬ መሰረት መሆን እንደሚችል በአሉ በመከበሩ አሳይቶናል፡፡
ምንአልባት ይሄ አሁን ካለው ሁኔታ ምን ያሳየናል ስንል ተግዳሮትም እንደነበረው አሳይቶናል፡፡ ልክ አሁን እንደተፈጠረው ችግር እንዳይፈጠር በይበልጥ መስራት እንደነበረብን የሚያሳይ ነገር አለ፡፡ ብዝሀነታችን ውበታችን እንደሆነ ጎልቶ እንዲወጣ የበዓሉ መከበር ምክንያት ሆኖ አሳይቶናል፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ሲከበር ስለ ህገ-መንግስትና ስለፌዴራል ስርዓታችን የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የስርፀት ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ በዚህ ረገድም ህገ-መንግስትን በተመለከተ በማህበረሰብ ዘንድ የንቃተ ህሊና ስራ ለመስራት ቀኑ ፋይዳው የጎላ ነበር፡፡ በዓሉን በማስመልከት በመላ ሀገሪቱ ከላይ እስከ ታች ባሉ መዋቅሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራቱ ጥልቀት፣ውጤት፣ አጥጋቢ ነው ባይባልም የቀኑ መከበር መሰል ስራዎች እንዲሰሩ መንስኤ ሆኗል፡፡ እንዲሁም ቀኑ መከበሩ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ከማጠናከር አንፃርም ፋይዳ ነበረው፡፡ የጋራ እሴቶቻችን ጎልብተው እንዲወጡ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ያሏቸውን ትውፊቶቻቸውን፣ ባህሎቻቸውን በአደባባይ በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ ሆኗል፡፡
ብሄር ብሄረሰቦች በማንነታቸው የሚያፍሩበት ሳይሆን በድፍረት የሚያሳዩበት ቀንም ሆኗል፡፡ እርስ በራሳቸው የሚተዋወቁበት መድረክ በመሆንም የአንዱን ባህል፣ ማንነት ሌላው እንዲያከብርና እንዲያውቅ ምቹ እድል ፈጥሯል፡፡ ህዝብ ለህዝብ ትስስር ስር እንዲሰድ ከዚያም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ በዚህ መነሻነት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል አሁንም የነበሩ ክፍተቶችን በማረም ሌሎች አዳዲስ ነገሮች በመጨመር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ከኢኮኖሚ አንፃርም የመሰረተ ልማት በመገንባት ትስስር እንዲፈጠር የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ሚናው የጎላ ነበር፡፡ ከልማት አንፃርም በበዓሉ ምክንያት የተለያዩ መንገዶች፣ የውሃ ፕሮጀክቶች፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች ተሰርተዋል፡፡ ይህ ደግሞ የህዝቡን የመልማት ፍላጎት ለማሟላት የሚደረገውን ጥረት ደግፏል ማለት ይቻላል፡፡ እንደ መልካም አስተዳደር፣ እንደ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የሚነሱ በመሆናቸው እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ በሚደረገው ጥረት በብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ምክንያት የተሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች የራሳቸውን ሚና ተወጥተዋል፡፡ በዓሉን የሚያስተናግደው ክልል ወይም አስተዳደር ከተማው እንዲታወቅ፣ እንዲያድግ፣በበዓሉ ምክንያት የሚሰሩ ስራዎችም የስራ እድል በመፍጠር፣ የንግድ ልውውጥም እንዲዳብር፣በማድረግ የራሱን ድርሻ ተጫውቷል፡፡ በበዓሉ ለመገኘት ወደ አገራችን የሚመጡ የውጭ ዜጎች መኖራቸውም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን እንዲጠናከር ያደርጋሉ፡፡ በአገር ገፅታ ግንባታም ፋይዳው የጎላ ነው፡፡ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው ጉዳዮች አጠንክረን ይዘን የምንሄዳቸው የቀኑ መከበር ፋይዳዎች ናቸው፡፡
ዘመን፡- ባለፉት አመታት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በየአመቱ ሲከበር ያጋጠሙ ተግዳሮቶች የዳሰሳ ጥናቱ ለይቷል ʔ
ወይዘሮ ኬሪያ፡- አዎ! የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ጠቅሶ የሚስተካከሉበትን መንገዶችንም ጠቁሟል፡፡ በመጀመሪያ በብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ላይ የሚጋበዙ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎችን የሚከውኑ /ጭፈራ፣ዘፈን፣አለባበስ…/ አካላት ከአመት አመት ሁሌም የሚከውኑት ተመሳሳይ ሰዎች መሆናቸው አንዱ ተግዳሮት ነው፡፡ ሁለተኛ በበዓሉ ዝግጅት ላይ የሚገኙ የባህል ቡድኖች የዳበረ እሴትን አጉልቶ በሚያወጣ መልኩ በማቅረብ ከታችኛው ህብረተሰብ ዘንድ ወርዶ ተግባራዊ በሚያደርገው መልኩ የሚከወን አልነበረም፡፡ በበዓሉ ላይ በየአመቱ የሚሳተፉ ትርኢት የሚያቀርቡ፣ከአገር ሽማግሌዎች ተወክለው የሚገኙ፣ ከአመራር አካላት የሚሳተፉ ሁሌም ተመሳሳይ ሰዎች በመሆናቸው ይህ ትክክል ባለመሆኑ ሊቀረፍ የሚገባ ችግር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሌላው በበዓሉ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላትን መርጦ መላክም ችግር ተስተውሏል፡፡ ወደ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ወርዶ የሁሉም ብሄር ብሄረሰብ የዳበረ ባህላቸውን፣ ትውፊታቸውን፣ ታሪካቸውን በመለየት ራሱ የባህሉ ባለቤት ለሌሎች የሚያሳይበትን መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ለበዓሉ ዝግጅት የሚደረገው በመጨረሻ ሰዓት መሆኑም ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡
የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል ቅድመ ዝግጅት ተደርጎበት፣በደንብ ተቀናጅቶ የሚከበር በዓል አይደለም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የበዓሉ አዘጋጅ ክልል ወይም አስተዳደር የተጠናከረ ቅንጅት ኖሯቸው በዓሉን የማክበር ችግርም ተስተውሏል፡፡ እንዲሁም የብሔር ብሄረሰቦች ቀን በዓልን ተንተርሶ የተከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎችም ሲሰሩ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት፣ ታቅዶ፣ የህብረተሰቡ ቀዳሚ ፍላጎት መሰረት ተደርጎ፣ ቀጣይነቱ ተረጋግጦ ነው ወይ? የሚለው ሲነሳ ሰፊ ችግር የታየበት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል መከበር ካቋረጠ በኋላ ይቋረጣሉ፡፡ በበዓሉ ምክንያት የሚሰራ መሰረተ ልማት ተጀምሮ ይቆማል፣ሳያልቅ መቋረጥ ብቻ ሳይሆን የጥራት ችግርም ይስተዋላል፡፡ የህብረተሰቡን ቀዳሚ ፍላጎት አለመለየት፣ የግዢ ስርዓቱ የማይፈቅድ፣ለብክነት ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠ፣ ግልፅነት የጎደለው መሆኑ የታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ በእርግጥ ይህ የመሰረተ ልማት ግንባታ የስራ የአስፈፃሚ አካል ስራ እንጂ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስራ አይደለም፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲፈፀም ማድረግ እንጂ ዋና ስራው በአመለካከት፣በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የህገ-መንግስት ስርፀት እና ውሳኔ የመስጠት ተግባራትን መከወን ነው፡፡
ዘመን፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህገ-መንግስቱ የተሰጠውን ሀላፊነትና ተግባር በአግባቡ ተወጥቷል ተብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል? ከተወጣ ማሳያው ምንድነው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠውን ሀላፊነት ተወጥቷል፣ አልተወጣም ለማለት መመዘኛው የተሰጠው ስልጣንና ተግባር ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ የተሰጠው ስልጣንና ተግባር ደግሞ በአዋጅ ተዘርዝሯል፡፡ በዚህ ረገድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲታይ ጥንካሬዎችም፣ ጉድለቶችም /ክፍተቶችም/ አሉት፡፡ ምክር ቤቱ በድፍረት መናገር የሚያስችሉት ስራዎች እንዲሁም በሚገባ መስራት የሚገባውን ያልከወናቸውም ተግባራት አሉት፡፡ ሁለቱንም በሚዛኑ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ዋናውና ትልቁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣን ህገ-መንግስትን መተርጎም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የህገ-መንግስት ትርጉም ‹‹ያስፈልገዋል፣አያስፈልገውም ›› የሚሉ ከቡድንና ከግለሰብ መብት ጋር ተያይዘው ብዙ አቤቱታዎች ወደ ምክር ቤቱ ይመጣሉ፡፡ ለዚህም በሙያ እንዲደገፍ የህገ-መንግስት ትርጉም አጣሪ ጉባኤ አለን፡፡
ይህም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተዋቀረ ነው፡፡ ይህ ጉባኤ ሙያዊ ድጋፍ እየሰጠ፤ሙያዊ ድጋፉን መሰረት ተደርጎ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ተወያይቶ ለብዙ ጉዳዮች ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ ከህገ መንግስቱ አንፃር ‹‹ትርጉም ያስፈልገዋል፣ አያስፈልገውም ፣የዜጎች መብት ተጥሷል፣ አልተጣሰም›› ብሎ የወሰናቸው ብዙ ውሳኔዎች አሉ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዚህ ረገድ በተለይ ከትርጉም አንፃር አመርቂ ስራ ሰርቷል፡፡ ምክር ቤቱ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ጥልቅ ውይይት በማድረግና በእውቀት ላይ የተመሰረቱ ውሳኔዎችን ያሳልፋል፡፡ ምናልባት ከዚሁ ጋር መነሳት ያለበት የምንሰጣቸው ትርጉሞች፣ የምንወስናቸው ውሳኔዎች ተግባራዊነት ምን ያህል ውጤታማ ነው? የሚለው ሲሆን በዚህ ረገድ የታዩ ክፍተቶች አሉ፡፡
ሁለተኛ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከተሰጠው ስልጣን መካከል የገቢ ክፍፍልን ይመለከታል፡፡ የገቢ ክፍፍል በተለይ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 98 የተመደቡ የጋራ ገቢዎች በፌዴራልና ክልሎች መካከል የሚሰጡ ድጎማዎች አሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ለክልሎች የሚሰጡ ድጎማዎች አሉ፡፡ የጋራ ገቢዎች በጋራ የሚከፋፈሉም አሉ፡፡ ለዚህ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር ያዘጋጃል፡፡ በተለይ ይህ ቀመር ሲዘጋጅ ከሌሎች አገሮችና ራሱ ካከናወናቸው ተግባራት ተመክሮዎችን እየወሰደ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳበረ፤ አሳታፊ፣ግልፅ፣ ፍትሀዊ ቀመር ያዘጋጃል፡፡ ቀመሩ ከተዘጋጀም በኋላ ከአከፋፈል አንፃር ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሩ ስራ ሰርቷል፡፡ በተለይም ፌዴራል ለክልሎች የሚሰጠውን ድጎማ በተመለከተ እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ ቀመር ተሰርቷል፡፡ ምናልባት በዚህ ረገድ ያለው ክፍተት የጋራ ገቢዎች ቀመር ከማዘጋጀት አንፃር ብዙ የተለዋወጡ ነገሮች ቢኖሩም ማለትም ኢኮኖሚያዊ እድገት ወይም ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮች ቢያጋጥሙም አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተዘጋጀው፡፡
ከተለያዩ ጉዳዮች አንፃር ተመልክተን በየጊዜው ቀመሩን እንደየጊዜው ሁኔታ በማየት ማዘጋጀት ያስፈልግ ነበር፡፡ ይህ ባይደረግም አሁን ላይ ቀመሩ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ብሄር ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተሸራርፏል፣ አልተከበረልኝም፣ እና በዚህ ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች ሲኖሩ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ ይወስናል፡፡ በዚህም የተሰሩ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለይ ህገ-መንግስቱ ያስቀመጠውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 251 አዋጅም ያስቀመጠው ስርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህን ስርዓቶች ተከትሎ የመጣ በተለይ ማንነቴ ተሸራርፏል፣ ህገ መንግስቱ ያስቀመጠልኝ መብት አልተከበረልኝም፣ ብሎ የመጣ ውሳኔ ከመስጠት አንፃር የተሰሩ ስራዎች ጥሩ ናቸው፡፡
በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ፓርላማ ዘመን ላይ እውቅና የተሰጣቸው የብሄር ብሄረሰቦች ቁጥር 56 ነበሩ፡፡ እነዚህ ብሄረሰቦች በፌዴሬሽን ምክር ቤት 108 አባላት ነበሯቸው፡፡ አሁን በአምስተኛው የፓርላማ ዘመን 76 የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነት እውቅና ተሰጥቷቸው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ማንነቶችን የሚወክሉ ማህበረሰቦች በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተወከሉ 153 አባላት አሏቸው፡፡ስርዓቱን ተከትለው የመጡ የማንነት እውቅና የተሰጣቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ራስን በራስ ከማስተዳደር አንፃር የቀረቡ ጥያቄዎችን ምላሽ በመስጠት ጥሩ ስራ ተሰርቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በማንነት ዙሪያ እየተፈጠረ ያለው ግጭት ፌዴሬሽን ምክር ቤት በጊዜው ምላሽ ባለመስጠቱ እንደሆነ የሚነሳው ሀሳብ የተሳሳተ ነው፡፡ ለምሳሌ ህግና ስርዓቱን ተከትሎ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የገባና ምላሽ ያልሰጠበት የማንነት ጥያቄ የለም፡፡ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችን በመጀመሪያ ህጉንና ስነ ስርዓቱን ተከትሎ ተዋረዱን ጠብቆ ወይም አክብሮ ሲቀርብ ክልል ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ የክልል አስተዳደር ጉዳዩን ጨርሶ ይወስናል፡፡ ክልል ከወሰነ በኋላ የጉዳዩ ባለቤት ካልረካ በይግባኝ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይመጣል፡፡ ከዚም ፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለጉዳዩ ማጥናት ካስፈለገው ያጠናና በቀጥታ ወደ ውሳኔ ይሄዳል፡፡
ስነ-ስርዓቱን ጠብቆ በክልል ተጠይቆ ክልል ሳይመልስ ሁለት አመት ካለፈው ፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብቶ ውሳኔ መስጠት ስልጣን አለው፡፡ በዚህ ረገድ የታዩ ጉዳዮች ቢኖሩም ምክር ቤቱ ውሳኔ ያልሰጠባቸው በመኖራቸው አንዱ የምክር ቤቱ ክፍተት ነው፡፡በዚህ ረገድ ውሳኔ ሳይሰጠው ከአስር አመታት በላይ የቆዩ የማንነት ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ከክልል ጋር ተገናኝቶ ተመካክሮ ምላሽ መስጠት ነበረበት፡፡ ያለበለዚያ ጥያቄዎቹን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ራሱ አጥንቶ ምላሽ ወይም ውሳኔ መስጠት ነበረበት፡፡ በዚህ ዙሪያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ችግር ነበረበት፡፡ ነገር ግን ትልቁና አብዛኛው የማንነት ጥያቄዎች ያልተፈቱት ከክልሎች በመነጨ ችግር ነው፡፡ ክልሎች በአግባቡ ምላሽ ባለመስጠታቸው የመነጨ ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም የማንነት ጥያቄ ላነሳ አካል ይገባዋል፣ አይገባውም ብለው አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ያለባቸው ክልሎች ናቸው፡፡ እንዲሁም የማንነት ጥያቄዎች ህግና ስርአቱን ጠብቀው ያለመምጣት ችግርም ይስተዋላል፡፡
በአጎራባች ክልሎች የሚፈጠሩ አለ መግባባቶች ሲኖሩ ተግባብተው መፍታት ካልቻሉ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ ይገባል፡፡ አለመግባባቱን አጥንቶ እንዲጠብ ወይም ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ ያደርጋል፡፡ በዚህ ረገድ የመጣ ችግር የለም ማለት ይችላል፡፡ ምናልባት በቅርቡ የተከሰተው የኦሮሚያና የሶማሌ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልሎች ግጭትን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ ገብቶ የፈታቸው ጉዳዮች ካልሆኑ በስተቀር ሌላ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ምክር ቤቱ ብዙ ነገሮችን ሰርቷል፡፡ አሁን ከሚታየው ችግር አኳያ መስራት የነበረበትን ያህል ሰርቷል ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ በአመለካከት ዙሪያና ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የመንግስታት ግንኙነት /በፌዴራልና በክልሎች/ እንዲጠናከር፣ የጋራ ችግር ቢፈጠር ችግሮችን በጋራ ከክልሎች ጋር ተወያይቶ እንዲፈቱ ከማድረግ አንፃር የሚቀር ነገር አለ፡፡
ዘመን፡- ህገ-መንግስት መተርጎም ማለት ምን ማለት ነው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ህገ-መንግስት በብዙ መንገድ ይተረጎማል፡፡ በአገራችን የህገ-መንግስት ትርጉም ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርገው በህገ-መንግስት ትርጉም አጣሪ ጉባኤ የሚደገፍ ነው፡፡ ይህ ሲባል ህገ-መንግስት መተርጎም ሁሉም የህገ-መንግስት አካላት ወይም የመንግስት አካላት ውሳኔ ከህገ መንግስት ጋር እንዳይጋጭና ህገ መንግስቱን እንዳይቃረኑ የማድረግ ተግባር ነው፡፡ የሚቃረን ካለ ህገ መንግታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ የህገ-መንግስት ትርጉም ያስፈልገዋል ወይም አያስፈልገውም ሲባል ወደ ትርጉም ተገባ ማለት ነው፡፡ በህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች አለመጣጣም ሲኖር የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋል፡፡ ህገ መንግስት ጠቅላላ ህግ እንደመሆኑ መጠን የተዘረዘረ ባለመሆኑ ዝርዝር ነገሮች ሲያስ ፈልጉ ደግሞ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህንና ሌሎች መሰል ነገሮችን መሰረት አድርጎ ህገ መንግስት ይተረጎማል፡፡
ዘመን፡- አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን ህገ-መንግስትን የመተር ጎም ስልጣን ከፖለቲካ ነፃ ለሆኑት ለፍርድ ቤቶች መሰጠት ነበረበት ይላሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አንዱ የፖለቲካ አሀድ በመሆኑ ጥያቄዎች እንዲዳፈኑና አድሏዊ አሰራር እንዲዘረጋ ያደርጋል የሚል ነው፡፡
ህገ መንግስትን የመተርጎም ስልጣን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መሰጠቱ ተገቢ ነው?
ወይዘሮ ኪሪያ፡- ህገ መንግስትን በማርቀቅም የመወሰንም መብት የብሄር ብሄረሰቦች ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ ትርጉም ያስፈልገዋል ሲባልም ዋናው ወሳኝ የሚሆነው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ናቸው፡፡ ትርጉም ሙያዊ ትርጉም ብቻ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ህገ-መንግስት ህጋዊ ሰነድ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሰነድም ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም የሚተረጉሙት ያረቀቁት፣ የወሰኑት፣ ያፀደቁት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በመሆናቸው ስልጣኑ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ተሰጥቷል፡፡ ከሙያ አንፃርም የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ለምክር ቤቱ እገዛ ያደርጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ባለሙያዎችም አሉ፡፡ እንዲሁም ተጨማሪ ውይይት፣ ተጨማሪ ማብራሪያ በማድረግ ሙያዊ ድጋፍ ይገኛል፡፡ ጥናት የሚያስፈልገው ነገር ካለም ጥናት ይካሄዳል፡፡ ስለዚህ የህገ መንግስቱ ባለቤቶች የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በመሆናቸው ብሄር ብሄረሰቦችን የሚወክለው አካል ደግሞ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በመሆኑ ህገ-መንግስት የመተርጎም ስልጣን መሰጠቱ ተገቢ ነው፡፡
ዘመን፡- ፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ-መንግስት ጥሰት ዳኝቶ ያውቃል?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- አዎ ዳኝቶ ያውቃል፡፡ በርካታ የህገ-መንግስት ጥሰቶችን ዳኝቷል፡፡ ለማሳያነትም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ በወቅቱ 47 በመቶ የሚሆኑ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች አሉ፡፡ ይህን ቁጥር ያህል ማህበረሰብ ባለበት ክልል የመምረጥ እንጂ የመመረጥ መብት አልነበራቸውም፡፡ ይህ ጉዳይ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መጥቶ ወሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡ በዚያ ወቅት ይህንን ጉዳይ የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ትክክል ነው ማህበረሰቦቹ የመምረጥ እንጂ የመመረጥ መብት የላቸውም ብሎ ወስኖ ነበር፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ግን የመምረጥም የመመረጥም መብት አላቸው ብሎ ወስኗል፡፡
የስልጤ ማህበረሰብ ጉዳይም እንደዚሁ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሪፈረንደም ተደርጎ ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡ በአማራ ክልልም የቅማንት ህዝብ የማንነት እውቅና መጀመሪያ ክልሉ ማህበረሰቡ ማንነት አያስፈልገውም አያሰጠውም ብሎ አስተያየት ሰጥቶ ነበር፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ ወደ ምክር ቤቱ መጣ፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አጥንቶ ሊወስን ሲቀርብ ክልሉ እንደገና አየዋለሁ ብሎ እንዲወስን አደረገ፡፡ ሌሎች እንደዚህ ያሉ ውሳኔዎችም አሳልፏል፡፡ የሱማሌና ኦሮሚያ ውሳኔ እስካሁን ባይቋጭም የሚጠቀስ ጉዳይ ነው፡፡
ዘመን፡- የሰብአዊ መብት ጥሰት የህገ መንግስት ጥሰት አይደለም?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ህገ-መንግስታዊ ጥሰት ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ያስቀመጠውን የሰብአዊ መብቶችም ሆነ የብሄር ብሄረሰቦች መብትን መሰረት አድርጎ ይፈታል፡፡ ይህን የምልህ የቡድን መብትን በተመለከተ ነው፡፡ የግለሰብ መብትን በተመለከተ ደግሞ ከትዳር፣ከንብረት፣ ከመሬት፣ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ ብዙ ጥያቄዎች ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህንም በተመሳሳይ ይፈታል ማለት ነው፡፡
ዘመን፡- በአገራችን ባለፉት አመታት በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ቢደረጉም የፌዴሬሽን ምክር ቤት እስካሁን ምንም ያደረገው ነገር የለም የሚል አስተያየት የሚሰጡ አካላት አሉ፡፡ ይህ አስተያየት ትክክል ነው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ይሄ ምንድነው እኛ የምንመለከተው ወደ ውሳኔ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ታች ወርዶ የሚቆጣጠረው፣ የሚከታተለው የሚመለከተውም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ነው፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ጥናት አድርጎ ለምክር ቤት የሚያቀርበው ኮሚሽኑ ነው፡፡ እኛ ይህ ጉዳይ ወደ ህገ መንግስት ትርጉም ከመጣ ነው ምላሽ የምንሰጠው፡፡ የሰብአዊ መብት ጥሰትን በቅርበት የሚመለከተው አካል አለ፡፡ ይህ ማለት እኛን አይመለከትም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በዋናነት የኮሚሽኑ ስራ ነው፡፡
ዘመን፡- ፌዴሬሽን ምክር ቤት በአገራችን ያሉትን ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች፣አስተዳደሮች ይወክላል ማለት ይቻላል? በምክር ቤቱ ያልተወከሉ ብሄሮች፣አስተዳደሮች የሉም?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ያልተወከለ የለም፡፡ አንዳንድ አካላት በኢትዮጵያ ያሉትን ብሄረሰቦች ቁጥር አንዳንዱ ከ80 በላይ፣ሌላው ከ85 በላይ ናቸው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉንም መስፈርት አሟልተው በምክር ቤቱ እውቅና የተሰጣቸው 76 ብሄር ብሄረሰቦች ናቸው፡፡ እነዚህ 76 ብሄር ብሄረሰቦች ደግሞ እያእዳንዳቸው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና አላቸው፡፡ ስለዚህ ውክልና የሌለው የለም፡፡
ዘመን፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በፌዴሬሽን ምክር ቤት በምን መልኩ ተወክለው መብታቸው እንዲከበር ይደረጋል?
ወይዘሮ ኬሪያ ፡- እነዚህ አስተዳደሮች በምክር ቤቱ ውክልና የላቸውም፡፡
ዘመን፡- በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና የላቸውም ማለት የአስተዳደሮቹን እና የነዋሪዎቹን ህገ መንግስታዊ መብቶች የሚያስከብር፣ህገ-መንግስታዊ ጥያቄዎችን የሚመልስላቸው አካል የለም ማለት ነው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ይሄ የከተማ አስተዳደሮች ጉዳይ በልዩ የሚታይ ነው፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሄር ብሄረሰቦች ቤት ነው፡፡ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከሌሎቹ የተለየ ነው፡፡
ዘመን፡- ታዲያ እነዚህ ሁለት የከተማ አስተዳደሮች መብቶቻቸው በምን መልኩ ሊከበሩ ይችላል?
ወይዘሮ ኬሪያ ፡- በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ የለኝም፡፡ የአዲስ አበባ ወይም የድሬዳዋ ማንነት የሚባል የለም፡፡ ሌሎች ግን ክልልን፣ብሄርን መሰረት አድርገው የተዋቀሩ አሉ፡፡ በክልል ውስጥም የተለያዩ ማንነቶች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ የተለዩ ማንነቶች እውቅና የተሰጣቸው አሉ፡፡ ልክ እንደ ሌሎች ክልሎች በአዲስ አበባና በድሬዳዋ እንደዚህ አይነት የለም፡፡
ዘመን ፡- ለበርካታ አመታት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የማንነትና የአከላለል ጥያቄዎች እስካሁን ድረስ ሲነሱ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ለምንድን ነው እልባት ያላገኙት?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- በዚህ ረገድ ከላይ እደገለፅኩልህ ዋናው ትልቁ ችግር የክልል መፍትሄ አሟጦ አለመጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ የማንነት ጉዳይ አንድ ማህበረሰብ ጥያቄ ካለው ራስን በራስ የማስተዳደር፣ ቋንቋን የማሳደግ፣ በቋንቋው መፃፍም ሆነ መናገር፣ማሳደግም አልቻልኩምና መሰል የማንነት መገለጫዎቼ ተሸራርፈውብኛል የሚል ስሜት ካደረበት ወይም በዚህ ጉዳይ ትክክለኛ ጥያቄ ካለው ተዋረዱን ጠብቆ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይመጣና ከዛ በኋላ ምክር ቤቱ ውሳኔ እንደሚሰጥ መመሪያው አስቀምጧል፡፡ ተዋረዱን ጠብቆ ማለት ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዋጅ የህዝቡ ጥያቄ መሆኑን ማረጋገጫ መኖር አለበት፣ ህዝቡ የወከለው መሆኑን እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ማሟላት የሚጠበቅበት መስፈርት ማለት ነው፡፡ በየደረጃው የሚመጣው ኮሚቴ ወይም ግለሰብ ደግሞ ህዝቡ የወከለው መሆኑን በአስተዳደሩ እውቅና የተሰጠው መሆን አለበት፡፡ ይህን ካሟላ በኋላ ክልሉ መፍትሄ ካልሰጠው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ይገባል፡፡
ይህን ቅደም ተከተልና መስፈርቶችን አሟልቶ አሟጦ የመጠቀም ችግር አለ፡፡ ቅሬታ አቅራቢው የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልቶ አሟጦ ካልተጠቀመ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ ሊገባ አይችልም፡፡ ይህ አንደኛው ችግር ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ህግና ስርዓቱን ተከትለው፣ ሁሉን አሟልተው ክልል ያነቃቸው፣ መልስ ያልሰጣቸውም አሉ፡፡ በህገ-መንግስቱ መሰረት አፋጣን ምላሽ አለመስጠት ችግርም አለ፡፡ እነዚህ መልስ ካልተሰጣቸው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ የሚገባበት ነገር የለም፡፡ ህጋዊ መሰረትም የለም፡፡ የተለያዩ አካላት ምክር ቤቱ አጥንቶ ምላሽ መስጠት አለበት የሚል ሀሳብ ያነሳሉ፡፡ የማንነት ጥያቄዎች ወደ ግጭት ከመሄዳቸው በፊት ምክር ቤቱ በጥናት መመለስ አለበት የሚሉም አሉ፡፡ ነገር ግን ፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሎች ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችልም፡፡ ጣልቃ ገብቶ ለጉዳዮች እልባት የሚሰጥበት የጊዜ ገደብ በህገ-መንግስቱ የተቀመጠው ሁለት አመት ነው፡፡ ከሁለት አመት በፊት ወደ ክልል ገብቶ መፍትሄ የሚሰጥበት መብት የለውም፡፡ ማድረግ ያለበት ጥያቄው የተነሳበት ክልል ምላሽ እንዲሰጥ ግፊት ማድረግ ነው፡፡ ህግና ስርዓቱን ያልተከተሉ ካሉ ደግሞ መረጃ በመስጠት ስርዓቱን ተከትለው እንዲሄዱ ማድረግ ነው፡፡
ዘመን፡ በዚህ ረገድ የማንነት ጥያቄ በማንሳት ከሁለት አመታት በላይ የቆዩ የሉም?
ወይዘሮ ኬሪያ ፡- የሉም፡፡
ዘመን ፡- ክልሎቻቸው ሳይፈታላቸው ሁለት አመት ያለፋቸው ጥያቄዎች የሉም?
ወይዘሮ ኬሪያ ፡- ክልሎች ያልፈቷቸውማ አሉ፡፡ ክልል መልሶት በይግባኝ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መጥቶ የተቀመጠ የለም፡፡ ክልል ከሁለት አመት በላይ ምላሽ ሳይሰጣቸው የቆዩ ጥያቄዎች ግን አሉ፡፡ በተለይ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል ብዙ ማንነቶች ከሁለት አስከ አስር አመታት የቆዩ ጥያቄዎች ምላሽ ያልተሰጣቸው አሉ፡፡ ግጭት እየተፈጠረ እስካሁን ምላሽ ያልተሰጣቸው የማንነት ጥያቄዎች አሉ፡፡ በኦሮሚያ ክልልም ያልተመለሱ የተወሰኑ ጥያቄዎች አሉ፡፡
ዘመን ፡- እንዲህ ከሁለት አመታት በላይ የቆዩ የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘታቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሀላፊነት አይደለም?
ወይዘሮ ኬሪያ ፡-ነው፡፡ ትልቁ ክፍተታችንም ይህ ነው፡፡ ለመፍታትም እንደ እቅድ የያዝነው ይሄንኑ ነው፡፡ ከሁለቱ ማለትም ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ከኦሮሚያ ክልሎች ውጭ ከሌሎች ክልሎች መሰል ጥያቄ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጣ የለም፡፡ እነዚህ ክልሎች አሁንም ችግሩን ካልፈቱ ጣልቃ ገብተን እንፈታለን፡፡ በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ ህግና ስርዓት ጠብቀው ወደ ፌዴሬሽን የመጡት ግን በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ አብዛኛው መሰል ጥያቄዎች እዚያው ታች ታፍነው፣ የማንነት ጥያቄን እንደስጋት የማየት ችግር ይስተዋላል፡፡ ማንነትን መጠየቅ ህገ መንግስታዊ መብት ነው ተብሎ ከማስተናገድ ይልቅ እንደስጋት የመቁጠር ችግር ይታያል፡፡ ስለዚህ ትልቁ ችግር ይሄ ነው፡፡
ዘመን፡- አንዳንዶች እንደሚሉት በአገራችን ግጭቶች የሚነሱባቸው በርካታ አካባቢዎች የተካለሉት በህገ መንግስቱ ማለትም ቋንቋን፣ አሰፋፈርን፣ማንነትን እንዲሁም ፈቃድን መሰረት አድርጎ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት የማንነት ጥያቄዎችና ግጭቶች በርክተዋል ይላሉ፡፡ ይህ አስተያየት ትክክል ነው?
ወይዘሮ ኬሪያ ፡- እንደዚህ አይነት ምክንያት ወይም ጥያቄ እስካሁን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አልገባም፡፡ በአከላለል ላይ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 48 መሰረት ‹‹ይሄ የኔ ነው፣ ያ ያንተ ነው፣›› የሚል ጥያቄ እስካሁን የመጣ ጥያቄ የለም፡፡ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ሲኖሩ ምላሽ ለመስጠት ከተቻለ ሁለቱ ክልሎች ተግባብተው ይፈታሉ፡፡ ልክ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች እንዳደረጉት በስምምነት ችግሩን ይፈታሉ፡፡ ሁለቱ ክልሎች ካልተግባቡ ግን ፌዴሬሽን ምክር ቤት ጣልቃ ገብቶ ችግሩን ይፈታል፡፡ በዚህ ረገድ የደረሰ ወይም ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጣ ጥያቄ የለም፡፡ የአከላለል ጥያቄ አለን ለመካለል መስማማት አልቻልንም ብሎ ወደ እኛ የመጣ ማንም የለም፡፡
ዘመን፡- ክልሎች ጣልቃ ግቡ ካላሏችሁ ገብታችሁ ችግሩን መፍታት አትችሉም?
ወይዘሮ ኬሪያ ፡- አይቻልም፡፡ ይሄ ያው ሁላችንም እንደምናውቀው ፌዴራል ወደ ክልል የሚገባው መጀመሪያ የክልሉ ፍቃድ መኖር አለበት፡፡ ክልሉ ሲፈቅድ ከአቅሜ በላይ ነው፤ መፍታት አልቻልኩም ብሎ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲገባ ሌሎች አካላትም እንዲገቡ ከጠየቀ ሁለቱ ምክር ቤቶች ተግባብተው የሚሄዱበት አግባብ አለ፡፡ ክልል ካልጠየቀ ግን ምክር ቤቱ ጣልቃ መግባት አይችልም፡፡ ህጋዊ መሰረትም የለውም፡፡
ዘመን፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአገር ላይ የሚከሰቱ መሰል ህገ-መንግስታዊ ጥሰቶችን ለመፍታት ተጠይቆ ካልሆነ ራሱ ጣልቃ ገብቶ የማይፈታና ህገ መንግስታዊ ትርጉም የማይሰጥ ከሆነ የምክር ቤቱ ስልጣን ምልዑ ነው ማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- እስካሁን በአከላለል ተጋጭተናልና እርዱን ያለ የለም፡፡ በማንነት ዙሪያም ሁለት ክልል የተጋጨ የለም፡፡ ህገ መንግስቱ አስቀምጦታል፡፡ ችግሩ በህገ መንግስቱ መሰረት መሄድ ላይ ነው፡፡ ህገ መንግስቱ የማይፈታቸው ችግሮች ካሉም ምንም ችግር የለውም ተመካክሮ ህገ-መንግስቱን ማሻሻል ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ግን በአከላለል አሊያም በማንነት ጥያቄ ዙሪያ ወደ ፌዴሬሽን የገባ ነገር የለም፡፡ ጥያቄ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ካልገባ ምንም ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ በአከላለል አሊያም በማንነት ዙሪያ ጥያቄ ያላቸው ሁለት ክልሎች ቁጭ ብለው መነጋገር ያለበለዚያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲፈታው ማቅረብ ነው ያለባቸው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋንኛው አላማ ውሳኔ መስጠት እንጂ ግጭት መሃል ገብቶ መፍታት አይደለም፡፡ እንዲህ አይነቱ ተግባር የአስፈፃሚ አካል ስራ ነው፡፡ የተፈጠረውን ችግር ወርዶ መፍታት አስፈፃሚ አካል ስራ ነው፡፡ የአንድ ወይም የሁለት ክልሎች ጥያቄ መሰረት አድርጎ ውሳኔ የመስጠት ስራ የምክር ቤቱ ነው፡፡ ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ችግሩ እንዲፈታ ግፊት የማድረግ ስራ ወይም ስልጣን ግን አለው፡፡
ዘመን ፡- እስካሁኑ ሰዓት ድረስ በኢትዮጵያ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ቋንቋዎች ቁጥር በተጨባጭ ስንት እንደሆኑ በጥናት ተለይተው ይታወቃሉ?
ወይዘሮ ኬሪያ ፡- ሰባ ስድስት ናቸው፡፡
ዘመን፡- በአገራችን ያሉ ብሄረሰቦች፣ ቋንቋዎች ከሰባ ስድስት እንደማይበልጡ ያረጋገጠው ጥናት መቼ የተጠና ነው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ማለት የማንነት እውቅና የተሰጠው በጋራ ነው፡፡ ቋንቋውም በተመሳሳይ፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች የማንነት እውቅና ሲሰጣቸው የሚግባቡበት ቋንቋም አላቸው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከማንነት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተለዩት ሰባ ስድስት ናቸው፡፡
ዘመን፡- የማንነት ወይም የእውቅና ጥያቄ ባይነሳ በጥናት ያረጋገጣችሁት የብሄሮች ወይም የቋንቋዎች ቁጥር የለም?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- ጥናት አላደረግንም፡፡ ይህንን ሌላ አካል ነው የሚያጠናው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ብሄር ብሄረሰቦች መብቴ ተሸራርፏል ብሎ የጠየቁት ጥያቄ አጥንተን መመለስ እንጂ ምን ያህል ቋንቋዎች እንዳሉ ማጥናት ስራው አይደለም፡፡ ገና ያልታወቁ፣ያላደጉ ወደፊት የሚመጡ ብሄር ብሄረሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ 56 የነበሩ ብሄረሰቦች አሁን 76 ደርሰዋል፡፡ ነገም የሚያድግ ብሄር ብሄረሰብ አለ፡፡ ይህንን ባህልና ቱሪዝም ወይም ሌላ አካል ሊያጠናው ይችላል፡፡
ዘመን ፡- የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማንነት ጥያቄ ዙሪያ እያወጣ ያለውን መግለጫ እንደ ተቋም ገለልተኛ ያልሆነና ወገንተኝነት የሚታይበት ነው ሲል በቅርቡ የወልቃይት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ገልጧል፡፡ ለዚህ አባባሉ እንደማስረጃ የሚያቀርበው እርስዎ በቅርቡ መግለጫ ሲሰጡ ‹‹ ለወልቃይት ጉዳይ ትግራይ መቆርቆር ሲገባው አማራ ክልል እየተቆረቆረ ነው ›› ማለትዎን ያነሳል፡፡ ይህን ጉዳይ በዚህ መልኩ የገለፁት ከሆነ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለልተኛ ነው ማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- በእርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ አሁንም ወደሌላ እንዳታዛባው ጥርጣሬ ስላለኝ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ምንድን ነው መጠየቅ ያለበት ህግና ስርዓቱን ያነሳው ፌዴሬሽን ምክር ቤት ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚል ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ ማንነት እንዴት እንደሚጠየቅ ገልጬልሀለሁ፡፡ ህጉ ስርዘቱ ምን እንደሚል ነግሬሀለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ የሚጠየቅ ማንነት ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመመለስ ሀላፊነት የለውም፡፡
ህጉ ትክክል ነው ወይስ አይደለም ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ ገለልተኛ ነው አይደለም የሚባለው ፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሄር ብሄረሰቦች ቤት ነው፣ የተሰጠው ስልጣንና ሀላፊነት አለ፣ ይህን ስልጣንና ሀላፊነት በህገ መንግስቱና በስርዓቱ መሰረት እንዲፈፀም ማድረግ አለበት፡፡ ሁሉም ጥያቄዎች ሲመለሱ በህገ መንግስቱ የሚከተሉት ስርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህን ስርዓቶች ተከትሎ የመጣ ጥያቄ ፌዴሬሽን ይመልሳል፡፡ ከዚህ ውጪ የመጣን ግን አይመልስም፡፡ በሁሉም አካባቢ ህግና ስርዓቱን ተከትላችሁ ኑ ነው የሚባለው፡፡ ይሄ በወልቃይትና በራያ ብቻ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የቅማንት ጥያቄ አለ፡፡ ቅማንት ያለው አማራ ክልል ነው፡፡ ህዝቡ ያለው አማራ ክልል ነው፡፡ መሬቱም አማራ ክልል ነው፡፡ የሚያስተዳድረውም አማራ ክልል ነው፡፡ ስለዚህ የማንነት ጥያቄ ካለው ሚያቀርበው ለአማራ ክልል ነው፡፡ አማራ ክልል ይመልሳል፡፡ ለአማራ ክልል ሲያቀርብ ህግና ስርዓቱን ይከተላል ክልሉ ደግሞ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ አማራ ክልል ምክር ቤት ውሳኔ ሰጥቶት ካልረካ ወደ ፌዴሬሽን መጥቶ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡
አማራ ክልል ከሁለት አመት በላይ ካቆየው ፌዴሬሽን ገብቶ አጥንቶ ይሰራል፣ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ህገ መንግስቱ ስርዓቱ የሚለው እንዲህ ነው፡፡
የቅማንትን ጉዳይ አንስቼ የምነግርህ አንተም ሳታዳላ አንድትናገር ብዬ ነው፡፡ እውነተኛ ከሆንክና አሁንም ካላዛባኸው ማለቴ ነው፡፡ ያልኩትም ስርዓቱም የሚለው ከላይ በገለፅሁልህ መልኩ ነው፡፡ ወልቃይት፣ ራያ ያለው ትግራይ ክልል ነው፡፡ ህዝቡም፣መሬቱም ትግራይ ነው ያለው፡፡ የሚያስተዳድረውም የትግራይ ክልል ነው፡፡ ማንኛውንም ጥያቄ ወደ ወረዳ ከዛ ወደ ክልሉ ያቀርባል፡፡ ጥያቄውን አቅርቦ መልስ ካላገኘ ተጠያቂው ትግራይ ክልል ነው፡፡ ስለዚህ መልስ መስጠት ያለበት፣ጥያቄውም መቅረብ ያለበት የትግራይ ክልል ነው፡፡ እኔ የመጣሁት አሁን ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ቀደም ባለው ጊዜ ያስቀመጠው አሰራር፣ ቀድሞ የወጣ አዋጅ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሚመጣ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም፡፡ ለምሳሌ ለቅማንት ጥያቄ የትግራይ ክልል የሚቆረቆር ከሆነ ማንም የሚያዳምጠው የለም፡፡ አያገባህም ነው የሚባለው፡፡ ይሄ የአማራ ነው፡፡ የሚያስ ተዳድረውም አማራ ክልል ነው፡፡ ስለዚህ አማራ ክልል ነው መቆርቆር ያለበት፡፡ ይህ ትክክል ነው፤ ነገም የምደግመው ነው፡፡ አሁንም እየደገምኩል ነው፡፡ ስርዓቱ የሚለው ስለሆነ ሌሎችም እንደዚያ ተብለዋል፡፡
እናም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገለልተኛ ነው አይደለም የሚባለው በህገ መንግስቱ የተሰጠውን ስርዓት ተከትሏል ወይስ አልተከተለም በሚሉ መስፈርቶች መታየት ነው ያለበት፡፡ በዚህ ረገድ ምክር ቤቱ ከስርዓቱና ከህጉ ውጭ ከፈፀመ ከተናገረ ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡
ዘመን፡- ከላይ ያነሳሁት ጥያቄ የወልቃይት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ያነሳውን ጥያቄ ነው እንጂ የኔ ጥያቄ አይደለም፡፡ ይህ ኮሚቴ ካነሳው ጥያቄ መካከል አንደኛው የማንነት ጥያቄ ለማቅረብ የተቀመጠው መስፈርት ለክልሉ ያደላል የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ ወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ሲያነሳ የትግራይ ክልል መፍቀዱን በፊርማ አሊያም በማህተም ማረጋገጥ አለበት፡፡ የሚለው መስፈርት ጥያቄያችንን እንዳናቀርብ እንዲዳፈን ያደርጋል ነው የሚሉት፡፡
ወይዘሮ ኬሪያ ፡- አይ! ለማንኛውም ያልኩህን ነገር ውሰድ፡፡ ስርዓቱ የሚለው እሱን ነው፡፡
ዘመን ፡- መስፈርቱስ ትክክል ነው?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- አዋጁን ማየት ይቻላል፡፡ ህገ-መንግስቱን ማየት ይቻላል፡፡ ማንኛውም ሰው የሚጠይቀው ደግሞ አዋጁንና ህገ-መንግስቱን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ ለአንዱ ክልል የሚሰራ ለሌላው ክልል የማይሰራ አይደለም፡፡ እዚያ የተቀመጠው ለአንዱ ክልል የሚሰራ በተመሳሳይ ለሌሎች ክልሎችም የሚሰራ ነው፡፡ የሚቀየር ከሆነ ደግሞ ለሁሉም ነው የሚቀየረው፡፡ ስለዚህ ተመሳሳይ አካሄድ ነው የተሄደው፡፡ ተመሳሳይ መልስ ነው የተመለሰው፡፡
ዘመን፡- የማንነት ጥያቄ ለማቅረብ ማሟላት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በቅርቡ አላወጣችሁም?
ወይዘሮ ኬሪያ፡- እሱ አይመለከታቸውም፡፡ ከወጣ ወጣ ይባላል፡፡ ያኔ ትሰማላችሁ፡፡ እስካሁን ግን የነበረውን ነው እየተከተልን ያለነው፡፡ ማሻሻል ሲያስፈልገው ደግሞ ተሻሻለ ሲባል በሚዲያ ትሰማላችሁ፡፡
ዘመን ፡- አመሰግናለሁ፡፡
ወይዘሮ ኬሪያ ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ዘመን መፅሄት ህዳር 2011