ኢትዮጵያን የተለየ ውበት የሚያላብሷት የተለያዩ ባህሎች፣ እምነቶች እና ቋንቋዎች ያሏቸው ብሔሮችና ብሔረሰቦቿ ናቸው፡፡ እነዚህ የተለያየ ባህል፣ ማንነትና እምነት ያላቸው ሕዝቦች ደግሞ በአገራቸው ጉዳይ ላይ ባላቸው አንድነትና ህብረት በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር ይታወቃሉ፡፡ በተለይ ቀደም ባሉት ዘመናት ከውጭ የመጣ ወራሪ ኃይልን በአንድነት በመመከትና አገራቸውን በመጠበቅ ያበረከቱት አስተዋፅኦ የላቀ እንደነበር የታሪክ ድርሳት ያሳያሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ለመጠበቅ ወደኋላ የማይሉ፣ ሕዝቦቻቸውም እርስ በርስ የሚከባበሩና የሚዋደዱ መሆናቸው በአርአያነት የሚነገር ሃቅ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር ቀደም ሲል በሕዝቦቻችን ውስጥ ጠንካራ መሠረት የነበራቸው ባህላዊ እሴቶቻችን የላቀ ሚና ነበራቸው፡፡ በዚህም መሠረት በአገራችን ለዘመናት የኖረው ታላላቆችን የማክበርና የመስማት፣ የእርስ በርስ የመከባበር፣ አንዱ ሌላውን የመውደድና አብሮ የመብላትና የመኖር ባህል ጠንካራ መሠረት ነበረው፡፡ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ የሄደ እንግዳ ከማንም በላይ የሚከበርበትና ከቤተሰቡ አባል በላይ እንክብካቤ የሚያገኝበት ጠንካራ ባህል ይዘን ኖረናል፡፡
ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ስፍራ የሚጓዝ መንገደኛ በድንገት ቢመሽበትና በደረሰበት አካባቢ እባካችሁ አሳድሩኝ ቢል ከምንም በላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት እግሩን አጥቦና የራስን መኝታ ለቆ እንግዳን ማሳደር የኢትዮጵያውያን መገለጫ ሆኖ እንደኖረ የታሪክ ማህደሮቻችን ያሰፈሩልን ባህላዊ እሴቶቻችን ናቸው፡፡
ከዚህም አልፈው ለዘመናት የቆዩትና ለዓለም ማህበረሰብ ጭምር የዴሞክራሲ ምንጭ እንደሆኑ የሚገመቱት የገዳና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶችም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከቆዩ ጠንካራ የኋላ እሴቶቻችን ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሥርዓቶች ያለማንም ጣልቃገብነት እንደየ ዕድሜ ክልሉ የታላላቆቹን ቃል እያከበረ ለዘመናት ያለምንም ግጭት የቆየባቸው ምስጢሮች ናቸው፡፡ በገዳ ሥርዓት ውስጥ የሥርዓቱ ዋነኛ ገዢ የሆነውን የአባገዳ ቃል መስማትና መተግበር ለእያንዳንዱ የሥርዓቱ ተከታይ የተሰጠ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ ሥርዓት መውጣት ፈጽሞ የማይታሰብና የተወገዘም ጭምር ነው፡፡
በሌላ በኩል በአገራችን እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ታላላቆችን በተለይ በዕድሜ የገፉ አባቶችና እናቶችን ማክበር የተለመደና በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥም የሰረፀ በመሆኑ ማንም ቢሆን ለዚህ ምክርን የሚሻበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በዚህም የተነሳ በአካባቢያችን የሚገኝ አንድ አባት ለሁላችንም የምናከብረው አባት ነው፡፡ የአካባቢያችን እናት ለሁላችንም እናት ናት፡፡ እናም እነዚህን እነሱን ማክበርና መከተል ግዴታችን እንደሆነ አምነን እንተገብረዋለን፡፡
በትምህርት ቤትም ቢሆን በመምህራንና በተማሪዎች መካከል የነበረው የመከባበር መንፈስ ጠንካራ ነበር፡፡ ለምሳሌ አንድ መምህር ወደ ምንኖርበት አካባቢ ቢመጣ እንዳያየኝ ብሎ መደበቅና በድንገትም ከተገናኘን ዝቅ ብሎ ሰላምታ በመስጠት አክብሮትን መስጠት የእያንዳንዱ ኢትዮጵዊ ተማሪ ባህል እንደነበር የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ከሃይማኖት ተቋማትም አንጻር የሃይማኖት አባቶች ከኅብረተሰቡ ጋር የነበራቸው ቁርኝት ጥብቅና እያንዳንዱ ዜጋም የሃይማኖት አባቶችን ምክርና ተግሳፅ የሚሰማበትና የሚያከብርበት ሁኔታ በስፋት እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡ በዚህ የተነሳም የሃይማኖት አባቶች የሚያስተምሩትን ትምህርት የመስማትና ከእነሱ ውጪ ላለመውጣት የሚደረገው ጥረት ጠንካራ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡
ያም ሆኖ አሁን አሁን በተለይ ባህላዊ እሴቶቻችን ቀስ በቀስ እየተሸረሸሩ የመጡበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በዚህ የተነሳም በአሁኑ ወቅት እነዚህ ሰላምን ለማምጣትም ሆነ ለመከባበር ጠንካራ መሠረት ጥለውልን በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ጭምር ስንከበርባቸው የነበሩ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ መጥተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ታላላቆችንም ሆነ አዛውንቶችን የማክበርና የሚሉትን ሰምቶ የመተግበር ሁኔታ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
በሌላም በኩል ኢትዮጵያ የሃይማኖት ነፃነትና ጠንካራ የሃይማኖት ተቋማት ቢኖራትም እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት በተለይ ዋነኛ ተግባራቸው የሆነውን ሰላም ከማስከበር አንጻር የሚፈለገውን ያክል ሚናቸውን እየተወጡ አይደለም፡፡ ለዚህም አሁን አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች ለምን ተከሰቱ? እንዴትስ እነዚህ ሁሉ ጠንካራ የሃይማኖት ተቋማትና ማህበረሰብ ይዘን ግጭቶች ይፈጠራሉ? በሚል በተለያዩ ወገኖች የሚነሳ ጥያቄ ማሳያ ነው፡፡
አሁን አሁን በኅብረተሰባችን ውስጥ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ የማንነት ጥያቄዎች ሲፈጠሩ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በአንድ በኩል እኛ ኢትዮጵያውያን ነን በሚል አንድነትን የምናቀነቅንበት ሁኔታ እያየለ ሲመጣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ አካባቢ የእኔ ነው፤ አንተ ማንነትህ ከዚህ ስላልሆነ ከዚህ ውጣ፤ ወዘተ እያልን በማንነት ጥያቄዎች ግጭት ስንፈጥር እንውላለን፡፡
በርግጥ መንግሥት ማንነትን ያከበረ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለአብሮነታችን ጠቃሚ ነው በሚል ሁለቱንም ባጣመረ መልኩ እየተጓዘ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎች ሲከሰቱም በምን ዓይነት ሁኔታ ሊፈቱ እንደሚገባም በሕገመንግሥቱ ተቀምጠዋል፡፡ ይህ በሆነበት ለግጭት መንስኤ መሆን ተገቢ አይደለም፤ አገርንም ያፈርሳል፡፡ ይህ ደግሞ ነባሮቹ ባህላዊ እሴቶቻችን ያኖሩልን ቅርስ ሳይሆን አዲስ ያዳበርነው የተዛባ የባህል ማንነት ነው፡፡
በርግጥ አሁንም ቢሆን ባህላዊ እሴቶቻችንና ሃይማኖታዊ ተቋማትን ሰምቶ የመተግበር እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ አልጠፋም፡፡ ለዚህም በቅርቡ በጋሞ ብሔረሰብ ዘንድ የታየው ሰላምን የማውረድና ግጭትን የማስቆም ተግባር ማሳያ ነው፡፡ ይህ በጋሞ የአገር ሽማግሌዎች የተፈፀመ ተግባር አገራችን ቀደም ሲል የነበራትን ጠንካራ ባህላዊ ማንነት ካኖረችበት አውጥታ እንደተጠቀመችበት ማሳያ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ ባህሎች ለእኛ የሚበጁን ማህበራዊ እሴቶች በመሆናቸው ከለበሱት አቧራ ውስጥ ወጥተው ሊታደሱና ሊጠናከሩ ይገባል፡፡
በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ምሁራን፣ ወላጆች እንዲሁም በተለያየ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚገኙ አካላት ሁሉ የቀደመውን የአገራችንን ጠንካራ የአንድነትና የመቻቻል እንዲሁም የመከባበር ባህል በመመለስና በማጠናከር አገራችንን ወደ ሰላምና ብልጽግና ለማምጣት ትልቅ ኃላፊነት ወስዳችሁ መስራት ይኖርባችኋል፡፡ ዛሬ ላይ አገራችንን ወደ አንድነትና ሰላም ሊያመጣት የሚችለው ይህ ነባሩ እሴታችን በመሆኑ፣ እንደዚህ ዓይነት እሴቶችን ከያሉበት በማውጣት ማደስና ወደ ተግባር መቀየር ለአገራችን ህልውና መሠረት ነውና ኃላፊነታችንን እንወጣ፡፡