
ሀገራችን ለዘመናት በዘለቁ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ስብራቶች ውስጥ አልፋለች ። እነዚህን ስብራቶች ለመጠገን ያለሙ ሕዝባዊ የለውጥ መነሳሳቶችን በተለያዩ ወቅቶች አስተናግዳለች ፤ እያንዳንዱ የለውጥ ምእራፍም የየራሱን አዎንታዊ እና አሉታዊ ሀገራዊ ዐሻራ አስቀምጦ አልፏል ።
የዚሁ ሀገራዊ የለውጥ መነሳሳት አካል የሆነው የ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥም ብዙ ፈተናዎች እና ተግዳሮቶችን በስኬት እያሳለፈ ዛሬ ላይ ተስፋ ሰጪ በሆነ ታሪካዊ ምእራፍ ላይ ይገኛል። ዓላማ ያደረገው ሀገርን የማበልጸግ ራእይም እለት እለት በሚከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ተጨባጭ ወደሆነ ትርክት እየተለወጠ ነው።
አሁን ላይ እንደሀገር ለውጡን ተከትሎ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች ውጤታማ እየሆኑ ፤ የተወጠኑ ኢኒሼቲቮች ፍሬ እያፈሩ፤ እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ መድረኮች ያለን ተሰሚነት እየጨመረ፤ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር የምናደርጋቸው ጥረቶችም ውጤት እያስመዘገቡ ነው። ይህም ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እንድናስመዘግብ አቅም ሆኗል።
ለዚህም በግብርና ፣ በኢንዱስትሪ ፣ በቱሪዝም ፣ በዲጅታል ቴክኖሎጂ እና በማአድን ዘርፎች እንደ ሀገር የተመዘገቡ እና እየተመዘገቡ ያሉ ስኬታማ አፈጻጸሞች ተጠቃሽ ናቸው ። ይህን እውን ለማድረግ እንደሀገር ወደ ሥራ ያስገባነው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በራስ መተማመናችን ላይ ተጨማሪ አቅም ፈጥሯል።
በፖለቲካው ዘርፍ ልዩነቶችን በውይይት እና በድርድር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው ዘመኑን የሚዋጅ ስልጡን አካሄድ ሀገር እና ሕዝብን ከከፋ አደጋ መታደግ አስችሏል ። ልዩነት ያላቸው የፖለቲካ አመለካከቶችን የማክበር ፣ ለሀገር ይጠቅማሉ ብሎ የመውሰድ እና በሀገራዊ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ስፍራ እንዲያገኙ እድል መስጠት፣ የፖለቲካ ባህሉም ከጠላትነት ፍረጃ ወጥቶ ወደ ተፎካካሪነት እንዲሻገር አስችሏል።
በልማትና በፖለቲካ መስክ እየተመዘገቡ ያሉ አዎንታዊ ለውጦች በራሳቸው በብዙ ፈተናዎች ውስጥ የነበረው ሀገራዊ ሰላም እንዲጸና አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል። በዚህም ሀገራዊ የሰላም እጦቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ አሁን ላይ ለሀገረ መንግሥቱ ስጋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ለዚህም አንድም መላው ሕዝብ የግጭትንና የጦርነትን አስከፊ ገጽታ በማየት ከግጭት ጠማቂዎች ጋር ላለመተባበር ያሳየው ቆራጥነት ፤ ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት እና በድርድር ለመፍታት የያዘው የጸና አቋም እና በተጨባጭ ያሳየው ቁርጠኝነት በዋንኛነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተፈጠረውን የሠላም ችግር ለመቅረፍ የሰላም መንገዶችን በማበረታታት እና ሕግን በማስከበር ባከናወነው ተግባር ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ታጣቂዎች የሰላም መንገድን መርጠው በሰላም ገብተዋል። ሕዝብ የሰላም ባለቤት በመሆን አካባቢውን ማስከበር ጀምሯል። ክልላዊ የጸጥታ መዋቅሮች አሁን ላይ ተጠናክረዋል።
በአንዳንድ ወገኖች እኩይ ዓላማ የትግራይ ሕዝብ የሚፈልገውን ያህል ሰላም ባያገኝም፣ በትግራይ የነበረው ጦርነት በሰላም እንዲፈታ መንግሥት ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት ሕዝቡ እፎይታ አግኝቷል። የሰላም ስምምነቱ መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎች እንዲከናወኑ፣ መሠረተ ልማቶችም እንዲጠገኑ አድርጓል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ለውጡን ለመቀልበስ ብዙ ሤራዎች ታቅደው ተተግብረዋል ፣ ወጥመዶች ተዘርግተዋል ፣ ዝርፊያ፣ እገታ፣ ጭካኔ፣ የተሞላባቸው ተግባራት ተከናውነዋል። ሕጋዊ የፓርቲ ሽፋኖችን ለሕገወጥ ተግባራት ለመጠቀም የሞከሩ ተስተውለዋል።
ከኃላፊነት የተነሱ አኩራፊ ፖለቲከኞችን በመጠቀም ሕገወጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ ፤ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለሁከት ተግባር ለመጠቀም መንቀሳቀስም በስፋት ታይቷል። በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በመተባበር፣ የመንግሥትን ሥራዎች በማደናቀፍ፣ የሕዝብን ምሬት በመጨመርና የሐሰት ወሬዎችን በማዛመት የተጠመዱም ብዙ ነበሩ፡፡
በማኅበራዊ ቦታዎች፣ በቤተ እምነቶች፣ በመሥሪያ ቤቶች እና በንግድ ቦታዎች ተሰግስገው እኩይ ዓላማቸውን ለማስፈጸም የሚሞክሩ። ሸቀጥ በመደበቅ የአቅርቦት እጥረት የሚፈጥሩ የውጭ ምንዛሬ ሥርጭትን የሚገድቡ ፤ በሕገወጥ የሰዎች እና የመሣሪያ ዝውውር፤ በሙስና፣ በዘመድ አዝማድ እና በብልሹ አሠራር ሕዝብ እንዲማረር ሆን ብለው የሚሠሩም በስፋት ነበሩ።
መደበኛውንና ማኅበራዊውን ሚዲያ በመጠቀም የሕዝቡን ሰላም የሚረብሹ፣ በጦር ሜዳ ሲሸነፉ፤ ሤራዎቻቸው ሲከሽፉባቸው፤ በሰልፍና በአመጽ የሚወድቅ መንግሥት ሲያጡ፤ የመጨረሻ አማራጫቸውን የሐሰት ታሪክ መፍጠር ፤ የሐሰት መረጃ መቀመር ፤ የሽብር ወሬ መንዛት ፤ የሁከት ዜና ማምረት ያደረጉ ግለሰቦች እና ቡድኖች አደባባዮችን ሞልተው የታዩበት ጊዜም እሩቅ አልነበረም ። ለውጡን አስከ ምን ድረስ እንደተፈታተኑም ለሕዘዝባችን የተሰወረ አይደለም።
የለውጥ ሃይሉ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች እና ተግዳሮቶች ሕዝቡን ከጎኑ በማሰለፍ በጽናት ታግሎ በማታገል መሻገር ችሏል። አሁን ላይ እንደሀገር ያለን ቁመና የጀመርነውን የለውጥ ጉዞ በአስተማማኝ መሠረት ላይ በማስቀጠል ሀገራዊ ብልፅግናን ከተስፋነት ወደ ተጨባጭ እውነታነት መለወጥ የሚያስችል ነው።
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2017 ዓ.ም