የሕዝብን የሰላም ጥማትና የትውልዱን ራስን የመሆን መሻት ተጨባጭ ለማድረግ የተሰጠ ታሪካዊ ኃላፊነት!

ትናንት እና ዛሬ ግጭቶች እና ጦርነቶች እንደ ሀገር ካስከፈሉን መጠነ ሰፊ እና ያልተገባ ዋጋ አንጻር መላው ሕዝባችን ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ የላቀ ነው። የትኛውም አይነት ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብሮቹ ሰላም እና ሰላምን ብቻ መሠረት እንዲያደርጉ ያለውም መሻት አልፋ እና ኦሜጋ ነው።

ሕዝባችን ይህንን ስለ ሰላም ያለውን የፀና መሻት በየዘመኑ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ የሰላም እጦቶችን ለመሻገር በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ጎልቶ የሚታይ ነው። የትኞቹም አይነት ችግሮቹ በሰላማዊ አማራጮች እንዲፈቱ የሕዝባችን መንፈሳዊ ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች አበክረው የሚናገሩት ፤ የሚያስተምሩት እውነት ነው።

በተለይም አሁን ላይ በሕይወት ያለው ትውልድ ከታሪክ ትርከት ባለፈ ባለፉት ሰባት አስርት ዓመታት ግጭቶች እና ጦርነቶች ምን ያህል አውዳሚ እንደሆኑ በተጨባጭ ማየት የቻለ ነው። በእነዚህ ዓመታት መላው ሕዝባችን እንደ ሕዝብ እንዳች ባላተረፈባቸው ግጭቶች እና ጦርነቶች ውስጥ ለማለፍ ተገድዷል።

በተለይም የትግራይ ሕዝብ አንደ ሕዝብ ለተደጋገሙ ጦርነቶች የተዳረገበት እውነታ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በእነዚህ ጦርነቶችም ተስፋ ያደረጋቸው የአብራኩን ክፋዮች ፤ ሀብት ንብረቱን ጨምሮ ብዙ ትናንቶችን የተቀማ ሕዝብ ነው። በእያንዳንዷ አውደ ውጊያ ተስፋዎቻቸውን የተነጠቁ እናት አባቶች ጥቂት አይደሉም።

ይህንን እውነታ ለትግራይ ሕዝብ ለመንገር መሞከር “ለቀባሪው አረዱት” እንደሚባለው አይነት አላዋቂነት ካልሆነ በስተቀር ትርጉም አይኖረውም። እውነታው በጊዜ ሂደትም ሆነ በተስፋ ስኬት ትርክት ከትግራይ ሕዝብ ህሊና የደበዘዘ አይደለም። ገና ጠባሳው ያላገገመ ፤ ማኅበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ስብራቱ ያልታከመ፤ የሕዝቡን ትከሻ ያጎበጠ ፣ ልብ የሰበረ አሁናዊ ህመምም ነው።

የትግራይ ሕዝብ ከሁሉም በላይ ከዚህ ህመም ፈውስ ማግኘትን ይፈልጋል። በተለይም አዲሱ ትውልድ ራሱን ከአሁናዊው ዓለም ጋር አናብቦ እጣ ፈንታውን ብሩህ እና ከዲስኩር ተስፋ ያለፈ ተጨባጭ ለማድረግ ከትናንት ህመሞቹ እና ህመሞቹ ከፈጠሩት ስቃይ እና መከራ ለዘለቄታው መፈወስ ፣ ለዚህ የሚሆን ባለ ራዕይ መሪ ይፈልጋል።

እንደ ትውልድ የራሱን እጣ ፈንታ የሚወስንበት ፣ ዘመኑን ተላብሶ በዘመኑ አስተሳሰብ ተስፋዎቹን ተጨባጭ የሚያደርግለት ፤ አሻጋሪ ማኅበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እሳቤዎችን እውን ማድረግ የሚያስችል ሁለንተናዊ መነቃቃት ያለው ለለውጥ እሳቤዎች የተገዛ መሪንና አመራርን ይሻል።

ከጽንፈኝነት እና ከጦረኝነት የራቁ ፤ ከመንፈሳዊ ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶቹ ጋር የተሳሠሩ ፤ ከእውነተኛ ማንነቱ የሚመነጩ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ይፈልጋል ።ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ በሰላም እና በፍቅር የሚኖርበትን ፣ ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሰላም ምንጭ የሚሆንበትን አስቻይ ሁኔታ ይናፍቃል ።

አንድም የአብራኩ ክፋይ የግጭት እና የጦርነት ሰለባ እንዲሆን አይፈልግም ፣ እስካሁን የመጣበት መንገድ ያስከፈለው ያልተገባ ዋጋ ከሚሸከመው በላይ ከሆነበት ውሎ አድሯል። ዛሬ ላይ ትውልዱ ስለ ሰላም የሚያሰማቸው የጭንቅ ድምጾች የዚህ ተጨባጭ እውነታ ማሳያዎች ናቸው። ራስን የመሆን ድምጾችም ናቸው።

እነዚህን ድምጾች በትናንት ትርክቶችም ሆነ በተለመዱ የፖለቲካ ዲስኩሮች ማስቆም ፣ በኃይልም ማፈን አይቻልም ። ድምጾቹ በዚህ ትውልድ ውስጥ የተፈጠሩ ድንገተኛ ክስተቶችም ሳይሆኑ ፤ የትግራይ ሕዝብ የዘመናት መሻት የወለዳቸው ፤ በዘመናት ውስጥ በትውልድ መካከል ሲብላሉ የነበሩ ፤ የመላው ሕዝባችን የጋራ ድምጽ አካል ናቸው።

ለትግራይን ሕዝብ እውነተኛ ተቆርቋሪ ነኝ የሚል የትኛውም ቡድንም ሆነ ፤ ማንኛውም ግለሰብ ከሁሉም በፊት ለዚህ አውነት ሊገዛ ያስፈልጋል። ከምንም በላይ ራሱን ለዚህ እውነት ታማኝ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ለዚሁ እውነት መሥዋዕት ለማድረግ ከራሱ ጋር የታረቀ ሊሆን ይገባል። አሁን ላይ የትግራይ ሕዝብ በተለይም፤ አዲሱ ትውልድ የሚፈልገው በዚህ እውነት የተገራ ዘመኑን የሚመስል እና የሚዋጅ መሪ ነው ።

በሰላማዊ መንገድ በአዲስ ሀገራዊ የፖለቲካ ባህል ትናንት ወደ ሥልጣን የመጡት ሌ/ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ከሌሎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር በመሆን የሕዝቡን የሰላም ጥማት ሆነ የትውልዱን ራስን የመሆን መሻት ተጨባጭ በማድረግ ሂደት ያለባቸውን ታሪካዊ አደራ በስኬት ለመወጣት ለዚህ የሕዝቡ እውነት ተገዥ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

በተለይም ጦርነት እና ግጭት የቱን ያህል አስከፊ እንደሆነ በተለያዩ የጦር አውድማዎች በተጨባጭ መታዘብ ለቻሉት ሌ/ ጄኔራል ታደሰ ፤ የሰላም ዋጋ የቱን ያህል ውድ እንደሆነ፤ ስለሰላም የሚከፈል ዋጋም ምን ያህል ትርጉም እንዳለው ነጋሪ የሚያስፈልጋቸው አይደሉም። ይህ የሕይወት ተሞክሯቸው ለትግራይ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ይታመናል!

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You