
ሰላም ለግለሰብ ፣ ለማኅበረሰብ ፣ ለሀገር ፣ ከዚያም አልፎ ለዓለም ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ አቅም ነው። ያለ ሰላም ሠብዓዊ የሆነው ፍጥረታዊ እድገት እንኳን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ እንደሚወድቅ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ከዚህም የተነሳ መላው ዓለም ለሰላም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ዓለም አሁን ላይ ከቀደሙት ዘመናት በተሻለ የሰላም አየር ውስጥ ትገኛለች።
ይህም ሆኖ ዛሬም ራስ ወዳድነት፣ ጽንፈኝነት ፣ ዳተኝነት ፤ ቡድናዊ እና ግለሰባዊ ተጠቃሚነትን የሚሸከሙ አስተሳሰቦች .. ወዘተ የዓለምን ሰላም እየተፈታተኑ ይገኛሉ። ሥልጣኔ እና ስልጡን አስተሳሰብ ችግሩን የመፍቻ ዋነኛ አማራጭ ተደርጎ ቢወሰድም ተጨባጭ እውነታው ግን አሁንም ስለ ሰላም የሚደረጉ ግለሰባዊ ፣ ማኅበረሰባዊ ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥረቶች ዘመኑን በማይመጥኑ ስንኩል አስተሳሰቦች እየተፈተኑ ነው።
እነዚህ ስንኩል አስተሳሰቦች በሚፈጠሩ መሳቶች እና ግራ መጋባቶች፤ ሁከት ፣ ግጭት እና ጦርነት በመላው ዓለም ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለከፋ መከራ እና ስቃይ እየተዳረገ ነው። እነዚህ ሕዝቦች እንደሰው የማይመጥናቸውን ሕይወት ከመኖር ባለፈም ነገዎቻቸው ተስፋ ቢስ እየሆኑ ነው። ችግሩ ከእነርሱ አልፎ የቀጣይ ትውልድ ዕጣ ፈንታ እየሆነ ያለበት ሁኔታም ሰፊ ነው።
በእርግጥ ሁከት ፣ ግጭት እና ጦርነቶች ባለባቸው አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘም ሆነ፤ እንደ ሰው ባላቸው ሠብዓዊ መሻት ፤ ለሰላም ያላቸው ፍላጎት ከፍ ያለ ቢሆንም ፤ በአንድም ይሁን በሌላ ፤ የችግሩ አካል ሆነው ወይም አማራጭ አጥተው፤ አንዴ ከእጃቸው የወጣውን ሰላም መልሶ በእጃቸው ለማስገባት የሚያደርጉት ጥረት ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ ያስገድዳቸዋል።
ይህ ደግሞ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንደ አዲስ የሚነገር እውነት አይደለም። በየዘመኑ የነበረውን ትውልድ ብዙ ያልተገባ ዋጋ ያስከፈለ፤ የታሪካችንን ሰፊ ምዕራፍ የያዘ ነው። ሕዝባችን ካለው መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች አኳያ ለሰላም ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጥ ነው። ስለሰላም የሚዘምር ሰላምን የዕለት ተዕለት የሕይወት መስተጋብሩ ዋነኛ አቅም አድርጎ የሚወሰድ ነው። ለዚህም በብዙ የተገዛ ነው።
ይህም ሆኖ ግን ፣ ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ዛሬም ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል የተገደደ እና በዚህም ብዙ ትናንቶች ያባከነ ፣ ለዛሬዎቹ የተሟላ ትርጉም ለመስጠት የተቸገረ ፣ ነገዎቹን በብሩህ ተስፋ ጠብቆ ለመቀበል ፈተናዎች የበዙበት ሕዝብ ነው። ተገንዘው ያልተቀበሩ ሙት ሃሳቦች በሚፈጥሯቸው ግራ መጋባቶች እና መሳቶች ዛሬዎቹን እስከ ተስፋቸው ለነዚህ ሙት ሃሳቦች ለመተግበር የተገደደ ነው።
ራስ ወዳድነት ፣ ጽንፈኝነት ፣ ቡድናዊ እና ግለሰባዊ ተጠቃሚነትን የሚሸከሙ አስተሳሰቦች ፤ ሆዳምነት እና ባንዳነት ፤ በሕዝብ ተስፋ እና መሻቶች መቆመር ፤ ሕዝብን እንደ ሕዝብ የፖለቲካ መቆመሪያ ካርድ አድርጎ መውሰድ ፤ በዚህም የሕዝብን ተስፋና ፍላጎት መናጠቅ ዛሬም እንደ ሀገር የሚፈታተነን ችግር ነው።
ችግሩን ትናንት ያስከፈለንን ዋጋ ቆም ብለን ማስተዋል አለመቻላችን ዛሬም እንደሀገር የዚህ ችግር ሰለባ ሆነናል። ስለ ሰላም በሚዘምር ሕዝብ መካከል ሆነን ለሰላም ባይተዋር የሆኑ፤ ከግጭት እና ከጦርነት ማትረፍ ይቻላል የሚል ስንኩል እስተሳሰብ በተሸከሙ ግለሰቦች እና ቡድኖች በሚፈጥሩት መቆሚያ ያጣ የሰላም እክል ሕዝባችን ዛሬም ያልተገባ ዋጋ እየከፈለ ነው ። የለውጥ መነሳሳቱም ሆነ ተለውጦ የመገኘት መሻቱም በብዙ እየተፈተነ ነው።
ከዚህ ሀገራዊ እና ማኅበረሰባዊ እውነታ ለዘለቄታው ለመውጣት ፤ ጦርነትን እና የጦርነትን አስከፊነት ፤ በሁለንተናዊ መንገድ ተረድተው ለሰላም ዋጋ ለመክፈል ፤ ለሀገር እና ለትውልዱ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገዎች ጭምር ኃላፊነት ወስደው ስለሰላም ዋጋ ለመክፈል ከራሳቸው ጋር መክረው በጽናት የሚቆሙ ብሄራዊ አርበኞች ያስፈልጉናል። ይህን አይነቱ አርበኝነት ትውልዶችን ከዘመን ጋር የማስታረቅ ተልዕኮ ያነገበ መሆኑ ጥኩረት የሚሻ ነው።
ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ላለፉት ሁለት ዓመታት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት በትግራይ ያለውን ችግር በሰላም ለመፍታት ከዚያም አልፎ ሰላምን ለማጽናት በቅንነት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ሲሠሩ ለነበሩት የክልሉ የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር ለአቶ ጌታቸው ረዳ ያቀረቡት ምስጋና የሚበረታታ ፤ ስለ ሰላም በቀጣይ ብዙ ጌታቸዎችን ማፍራት የሚያስችል ነው!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም