በታሪክ ከመቆመር ይልቅ ለመማር እንዘጋጅ !

ኢትዮጵያ በየዘመኑ በሚፈጠሩ የውስጥ አለመግባባቶች እና የውጪ ሃይሎች በብዙ ፈተና ውስጥ ለማለፍ የተገደደች ፤ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ባለቤት የሆነች ሀገር ነች ። ዜጎችዋም ፈተናዎቹን በላቀ የሀገር የፍቅር መንፈስ እና ከፍ ባለ መስዋእትነት በማሻገር የደመቀ ታሪክ ባለቤቶች ናቸው።

በእርግጥ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች የተለያዩ ፍላጎት ይኖራቸዋል ፤ ይህን ፍላጎቶቻቸውን ተጨባጭ ለማድረግ የሚሄድበት መንገድ በአንድም ይሁን በሌላ ዘመኑን የሚመስል እና በዘመኑ በነበረ እሳቤ የሚለካ ነው። ዘመኑን ሲሻገርም ለትውልዶች ማስተማሪያ ከመሆን ባለፈ የሚኖረው አሁናዊ አበርክቶ ብዙም የሚያነጋግር አይደለም።

ትናንቶች የተሠሩት የትናንቱ ትውልድ በደረሰበት የአስተሳሰብ ደረጃ ነው ፤ ዛሬ የሚገነባው ደግሞ በትናንት መሠረት ላይ ዛሬን በሚዋጅ የትውልዱ አስተሳሰብ ነው። ትናንት ዛሬ በነበረበት የጊዜ ትርክት ውስጥ ብቻውን በራሱ እንዳልቆመ ሁሉ ፤ ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ በራሱ የሚቆምበት መሠረት የለውም። ነገም ቢሆን ያለ ትናንት እና ዛሬ በራሱ ሊጸና የሚችል አይደለም።

እያንዳንዱ ትውልድ አዳጊ በሆነ ተለዋዋጭ ፍላጎቶች ውስጥ ይመጣል ፤ ያልፋል። ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት ነው። የሰው ልጅ ከዘመናት በፊት ጀምሮ በዚህ ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ ደርሷል። አሁን ያለው ትውልድም ፍጥረታዊ ጉዞው ብቻ ሳይሆን አሁን ያለበት የአስተሳሰብ ደረጃም የዚህ ሂደት አካል እና ውጤት ጭምር ነው።

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የብዙ ትውልዶች መንሰላሰል ውጤት ነች ፤ አሁን እንደሀገር ያለን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መስተጋብር ሆነ መስተጋብሩን የገዛው አስተሳሰብም የዚሁ ተጨባጭ እውነታ መገለጫ ነው። ይህንን ዓይናችንን ከፍተን በአግባቡ ማየት ካልቻልን ለአሁናዊ ችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ልናገኝለት አንችልም።

በተለይም ታሪክን ከመማሪያነት ይልቅ የፖለቲካ ካርድ አድርገው ያለአግባብ ለመጠቀም የሚሹ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች የጥፋት ተልእኮ አሸንፈን ለመሻገር ሆነ ፣ እንደ ትውልድ ከግጭት እና ከንትርክ ወጥተን የሚጠበቅብንን ሠርተን ለማለፍ ፤ ዛሬን ከትናንት እና ከነገ ጋር ፍጥረታዊ በሆነው መስተጋብራቸው ማየት እና መረዳት ይጠበቅብናል። ለዚህ የሚሆን አዲስ እይታም ያስፈልገናል።

ይህ አንድም አሁናዊ ሀገራዊ ፈተናዎቻችንን በጠራ እውቀት እና የአስተሳሰብ መሠረት ላይ ቆመን ለመሻገር፣ ከዛም አልፈን ነገን እንደ ትውልድ ለራሳችን ሆነ ለመጪ ትውልዶች ብሩህ እና ባለብዙ ተስፋ አድርገን ለመጠበቅ፤ ተስፋ ያደረግነውን ነገ በተጨባጭ የራሳችን ለማድረግ ይረዳናል።

ትናንት የተሠራው ትናንት በነበረው ትውልድ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ ነው ፤ ቀጣይ ትውልዶች አስተሳሰቡ በአንድም ይሁን በሌላ የፈጠረውን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ማዜም ሳይሆን ፤ ችግሩን በአደገ ዘመኑን በሚዋጅ አስተሳሰብ ማረም እና ወደ ቀጣይ የለውጥ ምእራፍ መሸጋገር ነው።

ኢትዮጵውያን እንደሀገር ከመጣንበት የረጅም ዘመን ትርክት አኳያ እያንዳንዱ ትውልድ ዛሬ ላይ ባለን ግንዛቤ መጠን የሚሰላ የራሱ ጥሩ እና መጥፎ የሚባል ትርክት አለው። የዛሬይቱ ኢትዮጵያም እንደ ሀገር የነዚህ ትርክቶች መሰላሰል ውጤት ነች። ትውልዱም ቢሆን እነዚህ ትርክቶች የፈጠሩትን ማህበረሰባዊ ማንነት የተላበሰ ነው።

የትኛውም ትውልድ ከትናንት ጋር በሚኖረው እሰጣ አገባ፣ ጊዜውን እና ጉልበቱን ከማባከን ፣ የነገ ተስፋውን ከማደብዘዝ ባለፈ የሚያስገኝለት ዘላቂ ተጠቃሚነት የለም። ነገሩ “የፈሰሰ ውሃ …” ከሚለው አባባል ያለፈ አይሆንም። ዘላቂ ተጠቃሚ የሚያደርገው ትናንትን እንደ ትናንት ተቀብሎ ፣ ከትናንት በአግባቡ መማር ሲችል ብቻ ነው።

ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት እንደ ሀገር ያጋጠሙን ችግሮች ሆኑ በነዚህ ዓመታት እንደ ሕዝብ የፈጠርናቸው የለውጥ መነቃቃቶች በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ የተገደዱት ፣ በታሰበው ደረጃ ፍሬ ማፍራት ያልቻሉት ከትናንት ጋር ከገባነው አሰጣ አገባ ጋር በተያያዘ ነው።

ትናንቶችን ዛሬ ላይ ባለ ፤ ዘመኑን ሊዋጅ በሚችል ያደገ አስተሳሰብ አርመን ከመጓዝ ይልቅ ፤ የትናንት ሀገራዊ “የታሪክ ጠባሳዎችን” አዋጭ የፖለቲካ ካርድ አድርገው ለመጠቀም በሞከሩ እና እየሞከሩ ባሉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ወጥመድ ውስጥ ገብተን ፤ ለስንኩል ተልእኳቸው ተጨማሪ አቅም እየሆንን ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ካለን ያደጉ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች አኳያ ከኛ አቅም በላይ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮች የሉንም ። በተለይም አሁናዊ ችግሮቻችን ፣ ትናንትን ታሳቢ አድርገው የሚነሱ ፣ ትናንትን ባልተገባ መንገድ ከማየት እና ከመገምገም የሚቀዱ ከመሆናቸው አኳያ ለታሪክ ያለንን አተያይ በመለወጥ ብቻ በቀላሉ ልንሻገራቸው የምንችልበት እድል ሰፊ ነው።

ይህ ትውልድ ከየትኞቹም ትውልዶች በተሻለ መልኩ ትናንቶችን አርሞ፤ ዛሬ እና ነገን ለራሱ እና ለመጪ ትውልዶች ብሩህ ማድረግ የሚያስችል የታሪክ እጥፋት ላይ ነው። ትናንቶችን ብቻ ሳይሆን ያልተገሩ ትናንቶች የቱን ያህል የከፋ ዋጋ እንደሚያስከፍሉ በተጨባጭ ማየት የቻለ ነው።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተግዳሮት በመሆን የለውጥ ተስፈኛ የሆነውን ሕዝባችንን ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉት ያሉት ፈተናዎቻችን ፤ ትናንትን በዛሬ አእምሮ መገምገም እና በግምገማው ውጤት ታምኖ ሰልፍ የማሳመር፤ ከታሪክ ከመማር ይልቅ የመቆመር ያልተገባ የፖለቲካ አካሄድ መከተል ነው። ከዚህ ያልተገባ መንገድ መውጣት ለጀመርነው ለውጥ ስኬት “አልፋ እና ኦሜጋ” ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You