በአትሌቲክስ ስፖርት በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ታሪክ በመሥራት የአገርን ስም ማስጠራት የቻሉ ጀግኖች አስታዋሽ አጥተው ቆይተዋል። ይህም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን የአገር ባለውለታዎችን እጀ ሰባራ አድርጓል በሚል ለሰላ ትችት መዳረጉም ይታወቃል። ይህም አገራቸውን በአትሌቲክሱ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረጉ ጀግኖችን ማስታወስና መዘከር የማይሆንለት እስከመባል አድርሷትም ነበር።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም ከሳምንታት በፊት «የአገር ባለውለታዎችን ፍውሶ ሳይሆን ገድሎ የመፎከር ብሂል!» በሚል ርዕስ የቀድሞውን አትሌት ሸምሱ ሀሰንን መሰረት በማድረግ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ባለውለታዎችን የመርሳት ብሂል ለማመልከት መሞከሩ ይታወሳል።
ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ባለውለታዎቹን ባለማስታወስ፣ ባለመደገፍ፣እውቅና ባለመስጠት ብዙ ቢባልበትም ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ቆይቷል። ይሁንና ከሰሞኑ የተሰማው ዜና ግን «ፌዴሬሽኑ ልብ ገዛ» የሚያሰኝ ሆኗል። የአገር ባለውለታዎቹ ህይወት ቀውስ ውስጥ ሳይገባ በፊት ድጋፍ ባለማድረጉ ሳቢያ በተደጋጋሚ ይነሳበት ከነበረው ወቀሳ የሚያድነው ተግባር መፈጸም መጀመሩ ተሰምቷል። ይህም ተግባሩ በተደጋጋሚ የሚነሳበትን ወቀሳ በጽኑ ፈትሾ ራሱን ወደማስተካከሉ እንደገባ ያመለከተ ሊባል ይችላል። ፌዴሬሽኑ ትናንት ከሠራው ስህተት በመማር፤ሌላ አዲስ ታሪክ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ከቀናት በፊት በፈጸመው በዚህ ተግባር አስመስክሯል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጤና መታወክ ለደረሰባቸው ለአምስት የቀድሞ አትሌቶች ከ125 ሺ ብር በላይ ድጋፍ ሰጥቷል፤ ይህም የአገር ባለውለታዎቹ ከገጠማቸው የጤና ቀውስ ማገገም እንዲችሉ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡ የአገር ባለውለታዎቹ የገንዘብ ድጋፉን የተረከቡት ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አትሌት ደራርቱ ቱሉ እጅ ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገላቸው የቀድሞ የዕርምጃ ተወዳዳሪው አቶ ሸምሱ ሀሰን፣ አትሌቶቹ ባሻ ፍቅሩ፣ ደገፋ መለሰ ፣ፈይሳ ፀጋዬ ሰኚ እንዲሁም ሽብሩ ረጋሳ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አንጋፋ ባለውለታ አትሌቶቹ ከሜልቦርን እስከ ሞስኮ አሎምፒክ ከ100 ሜ. እስከ ማራቶን፣ በዕርምጃ እንዲሁም በጦርና ዲስከስ ውርወራና በከፍታና ርዝመት ዝላይ ውድድሮች ሃገራቸውን በዓለም አደባባይ የወከሉ ናቸው። ከድጋፉ በኋላም ፕሬዚዳንቷ ለእነዚህ ባለውለታ አንጋፋ አትሌቶች ምሣ የገባዙ ሲሆን፣ ባለውለታዎቹም አስታዋሽ በማግኘታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ደስታ ዕንባ እየተናነቃቸው ገልጸዋል።
አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስፖርቱ የአገር ባለውለታዎችን ለማሰብ የጀመረው እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝና ሊቀጥል የሚገባ ነው። ይሄንኑ ጅምር ተግባሩን በማጠናከር በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙትን የቀድሞ አትሌቶችን በማፈላለግ በዚሁ ተግባር ርቆ መጓዝ ይጠበቅበታል። ፌዴሬሽኑ የአገር ባለውለታዎችን ወደ ጎን ከመዘንጋት ወጥቶ ወደፊት መጓዝ ይችል ዘንድ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊኖር እንደሚገባም መዘንጋት የለበትም።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011
ዳንኤል ዘነበ
Your positive and uplifting words are like a ray of sunshine on a cloudy day Thank you for spreading light and positivity in the world