ታኅሣሥ 24ቀን 2011 በአማራና በትግራይ ክልል እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረገው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ከአንድ ዓመት በኋላ በሜዳቸው ሊከናወን መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማስታወቁ ይታወሳል። በዚሁ መሰረትም በፕሪሚየር ሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት ዕሁድ ታኅሣሥ 28 ቀን 2011 ዓ.ም በትግራይ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከፋሲል ከተማ ለማድረግም ቀን ተቆርጦለታል። የብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ በብዙ መልኩ መነጋጋሪያም ነበር። ከስፖርት ቤተሰቡ በመሻገር በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ አትኩሮት የተቸረውና በስፋት ሃሳብ እንዲንሸራሸር ያደረገም ክስተት ነበር። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በስፖርታዊ ጨዋነት ችግር እየታመሰ መምጣቱ በይፋ እየተንጸባረቀ ያለው ውድድሩ ከስፖርታዊ መድረክነቱ እያፈነገጠ በመገኘቱ ነው፡፡ ስፖርታዊ ጨዋነት ከስፖርታዊ ይዘቱ እየወጣ የብሄር መልክ መያዙ ችግሩ አሳሳቢ እየሆነ እንዲመጣ አድርጎታል።
ችግሩ ሁለቱ ክልል ክለቦች ጨዋታ ወቅት ጎልቶ ታይቷል። በዚህ ምክንያትም ነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የአማራና የትግራይ ክልል ክለቦች በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወቱ ለመወሰን የተገደደው። ለዚህም በ2010 ዓ.ም የነበሩ የሁለቱ ክልል ክለቦች ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም መደረጋቸው በአብነት ሊጠቀስ ይችላል። ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ የችግሩ ሰንኮፍ ባለመነቀሉ በዚህ መልኩ ሲጓዝ ቆይቶ በቅርቡ ግን እገዳውን አንስቷል። ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ስጋት በነበረበት ወቅት ያስተላለፈውን ውሳኔን ማንሳቱ፤ ባለፈው በትግራይ ስታዲየም የሚደረገው የሁለቱ ክልል ክለቦች ጨዋታ በከፍተኛ ጉጉት እንዲጠበቅ አድርጓል።
በፕሪሚየር ሊጉ የሚታየው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር መግዘፍ፤ እግር ኳሱ ፖለቲካዊ መልክ በመያዙ ለጸጥታ ስጋት ፈጥሮ እንደመቆየቱ ትልቅ ትኩረት እንዲሰጠው ሆኗል። በተለይ ደግሞ በአማራና በትግራይ ክልል እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረገው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ከአንድ ዓመት በኋላ በሜዳቸው እንዲካሄድ መወሰኑ ሊፈጠር የሚችለውን ለመገመት አዳጋችም እንዲሆን ያደረጎም ነበር።
በብዙ ስጋት በጥቂት ተስፋ የታጀበው የፋሲል ከነማና ወልዋሎ አዲግራት ጨዋታ ለማከናወን ዓፄዎቹ መቀሌ ሲገቡ ምን ዓይነት አቀባበል ይደረግላቸው ይሆን? የልዑካን ቡድኑም ሆነ ደጋፊዎቹ መቀሌን ሲረግጡ ምን ዓይነት ስሜት ያንጸባርቁ ይሆን? የሚሉ ምናባዊ ጥያቄዎች መኖራቸው እርግጥ ነው። ይህን ትዕይንት ከማመልከታችን በፊት አንድ ሁነት ማስታወስ ያስልጋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሳምንት በፊት በእጅጉ አነጋጋሪ ጉዳይ ይከሰታል። በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስምንተኛ ሳምንት ከተከናወኑት ጨዋታዎች ሁለቱን ኃያላን የሸገር ደርቢ የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች አገናኝቷል። በሁለቱ ክለቦች መካከል ያለው የተፎካካሪነት የስሜት ጥግ እጅጉን የበዛ መሆኑ ጨዋታውን ተጠባቂ አድርጎትም ነበር።
እግር ኳስ ሜዳዎች የጸብና አንባጓሮ መፈልፈያ መቼት እየሆኑ መምጣታቸውም ሌላው ጨዋታው ተጠባቂ እንዲሆን ያደረገ ጉዳይ ነው። የሁለትን ክለቦች ጨዋታ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በመዘንጋት የብሄር ስሜትን በማላበስ የግጭት መንስኤ እየሆነ የመጣው ኳስ ዛሬ ደግሞ ምን ያሳየን ይሆን የሚለውን ስሜት አብሮ ያዘለም ነበር።
ይህን የስፖርቱ ስር የሰደደ ችግር ሃይ ለማለት፣ስፖርት የሰላም እንጂ የጸብ መናኸሪያ መሆን እንደሌለበት የኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር ያስተላለፈው መልዕክት ትልቅ ስፍራ አግኘቷል፡፡ በሰላም ሚኒስቴር አማካይነት እየተስተጋባ የሚገኘው የሰላም ዘመቻ፣ በሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ በሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ያለም ፀጋይ፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሒሩት ካሰው እና በሌሎችም ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና በክለብ አመራሮች ታጅቦ ልብ በሚነካና ለሰላም ስለሰላም ተብሎ የቀረበው ጥሪና ፀሎት ስታዲየሙን እስካፍንጫው የሞላውን የሁለቱን ክለቦች ደጋፊ ልብ አቅልጦ፣ ፀብ ያለሽ በዳቦን ወደ መተቃቀፍ ቀይሮ የአብሮነት ዝማሬ እንዲስተጋባ አድርጓል፡፡
የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በስፋት ከሚታይባቸው ጨዋታዎች መካከል የሸገር ደርቢ በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል። በእርግጥ የጊዮርጊስና የቡና ደጋፊዎች ቢጋጩ እንኳ በጎሳ ወይም በዘር ተቧድነው ባይሆንም፣ የሚኒስትሮቹ ‹‹የሰላም ያለህ›› ጥሪ፣ ተንበርክከው ስለሰላም ያቀረቡት ተማጽኖ አንጀት የሚበላ ነበር፡፡ የሁለቱን ክለቦች ደጋፊዎች የባላንጣነት ስሜት አስረስቶ በፍቅር ተጀምሮ በፍቅር በመጠናቀቅ ለሰላም ጥሪው ዋጋ ሰጥቶ አልፏል።
ይህ ተግባር በተለይ በአማራና ትግራይ እንዲሁም በዚህ ዓመት የተጀመረው በደቡቦቹ ደርቢዎች ሲዳማና ወላይታ ዞኖች ወደ ብሔር የሚወስድ የሜዳ ውስጥ ግጭት በሚስተዋልባቸው ጨዋታዎች ወቅት ቢደረግ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን አስተያየት እየተሰነዘረ ይገኛል፡፡
በሰላም እጦት ሳቢያ መደበኛ መርሐ ግብራቸውን ማከናወን ከተሳናቸው በርካታ ክለቦች መካከል የአማራና ትግራይ ክለቦች ግንባር ቀደም ናቸው። የስፖርቱን መልክ የብሄርና የጎሳ ካባ በማላባስ የግጭት ትዕይንቶች በሁለቱ ክልል ክለቦች መካከል ሲንጸባረቁ ቆይተዋል።
የኢትዮጵየ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ፖለቲካዊ መልክ እየያዘ መምጣቱን ተከትሎ በሁለቱ ክልል እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረገው ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ እንዲሆን ውሳኔ እስከማስተላለፍ መድረሱ ይታወሳል፡፡ የፌዴሬሽኑ የሊግ ኮሚቴ ለአንድ ዓመት ጸንቶ የቆየውን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ ታኅሣሥ24ቀን 2011 ባሳለፈው ውሳኔም በአማራና በትግራይ ክልል እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረገው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በሜዳቸው የሚያደርጉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ ልዑካን ቡድንና ደጋፊዎች መቀለ ከተማ የተገኙትም ይሄንኑ ተከትሎ ነበር፡፡ በብዙ ስጋት በጥቂት ተስፋ የተጠበቀው የሁለቱ ክልሎች ክለቦች ጨዋታ በሜዳቸው መደረግ የመጀመር ትዕይንት ለሀገሪቱ እግር ኳሱ ትዕንሳኤ ፤ለሁለቱ ክልሎች የአብሮነት ስሜት ወደ አሸናፊነት እንዲመጣ የራሱን ሚና ይጫወታል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ እንግዳውን ክለብ ፋሲል ከነማን በልዩ ፍቅርና ወንድማዊ ስሜት በመቀበል የስጋት ጥያቄዎችን በበጎ በመመለስ ነበር የተጀመረው። በስታዲየም የታየው ሁኔታ በተመሳሳይ የስጋቱን መጠን ከዜሮ በታች ያደረገ ነበር።
ዓፄዎቹ በመቀሌ ኤርፖርት ፣በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፤ በመቀሌ 70 እንደርታ ደጋፊዎች እና የክለብ አመራሮች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በጨዋታው ዕለትም ተመሳሳይ ሁኔታ ታይቷል፡፡ ከአፍ እስከ ገደፍ የሞላው የትግራይ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በፍቅር የተሞሉ ጣዕመ ዝማሬዎችንና የአንድነት ቅኝቶች የተሰሙ ሲሆን፣ይህም በሁለቱ ደጋፊዎች መካከል ትስስር እንዲፈጠር አድርጓል።
በዕለቱ የሰላም ሚኒስቴር መልዕክተኞች ፣ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻውን ጨምሮ የእግርኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡ ጨዋታውም ስለ ሰላም የሚሰብኩ ባነሮች፤ ባንዲራዎች እና ቲሸርቶች ድምቀትን እንዲጎናጸፍ ተደርጓል፤ ጨዋታውም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተጠናቋል።
ጨዋታውም ያለምንም ግብ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ስፖርታዊ ጨዋነትን ጠብቆ የተካሄደ መሆኑንም የክለቦቹ አሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል። «ውድድሩ ፍፁም ስፖርታዊ ጨዋነት የተሞላበት ነበር» ያሉት የፋሲል ከተማ አሰልጣኝ ሀብታሙ ዟለ በመቀሌ ስታዲየም የታየውን ስፖርታዊ ጨዋነት በጎንደርና ሌሎች ከተሞች ለመድገም እንደሚሠሩም አስታውቀዋል።
የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ አሰልጣኝ ጸጋይ ኪዳነማርያም በበኩላቸው «ጨዋታው ጥላቻ ሳይሆን ፍቅርና አንድነት የታየበት ነበር» ብለዋል። ጨዋታውን የመሩት የፌዴራል ዳኛ አክሊሉ ደግፌ «ጨዋታው ያለምንም ችግር የተጠናቀቀ በመሆኑ ደስተ ተስምቶኛል» ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ ያስጀመሩት የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት አፋ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ሲሆኑ በጨዋታው በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በመታደም ለድባቡ ሞገስ ሆነውት አምሽተዋል።
ትዕይንቱ በዚህ ብቻ አልተቋጨም ነበር። የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ የቡድን አባላት በገዛ ገብረ ሥላሴ የባህል እና ምግብ አዳራሽ የሁለቱም ተጫዋቾች በተገኙበት የእራት ግብዣ አድርገዋል። የሁለቱ ክለቦች ፍጥጫም በተለያዩ መልኮች ሲገለጽ የነበረውን ፍርሽ ያደረገም ሆኗል።
የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አደና ፋሲል ከነማ በዛሬው ዕለት የጥሎ ማለፍ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ይህ ጨዋታም በተመሳሳይ ሰላም የሰፈነበት ሆኖ እንዲጠናቀቅ ክለቡም ሆነ ደጋፊ ማህበሩ የተለመደ የማስተባበር ሥራቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ በመቀሌ የተደረለት ልዩ አቀባበል ወደ ከተማችን ጎንደር ስትመጡ ትልቅ ሥራ እንዳለብን ያስገነዘበ እንደሆነ እየተረዳን ለተደረገልን እንክብካቤ ሁሉ የመቀሌን ደጋፊዎች ጨምሮ ምስጋናችን ላቅ ያለ ነው ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።
በአማራና ትግራይ ክልል ክለቦች መካከል የነበረውን የገለልተኛ ሜዳ ጨዋታ በመቀልበስ በመቀሌ ሜዳ ጨዋታቸውን በሰላም ጀምረው ማጠናቀቃቸው ፋይዳው ከፍተኛ ነው። ይህም የስፖርታዊነት ችግሩ ፖለቲካዊ መልክ መያዙን ተከትሎ ውሳኔው ትክክል እንደነበር አስመልክቷል ።
በአማራና በትግራይ ክልል እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚደረገው ጨዋታ በሜዳቸው እንዲሆን መደረጉም ትክክለኛና ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ ያስብለዋል። የአገራችን የፖለቲካ ትኩሳት በተለየ መልኩ በሁለቱ ክልሎች ዘንድ ጎልቶ መታየቱ ብዙዎችን ማሳዘኑ ይታወሳል፡፡ በተለይ ባሳለፍነው የውድድር ዓመት የሁለቱ ክልል እግር ኳስ ክለቦች ጨዋታዎች የዚህ ስሜት መወጫ መድረክ በመሆን የችግሩ አካል ነበሩ።
እነዚህ ሁኔታዎች የሁለቱ ክለቦችን የስታዲየም ቆይታዎች አስጊና አሳፋሪ መልክ እንዲይዙ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ነግር ግን ከቀናት በፊት የሆነው ይሄንኑ ያሸነፈ ነበር። ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘረውን «የስጋቱን አድማስ አጥብቦ የተስፋውን አድማስ አስፍቷል።» የዓፄዎቹና የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጨዋታ በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት ተጀምሮ መጠናቀቅ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው ባይነን።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011
ዳንኤል ዘነበ