አናርኪዝም እና ዴሞክራሲ የሚሉትን ሁለት ቃላት ባሰብኩ ቁጥር በውስጤ የሚፈጥሩብኝ ጨፍጋጋ ስዕላዊ ገለጻዎች አንዱ የፍርሃት አንዱ የጥርጣሬ መንፈስ እያረበቡ ነው። “ዴሞክራሲ” የሚለው ቃል ነጋ ጠባ የፖለቲከኞቻችን የአፍ ማሟሻ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሰማሁት ቁጥር ይቸክብኛል። ለምን ቢሉ ከስሙ ጋር እንጂ ከግብሩ ጋር ሀገሬ መቼ ተዋወቀችና። ስምን መልአክ ያወጣዋል የሚሉት ብሂል ከዴሞክራሲው ደምና ሥጋ ጋር ተዋህዶ በሀገሬ ምድር ሲራመድ ባስተውል ባልከፋኝ ነበር። ዳሩ ፍየልና ቅዝምዝም ማዶ ለማዶ እየተባረሩ እንዴት ይሆናል።
ከአሁን ቀደም በዚሁ በአዲስ ዘመን ቋሚ የመተከዣ አምዴ ላይ “ኦ ዴሞክራሲ በስምህ ስንት ግፍ ተሠራ” በሚል ርዕስ የብዕሬን ትሩፋት “ይድረስ” በማለት ለንባብ ማብቃቴ ይታወስ ይመስለኛል። አንባቢው ጹሑፉን አላነበበው ከሆነ ወይንም ማንበቡን ረስቶትም ቢሆን የርዕሱ ጨኸት ራሱ ብዙ ስለሚናገር መልዕክቱን ለማድረስ አይሰንፍም። በአጭሩ ማስታወስ ካስፈለገ ግን ፖለቲካችን እንክርዳድ አናቱ ላይ እንደወጣ ሰካራም ከወዲያ ወዲህ እየተላጋ ያናጋቸውንና የሰባበራቸውን ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች እየጠቃቀሱ መከለሱ እጅግም የሚያዳግት አይደለም።
በንጹሃን የደም ቅብ የቀላውን “አናርኪዝም” የሚለውን የዘመነ ደርግ የጭካኔ መገለጫ ቃል ግን አንኳንስ ደጋግሞ ሊጻፍበት ቀርቶ ቃሉን መስማቱ ራሱ ነፍስንና ሥጋን ያሳምማል። ዝናውም ቆሌውም ከሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት የተገፈፈውን ይህንን የባዕድ ቃል ዛሬ ለማስታወስ የተገደድኩት በውድ ሳይሆን የኅሊና ጨኸት ስላስገደደኝ ብቻ ነው። እኮ ለምን? አሰኝቶ ለተጠያቂነት ከዳረገኝ ምክንያቴ ቃሉና የቃሉ ድርጊት ዛሬም እንደ ትናንቱ እንደ እባብ ገላ ያረጀና ያፈጀውን ቆዳውን ገፎ ነፍስ ሲዘራ በማስተዋሌ አሳስቦኝ፣ አስግቶኝና አስፈርቶኝ ጭምር ነው።
“ነገርን ከሥሩ ውሃን ከጥሩ” እንዲሉ ክፉ ትርጉም የተሸከመው ይህ “አናርኪዝም” የሚሉት የቃል አራሙቻ (ቃልንም እንደ ክፉ ሰው በቃል ለመሸንቆጥ መብት ስላለን) በየትኛው የዓለማችን ቋንቋ ውስጥ ተወልዶና ጎልምሶ አገልግሎት ላይ ሊውል እንደቻለ ጥቂት ወደ ኋላ ተንደርድሬ የት መጣውን ለአንባቢያን ለማስተዋወቅ ልሞክር።
“anarchia” የሚለው ቃል የተገኘው ከጥንታዊው የግሪክ ቋንቋ ሲሆን በእንግሊዘኛ የተሰጠው ብያኔ “The state of a people without government`” የሚል ሲሆን (an=without + archon=leader) ወደ ቋንቋችን ብንመልሰው “መንግሥት አልባ የሕዝብ ሀገር” ወይንም “መሪ አልባ ሀገር” ብለን ልናጣቅስ እንችላለን። ይሄው ቃል በዘመነ ደርግ እንደ ወረርሽኝ ከሰው ሰው በቅብብሎሽ እየከነፈ በሺህ የሚቆጠሩ የሀገሬን ንፁሃን ወጣቶች የደም ግብር እንዳስከፈላቸው ሦስት ዐሥርት ዓመታት ወደ ኋላ ብናፈገፍግ ታሪኩን በሚገባ መረዳት እንችላለን። ቃሉ ወደ እኛ ቋንቋዎች ቤትኛ ሆኖ ተዳብሎ የነበረው አመፀኛ፣ ፀረ አብዮተኛ፣ እምቢኝ ባይ፣ ሥርዓት አልበኛ ወዘተ. የሚሉ የጭካኔ ቀስቃሽ ጽንሰ ሃሳቦችን ተሸክሞ ነበር።
በወቅቱ በወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ላይ ያመጹ ዘመነ አቻዎቻችን “አናርኪስት ወይንም ፀረ አብዮተኛ” እየተባሉ በየሜዳው ደማቸው ደመ ከልብ ሆኖ ሲፈስ ቆመን እንባችንን እያዘራን በድናቸውን እንኳ መቅበር ተስኖን ተሰናብተናቸዋል። “የአንድ አብዮተኛ ደም በሺህ አናርኪስቶች ደም ይመነዘራል” እየተባለ በጨካኞች ሲፈከር የነበረውም ከስብዕና ባህርያት ወደ አውሬነት ዝቅ ባለ የጭከኔ ተግባር ታጅቦ ነበር።
“አናርኪስት” እየተባሉ ከየትምህርት ቤቶቹ እየታፈኑ የተወሰዱና ከሰላማዊ ቤታቸው ተጠልፈው ደብዛቸው የጠፋ፣ በየአውራ ጎዳናዎችና አደባባዮች ላይ “ቀይ ሽብር ይፋፋምብኝ” የሚል መፈክር እንዲያነግቡ ተደርገው በጨካኞች ጥርስ የተላመጡ ጓደኞቻችን የኢትዮጵያ ልጆችን የምናስታውሰው ዓይናችን ብቻ ሳይሆን ልባችንም ጭምር ዛሬም ድረስ እያነባ ነው።
ያ መራር ግፍ የተገለጸበት ቃል ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ዛሬም ሥርዓት አልበኝነትን ተጎናጽፎ ሲያቆጠቁጥ ማስተዋል ያስደነግጣል ብቻ ሳይሆን ያስፈራልም። የቁጥቋጦው ዘር ወደ መላ ሀገሪቱ ተስፋፍቶ ስንመለከትም “ቃሉ” ዳግም እንደምን ነፍስ ሊዘራ እንደቻለ ለማሰላሰል እንኳ ፋታ ሳናገኝ ነበር። እንደ ሀገር በአናርኪዝም መንፈስ ለሁለተኛ ጊዜ ደም የተቀላቀለበት እንባ እንድናነባና የሾህ አክሊል በነፍሳችን ላይ እንዲነግስ ለምን እንደፈቀድንለት ማሰቡ በራሱ ያልተፈታ ዕንቆቅልሻችን ሆኗል።
በሀገራችን ብልጭ ያለው የለውጥ ፋና በምንም ዓይነት ሁኔታ መልኩን በዴሞክራሲ ማስክ በሸፈነ የአናርኪዝም ተግባር እንዲጨነግፍ እንደማይገባ ጸሐፊው በጽኑ ያምናል። ለውጡን ነውጥ እየተፈታተነው መሆኑ ባይካድም ፖለቲከኞችና ሴረኞች በሚካድሙለት የአፋዊ ዴሞክራሲ ጥላ ሥር ተሸሽጎ ክፉው የአናርኪዝም ዛር ከቁጥጥር ውጭ ወጥቶ በምድራችን ላይ እንዳይሰለጥን በየፊናችን የዘብ ተራ ሕዝቡንና ሀገሪቱን ልንጠብቅ ግድ ይሏል። ከብርሃን ውጋጋን ይልቅ ጨለማን የሚናፍቁት ፖለቲከኞቻችን ምን ለማትረፍ የአመጽ ሰበብ እንደሚሆኑ ማሰቡ በራሱ ስሜትን ያናውጣል።
አናርኪዝም በአዲስ ፋሽን በምድራችን ላይ መንገሥ የጀመረው ሕገ ወጥነትንና ለውጡን ለማደናቀፍ በሚሸረብ የሤረኞች ሤራ ብቻ ሳይሆን የደም ግብር እያስከፈለን ጭምር ነው። መጠኑ ይብዛም ይነስ የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በአኬልዳማ መንፈስ የተለከፈ ይመስላል። ግጭት፣ ሞት፣ መፈናቀል እንደ ተራ ወሬ የሚወራበት ደረጃ ላይ መድረሱን ስናይ ተስፋችን ይወድቃል።
ከአሁን ቀደም ያልተሞከሩ በርካታ ሀገራዊ የአናርኪዝም የጥፋት ሤራዎችና ውድመቶች ነፍስ ዘርተው በአደባባይ ሲጋልቡ እያስተዋልን ነው። የአናርኪዝም ፈረስ ሆኖ የሚጋለብበት ጌኛ ደግሞ ስሙን እንጂ ግብሩን ያላየነው ዴሞክራሲ መሆኑ ነው።
“ዴሞክራሲ – እኩልነት የሰፈነበት የሕዝብ አስተዳደር” መሆኑ ቀርቶ “ጥፋት የሚታጨድበት የአናርኪዝም መስክ” መሆኑ በእጅጉ ያሳስባል። ማንም ሰው የሃሳብ ልዩነት ኖሮት ቢከራከርና ቢያከራክር መብቱ ነው። የእኔ ሃሳብ አልተደመጠም ወይንም አልተከበረም ብሎ ማኩረፍና ከእንቅስቃሴ መገታትም የዚያንው ያህል መብት ነው።
“የሕዝብን የጋራ መብት አዋርዶ የእኔ ብቻ ካልሆነ” ብሎ ለጠብ፣ ለግድያና ለጥፋት ማቀድና ማስተባበር ግን “የዴሞክራሲ መብት” ሳይሆን የአናርኪዝም መገለጫ ስለሆነ ዳግም “እንጨራረስ አዋጅ!” በኢትዮጵያ ምድር ሊፈጸም ቀርቶ መታሰብ አንኳ የሚገባው አይደለም።
የዛሬው የሀገራችን አናርኪዝም መገለጫው ብዙ ነው። ሕዝብን እየተሳደቡ መፎከር እንደ ቀላል ታይቷል። ሰውን በአደባባይ ቀጥቅጦ መግደል የዱር አውሬ ግዳይ ጥሎ እንደ ማቅራራት የቀለለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ሕዝብን አፈናቅሎ እርቃን መስደድ ጀብድ ሆኖ ተቆጥሯል። “እኔ ነኝ ያለ!” እንዲል ዜመኛው እየፎከሩና ጃሎ መገን እያሉ ቤተ እምነቶችን በእሳት መለኮስ ጧፍ ከማቀጣጠል፣ ወይንም ኩራዝ ከመለኮስ የቀለለ ድርጊት ሲሆን ይስተዋላል።
የሕዝብ አውራ ጎዳና ዘግቶ “ወንድ ከሆንክ እለፍ!” እያሉ መፎከር፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ተስፈኛ ወጣቶች አፍኖ በመውሰድ የቦኩ ሃራምን ድርጊት በኢትዮጵያ ምድር መተግበር “አናርኪዝም ሰፍኗል” ማለቱ ብቻ በሚገባ ላይገልጸው ይችላል።
ቀደም ሲል ለሕዝብ ልዕልናና አርነት ጥብቅና እንደቆሙ አምነን ስናጨበጭብላቸው የነበሩ ባለ መልከ ብዙ ስብዕና አንዳንድ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ጭምብላቸው ሲገለጥ ዋነኞቹና ከዘመነ ደርግ የባሱ የከፉ “የግፍ ኮሮጆ” እና ፀረ ለውጥ ሆነው ማስተዋል ምንኛ ኋላ መቅረት ነው?
በእሳቸው ስር ያሰለፏቸው ወጣቶች ለሰላም እየዘመሩ የሕዝብን ፍቅር እንዲማርኩ ከማሰራት ይልቅ ዱላና ቆንጨራ አሲዞ “ዝመት! ተዋጋ! ግደል ተጋደል!” እያሉ መቀስቀስና ማስቀስቀስ ምን ስያሜ ሊሰጠው እንደሚችል ግራ ያጋባል። “አናርኪዝም” ብሎ መፈረጅም ለተግባሩ በእጅጉ ያንስ ካልሆነ በስተቀር የሚያንስ አይሆንም።
መንግሥትም ቢሆን እንደ አኩራፊ ታዳጊ ሕጻን ከሕዝብ ጋር እልህ መጋባቱን ትቶ ለብዙኃኑ ጥያቄና ኡኡታ ተገቢውን ምላሽ በተገቢው ጊዜ መስጠት እንዳለበት ተደጋግሞ ተጩኾበታል፣ በአክብሮትም ተነግሮታል። ሕዝብ ሁሌም በእጥረትና በጉድለት እያማረረ ብሶቱን ሲገልጽ መንግሥት ደግሞ በፊናው “ቅብጠት ካልሆነ በስተቀር ምን ጎድሎባችሁ ትጮኻላችሁ፤ ምንስ ጎድሎባችሁ ታጉረመርማላችሁ” እያለ ቢሳለቅ ዕድሜውን ከማሳጠር ውጭ ይህ ነው የሚባል ትሩፋት አያተርፍም።
ዛሬ በየአቅጣጫው የሚስተዋለው አናርኪዝም ብዙ ትምህርት ሰጥቶን እንደሚያልፍ እየተገለጠልን መጥቷል። በሚያራምዱት ሕዝባዊ አቋም ምሳሌያችን ሆነው ወህኒ ቤት ተወርውረው የነበሩና በእስራት ዘመናቸው ሲዘመርላቸው የነበሩ ፅኑዓን የከርቼለው የብረት በር በሕዝብ ትግል ተገንጥሎና የእጃቸውም ሰንሰለት ተበጣጥሶ ነፃ ከሆኑ በኋላ ከእንቅስቃሴያቸው እያስተዋልን ያለነው ኮሜዲና ትራዤዲ በእጅጉ ለግርምትና ለትዝብት የሚዳርግ ነው።
ሆ! ብለን ለነጻነታቸው የጮኽነውና የሕዝብ ልጆች ብለን ያሞካሸናቸው ግለሰቦች እንደ ጠማማ ቀስት ተገልብጠው ሀገር ወደማተረማመስና ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨታቸውን ስናስተውል በእጅጉ እናፍራለን። ሀገር ይመራሉ፤ እኛንም ከኋላ ያስከትላሉ ብለን እንዳልደመደምን ሁሉ ዛሬ ዛሬ ግን ቀን ወጣልን ብለው በተውሳክ ንግግራቸውና በተመረዘ ተግባራቸው እየከፋፈሉ ሲቃረጡንና ሲያጋጩን እንኳን ሀገርና ራሳቸውንም የመምራት ብቃት እንደማይኖራቸው በሚገባ ተረድተን አንቅረን ተፍተናቸዋል።
አናርኪዝም ትርፉ ጥፋትና እልቂት እንጂ በጎነት የለውም። “እባብ ያየ በልጥ በረየ” እንዲሉ በምናየው ሁሉ በርጋጊ የሆንነው የትናንቱ ክፉ ጠባሳ ዛሬም መልኩን ቀይሮ ሲያመረቅዝና ከትናንት በከፋ ሁኔታ ሲያስለቅሰን ስላስተዋልን ነው። በስመ ዲሞክራሲ አናርኪዝም ሊፋፋ የቻለውም የውጭው ኃይል አቅሙ ከመንግሥት አቅም ስለበለጠ ሳይሆን መንግሥት በብዙ ጉዳዮች “ምን እንዳያመጡ ነው!” የሚል ፍልስፍና መርሁ ስላደረገ ይሆንን እያልን በማጉተምተም ቀናችንን እያጨፈገግን ውለን እንገባለን። የሰቀቀን ውሏችን ውሎ ከተባለ። በእንቅፋት መመታት ያለና የነበረ ነው። ትናንት ያደናቀፈን የድንጋይ እንቅፋት ደጋግሞ ካደናቀፈን ግን እንቅፋቱ ድንጋዩ ሳይሆን ተደንቃፊው ራሱ ነው። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)