አንዳንድ ነገሮች ሲለመዱ ሕይወት ይሆናሉ። አንድን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ስናየው ‹‹ምፅ›› ብለን ከንፈራችንን በመምጠጥ ‹‹ለካ እንዲህም ይኖራል›› እንላለን። እንደዚያ አይነት ተመሳሳይ ነገር ሲያጋጥመን ግን እየለመድነው እንሄዳለን። ለምሳሌ አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ውስጥ ሲገባ በብዙ ነገር ይገረማል። ብዙ አይነት አሳዛኝ ሕይወት ባስተዋለ ቁጥር አንጀቱ ይላወሳል። በወራት ውስጥ ግን ይለምደዋል። አነስተኛ ጉዳት ሲያስተውል አንጀቱ ይላወስ የነበረው ሰው፤ ከፍተኛ ጉዳት አይቶም ምንም ላይገርመው ይችላል። በጣም አሳዛኝ ኑሮ የሚኖር ሰው እያየ ምንም ላይመስለው ይችላል፤ እንዲህ ሲሆን ጉዳዩን ውስጡ ለመደው ማለት ነው።
ይሄ ለሌላው ሰው ብቻ ሳይሆን ራሱ ለባለጉዳዩም ነው። ባለጉዳዩም እየለመደውና ሕይወቱ እያደረገው ይሄዳል። ብዙ ጊዜ የአካል ጉዳት ያለባቸው ወይም ከችግሮች ጋር የሚኖሩ ሰዎች ጉዳቱ ወይም ችግሩ አዲስ የሚሆነው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው። ያው በእርግጥ በዚህ ብቻ አይደለም፤ ሙሉ ጤነኛ ሆነውም አሳዛኝና አስገራሚ ሕይወት የሚኖሩ ብዙ ሰዎች አሉ። በዚሁ ዓምድ ሥር እንኳን ሙሉ ጤነኛ ሆነው አስገራሚ ሕይወት የሚኖሩ የብዙ ሰዎችን ታሪክ አንብበናል። የእነዚህኞቹ ሰዎች (የጤነኞች ማለት ነው) አሳዛኝ ሳይሆን አስገራሚ ልንለው እንችላለን። የአካል ጉዳተኞች ግን አሳዛኝም ጭምር ነው።
እነዚህ የአካል ጉዳተኞች እየቆዩና እየለመዱት ሲሄዱ መደበኛ ሕይወታቸው ይሆናል። እኛ እንደምናስበው የሚጨነቁ አይሆኑም። ለምሳሌ አይነ ሥውር ስናይ ‹‹እንዴት ነው ግን የሚኖረው!›› እንላለን፤ እነርሱ ግን ‹‹ወይኔ! እንዲህ ሆኜ እየኖርኩ ነው !›› እያሉ የሚጨነቁ አይደሉም። የእግርና የእጅ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም እንደዚሁ ነው።
መለመዱ ችግር የሚኖረው እንግዲህ ከኑሮ ጋር ሲያያዝ ነው። እንግዲህ የተሻለ ሕይወት የሚኖሩት ወገኖች ላይ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ወቅታዊ አደጋ ቢደርስበት ተደናግጠን፣ ተረባርበን እርዳታ እገዛ እናደርጋለን። የሙሉ ጊዜ አካል ጉዳተኛ ለሆነ ግን አንደናገጥም፤ ለምደነዋል። በተለይም አብረን የምንኖርና አቅራቢያችን ከሆነ በብዙ ነገር ልብ አንለውም፤ ብናየውም ያው ከመልመድ ብዛት ትኩረት አንሰጠውም።
የዛሬው የ‹‹እንዲህም ይኖራል›› እንግዳችን ለዚህ ማሳያ ናቸው። በነገራችን ላይ የአካል ጉዳተኞች ሕይወት ሁለት አይነት ነው። የአንዳንዶች መንገድ ዳር ቁጭ ብሎ መለመን ነው፤ ያገኟትን ነገር እየቀማመሱ ይኖራሉ፤ ካጡም ያድራሉ። የአንዳንዶቹ ግን እንደማንኛውም ሙሉ ጤነኛ ሰው ሰርተው የሚኖሩ ናቸው። ለመስራት የሚፍጨረጨሩት መጠነኛ ድጋፍ ቢደረግላቸው እንደማንኛውም ሰው የሚኖሩ ናቸው ማለት ነው። ችግሩ እንዲህ አይነት ድጋፍ ካላገኙ ሕይወታቸውን ከባድና አሳዛኝ ይሆናል። እንግዳችን ሁለቱንም እግራቸውን ከልጅነታቸው ጀምሮ ያጡ ናቸው። ለመውጣት ለመግባት እንኳን በሰው ድጋፍና እርዳታ ነው። ይህ ድጋፍና እርዳታ ከሌለ ዝናብና ፀሐይ ነው የሚፈራረቅባቸው።
አባዝናብ አባ ቦር ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ሰኮሩ ወረዳ ዶቦ ቀበሌ ውስጥ ነው። አሁን አርባ ዓመታቸው ነው። እንግዲህ የሕይወታቸው ምስቀልቅል ከዚህ ይጀምራል። እንደተወለዱ እናትና አባታቸው አረፉ። ብቻቸውን እንደምንም ጥረው ግረው በፈጣሪ ፈቃድ አደጉ። የልጅነት ዕድሜያቸው ላይ እያሉ ግን ይሄ የሕይወት ዘመናቸው ችግር ተፈጠረ። ገና የ12 ዓመት ልጅ እያሉ እግራቸውን ታመሙ። ምን ሆነው እንደታመሙ አያውቁትም። ህመሙ እየጠነከረ ሄደ። በዘመኑ በአቅራቢያ ህክምናም ማግኘት አይቻልም፤ በዚያ ላይ እናትና አባት የሌላቸው ናቸው። ይሄ የእግር ህመም ግን እየከፋ መጣ። አንደኛው እግራቸው ያልምንም ህክምና በራሱ ጊዜ ቆስሎ ተቆረጠ። ህመሙ ሁለቱንም እግራቸውን ነበር ያጠቃው። ከሳምንት በኋላ የቀረው እግራቸውም የመጀመሪያው እጣፋንታ ደረሰበት፤ በቃ! ሁለቱንም እግራቸውን አጡ። የተቆረጡት እግሮች ቁስል የቆየውን ያህል ቆይቶ በራሱ ጊዜ ዳነ፤ ከቁስለቱ ጀምሮ እግራቸው በራሱ ጊዜ ተቆርጦ የዚያም ቁስል መልሶ እስከሚድን ድረስ ያለውን ህመምና መከራ ሁሉ ችለው አሳለፉት። ሕይወት በዚህ ሁኔታ ቀጠለች።
እንዲህ እንዲህ እያሉ ትዳር መሰረቱ፤ ከባለቤታቸው ጋር ስድስት ልጆችን አፍርተዋል።
የሚተዳደሩት በሰው እጅ ነው፤ እንደሌላው የአካባቢ ነዋሪ እንኳን መሬት የላቸውም። በዘመኑ ባለርስት ይባል ስለነበርና እናትና አባታቸው ስለሞቱ ማግኘት አልቻሉም። አንድ እህትና አንድ ወንድም አላቸው። እህትየዋ ትዳር ይዛለች፤ ወንድማቸው ግን የአዕምሮ ህመምተኛ ነው።
አባዝናብ የሚኖሩት በሾፌሮች እርዳታ ነው። ሾፌሮች በሚሰጧቸው ሳንቲም እየሸመቱ ኑሯቸውን ይገፋሉ። ከተገኘ ይበላሉ፤ ካልተገኘም ይቀራል። አጋዦቻቸው ሾፌሮች የሆኑት ደግሞ ብዙውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት መንገድ ላይ ስለሆነ ነው። በዚያ የሚመላለሱ የአገር አቋራጭና የንግድ ዕቃዎችን የሚያመላልሱ ሾፌሮች የቻሉትን ያህል እገዛ ያደርጉላቸዋል።
እኝህ ሰው የአካል ጉዳተኛ ናቸው። ዳሩ ግን መንግስትም ድጋፍ አላደረገላቸውም። ከስምንት ዓመት በፊት ዊልቸር ተሰጥቷቸው ነበር። አሁን ጎማው ተበላሽቶ አይሠራም። ጎማውን ያሰራላቸው ሰውም የለም። ልሥራላችሁ ብሎ የጠየቃቸውም የለም፤ ወደ ተቋማት ለመሄድም አቅም አጡ፤ ወይም የሚወስዳቸው ሰው አጡ። ሁሉም የየራሱ ኑሮ ሩጫ ላይ ሆነ። ዳሩ ግን ማንም ከእርሳቸው ይሻል ነበር። በሰውየው ቦታ ሆነን ችግሩን ስናስበው፤ ቁጭ ብሎ ሀሳብን የሚረዳ እንኳን ይናፍቃል።
የእኝህ ሰውዬ ኑሮ የመንግስትን፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና የማህበረሰቡን እርዳታ ይፈልጋል። ልጆቻቸው ተማሪዎች ናቸው። እነዚህ ልጆች ነገ የዚች አገር ተረካቢ ይሆናሉ። ማን ያውቃል ተፅዕኖ ፈጣሪ የአገሪቱ ተረካቢ ቢሆኑስ? ማን ያውቃል ሀብታም ቢሆኑስ? ማን ያውቃል ሳይንቲስት ቢሆኑስ? ማን ያውቃል የአገር መሪ ቢሆኑስ? ምንም ይሁኑ ምን እነዚህ ልጆች እየተማሩ ነው። ትልቁ ሰባትኛ ልፍል፤ ሁለተኛው አምስተኛ ክፍልና ሦስተኛው ሦስተኛ ክፍል ናቸው።
ልጆች የሚማሩት ያለማንም ድጋፍ በአባ ዝናብና ባለቤታቸው ጥረት ብቻ ነው። ባለቤታቸው ቅመማቅመምና ሽንኩርት ነገር ከተለያየ ቦታ እያመጡ ይነግዳሉ። በዚያች ነው የሚተዳደሩት። የልጆች ልብስና የትምህርት መሳሪያ የሚሸፈነው በዚቹ ገቢ ነው።
ዘመዶቻቸውም እያገዟቸው እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። ዕድርም የላቸውም፤ የአካባቢው ሰውም እያገዟቸው አይደለም። አንዳንዶቹ ጎረቤቶች ግን ለነፍሳቸው ሲሉ ያግዟቸዋል፤ የጉልበት እገዛ ያደርጉላቸዋል። ከእነዚህም ጎረቤቶቻቸው አቶ ቃሲም አባዲጋ አንዱ ናቸው። አቶ ቃሲም የሚከተለውን ተናግረዋል።
‹‹ከአቶ አባዝናብ ጋር ከረጅም ጊዜ ጀምሮ እንተዋወቃለን። የኑሮ ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነው። እዚሁ ደረቅ መሬት ላይ ነው የሚቀመጠው፤ እንደዚሁ ነው ውሎ የሚያድረው። ባለቤቱ በየቦታው እየዞረች ዱቄትና ሽንኩርት በመሸጥ ነው ቤተሰቡን የምታስተዳድረው። ከዚህም በሚገኝ ገቢ ነው ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት።
ባለቤቱ ከሌለች ዝናብ ሲመጣ እኛ ጎረቤቶች ነን ወደ ቤቱ የምናስገባው። እኛ በአካባቢው ከሌለን ግን እዚሁ ላይ ነው ዝናብ የሚያልቅበት። ወንድሙ ደግሞ የአዕምሮ ህመምተኛ ስለሆነ ጭራሽ ከእነርሱ እጅ ነው የዕለት ጉርሱን እንኳን የሚያገኘው። ወንድምየው በቅርቡ ነው የታመመው። አዲስ አበባ ውስጥ ከሰው ቤት ተቀጥሮ ነበር ነገር ግን እንዴት እንደሆነ አላውቅም ጤኔኛ የነበረው ሰው ታሞ መጣ፤ አንዳንድ ጊዜ ህይወት ችግርን ይዛ ስትመጣ እየደራረበች ነው።
መሬት የላቸውም፤ ያላቸው ጓሮ ብቻ ነው። የሰው እጅ ያን ያህል ባያረካም የተገኘውን ያህል እንቃመሳለን። ከዚያች የጓሮ መሬት የሚገኘው ግፋ ቢል የሁለት ቀን ቀለብ ቢሆን ነው።››
የአቶ አባዝናብ ኑሮ እንዲህ ነው። አሁን የልጆቻቸው ነገር ነው የሚያሳስባቸው። ያቺ ከእናታቸው ዱቄትና ሽንኩርት ሽያጭ የምትገኝ ገቢ ከዕለት ጉርስ ተርፋ ሦስት ልጅ ታስተምራለች ማለት ከባድ ፈተና ነው። እነዚህ ልጆች በልጅነት አዕምሮ ብዙ ነገር ያስፈልጋቸዋል። ዳሩ ግን እንኳን የፍላጎታቸውን ለማግኘት መሰረታዊ የሆኑ የትምህርት መሳሪያዎችን ማግኘትም ይቸገራሉ። የልጅነት አዕምሯቸው ስለትምህርት ሳይሆን ስለዕለት ጉርስ ያስባል። የልጅነት ምኞታቸው ተምሮ ሰው ስለመሆን ሳይሆን ደብተርና እስኪርቢቶ ማግኘት ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህም አነዚህ ህጻናት ባልዘሩት የመከራ ምርትን እያጨዱ ነው። ስለዚህም የእነዚህን ህጻናት መከራ መታደግ ታላቅ የህሊና ዕረፍት የሚሰጥ ነው። መንግትም ይሁን ሌላ አቅም ያለው አካል እነዚህን ወገኖች ቢያግዝ ትልቅ የህሊና እርካታ ያገኛል ። ማን ያውቃል እነዚህ ልጆች የዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ቢሆኑስ? የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የአለም ኖቤል ሽልማት አሸናፊና ከ15 በላይ ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ሽልማቶችን ማሸነፍ የቻሉት ዶክተር አብይ አህመድ ከድሃ ቤተሰብ ተወልደውና ከትንሽዋ መንደር በሻሻ ተነስተው ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር