የሰው ልጅ ካለመኖር ተነስቶ ወደ መኖር በውልደት ይመጣል። ውልደት ህፃንነት ወጣትነት አዋቂነት ዕርጅናና ሞት በሰው ልጅ የህይወት ዘመን የሚከሰቱ ተፈጥሯዊ ሂደቶች ናቸው። ከወንዶች እስፐርምና ከሴቶች እንቁላል ጥምረት ከሰው የሚፈጠረው የሰው ልጅ ተመልሶ ወደ አለመኖር በሞት ይሄዳል።
የሰው ልጅ በመኖር መማር መስራት ማግባት መዋለድ ለሀገር መከታ መሆንና ማህበራዊ ኑሮን በመመስረት ተለመዷዊ ተግባራት ናቸው። ሰው ከሰው በማህበራዊ ትስስሮሽ የመኖር ጣዕምን ያጠናክራል። ከማህበራዊ አስተሳሳሪዎች መካከል ጋብቻ ሀይማኖት ባህል አካባቢ ብሄርና የመሳሰሉት ናቸው።
በሀገራችን ባህል ሰው ሲሞት አብዝቶ ማዘን የተለመደ ነው። እንባ አልቆ አይኖቻችን እስኪደርቁና እስኪያብጡ ማዘን ማህበራዊ ሞገስ ያሰጣል። ጎረቤቶችና ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ በድንኳን በኋላም በቤት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ያዝናሉ። ሀዘን የሞትን የመቀስቀስ አቅም ፈፅሞ የለውም። ለሞተ ማዘንም ዋጋ የለውም። በእርግጥ ብዙ አብሮ የቆየና ያሣለፈ ሰው በሞት ሲለይ ለጊዜው መታዘኑ አይቀርም።
አንድ ሰው በህይወት ሳለ የሚቻለንን እርዳታና ድጋፍ ማድረግ ምንም አማራጭ የሌለው አስፈላጊ ተግባር ነው። የሰው ልጅ ሲቸገር መርዳት ሲራብ ማብላት ሲጠማ ማጠጣት ሲበርደው ማልበስ አስፈላጊ ነው። ምንም ሳይረዱት አንድ ሰው ሲሞት ከመጠን ባለፈ መልኩ እንባ ማንጋጋት ግን እርባናቢስ ነው። ለሚወዱት ሰው ከተቻለ የሚችሉትን ማድረግ ተገቢ ነው። መርዳት ከማንባት ሁሌም ይበልጣል። ሰው ከሞተ በኋላ የሚደረግ ለቅሶ ጥቁር መልበስና የመቃብር ጉብኝት ፋይዳ የለሽ ተግባራት ናቸው።
ሞት ለሰው ልጅ የተቀመጠለት ተፈጥሯዊ ሁናቴ ነው። ገንዘብ መልካምነት ስልጣንና ሌሎች የሚያስቆሙት ነገርም አይደለም። ሞት ሰው የሆነ ሁሉ የሚጠጣው መራር ፅዋ ነው። መኖር ጣፋጭ ነው። መሞት ደግሞ መራር ነው። ሁሉም ሰው በሞት ሰልፍ ውስጥ ተራውን እየጠበቀ ነው። ዛሬ ላይ በህይወት የቆመ ሁሉ ጊዜው ሲደርስ የሞትን ፅዋ ይጠጣል። ዛሬ ላይ ለሞተ ከመጠን ባለፈ መልኩ ማዘን ሞኝነት ነው። ምክንያቱም ሁላችንም የፅዋው ቀማሾች ስለሆንን ልኩን ልናልፍ አይገባም። ደረት መደለቅ አላቃሽ መቅጠር እራስን መጣልና መጉዳት በሌሎች አዝነዋል ለመባል ማድረግ አይጠቅምም። የሞተ ሞቷል። የኖረም እስኪሞት በሰላም መኖር አለበት። የኖረ ደግሞ ጊዜው አስኪደርስ ለሞተ ሰው የአንበሳ አስተዛዘን ማዘን ከንቱ ነው። ሀዝን በልኩ ሲሆን ያምራል።
በአንድ አጋጣሚ አንድ የልጅነት ጓደኛዬ በመኪና አደጋ በ25ተኛ ዓመቱ ይሞታል። ይህ ጓደኛዬ ለእናቱ የመጨረሻ ልጅ ነበር። አንድ ታላቅ እህትና አንድ ታላቅ ወንድም ነበረው። ዕድሜው 3 ዓመት እያለ ወላጅ አባቱ ስለሞተበት እናቱ ነበረች አባትም እናትም ሆና ያሳደገችው። ባበህሪው እጅግ መልካም ሰው ስለነበረ እናቱ ለእሱ የተለየ ቦታ ነበራት። ታድያ ይህ በልዩ የምትወደው ልጇ ሲሞትባት እናቱ ሀዘኗን መቆጣጠር ስላልቻለች ልጇ በሞተ በሁለተኛ ወሩ እራሷን ለማጥፋት ተዳረገች። ይህን ያየው ታላቅ ወንድሙም እራሱን መቆጣጠር ከብዶት እራሱን አጠፋ። እህቱም ደገመችው። ቤተሰቦቹ ሁሉ ተከታትለው በሞት ተጥለቀለቁ። ሀዘን ሀዘንን ይጠራል እንደሚባል ሆነ ለመስማት በሚከብድ መልኩ።
በሌላ አጋጣሚ አንዲት የ63 ዓመት እናት ነበረች። ባልዋም ከሞተ 10 ዓመታት አልፏል። ይህቺ እናት የአምስት ልጆች እናት ነበረች። ልጆችዋ ሁሉም በስራ ላይ ናቸው። ታድያ ግን የባልዋን 450 ብር ጡረታ ብቻ እያገኘች በቀበሌ ቤት ትኖር ነበር። አምስቱም ልጆችዋ ግን ምንም እርዳታ አያደርጉላትም ነበር። በህመምና ችግር ትንገላታም ነበር ያለረዳት ምንም አንኳ ለስሙ አምስት ልጆች ቢኖራትም። ልጆችዋ እንዲረዷት ብዙ አማላጅ ሰዎችን ብትልክም አይሰሟትም ነበር። ሰው እያላት ሰው እንደሌላት በከፍተኛ መከራ ውስጥ ነበረች። ይህም ሆኖ በወር የምታገኘውን ያችኑ የሙት ባልዋን የጡረታ ብር እንደምንም አበቃቅታ የትየለሌ ኑሮ ትኖር ነበር። አንድ ቀን በጠና ታመመችና ላትመለስ አሸለበች። ልጆችዋም መሞትዋን እንደሰሙ ሊያስቀብሯት ተሰበሰቡ። በለቅሶው ጊዜ ድሮ ያልነበሩ ዘመድ ተብዬዎች ሁሉ ከየትም መጥተው ነበር። አምስቱ ልጆችዋ ከልክ ባለፈ መልኩ እንባቸውን ያነቡ ነበር። ልክ ብዙ ሆነውላት እንዳጧት መስለው ታዩ። በህይወት ላልረዷት ምስኪኗ እናታቸው በእምባ ለመካስ በሚመስል መልኩ አደረጉ። ይህን ሲያደርጉ ግን ሚስጥሩን የሚያውቁ ጎረቤቶች በአግራሞት ይመለከቷቸው ነበር። ከሙት በኋላም ለ5 ዓመታት የሀዘን ጥቁር ልብስ ለበሱና ለሰዎችም ብዙ እንዳዘኑ ለመምሰል ሞከሩ። ለእናታቸው ልዩ ክብርና ቦታ እንዳላቸው በውሸት እንዲታወቅላቸው ጣሩ። የቻሉትንም ያህል ለማስመሰል ሞከሩ። እውነቱን ሳያውቅ ያመናቸው አመናቸው አሞገሳቸው። ያወቀባቸው ደግሞ ተሳለቀባቸው። ምጎሳውም ሆነ መሳለቁ ግን ለዛች ምስኪን እናት ምንም አይጠቅማትም። ሊጠቅማትም አይችልም። ከሞት በኋላ የሚደረግ ሁሉ ከንቱ ነው። መልዕክቴን ሳጠቃልልም ወዳጆቼ ሆይ ሞት ለማንም የማይቀር ዕጣ መሆኑን እንገንዘብና በቁም የሚቻለንን ያህል እንረዳዳ የአውነትም እንፋቀር እላለሁ! የውሸትና የማሰመሰል ብሎም የመቃብር ላይ እዩኝ እዩኝ ትዝብት ላይ ይጥላልና በህይወት ሳለን እንተዛዘን፤ መጽሐፉስ የሚለው መዋደዳችሁ የአፍ ሳይሆን የተግባር ይሁን አይደል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
በላይ አበራ
(ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኝ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ)