ብዙ ጊዜ አዕምሮአችን የለመደውን እውነት ይቀበላል። ዓይኖቻችንም ቢሆኑ ከውስጣችን የተቀበሉትን አምነው ይመለከታሉ። ይህኔ የጎደለ እንኳን ቢኖር እየሞሉ ማለፍ የተለመደ ይሆናል። የተጻፈው ጉዳይ ምንም ይሁን ምን አይኖቻችን እንደለመዱት ሞልተውና አሟልተው ያነቡታል። እንዲህ በሆነ ጊዜም ስለትርጉሙ መዛባትና ስለተላለፈው መልዕክት ትኩረት ባይሰጥ የሚያስገርም አይሆንም።
ወዳጆቼ! መቼም የዚህን ጽሁፍ ርዕስ እንደማንበባችሁ አትኩሮታችሁም ሊለያይ እንደሚችል እገምታለሁ። ምንአልባትም «ካልጠጡ አይንዱ» የሚለውን መልዕክት «ከጠጡ አይንዱ›› በማለት አንብባችሁትም ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው ዓይኖቻችን የጎደለውን ሞልተው ያነባሉ ማለቴ።
ቃላቶች የራሳቸው ተጽዕኖ የማሳደራቸውን ያህል በማስታወቂያ መልኩ ስንጠቀማቸው ደግሞ ሀያልነታቸው ይበልጥ ይገዝፋል። እኔ ይህን «ካልጠጡ አይንዱ» ይሉትን ጽሁፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት ለስራ ከከተማ ወጣ ባልኩበት አጋጣሚ ነበር። በወቅቱም የጽሁፉን መልዕክት «ከነዱ አይጠጡ» በሚል ሞልቼ አንብቤው እንደነበርም አልዘነጋም።
ሁላችንም እንደምንረዳው «ከጠጡ አይንዱ» የሚለው መልዕክት ታላቅ ትርጓሜ አለው። ጠጥቶ ያሽከረከረ በመንገዱ ሁሉ ለእራሱም ይሁን ለሌሎች ሞትና ጉዳትን ማስተናገዱ የሚገመት ነው። ይህን የማስታወቂያ ወዝ የተከተሉ አንዳንዶች ደግሞ እውነታውን ገልበጥ አድርገው አትኩሮትን ሲስቡ አትራፊ መሆናቸው የማይቀር ነው። እንዲህ ሲያደርጉ ግን የትኛው ለማን እንደሚበጅ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ጠጥቶ ለመንዳት ቡና እንጂ አልኮል እንደማያበረታም ከስር በሚያሰፍሩት ቃል ለይተው ያሳያሉ።
በእኔ ግምት አንድ ጉዳይ ይበልጥ ተነባቢ ይሆን ዘንድ የራስን ዘዴና ብልጠት መጠቀም ይሻላል ባይ ነኝ። እንዲህ ከሆነ ምንአልባትም በርከት ያለ ገንዘብ አፍስሶ ማስታወቂያ ማስነገር አያስፈልግ ይሆናል። ለነገሩ ማስታወቂያ ሁሉ ጫን ያለ ገንዘብ የወጣበትን ያህል ሆኖ መልዕክት ላያስተላልፍ ይችላል።
አንድን ምርት ተወዳጅ አድርጎ ለሽያጭ ለማቅረብ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዳንስና ሙዚቃ የተለየ መገለጫ ሆኗል። ለቢራም ይሁን ለውሀው ሙዚቃና ጭፈራ፣ ለንጽህና መጠበቂያውም ውዝዋዜና ዳንስ በናኘበት ዘመን ደግሞ በእንዲህ አይነቱ የተመጠነ ቃል ብቻ በውድድሩ አሸናፊ መሆን ቀላል አማራጭ መሆኑ አያጠራጥርም ።
ወዳጆቼ!መቼም ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የማስታወቂያዎቻችን ጉዳይ አስገራሚ እየሆነ መምጣቱን እናንሳ። አንድን የአልኮል መጠጥ «ተጋበዙልን» ለማለት አዳራሽ ሙሉ ሰው ሰብስቦ በጭፈራና በሆታ መጯጯሁ እየተለመደ ነው። በእኔ እይታ ጉዳዩ መጠጥ ሆኖ ሳለ እርካታውን ለማሳየት የግድ ጭፈራን ማሳያ ማድረጉ ተገቢ አይመስለኝም።
አብዛኞቹ የቢራ ማስታወቂያዎች ለሽያጩ የሚጨነቁትን ያህል ከእርካታው በስተጀርባ ስለሚኖረው የጎንዮሽ ጉዳት ማንሳት አይፈልጉም። ሁሌም እንደሚደረገው ለመጎንጨት ብርጭቆን ያነሳ ሁሉ ደስታን በቀላሉ ወደሱ እንደሚጋብዝ ተደርጎ ይሳልለታል። የማስታወቂያውን አጋጣሚ ተጠቅመው በስሱ የሚያነሱት የዕድሜ ገደብ ጉዳይም በአንድ መስመር ጽሁፍ ብቻ ተገልጾ እንዲያልፍ መደረጉንም ጆሯችን እየለመደው ነው።
«ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ አይሸጥም» የሚለው ታላቅ መልዕክት ሁሌም የሚተላለፈው ራሱን ችሎ አይደለም። ይህ ታላቅ ሀሳብን የሰነቀ አባባል በየጊዜው ከመጠጡ መጎንጨት አልያም ከስካርና ደስታው በስተጀርባ ተከልሎ የሚያልፍ ነው።
ሁላችንም እንደምናየውና እንደምንረዳው የማስታወቂያው ግብ የመጠጡ መሸጥ ላይ ብቻ በማተኮሩ በደመቀ ሙዚቃና ጨኸት ታጅቦ እንዲያልፍ ይደረጋል። ለዚህ ጉዳይ ትኩረት የመሰጠቱን ያህልም ከዕድሜያቸው በታች የሚገኙ ታዳጊዎች በዘፈኑ ብቻ ሊማረኩ ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ከግምት ውስጥ የሚገባ አይደለም።
ወዳጆቼ! በእኔ እሳቤ ታዳጊዎቹ ከማስታወቂያው ምን ተረዳችሁ? ተብለው ቢጠየቁ የሙዚቃውን ግጥም ከዳንስና ግጥሙ ጋር አዋዝተው ማቅረቡ ላይ የሚያተኩሩ ይመስለኛል። ለምን? ከተባለ ደግሞ መልዕክቱ እንዲደርሳቸው የተደረገው በአንድ መስመርና በተወሰነ ቃላት ብቻ በመሆኑና የመልዕክቱ ሚዛንም ከጉዳቱ ይልቅ ጠቀሜታው ላይ ስለሚያጋድል ነው።
ሁሌም እንደሚባለው መልካም የሚባል ዕቃ ሁሉ ማስታወቂያ አያሻውም። ጥሩ ይዘትና የተሻለ ጥንካሬን ከተላበሰ አመታትን በስሙ መሻገር ይቻለዋል። ይሁን እንጂ እጅግ የተጋነነለትና ረብጣ ገንዘብ የፈሰሰለት ማስታወቂያም ቢሆን ከሌሎች የተሻለ ነው ለማለት አያስደፍርም።እንደውም ብዙዎች እንደሚሉት እንዲህ አይነቱ አሰልቺ ልማድ በራስ ያለመተማመን የእውቅና ጥላ ስር ተጠልሎ ለማለፍ የሚደረግ ዘዴ ሊሆን ይችላል።
እንደ «ካልጠጡ አይንዱ» ይሏትን ምጥን ሃሳብን ስናያት ደግሞ ጥቂት ቅመምን በትና የእውቅና ጉልበትን ለመያዝ መንገዱን የምታሳጥር ትሆናለች። ይህን ሲያስቡ ደግሞ ለማስታወቂያ ፍጆታ የሚውለው የሰው ጋጋታና የሙዚቃ ጨኸት ሁሉ ዋጋው ያንስብዎታል። በቀላል ዘዴ ርቀው ሳይጓዙ ደንበኛን መሳብ እንደሚቻልም ይገምታሉ። እግረ መንገድዎንም የዚህን ሃሳብ ፈጣሪ መለኞችን ማድነቅ ይቻልዎታል።
አንዳንዴ ደግሞ አንዳንድ መለኞች ስለያዙት ዕቃ ማስተዋወቅ ሲሹ የራሳቸውን ዘዴ ይጠቀማሉ። እንዲህ አይነቶቹ ታዲያ ለደንበኞች መሳቢያ በርከት ያለ ገንዘብ መክፈል ልማዳቸው ሆኖ አያውቅም። በሰፊ የማስታወቂያ መለጠፊያ ላይ ዝርዝር አስቀምጠው በቀላሉ ማንነታቸውን ያሳያሉ። በውስጠ ወይራ ዘዴያቸውም «አንብቡን ጎብኙን» ሲሉ ይጠቁማሉ።
ብዙዎቻችን በጉልህ የተቀመጠ ጽሁፍን እያየን «ይህን ማስታወቂያ ማንበብ አይቻልም» የሚል መልዕክት ቢደርሰን መገረማችን አይቀርም። በግልጽ የተቀመጠ ዝርዝርን አስፍሮ ለማንበብ መሞከርን እንደ ድፍረት ስለታየብንም ሊያበሽቀን ይችላል። ይህን አድራጊዎቹ ግን እንዲህ መሆኑን በእጅጉ ይፈልጉታል። ሰዎች በዚህ አባባል ተገርመው ለማንበብ እንደሚጣደፉ ይገባቸዋልና ከዚህ ስሜት በስተጀርባ ሁሌም አትራፊዎች ይሆናሉ።
በእንዲህ አይነቱ የአታንብቡን መልዕክት ማንም ቢሆን ሚስጥሩን ለማወቅ ይጓጓል። እነሱ ካሰፈሩት ማስጠንቀቂያ አዘል ማስታወቂያ ስርም ስለማንነታቸው የሚገልጸውን ሙሉ መረጃ በገሀድ ማግኘት ይቻላቸዋል።
እንግዲህ ወዳጆቼ እንዲህ አይነቶቹ ብልሆች በቀላሉ ማንነታቸውን አስተዋውቀው በአቋራጭ መንገድ ይፈጥናሉ። በሩጫ ሳይሆን በመላ ገበያውን ተሻምተውም ገበያተኞችን ያፈራሉ። ይሁን ብሎ የሚቀርባቸው ባገኙ ጊዜም የሚሸጡትን ሁሉ እያዋዙ እነሆ! ማለቱን ያውቁበታል። እንግዲህ ሳይጮሁና ሳያጯጯሁ ባቋራጭ መቅደም ማለት ይህም አይደል? እንደቡናዋ «ካልጠጡ አይንዱ» ግልገል ማስታወቂያ።
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011
መልካምስራ አፈወርቅ