አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት 174 የተለያዩ የግብርና ምርት ማቀናበሪያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት ማቀዳቸው ተገለጸ። ዘጠኝ ዩኒየኖች ደግሞ ቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ገብተው በ600 ሚሊዮን ብር የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ሊያቋቁሙ መሆኑን ተመልክቷል።
የኦሮሚያ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ሀላፊ አቶ ታረቀኝ ሱሉልታ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የህብረት ስራ ማህበራት የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ ኢንዱስትሪዎችን እየገነቡ ይገኛሉ። በተያዘው ዓመት ማህበራቱ በኦሮሚያ ክልል 174 የግብርና ምርት ማቀናበሪያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት አቅደው እየሰሩ ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ የተለያዩ ፋብሪካዎችን እየገነቡና ለመገንባት ዕቅድ ይዘው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸው ለአብነትም የኦሮሚያ ህብረት ስራ ፌዴሬሽንና ቄለም ወለጋ የሚገኘው ሀርጉ ዩኒየን ፋብሪካዎችን ለመገንባት ጥናት አስጠንተው ለኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዘጠኝ ዩኒየ ኖችም ቡልቡላ የግብርና ምርት ማቀናበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በ600 ሚሊዮን ብር የካፒታል ፋብሪካዎችን ለመቋቋም በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አመልክተው ለዩኒ የኖችም በባንክ በኩልም አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግላቸው ቴክኒካል ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የህብረት ስራ ማህበራቱ ከሚገነቧቸው ፋብሪካዎች መካከልም የዘይት፣ የቡና፣የፍራፍሬ፣የዱቄት ፋብሪ ካዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።የህብረት ስራ ማህበራቱ ፋብሪካዎችን መገንባታቸውም የአርሶ አደሩን ምርት እሴት ጨምሮ ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ የስራ ዕድል እንደሚፈጥርና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።የኦሮሚያ ክልል 22ሺ የሚጠጉ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራትና 120 የሚሆኑ ዩኒየኖች እንዳሉ ይታወቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ከ61 በላይ ዩኒየኖች ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩና በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቻቸውን ለማቅረብ የሚያስችላቸውን በግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የፌዴራል ሕብረት ስራ ኤጀንሲ አስታውቋል።ዩኒየኖቹ እሴት ጨምረው ለገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ እንደሚሰማሩ ኤጀንሲው ገልጾ በተለይም በምግብ ዘይት፣ በእንስሳት ተዋጽኦ እና አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ መዋዕለነዋያቸውን በማፍሰስ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ማቀዳቸውንም ጠቁሟል።
ዩኒየኖች በአብዛኛው ጊዜ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለህብረተሰቡ የሚያቀርቡ በአምራች አርሶአደሮች እና አርብቶአደሮች የተመሰረቱ ተቋማት ሲሆኑ በኢትዮጵያ የሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ቁጥር 89 ሺህ መድረሱንና 907ቱ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርተው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ጌትነት ምህረቴ