በአፋር ክልል በአፋምቦና አሳይታ አከባቢዎች ዛሬ ላይ የሰብል ልማት ስራ ጅማሮ እየታየ ቢሆንም በደርግ ዘመን እስከ 35ሺ ሄክታር መሬት በተለያየ መልኩ ይለማ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። በሂደትም በአካባቢው ያለው ለም አፈር እና የአዋሽ ወንዝ ታላቅ በረከትነት መቀዛቀዙን፤ የሰብል ልማት ስራውም መቋረጡን ይናገራሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በባለሃብቶችና በጥቂት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደ ጥጥና በቆሎ ያሉ ምርቶችን ወደማልማት እንደተገባ በማውሳትም፤ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ግን ስንዴን በቆላማ አካባቢዎች በመስኖ የማልማት አቅጣጫን ተከትሎ አካባቢው የስንዴ አምራች መሆን የሚችልበትን እድል ማግኘቱን ያብራራሉ።
አቶ ሀቢብ አብዱርቃድር፣ በአፋር ክልል በመስኖ የሚለሙ የቆላ ስንዴ ልማት ተጠቃሚ ከፊል አርብቶ አደሮች መካከል አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ አዋሽ ወንዝ በለም አፈር ላይ ሲፈስ ውሎ ቢያድርም ለም አፈሩ ሊለማ፣ ውሃውም የልማት አለኝታነቱን በተግባር እንዲገልጽ ማድረግ ሳይቻል ዓመታት ተቆጥረዋል። ጥቂት ባለሃብቶችና የአካባቢው ነዋሪዎችም ቢሆኑ ከጥጥና ከበቆሎ ያለፈ ሳይሰሩበት ባክኖ ኖሯል። የቆላ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ መጀመሩ ግን አርብቶ አደሩ የሚጠቀምበትን፤ ከጥጥና በቆሎ ያለፈ ስንዴን ማልማት እንደሚቻል ያረጋገጠበትን፤ የእውቀትና ልምድ ሽግግር ያገኘበትን እድል የሰጠው ሆኗል።
ይሄም ለህብረተሰቡም ሆነ ለአገር ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ሲሆን፤ ከስራ እድል ፈጠራ ጀምሮ የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የማጎልበትና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ለመተካት የጎላ ሚና ይኖረዋል። በመሆኑም አዋሽን ከለም መሬት በልማት የማጋመዱ ተግባር ዘላቂነት እንዲኖረው በሙያም፣ በግብዓትም፣ በማሽነሪም ሆነ መሰል የስራው አጋዥ ግብዓቶች ድጋፍ ሊጠናከር ይገባል። ይህ ሲሆን ፍላጎቱ እያደገ፤ ተጠቃሚነቱም እየጎለበተ ስለሚሄድ የሚፈለገውን አካባቢያዊም ሆነ አገራዊ ጥቅም ማግኘት ይቻላል።
አቶ መሐመድ ጀባ እና አቶ ሁሴን አብዶ፣ በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ የሚከናወነው የቆላ ስንዴን በመስኖ የማልማት ተግባር ተጠቃሚ አርሶአደሮች ናቸው። አርሶአደሮቹ እንደሚሉት፤ አካባቢው ቀደም ሲል ከበቆሎና ሽንኩርት ውጪ አያመርትም። ስንዴንም ዘንድሮም በባለሙያዎች ጉትጎታና ማግባባት ተገፍተውና በሙያ ምክራቸው ታግዘው ለመጀመሪያ ጊዜ መዝራታቸው ነው።
ሆኖም ያዩት ነገር እጅጉን አስደሳችና በቴክኖሎጂና ባለሙያ ታግዞ መስራት ከተቻለ ቆላማ አካባቢዎችም ስንዴን ማምረት እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጡበት፤ በዓመት አንዴ ብቻ ሳይሆን ሶስቴ ምርት ማግኘት እንደሚቻልም የተገነዘቡበት ነው። ስራውም በበርካቶች መነሳሳትን የፈጠረ ሲሆን፤ እነርሱም በቀጣይ በስፋት ለመዝራት አቅደዋል። ለዚህ ተግባር ውጤታማነትም የመንግስትና የባለሙያ ያላሰለሰ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
እንደ አገር ለተያዘው ከውጭ የሚገባ የስንዴ ምርትን በአገር ውስጥ የመተካት ጉዞን ከማሳካት አኳያ ትልቅ ሚና ካላቸው ተቋማት መካከል የምርምር ማዕከላት ግንባር ቀደም ሲሆኑ፤ የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ደግሞ ቀዳሚውን ድርሻ ወስዶ እየሰራ ያለ የምርምር ማዕከል ነው። በማዕከሉ የአፈር ጨዋማነት ተመራማሪ እና የተፈጥሮ ሃብት አያያዝ የስራ ሂደት ተጠሪ አቶ ለማ ማሞ፣ እንደሚሉት፤ በማዕከሉ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ የስራ ሂደት ስር ሶስት የምርምር መስኮች (በሰብል አያያዝና በአፈር ለምነት ላይ፤ በአፈር ጨዋማናነት አያያዝና መከላከል ላይ፤ ከመስኖ ውሃ አያያዝ ላይ) ምርምሮችን እያደረገ ይገኛል። በዚህም በሚከናወን የሰብል ልማት ስራ ከዘር ወቅት መረጣ ጀምሮ ከዘር፣ ከግብዓት፣ ከክትትልና እንክብካቤ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ይሰራል።
አካባቢው የመስኖ ልማት ስራ የሚካሄድበት እንደመሆኑ የመስኖ ውሃን በአግባቡ ካለመያዝና ካለመጠቀም ጋር በተያያዘ የተከሰተን የአፈር ጨዋማነትን ለመቀነስ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን ለተጠቃሚዎች እያደረሰም ይገኛል። በተለይ ከሰብል ልማት ጋር በተያያዘ በቆላ ስንዴ መስኖ ልማት ዙሪያ በሰፊው እየተሰራ ሲሆን፤ ለአካባቢው ተስማሚ የስንዴ ዝርያዎችም ተለቅቀዋል። ስራውም በኦሮሚያ ቆላማ አካባቢዎች፣ በሶማሊያ እና አፋር አካባቢዎችን ጨምሮ በመስኖ ለሚያለሙ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ታሳቢ ተደርጎ የሚከናወን ነው።
አቶ ታምሩ ደጀን፣ በማዕከል የቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር የስራ ሂደት አስተባባሪ እና የማዕከሉ ዳይሬክተር ተወካይ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ማዕከሉ ቀደም ሲል በጥጥና ሌሎች የቅባት ሰብሎች ግንባር ቀደም ስራን ሲያከናውን ቆይቷል። ላለፉት 10 ዓመታት ደግሞ በመስኖ የሚለሙ የቆላማ አካባቢ ስንዴዎችን በምርምር የማውጣት ሂደት ላይ ተሰማርቶ ከላይኛው እስከታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ ላይ እያለማ ይገኛል።
እስከ አምና ሰባት ዝርያዎች የወጡ ሲሆን፤ በዚህ ዓመትም ተጨማሪ ሁለት በቆላ አካባቢዎች የሚለሙ የስንዴ ዝርያዎችን አውጥቷል። በዚህም የየአካባቢውን አየር ሁኔታ ያማከሉና ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ ዘጠኝ የቆላ ስንዴ ዝርያዎችን በባለቤትነት ያወጣ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ዝርያ የፓስታና መኮረኒ፣ የተቀሩት የዳቦ ስንዴ ዝርያዎች ናቸው። እነዚህም በየአካባቢው እንዲላመዱ ተደርጎ ለአርብቶ አደሩም ሆነ ለባለሃብቱ ደርሰው በሰፊው እንዲለሙ ማድረግ ተችሏል።
በዚህ ተግባሩም አካባቢውን ተጠቃሚ እያደረገ ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ ቀደም ሲል በአካባቢው የጥጥ እርሻ ብቻ ይከናወን ስለነበር አርብቶ አደሩ የጥጥ እርሻው እንደተነሳ በመኖ እጥረት ምክንያት ወደሌላ ቦታ እንዲንቀሳቀስ ይገደዳል። አሁን ግን በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ማምረት ስለተቻለ እንዲሁም ለእንስሳቱም የመኖ ልማት ስለተጀመረ አርብቶ አደሩም ለእንስሳቱ መኖ ስለማያጣ የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖረው ሆኗል። በቀጣይም ይሄው የመኖ ስራ ከተጠናከረና ሳርና ገለባውን መሰብሰብ ከተቻለ ከብቶችን ማድለብ የሚቻልበትን እድል ይሰጣል። በመሆኑም ይሄን ስራ የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ የማሽነሪና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለአካባቢው ማቅረብ እንዲሁም ባለሃብቶችን ማበረታታትና መደገፍ ይገባል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ወንድወሰን ሽመልስ