አዲስ አበባ፡- የበረሃ አንበጣ የተስፋፋባቸው ኢትዮጵያ፥ ሱማሊያና ኬኒያ ስርጭቱን በቅንጅት ለመቆጣጠር በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ፡፡
በአለም የምግብ ድርጅት አስተባባሪነት የየአገራቱ ሚኒስትሮችና የኢጋድ አመራሮች የአንበጣ መንጋ ስርጭትን በጋራ መቆጣጠር በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ትናንት በስካይ ላይት ሆቴል ውይይት አድርገዋል፡፡ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገብረእግዚአብሄር ገብረሃዮሃንስ ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ በውይይቱ የአንበጣ ስርጭት በተስፋፋባቸው አገራት እያደረሰ ያለውን ጉዳትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በሚመለከት የጋራ ግንዛቤ መያዝ ተችሏል፡፡ በቀጣይም አገራቱ የቁጥጥር አቅማቸውን በማጠናከር፥ መረጃ በመለዋወጥና በመደጋገፍ ስርጭቱን መግታት የሚያስችል ስራ ለመስራት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡
የበረሃ አንበጣ ያለፈው ሰኔ ወር ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል አፋርን ማዕከል አድርጎ የአንበጣ መንጋ መግባት መጀመሩን የአፋር ክልል ወደ 21፥ አማራ ክልል 10 እንዲሁም ትግራይ ክልል ዘጠኝ ወረዳዎችን ማካለሉን አመልክተዋል፡፡ መንግስት በወሰደው እርምጃም በአየርና በምድር ባደረገው የኬሚካል ርጭት የአንበጣውን መንጋ መቆጣጠር መቻሉን አስገንዝበዋል፡፡ በተለይም ደግሞ የአንበጣ መንጋው የተከሰተው አብዛኛው ሰብል ከተሰበሰበ በኋላ በመሆኑ በምርት ላይ ይሄነው የሚባል ጉዳት አለማድረሱን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ካለፈው ወር ጀምሮ መንጋው ዳግመኛ በሱማሌ ክልል አድርጎ ከውጭ አቋርጦ መግባቱን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት በሱማሌ ክልል 32፥ በኦሮሚያ 34 እና ደቡብ ክልል28 ወረዳዎች ላይ እየተስፋፋ መሆኑን ዶክተር ገብረእግዚአብሄር ጠቁመዋል፡፡ «በአሁኑ ወቅት የቁጥጥር ስራችንን አጠናክረን ቀጥለናል፤ ባሉን አራት አውሮፕላኖች ኬሚካል እርጭት ስራ እያከናወንን ነው» ብለዋል፡፡ ይሁንና ከእርጭቱ ያመለጡ አንበጦች አሁንም ወደመሃል የሚነፍስ ንፋስን ተከትለው የመስፋፋት ሁኔታ እንደሚታይባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቦረና አካባቢ ፤በሱማሌ ፤በደቡብ ክልል በተለይ ከኬኒያ ጋር በምንዋሰንባቸው አካባቢዎች አቋርጦ የሚመጣው የበረሃ አንበጣ መንጋ መኖሩን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመው ለቁጥጥር ስራው ከሚኒስቴሩ ጀምሮ እስከታች ቀበሌ ድረስ በኮማንድ ፖስት የሚመሩ 135 ባለሙያዎችን ማሰማራት መቻሉን አስረድተዋል፡፡ የተደረጉ ጥናቶች መንጋው ወደ መሐል አገርም የሚስፋፋበት እድል መኖሩን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ጠቅሰው በተለይም በኦሮሚያ ክልል ቦረና አካባቢ የሚገኙ አርብቶአደር ቀበሌዎችን ሊያጠቃ የሚችልበት ሁኔታ ስለሚኖር ቁጥጥሩን የማጠናከር ስራ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከመሃል ኢትዮጵያም አልፎ ሱዳን ደቡብ ሱዳን፥ ኬኒያና ኡጋንዳም የአንበጣው ስርጭት ሊቀጥል የሚችል መሆኑን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ጠቁመው በመሆኑም ስጋቱ ካለባቸው አገራት ጋር በቅንጅት መስራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የአለም አቀፉ የምግብ ድርጅትና የሌሎችም የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በአለምአቀፍ የምግብ ድርጅት የአየር ንብረትና የተፈጥሮ ሃብት ምክትል ዳይሬክተር ሚስ ማርያ ሄለና በበኩላቸው፤ የአንበጣ ስርጭቱ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት አልፎ ወደ ሌሎችም አገራት የመስፋት እድል እንዳለው አመልክተው፤ አገራቱ ስርጭቱን ለመቆጣጠር በሚያደርጉት ጥረት ድርጅቱ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እስካሁንም 76 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉን አመልክተው ለጋሽ አገራትን በማስተባበር የኬሚካልና አንዳንድ ግብዓቶች ለእነዚህ አገራት ለማሰራጨት እቅድ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የበረሃ አንበጣ በኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት ከ10 ጊዜ ላላነሰ የተከሰተ ሲሆን የዘንድሮው ግን በመጠንም በስርጭትም ሆነ በፍጥነት የላቀ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በተመሳሳይ በሱማሊያ ከ25 ዓመታት በኬኒያ ደግሞ ከ75 ዓመታት በፊት ተከስቶ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ማህሌት አብዱል