አዲስ አበባ፡- በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የማህበረሰብ ክፍሎች ለሀገራቸው የሰላም ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲ ያበረክቱ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ጥሪ አቀረበ።
የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም በላይ የካቲት 03 ‹‹ዲያስፖራው ለሀገር ሰላም ግንባታ›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ በስካይ ላይት ሆቴል የሚካሄደውን ውይይት አስመልክቶ ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ዲያ ስፖራ ማህበረሰብ ያካበተውን የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ የውይይት ባህል እና ዘርፈ ብዙ ልምድ ወደ ተግባር በመመንዘር ሰላምና መግባባት ይፈጠር ዘንድ ለሀገሩና ለማህበረሰቡ የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ አብርሃም እንዳሉት፣ በየሀገሩ የሚገኝ ዳያስፖራ በአብዛኛው አንቱ በተባሉ የእውቀት ዘርፎች የተካነና ሀገርን የመታደግ ብርቱ አቅም ባለቤት ነው። በመሆኑም ያለውን ያልተነካ አቅም በማስተባበርና በማደራጀት በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የሰላም እጦት በውል አጢኖ የመፍትሄው አካል ለመሆን በጋራ መምክር የሚያስፈልግበት ወሳኝ ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን አሁን ላይ ከሠላም በላይ የሚያስፈልጋቸው ሌላ ቀዳሚ ጉዳይ እንደሌለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣የሀገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ ስርዓት በመገንባት በኩል ዳያስፖራው ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
በየጊዜው ብልጭ ድርግም እያሉ የቀጠሉት ብጥብጦች እና አስተማማኝ ያልሆኑ የሰላም ሁኔታዎች በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ፍሰትም ሆነ አጠቃላይ በሀገሪቱ ገጽታ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ አቶ አብርሃም ገልጸው ስለሰላም ከመናገር፣ከመዘመር፣የሀዘን መግለጫ ከማውጣት እና ሰልፍ ከመጥራት ባለፈ ከየትኛውም ዓለም የመጣ ዳያስፖራ በጉባኤው ላይ ተገኝቶ በአካል መፍትሄ በመፈለግ ሀገሩን እንዲታደግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢድሪስ መሐመድ በበኩላቸው ዲያስፖራው ማህበረሰብ አገሩን በተለያዩ መንገዶች በትራንስፖርት፣በኢኮኖሚ፣በኢንቨስትመንት፣በእውቀት ልምድ ልውውጥ፣በትምህርት እና በሌሎችም ዘርፎች ሀገሩን ሲረዳ የኖረ ቢሆንም ሀገሪቱ ከዲያስፖራው መጠቀም ካለባት ግዙፍ ሀብት አኳያ በቂ ካለመሆኑም በላይ በሰላም ግንባታ ሂደት የነበረው አስተዋጽኦ እምብዛም በመሆኑ በእጅጉ ማደግ እንዳለበት ተናግረዋል።
አክለውም ሀገሪቱ አሁን ወደ ምርጫ በመንደርደር ላይ መሆኗን አስታውሰው፣ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር እንደ ሲቪክ ማህበር ለሀገሪቱ የሰላም ግንባታ ሂደት ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሰላም ጉዳይ ላይ በምንም መልኩ ልንደራደር አይገባም ያሉት አቶ ኢድሪስ፣ በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገር ሆነው ሰላምን የሚያደፈርሱ አካላትን በምንም መልኩ ልንታገስ አይገባም፤ተላልፈው በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በዲያስፖራ ማህበሩ አማካኝነት በመሰባሰብ ለአገሪቱ ሰላም ከመቼውም በላይ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመላው ዓለም ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ሙሐመድ ሁሴን