ቦንጋ፡- የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የከፋን ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት የሚሰንድ ቤተ መዛግብት ሊያቋቁም ነው። ዩኒቨርሲቲው በከፋ ታሪክ ላይ የተጻፉ መዛግብትንና ድርሳናትን ለማሰባሰብ ከዞኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት ላይ ይገኛል።
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ከክልሉ፣ ከዞኑና ከቦንጋ ከተማ ባህልና ቱሪዝም አካላት ጋር በመሆን የአካባቢውን ታሪክ ወግና ባህል ለመሰነድ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በከፋ ታሪክ ላይ የተጻፉ ድርሳናትን ከባለሙያዎች ጋር በመሆን የመሰብሰብ ሥራ ይሰራል።
እንደ ዶክተር ጴጥሮስ ገለጻ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የታሪክ ውዝግብ የተፈጠረው ታሪኮችና ሰነዶች በአግባቡ ባለመያዛቸው ነው። ለዚህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምር በማድረግ ከመደበኛው ቤተ መጻሕፍት በተጨማሪ የብሄር ብሄረሰቦችን ታሪክ፤ባህልና ወግ ጠብቆ የሚያቆይና ለምርምር መነሻ የሚሆኑ ቤተ መዛግብት ሊኖራቸው ይገባል።
የአካባቢን ባህልና ታሪክ አጥንቶ በመሰነድና በማህበረሰብ ምርምር ‹‹ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተሞክሮ ወስደናል›› ያሉት ዶክተር ጴጥሮስ፤ የቦንጋ አካባቢን ታሪክ ለመሰነድ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ቃል እንደገቡም ተናግረዋል። የዩኒቨርሲቲው ዓላማም የማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ነው። ከንጉሳውያኑ ዘመን ጀምሮ በደርግም ሆነ በኢህአዴግ የተከናወኑ ሁነቶች እንዳይጠፉ ሰነዶች እንደሚሰበሰቡና በቀጣይም ለጥናትና ምርምር የሚውልበት መንገድ እንደሚመቻች ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ አራተኛ ትውልድ ከሚባሉት ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን ታህሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም ነው ሥራ የጀመረው። ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀበለውም በአራት ኮሌጆችና በአሥራ አራት የትምህርት ክፍሎች 1288 ተማሪዎችን ነው። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የቅበላ አቅሙ ከ2700 በላይ አድርሷል። አራት የነበሩት ኮሌጆችም ወደ አምስት ያደጉ ሲሆን የትምህርት ክፍሎችም 26 ሆነዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ዋለልኝ አየለ