መቀሌ ከተማ ነው ተወልደው ያደጉት። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፄ ዮሃንስ 1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፍልስፍና ትምህርት ክፍልም ገብተው ለአራት ዓመት ፍልስፍና ከተማሩ በኋላ «ወያኔ ነህ» በሚል በደርግ መንግሥት ይታሰራሉ።ከስምንት ዓመት የእስር ቆይታ በኋላ ግን የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ተዘግቶ ይጠብቃቸዋል። በመሆኑም በህግ ትምህርት ክፍል ገብተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ። ትምህርታቸውን እንደጨረሱም በቀጥታ ለትምህርት ወደ አሜሪካ ይሄዳሉ። በአሜሪካም በዓለምአቀፍ ህግ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የጥብቅና ሥራ ፈቃድ አውጥተው በዋሽንግተን ዲሲ ለ20 ዓመታት ሰርተዋል። በእ.ኤ.አ 2016ዓ.ም ወደ አገራቸው ተመልሰው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። በተጨማሪም በቅርቡ ከዶክተር አብይ መምጣት ጋር ተያይዞ በአገሪቱ በመሻሻል ላይ ባሉ የተለየዩ ህጎች ላይ ግንባር ቀደም ሚና በመጫወት ላይ ናቸው።ከዛሬው የዘመን እንግዳ ከአቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ጋር በተለዩ ፖለቲካዊና ወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ያደረግነውን ውይይት እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ከ20ዓመት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ምንአይነት ነገሮች ተለውጠው ጠበቆት? በተለይ በፖለቲካው መስክ ምን ታዘቡ?
አቶ ሙሉጌታ፡- እኔ በውጭ በነበርኩበትም ጊዜ ቢሆን እድሜ ልኬን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ ስከታተል ነው የኖርኩት። ሃሳቤንም በገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ እገልፅ ነበር። እኔ ቀድሞውኑ ኢህአዴጎች ጉልበተኞች ስለነበሩ ለኢትዮጵያ ትክክለኛ መንግሥት ናቸው ብዬ አላስብም ነበር። አሁንም ቢሆን ኢህአዴግ በመሰረታዊነት ተቀይሯል ብዬ አላስብም። በእርግጥ ዶክተር አብይ ስልጣን ላይ ከመጡ በኋላ አንዳንድ የታዩ ለውጦች አሉ። በተለይም እኔ የማደንቀው የመናገርና የፕሬስ ነፃነት በተጨባጭ መሰጠቱ ነው። ከሱ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ድርጅቶች ነፃ ሆነው ፖለቲካቸውን የሚያራምዱበት ምህዳር ተፈጥሯል። ግለሰቦች እንደፈለጋቸው ሃሳባቸውን ይገልፃሉ፤ ይደራጃሉ። ህጎችንም ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት በራሱ ሌላው የሚደነቅ ተግባር ነው። ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው። ይሁንና ይሄ ሁሉ ነገር ችግር ላይ የሚወድቀው ኢትዮጽያ ውስጥ ሰላም ባለመኖሩ ነው። ስለዚህ በአጭሩ ሰላም ከሌለ ነፃነት ምንም ትርጉም የለውም ባይ ነኝ። ምክንያቱም ስጋት የሚሰማሽ ከሆነ ነፃነኝ ማለት አይቻልም። መናገርም፥ መስራትም፤ መንቀሳቀስም አይቻልም። እናም በዚህ ምክንያት በጥሩ መንገድ የተጀመረው ለውጥ አሁን ችግር ላይ የወደቀ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ለዚህ ሰላም መታጣት አብይ ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ሙሉጌታ፡- ዋናው ችግር ብዬ የማምነው ኢህአዴግ ነው። ከዚህ ቀደምም የነበረው ኢህአዴግ ነው፤ አሁንም ያለው ኢህአዴግ ነው። ዶክተር አብይም ኢህአዴግ ናቸው። ለእኔ ኢህአዴግ ስሙና መልኩ ነው የተቀየረው። ምክንያቱም አሁንም ፓርቲው ከመሰረቱት ድርጅቶች መካከል ኦዴፓ፥ አዴፓና ደህዴን አሉ። እነዚህ ድርጅቶች ናቸው የብልፅግናን ፓርቲ የፈጠሩት። ህወሃትም የብልፅግና ፖርቲ አባል ባይሆንም ያንን የኢህአዴግን አላማ ይዞ አንድ ክልል ያስተዳድራል። ስለዚህ ለእኔ በተግባር የተቀየረ ነገር የለም። ምንአልባት ፍላጎት ሊኖር ይችላል። ለውጥ የሚፈልጉ መሪዎች አሉ። ግን እነዚያ ለውጥ ፈላጊዎች ለውጡን እንዴት ማስቀጠል እንዳለባቸው አያውቁም። ይህንን ደግሞ እነሱም ራሳቸው የሚክዱት አይመስለኝም። ለምሳሌ ከየት ወዴት እንደሚሄዱ ግልፅ አይደለም። እኛም ከየት ተነስተን ወዴት እንደምንሄድ የዶክተር አብይ መንግሥት አላስረዳንም። መደመር ራሱ ፍልስፍናው ግራ የሚጋባ ነው። ምክንያቱም እያየን ያለነው ችግሩ ሲባባስ ነው። ጭራሽ ችግር በተፈጠረ ቁጥር መንግሥት ጥያቄ ሲጠየቅ እንኳን አይመልስም። ለምሳሌ በቅርቡ የታገቱ ተማሪዎችን በሚመለከት መንግሥት ምላሽ ሳይሰጥ ለረጅም ጊዜ ቆይቷል። እነዚህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መንግሥትን አምነው ከተወለዱበት አካባቢ ርቀው ሄደው መንግሥት በመደባቸው ዩኒቨርሲቲ እየተማሩ የነበሩ ናቸው። መንግሥትን አምነው ወደ ዩኒቨርሲቲው በመግባታቸው የእነሱን ደህንነት ማረጋገጥ ነበረበት። አሁን ግን ጭራሽ የት እንዳሉ እንኳን ሲናገር አንሰማም። ያ በጣም የሚያስፈራ ነው። አገሪቱ አሁን በሰላማዊ ሰልፎች እየተናጠች ነው። ለዚህ ደግሞ ችግሩ የሚመስለኝ ኢህአዴግ ነው። ድሮም ኢህአዴግ ነበር ችግሩ አሁንም ኢህአዴግ ነው ችግሩ የምለው ለዚህ ነው።
የብልፅግና ፓርቲ የብልፅግና ፓርቲ ነኝ ብሎ ስሙን ቢቀይርም በመጀመሪያ ደረጃ ሰዎቹ አንድአይነት ናቸው። የኢህአዴግ መሪዎች የነበሩ ናቸው አሁንም የብልፅግና ፓርቲ መሪዎች የሆኑት። እናም ለስሙ እንቀይራለን ተባለ እንጂ ኢህአዴግ ሲሰራ ከነበረው የተለየ ነገር ወይም መሰረታዊ የሚባል መዋቅራዊ ለውጥ አላየሁም። እንዳልኩሽ ሰው አሁን ሃሳቡን የመግለፅ መብት አለው። ግን እንደልብሽ መንቀሳቀስ አትቺይም። ነፃነኝ ብለሽ በእርግጠኝነት ከአንዱ ክልል ወደ አንዱ ክልል ለመሄድ ትሰጊያለሽ። በሆነ ሰዓት የሆነ ነገር ሊፈጠር ስለሚችል ከባድ ነገር ነው ያለው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚታገቱ ከሆነ እንዴት ነው አንድ መንግሥት ሰላም አረጋግጫለሁ ሊል የሚችለው?። ስለዚህ ለእኔ ለውጡ ተጨናግፏል። በመጀመሪያ ደረጃም ቢሆን ኢህአዴግ አልቻልኩም ብሎ በተደጋጋሚ ሲናገር እንደነበር ይታወቃል። እናም ስሙን ብቻ በመቀየር አገር ይቀራል ብሎ ማሰብ በጣም ከባድ ነው። እናም ነገሩን ስታዪው ትንሽ ጨዋታ ይመስልሻል። መሰረታዊ ለውጥ የለም። ፖሊሶቻችንና ፍርድቤቶቻችን እንዴት እንደሚሰሩ ይታወቃል። ህዝቡ ተረጋግቶ እየኖረ አይደለም። ለነገሩ ሰላም እንደሌለ መንግሥትም ያምናል። እንደሚመስለኝ ኢህአዴጎች የፈጠሩትን ችግር እኛ ራሳችንን እናስወግደዋለን ብለው ስለተነሱ ነው ሁኔታው እየተባባሰ የመጣው። አንቺ ራስሽ የፈጠርሽውን ችግር እንዴት ብለሽ ነው አንቺ ራስሽ የምታስወግጅው? ቀላል ነገር አይደለም። ምክንያቱም አዲስ መንግሥት አይደለም የመጣው። 28 ዓመት የቆየ መንግሥትና በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ሲሰራ የቆየውን ስህተት ራሱ ሊያስተካክል የሚችለው በምን አግባብ ነው ራሱ የሚቀይረው? ሰው፥ አመለካከትና አሰራር ሳይቀየር እንዴት ነው አንድ መንግሥት ራሱን በራሱ እኔ ያጠፋሁትን ጥፋት መልሼ እክሳለሁ የሚለው? ከባድ ሥራ ነው? እሱ ይመስለኛል ዋነኛው ችግር።
አዲስ ዘመን፡- የአመራር ብቃትና ቁርጠኝነት ችግርስ አለ ብለው አያምኑም?
አቶ ሙሉጌታ፡- ዋናው ተቀባይነት ነው የሚመስለኝ። ይኸውልሽ ዶክተር አብይ እንደሰው ብቁ ሊሆን ይችላል። በጣም የተማሩ፤ አገራቸውን የሚወዱ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ናቸው ብዬ ነው የማስበው። ቀናነታቸውንም አልጠራጠረውም። አገር ስትመሪ ጥሩ ሰው መሆን ብቻ በቂ አይደለም። መሪ ስትሆኚ ወዴት መሄድ እንደምትፈልጊ ማወቅ መቻል አለብሽ። እንደ መሪ ሃይል ማሰባሰብ መቻል አለብሽ። ስለዚህ ዶክተር አብይ የሚመሩትን አዲስ ሃይል ማሰባሰብ አልቻሉም። በሌላ በኩል ደግሞ ከውጭ የመጡ ተቋዋሚ ሃይሎች በርካታ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ የታጠቁም ናቸው። አሁን ላይ ጫካ ውስጥ ጦርነት አለ። ያን ያህል ነው ችግሩ የከፋ የሆነው። እነዚህ በርካታ ተቃዋሚ ሃይሎች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከመንግሥት ጋር ተገናኝተው የሚደራደሩም አይደሉም። ስለዚህ ብዙ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። ልክ ግን እንዳልሽው የአመራር ችግር አለ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መስጠት የሚገባቸውን አመራር እየሰጡ አይደለም። ወይም ከእሳቸው የሚጠበቀውን አመራር እያየን አይደለም። ተመልካች እነዚህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከታገቱ ሁለት ወር ሆኗቸዋል!። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ዶክተር አብይ ተናግረው አያውቁም። ይህ አመራር አይደለም። ይሄ ደንበኛ ማስረጃ ነው። እንዴት ሁለት ወር ሙሉ ዝም ብሎ ይቀመጣል። ያውም የተለየዩ የመንግሥት ባለስልጣናት የተለያየ አይነት እርስበርሱ የሚጋጭ መረጃ እየሰጡ ባሉበት ሁኔታ ማለት ነው። አገር በሰላማዊ ሰልፎች እየተናጠ እንዴት ነው ዝም የምትይው?። በነገራችን ላይ
ዶክተር አብይ በባህሪያቸው ዝም የሚሉ አይነት መሪ አይደሉም። በጣም ተናጋሪ ሰው ናቸው። ታዲያ እንዴት እንደዚህ አይነት ነገር ተፈጥሮ ዝም ይላሉ?
አዲስ ዘመን፡- ዝምታቸው የታገቱት ተማሪዎች ላይ ችግር እንዳይፈጠር ከሚል ስጋት የመነጨ ቢሆንስ?
አቶ ሙሉጌታ፡- ትክክል ነው፤ መጀመሪያ ላይ ልጆች የት እንዳሉ፤ ማን እንዳፈናቸው፤ አሁን በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ላያውቁ ይችላሉ የሚል እምነት ነበረኝ። ምንአልባትም ደግሞ ካገቷቸው ሃይሎች ጋር እየተደራደሩ ከሆነ አውቀውም መናገር ላይፈልጉ ይችላሉ ብዬም አስቢያለሁ። ወይም ደግሞ ልጆቹ ላይ ችግር ደርሶባቸውም ሊሆን ይችላል። ይሄ የእኔ ግምት ነው። ምክንያቱም የማውቀው መረጃ ስለሌለ ነው። ግን ለረጅም ጊዜ ዝም ማለት ልክ አይደለም። መሪ ዝም አይልም። እንኳን ታዲጊ የሆኑ ልጆች ከዩኒቨርሲቲ ተወስደው ቀርቶ መንገድም ሲዘጋ መንግሥት ማብራሪያ መስጠት መቻል አለበት። እናም ከሁለት ወራት ላለነሰ ጊዜ ዝም መባሉ ሳያንስ ጭራሽ እርስበርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎች መስማታችን የጥሩ አመራር ምልክት አይደለም ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጉዳይ ሳንወጣ ከታገቱት ሰዎች በአብዛኛው ከአማራ ክልል የመጡ እንደመሆናቸው በሌላ በኩል ድርጊቱንም በይፋ አውግዘው ሰላማዊ ሰልፍ የወጡትም በአማራ ክልል ያሉ ዜጎች መሆናቸው በራሱ ምን ያሳያል? ደግሞስ ነገ የሌላው ብሄር ተወላጅ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ የማይደርስበት ስለመሆኑ ምን ዋስትና ይኖረዋል?
አቶ ሙሉጌታ፡- እውነት ነው! በመጀመሪያ ደረጃ በስምንቱ ክልሎች እኔ አፍረት ተሰምቶኛል። አንድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ችግር ገጠመው ሲባል አንድ ኢትዮጵያዊት ችግር ገጥሞታል ተብሎ ነው መታየት ያለበት። ይህ አለመደረጉ በጣም ነው የሚያሳፍረው። አማራ ክልል ብቻ ነው ሰልፍ እያየን ያለነው። በእውነት የሚያሳዝን ነው። ሌሎቹ ስምንት ክልሎችስ የት ሄዱ? እንዴት ጥያቄ አያነሱም?። ልጆቻችን የት ሄዱ እንዴት አይሉም? ደግሞስ የአማራ ልጅ እንዴት ነው የትግራይ ልጅ የማይሆነው? ታዲያ ለምን እዚያ ሄዱ ተማሪዎቹ? ለምንስ ታዲያ ደንቢ ዶሎ ተላኩ? አገራችን ኢትዮጵያ ምድር ነው ብለው አይደለም እንዴ የተላኩት? እናም ይህ ችግር ሲያጋጥም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሰው ሁሉ መረባረብ ነበረበት። አሁን ግን በጣም የሚያሳፍረው ልጆቹ ከአማራ ክልል የሄዱ ስለሆኑ ብቻ የአማራ ክልል ህዝብ ብቻ የሚጨነቅላቸው ከሆነ በእውነት ሰውነታችንን አጥተነዋል። ሰው መሆናችንን አቁመነዋል። ያሳፍራል። እናም ሁሉም ክልሎች መጠየቅ ነበረባቸው። በዚህ ደረጃ ፖለቲከኞችም ከስረዋል። ስምንቱን ክልሎች የሚመሩ መንግሥታት በጣም በከፍተኛ ደረጃ የፖለቲካ ኪሳራ አሳይተዋል።
በእርግጥ ይሄ ሁኔታ ከመሬት የመጣ አይደለም። ላለፉት 28 ዓመታት ሥራ ሲሰራበት የነበረ ጉዳይ ነው። ሁሉም በየክልሉ፤ በየጎጡ ተሸንሽኖ እንዲቀመጥ ሥራ ሲሰራበት ስለቆየ ከሼላችን፤ ከጎጣችን ወጥተን ማሰብ መቻል አቃተን። ሰው መሆናችን እየቀረ የሆነ ብሄር የሆነ ዘር ሆነን ቀርተናል። እናም በዚያ ምክንያት መንግሥታትም ጉዳዩን ችላ ማለት ጀመሩ። የክልል መንግሥታት የእኔ ክልል ሰው ካልሆነ አያገባኝም ማለት ነገር ታይቶባቸዋል። እሱ ማለት ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱም ትርጉም የለውም ማለት ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ተመራጮች ናቸው ምክርቤት ውስጥ የሚቀመጡት። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ፓርላማው እንኳን አፍ አውጥቶ መከራከር አልቻለም። ለምሳሌ ሰሞኑን ጠቅላይ አቃቢ ህግን አናግሮ ነበር፤ ነግር ግን ፓርላማው ስራውን አልሰራም፤ ጠቅላይ አቃቢ ህጉን እዛው ማውረድ ነበረበት። መቅጣት፥ ማስጠንቀቂያ መስጠትና ማዘዝም ይችል ነበር። በነገራችን ላይ እኔ የማስተምረው ህገመንግሥት ነው፤ ስለዚህ የምናገረውን አውቃለሁ። ምክርቤቱ የመጨረሻ ስልጣን ነው ያለው። እንኳን አቃቢ ህግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን «ለምንድን ነው ስራህን ያልሰራኸው?» ብሎ መጠየቅ ይችላል። ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነታቸው ለምክርቤቱ ነው። ምክርቤቱ የመረጣቸው በመሆኑ ሊያወርዳቸው ይችላል። ስለዚህ በእኔ እምነት ምክርቤቱ ዶክተር አብይን ጠርቶ ካልቻልክ ንገረንና ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር እንመርጣለን እስከማለት መድረስ ነበረበት። ህጉ የሚለው እንደዚህ ነው። አሁን ግን ጠቅላይ አቃቢ ህጉ ቀርበው የሰጡት መልስ እሳቸውም የታገቱት ተማሪዎች የት እንዳሉ እንደማያውቁ ነው። የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ስለታገቱት ሰዎች የማያውቅ ከሆነ በጣም አሳሳቢ የሆነ ችግር ውስጥ ነን ማለት ነው። ሰው ማገት ወንጀል ነው፤ ስለዚህ ወንጀል እሳቸው ካላወቁ ማን ሊያውቅ ይችላል? በቃ በዚህ ደረጃ ነው ኪሳራችን።
አዲስ ዘመን፡- አጋች ናቸው ተብለው የሚጠረጥሩ ሃይሎች በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ወጥተው እንደሚናገሩትም በዚህ ጉዳይ ላይ እንደሌሉበት ይገልፃሉ። ይህንን ሁኔታ አንዳንድ ሰዎች የፖለቲካ ጫወታ ነው ይሉታል፤ ለእርሶዎ ምንድን ነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- እኔ የመረጃ ነፃነት ህግ በቅርቡ በማርቀቅ ተሳትፊያለሁ። ይኸውልሽ መረጃ ሳይኖርሽ ማውራት ማለት ችግር ማቃለል ሳይሆን ችግር ላይ ችግር መጨመር ማለት ነው። አሉባልታና ግምት ነው የሚሆነው። ዝም ብሎ መላምት ነው የሚሆነው። ይሄ ደግሞ ነገሩን ያባብሰዋል። ይሄ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው የሚሆነው። በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃንም ላይ እየቀረቡ ያሉት መላምቶች ነው። ማንም ሰው በእርግጠኝነት የማውቀው ነገር አለኝ ብሎ ሲናገር አልሰማሁም። ምክንያቱም መረጃ መንግሥት ካልሰጠሽ ከየት ይመጣል?። መንግሥት ራሱ በተወናበደበትና የተለየዩ የመንግሥት ባለስልጣናት የተለያየ መረጃ እየሰጡ ባለበት ሰዓት ያለሽ እድል አንቺም የራስሽን መረጃ መልቀቅ ነው። በቃ መረጃ ትፈጥሪያለሽ። የምትፈጥሪው ደግሞ በስሜትሽና በፖለቲካ እምነትሽ ነው። የግልሽን ፍላጎት ያስፈፅምልኛል በምትይው ነገር ነው የምትመሰረችው። አሁን ሁሉም ሰው የመረጃ ምንጭ ሆኗል። ምክንያቱም ትክክለኛ መረጃ ሊሰጥሽ የሚገባው ሃይል እየሰጠሽ ስላልሆነ ማለት ነው። እሱ በጣም አደገኛ ነው። መረጃ እንደዚህ ከተበጣጠሰና ከተበታተነ አንቺ የምትፈልጊውን ነው የምታምኚው። የግድ እውነት መሆን የለበትም። እነዚህን ሰዎች መንግሥት ነው ሆን ብሎ ያጠፋቸው፤ ብሎ የሚያምን ሰው አለ። ምክንያቱም መንግሥት ትክክለኛውን መረጃ እየሰጠው አይደለም። አሉባልታው እየተስፋፋ በመጣ ቁጥር ወደ እውነት እየተቀየረ ይመጣል። ይህም ሲሆን ሰዎችን ወደ አላስፈላጊ ንዴት ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል። በተለይ የቅርብ ዘመዶቻቸውና የእኛ ናቸው ብለው የሚያስቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ጊዜው እየተራዘመ በሄደ ቁጥር ወደ ረብሻና ተቃውሞ ሊገቡ ይችላሉ። ይህ ጉዳይ ቀላል አይደለም።
አዲስ ዘመን፡-በአገሪቱ ያለው የሰላም እጦትና ውጥንቅጥ በብልፅግና ስም የተደረጁት ፓርቲዎች መካከል መግባባት አለመኖሩን ያሳያል ብለው የሚያምኑ አካላት አሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ።
አቶ ሙሉጌታ፡- እውነት ነው፤ መግባባትማ የለም። መግባባትማ እንደሌለ እነሱም ራሳቸው እኮ ነግረውናል። ኦዴፓን ውሰጅ፤ በዶክተር አብይና በአቶ ለማ አደባባይ የወጣ ፀብ አለ። እነዚህ ሰዎች በጣም ቅርብ የነበሩ ሰዎች ነበሩ። ማን ከማን ጋር እንደሚስማማ በትክክል ማወቅ አትችይም። በእኔ እምነት የኢህአዴግ መሪዎች አብረው ለዘመናት እንደመኖራቸው ተቋስለዋል።በዚህ ምክንያት የተጠናከረ አመራር እያየን አይደለም። ለምሳሌ ችግር ሲፈጠር ፓርቲው ተሰብስቦ መፍትሄ ማምጣት አልቻለም። በነገራችን ላይ ይህ የተማሪዎች መታገት ጉዳይ ሌላ አገር ቢሆን ኖሮ እኮ ትልቅ ፖለቲካዊ ቀውስ ባስከተለ ነበር። አሁን ቁጥራቸው እንኳ በአግባቡ አይታወቅም፤ ያሳፍራል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በውጭ ሃይል ሳይሆን በገዛ ወገናቸው ታግተው መገናኛ ብዙ ኃን በአግባቡ እየዘገቡ አይደለም። ይህ አይነቱን ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው የምታይው። በጣም አሳዛኝ ነገር ነው። የመንግሥት ባለስልጣናት አይጠይቁም። በዚህ ሰዓት ማበድ ነው የሚገባን የነበረው። ሰላማዊ ሰልፍ ለምንድን ነው አዲስ አበባ ላይ የማይወጣው?
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተው በአስተዳደሩ መከልከላቸውን ሲገልፁ ነበር?
አቶ ሙሉጌታ፡- እንዴ! ብትከለከይስ መብትሽ እኮ ነው። ምክንያቱም መንግስት ሰላማዊ ሰልፍ የመፍቀድ መብት የለውም። አንቺ ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ብቻ ነው የሚጠበቅብሽ። ነገር ግን አሳውቀሽ ስትከለከይ ምክንያቱ ለአንቺም ሆነ ለህዝቡ በይፋ ሊገለፅ ይገባል። አሁን ግን በሃሜት ደረጃ ነው የምንሰማው። ጋዜጠኞችም ብትሆኑ ስራዎቹን እየሰራችሁ አይደለም። ሰላማዊ ሰልፍ ተጠይቆ ለምን አልተካሄደም ብላችሁ አትጠይቁም፤ ሁሉነገር ሚስጥር ነው። አንቺ በስራሽ እንደምትጠየቂው ሁሉ መንግሥትም መጠየቅ አለበት። አሁን መንግሥትም የማስተዳደር ስራውን እየሰራ አይደለም። ሲፈልግ ሰላማዊ ሰልፍ ውጡ፤ ሳይፈልግ ደግሞ አትውጡ ማለት አይችልም። ለምሳሌ አማራ ክልል ሰልፍ መውጣት ከተቻለ ለምንድን ነው አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ ማካሄድ የማይቻለው?። ለምድን ነው በመቀሌ ሰላማዊ ሰልፍ ያልተደረገው?። እናም የክልል መንግሥታት በእውነት ጥሩ ሥራ እየሰሩ አይደለም። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሪዎች የእውነት መሪዎች አየደሉም። አቅሙምየላቸውም፤ ኃላፊነትም አይሰማቸውም።
አዲስ ዘመን፡-የሕወሃት ብልፅግናን አለመቀላቀሉ አጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳሩ ላይ ምንአሉታዊ ሚና ያንፀባርቃል?
አቶ ሙሉጌታ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ይሄ ነገር መፈጠር አልነበረበትም። እንዳልኩሽ ኢትዮጵያ ውስጥ የበሰሉ የፖለቲካ መሪዎች የሉንም። ያው ኢህአዴጎች ናቸው። ኢህአዴጎች ራሳቸው በተደጋጋሚ እንዳሉት በስብሰዋል። ስለዚህ ከበሰበሰ ድርጅት ነው እንግዲህ ለውጥ እየጠበቅን ያለነው። አሰራራቸው አመለካከታቸው ያረጀ ነው። አስቀድሜ እንዳልኩሽ እርስበርሳቸው ሲጎነታተሉ የቆዩ በመሆኑ ተቋስለዋል። በዚህ መሰረት ሕውሃቶች በራሳቸው ምክንያት ጥጉን ያዙ። እነሱ ነበሩ ይህችን አገር የሚቆጣጠሩት ነገር ግን ደከማቸው፤ ባለጉ። ይህንን የምልሽ ከራሴ ጨምሬ አይደለም፤ ራሳቸው ያመኑት እውነታን ነው። አንድ መንግሥት በስብሰናል ካለ ከዚያ በኋላ ለምን እንደሚቀጥል ግራ ነው የሚያጋባሽ። እነሱ ግን ይቅርታ ህዝቡን ጠይቀን ይቅርታ ተሰጥቶናል ባዮች ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ መቼ ይቅርታ እንደተጠየቀ፤ መቼ እንደሰጠ እኔ አላውቅም። ሁሉንም ነገር ራሳቸው ናቸው የሚያወሩት። ስለዚህ የራሳቸውን ወሬ ራሳቸው አምነውት ይቀጥላሉ። ከዚህ አንፃር እንግዲህ ሕወሃቶች ተገፍተው መቀሌ ገቡ። የህወሃቶች የፈለጉትን ምክንያት ሊሰጡ ይችላሉ፤ ለእኔ ግን የስልጣን ችግር ነው። ስልጣናቸው ተቀነሰ፤ ለነገሩ ማነው ስልጣኑ ተቀንሶበት መኖር የሚፈልገው? እኔ እንኳን የአገር ስልጣንን ያክል ነገር ይቅርና የለበስኩትን ጃኬት ብትወስጅብኝ በጣም ነው ቅር የሚለኝ። ስለዚህ ሌላ ታሪክ የለውም።
በነገራችን ላይ «የትግራይ ህዝብና ሕወሃት አንድ ናቸው» የሚባለው ነገር ለእኔ ትርጉም የለውም። የትግራይ ህዝብ ድሮም ነበር፤አሁንም አለ። ሕወሃቶች 28 ዓመት ሙሉ አዲስ አበባ ተቀምጠው አገር ሲገዙ የትግራይ ህዝብ ነበር።የትግራይ ህዝብ ያኔም ሲያለቅስ ነበር፤ አሁንም እያለቀሰ ነው።ስለዚህ ህዝቡ ላይ የተለወጠ ነገር የለም።ይሁንና ፖለቲከኞች ስለሆኑ የሌለ ችግር ይፈጥሩና እሱን ችግር እውነት በማስመሰል ህዝቡን ያልሆነ ውዝግብ ውስጥ ይከቱታል። ለምሳሌ የትግራይ መንግድ ተዘግቶ ነበር፤ እኔ መቀሌ ተወልጄ ባድግም፤ መንገዱን ማን እንደዘጋው እስካሁን አላውቅም። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሲናገር ሰምቼ አላውቅም። የትግራይ መንግሥት ራሱ ይህንን መንገድ የዘጋው እከሌ ነው ብሎ አያውቅም። እኔ በአደባባይም ጠይቄ አውቃለሁ። ህዝቡ ግን እንደምታውቂው ጥያቄ አይጠይቅም። ተዘጋ ሲባል ይናደዳል። ብሄርተኝነቱም ሰማይ ነክቷል። ሕወሃቶችም «በሌላ አካል ልትዋጥ ነው፤ ልትወረር ነው»እያሉ ብሄርተኝነቱን ያጋግሉታል። በዚህ ምክንያት በአሁኑ ወቅት የትግራይ ህዝብና ሕወሃት አንድ ናቸው ወደሚባልበት ደረጃ ተደርሷል።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ሁሉም ህዝብ ብሄርተኛና ወገንተኛ ነው ብሎ መጨፍለቅ አይሆንም?
አቶ ሙሉጌታ፡- በነገራችን ላይ በየትም አገር ድርጅትና መንግሥት አንድ ሆኖ አያውቅም። ለወደፊቱም አይሆንም። ምክንያቱም አንድ ድርጅት የሚያስፈፅመው ወይም የሚያራምደው የተወሰኑ አካላትን ፍላጎት ነው። ትግራይ ውስጥ እንኳ በርከት ያሉ ድርጅቶች አሉ፤ ይህም የሚያሳይሽ ትግራይም ቢሆን በአንድ ድርጅት ብቻ ሊወከል እንደማይችል ነው። ድርጅት ማለት የፍላጎት ተወካይ ማለት ነው።የህዝብ ፍላጎት ደግሞ አንድ አይደለም። የገበሬውና የነጋዴው ፍላጎት አንድ አይደለም። የክርስቲያኑና የሙስሊሙ ፍላጎት አንድ ላይሆን ይችላል። በሁለተኛ ደረጃ የፖለቲካ ድርጅት የሚፈጠረው በታሪክ አንድ ወቅት ላይ ነው። ዛሬ ተፈጥሮ የዛሬ ዓመት ደግሞ ላይኖር ይችላል። ህዝብ ግን ዘላለማዊ ነው፤ ይቅጥላል። አሁን ትግራይ ውስጥ ያለው ነገር የድርጅት ጉዳይ አይደለም። ብሄርተኝነት የተለየ ክስተት ነው።ጣሊያን ኢትዮጵያን ወረረ ሲባል የኢትዮጵያ ህዝብ ወረራውን ከመከላከልና ከመመከት ውጭ ሌላ ፍላጎት አይኖረውም። ስለዚህ ስትወሪሪ እንደአንድ ሰው ነው የምትሆኚው። መሪውና ተመሪው አንድ ነው የሚሆነው። ለዚያች ጊዜ ለዚያች ወቅት ማለት ነው። ትግራይ ሊወረር ነው ሲባል ሁሉንም ፍላጎትሽን አቁመሽ ወረራውን ለመመከት ነው የምትቆሚው።
በሌላ በኩል ግን አሁን ትግራይ ውስጥ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ የፖለቲካ ቀውስ ነው። በተለይ ደግሞ የሕወሃት መሪዎች አሁንም ምንም አይነት ለውጥ ሳያካሂዱ በስልጣን ላይ መኖራቸው የሚፈጥረው ቅሬታ አለ። እነዚያ ሽማግሌዎቹ አሁንም አሉ። የትውልድ ለውጥ እንኳን አልተደረገም። ትናንት ሲበድሉት የቆዩ አመራሮች እኮ ናቸው ዛሬም ያሉት። በዚህ ህዝቡ ቅሬታ ሳይሰማው ቀርቶ አይደለም። ነገር ግን እየተወረርክ ነው ስለተባለ በአንድ ልብ የመነሳት ነገር ይታያል። ይሁንና ይህ ሁኔታ አይቀጥልም። በአሁኑ ወቅት ትግራይ ወረዳዎች ሳይቀሩ ጥያቄ እያቀረቡ ነው። ይህ ጥያቄ ደግሞ ስለታፈነ ብቻ አይቆምም።
አዲስ ዘመን፡- የትውልድ ለውጥ አልተደረገም፤ አሁን ሕወሃት በሽማግሌዎች ነው እየተመራው ብለዋል፤ ይህ ሁኔታ የህውሃትን ለውጥ ፈላጊ ያለመሆን አመላካች ነው ማለት አንችልም?
አቶ ሙሉጌታ፡- ልክ ነሽ፤ ለውጥ እንደማይፈልግ እኮ ራሱ ተናግሯል። በተግባርም አሳይቷል። ላለፉት አምስት ዓመታት ሕወሃቶች ሳያቋርጡ ተሰብስበዋል። ነገር ግን አዲስ ነገር ማምጣት አልቻሉም። እኔ ከዚህ በኋላ ቢሆን ሕወሃቶች ራሳቸውን መለወጥ ይችላሉ ብዬ አላስብም። ግን የትግራይ ህዝብ ይነሳባቸዋል። ትግራይ የራሱ አብዮት ይኖረዋል። በእርግጥ ህውሃት በጣም ተዳክሞ ነበር። ዶክተር አብይ ሲመጡ አይተሽ ከሆነ ትግራይ ውስጥ 95 በመቶ ድጋፍ ነበራቸው። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ በህውሃቶች በጣም ተሰላችቶ ስለነበር ነው። ከዚያ በተለያየ ምክንያት ዳግመኛ ድጋፉን ለሕወሃት መስጠት ጀመረ። ይህ ሁኔታ ግን መቀየሩ አይቀርም። ምክንያቱም ነገ ህዝቡ ጥያቄዎቹ ካልተመለሱለት ወደ ተቃውሞ መሄዱ አይቀርም። ሌላው ይቅርና ከምርጫው በኋላ ሕውሃት እንዴት እንደሚቀጥል ራሱ ጥያቄ ነው የሚፈጥረው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች በዚህ ሁኔታ ክልሉ ራሱን አግልሎ መቆየት ስለማይችል ኮንፈዴሬሽን የመሆን እጣፈንታ እንዳለው ይገልፃሉ። በእርሶ እምነት ይህ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ አለ?
አቶ ሙሉጌታ፡- በነገራችን ላይ ኮንፌዴሬሽን የሚለውን ቃል የተማሩ ሰዎች ሳይቀሩ ሲጠቀሙበት ሳይ በጣም ነው የሚያስቀኝ።
ከፌዴሬሽን ወደ ኮንፌዴሬሽን የሚኬድበት አግባብ የለም። ኮንፌዴሬሽን ማለት ሁለት የተለየዩ መንግሥታት በስምምነት የሚፈጥሩት ግኑኝነት
ነው። ይህንን በቀላሉ ለማስረዳት እንግሊዞች በቀኝ ገዝተዋቸው የነበሩ 13 የአሜሪካ ግዛቶች ነፃ ሲወጡ 13 አገራት ተፈጠሩ። እነዚህ
አገራት ጠላታቸው አንድ ነው። ስለዚህ ይህ ጠላታቸው ዳግም ሊወረን ስለሚችል አብረን እንዋጋ ብለው የፈጠሩት ስምምነት ነው። ለምሳሌ
እኛም ከኤርትራ ጋር ኮንፌዴሬሽን መፍጠር እንችላለን፤ ነገር ግን አንድ አገር ውስጥ ኮንፌዴሬሽን የሚባል ነገር መፍጠር አይቻልም።
በጥቅሉ ከፌዴራሊዝም በኋላ የሚቀጥለው ግን መገነጣጠል ነው። እናም ትግራይ ወደ ኮንፌዴሬሽን ትሄዳለች የሚባለው የመገንጠል ሌላ
ስሙ ነው። ተማርን የሚሉ ሰዎች መገንጠል የሚለው ቃል ስለማይመቸው
ኮንፌዴሬሽን የሚል ቃል ይጠቀማሉ።
አዲስ ዘመን፡-በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በሰላም እጦት እየተናወጠች ባለችበት ወቅት ምርጫው መካሄድ የለበትም የሚሉ ወገኖች በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል ህገመንግሥቱ ይጣሳል፤ ያልተመረጠ መንግሥት ሊመራን ስለማይገባ ምርጫው መካሄድ አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ። እርሶ ከየትኛው ወገን ነዎት?
አቶ ሙሉጌታ፡- የሁለቱም ወገኖች ክርክር ጠንካራ ነው። አንዱ ብቻ ልክ ሌላው ስህተት የምትይው ነገር አይደለም። ለምሳሌ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ ላይ ምርጫ እናካሂድ ብሏል፤ ነገር ግን ነሐሴ ምርጫ ማካሄድ ይችላል ወይ? የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም። የሚመች ስለመሆኑ አልተረጋገጠም። ምክንያቱም ብዙ አካባቢዎች ላይ ዘናብ ይዘንባል፤ ጎርፍ አለ። በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ምርጫ የሚካሄደው?። ስለዚህ በመሰረታዊነት የቴክኒክ ችግር እንኳ ቢፈጠር መራጮች ወደ ምርጫ ላይሄዱ ይችላሉ ከተባለ እሱን ነገር ባሳማኝ መልኩ መመለስ መቻል አለበት።የሆነ ዋስትና መስጠት መቻል አለብሽ። ሌላው ዋነኛውና ከባዱ ችግር ሰላም ያለመኖሩ ነው። ሰዎች በነፃነት መንቀሳቀስ ካልቻሉ እንዴት ተደርጎ ነው ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው?። ምርጫውን የሚያውኩ ሃይሎች ቢኖሩስ? መንገድ ቢያፈርሱ፤ ረብሻ ቢፈጥሩስ? እሱን ነገር መንግሥት እያስረዳን አይደለም። ለምንድን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጥተው በእርግጠኝነት ሰላም አሰፍናለሁ ምርጫው በሰላም እንደሚካሄድ አረጋግጣለሁ ብለው የማይናገሩት? ለዚህ ነው አየሽ አመራር የለም የምልሽ። የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበሯ ራሳቸው በተደጋጋሚ እየገለፁ ያሉት መንግሥት ይተባበረናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ነው።
ምክንያቱም ቦርዱ ነፃ ስለሆነ ምርጫ የሚያካሂደው ቦርዱ ነው፤ ሰላም የሚያስጠብቀው መንግሥት ነው። ነገር ግን ከዚያ በላይ እርዳታ ነው የሚያስፈልገው። ለምሳሌ ትራንስፖርት የማይገባበት ቦታ አለ፤ የመከለካያ ሰራዊት ድጋፍ ያሻል። በመሰረቱ መከላከያ ሰራዊት ምርጫ ውስጥ መግባት የለበትም። መከላከያ ሰራዊት የሚገባው የውጭ ወረሪ ሲኖር አልያም ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ስንገባ ነው። መከላከያ መኪና የማቅረብ ግዴታ የለበትም። ሰራዊቱን «ና ጠብቅልኝ»አትይውም። ምርጫ በፖሊስ እንጂ በጦር ሰራዊት አይጠበቅም። ግን ሁኔታው ከፖሊስ አቅም በላይ ሊሆን ይችላል ተብሎ ስለሚገመት መከላከያውን እባካችሁ ተባበሩን ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ግን ግዴታ የለባቸውም። በአጠቃላይ መንግሥትን ግን ለምርጫም አመች ሁኔታ መፍጠር አለበት። በአሁኑ ወቅት መንግሥትም በይፋ ሰላሙን እንደሚያረጋግጥ ባለመናገሩ እኔም ሳልቀር ምርጫው ላይካሄድ ይችላል የሚል ጥርጣሬ አለኝ። ስለዚህ ምርጫው መራዘም አለበት የሚሉ ሰዎች እነዚህ ጥያቄዎች ስላልተመለሱላቸው ነው የሚመስለኝ።
በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫው መራዘም የለበትም የሚሉ ሰዎች ደግሞ ለምሳሌ ሕወሃትን ብትወስጂ በጭራሽ አንድ ቀንም ቢሆን እንዲያልፍ አልፈልግም ብሏል። ምክንያቱ ደግሞ ህገመንግስቱ አይፈቅድም የሚል ነው። ስለዚህ ህገመንግስቱ ህገመንግስቱ የሚጣስ ከሆነ ህጋዊ አገዛዝ የለም ማለት ነው። በጣም የሚያስቀው ነገር ደግሞ ምርጫውን ራሳቸው ብቻቸውን ማካሄድ ይችላሉ። አካሄዱ ማለት ግን ትክክለኛ ምርጫ ይካሄዳል ማለት አይደለም። ምክንያቱም አሁንም ቢሆን ትግራይ ውስጥ ለውጥ የለም፤ ምርጫውን የሚያሸንፈው ማን እንደሆነ መገመት ከባድ አይደለም። ስለዚህ ቶሎ ምርጫ ቢካሄድ ሕወሃት ተጠቃሚ ነው የሚሆነው። እየቆየ ከሄደ ግን ትግራይም ውስጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አናውቅም፤ ምክንያቱም ህዝቡም ለዘላለም ተሸክሞ መቆየት ስለማይችል ነው። ይህ ጉዳይ የፖለቲካ ሂሳብ ነው። መጥፎ ወይም ጥሩ ሰው ከመሆን ጋር አይገናኝም። እነዚህ ሰዎች የፖለቲካ ሰዎች ናቸው የፖለቲካ ሂሳብ ነው የሚያስቡት። ስለዚህ ለእኔ በሁለቱም በኩል ችግር አለ። እናም ይሄኛው ነው ትክክል ብሎ መምረጥ ከባድ ነው። ብልፅግና ፓርቲ ራሱ የህግ ክፍተት ስላለበት ይህንን ማስተካከል የሚችለው ምርጫው ቶሎ ቢካሄድ ነው። በተለይም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫው ተካሂዶ ካሸነፉ ህጋዊ ቅቡልነት የሚኖራቸው በመሆኑ ረብሻ እንኳ ቢፈጠር በጉልበት የማስቆም እድል ይኖራቸዋል። ህጋዊ መሰረት ስላላቸው ለምን አደረጉ ብሎ የሚጠይቃቸው አይኖርም፤ ምክንያቱም የአገር ሰላምን ማስጠበቅ ስለሚገባቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡-አሁን ባለው ሁኔታ ትግራይ ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በእኩል መንገድ መሳተፍ በሚችሉበት መንገድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል?
አቶ ሙሉጌታ፡- ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንኳን ትግራይ ሌሎች አካባቢዎችም መካሄድ ይችላል ብዬ አላምንም። የዴሞክራሲ መሰረት እኮ ሰላም ነው። ለምሳሌ አሁን ትግራይ ውስጥ ሰላም አለ ይባላል አይደል? እኔ ግን አይመስለኝም።መቀሌ ውስጥ እኮ በየቦታው አስቁመውሽ ትፈተሺያለሽ። ይህ ባለበት ሁኔታ ሰላም አለ ማለት አይቻልም። ሰላም በሌለበት እንዴት ነው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የምታስቢው? እኔ በመሰረቱ ዴሞክራሲያዊ እንዲኖረን አይደለም የምመኘው፤ ሰላም እንዲመጣ እንጂ። እኔ ኢትዮጵያና ዴሞክራሲ ለጊዜው የተራራቁ ናቸው ብዬ ነው የማስበው። አሁን እኔ የምፈልገው ሰላም ማስከበር የሚችል መንግሥት ነው። ሰው ሥራ መስራት የሚችልበት፥የተረጋጋ ህይወት እንዲኖር የሚያደርግ መንግሥት ነው የምጠብቀው። ይህንን ስልሽ ዴሞክራሲ የሚጠላ ሰው አለ ማለቴ አይደለም። በዚህ ሰዓት ለእኔ ዴሞክራሲ ቀልድ ነው። እንደቅንጦትም የሚታይ ነገር ነው። ለነገሩ ኢህአዴጎችም በዴሞክራሲ ስም ነው ሲቀልዱ የቆዩት። በሠላሙም ጊዜ ዴሞክራሲ አልነበረም። አቅማችን ለዚያ የደረሰ አይመስለኝም። ስለዚህ ወደድሽም ጠላሽም እኔ ትግራይን ለህውሃት ሰጥቼዋለው። ህዝቡ የብሄርተኝነት ስካር ውስጥ ያለ ነው የሚመስለኝ፤ በስሜት ነው እየተመራ ያለው። ስሜታዊነት ሲኖር ደግሞ ምክንያታዊነት አይኖርም። ምክንያታዊነት ከሌለ ውይይት አይኖርም። አሁን ላይ የሕወሃትን መንግሥት በትግራይ ውስጥ መቃወም ከባድ ነው። እድል እንኳን ቢሰጥሽ ልትሰሪ የምትቺይበት ሁኔታ የለም።ዶክተር አረጋዊ ለትግል ጓዶቻቸው ቀብር ሄደው እንኳ ድንጋይ ተወርውሮባቸዋል። ይሄ የሚያሳያሽ ሕውሃት እንኳ ሊያስከብረው የሚችል አለመሆኑ ነው። የብሄርተኝነት ስሜቱ ጣራ ነክቷል። የመቻቸል አቅሙም ሙሉ ለሙሉ ጠፍቷል። እናም ምንም ነገር መስማት አይፈልግም። አረናዎች «እየተበደልን ነው» ሲሉ «አሁን እንደሱአይነት ልዩነት አንፈልግም» ይባላሉ። «አሁን ጠላት ስላለን ይሄ ጉዳይ ለበኋላ ይቆይልን» የሚል ህዝብ አለ። ያንን ጠላት አንድ ሆነን ነው መመከት አለብን የሚል እሳቤ ነው የተፈጠረው። ይህንን እኮ ነው ቀውስ ያልኩሽ።
አዲስ ዘመን፡-ግን የትግራይ ጠላት የሚባል ህዝብ አለ እንዴ?
አቶ ሙሉጌታ፡- ህዝብ የህዝብ ጠላት ሆኖ አያውቅም። ሊዮ ቶልስቶይ የሚባል የራሺያ ደራሲ ሰዎች ጦርነት እንደሚኖር አውቀው ቢገቡ ኖሮ ጦርነት አይኖርም ነበር ይላል። ጦርነት ውስጥ የሚያስገባሽ የሆነ ጉልበተኛ ነው። በታሪካችንም የምናየው መንግሥታት ያዋጉናል እንጂ ህዝብ ራሱ ልዋጋ ብሎ ተነስቶ አያውቅም። ብሄርተኝነት በተለይ በህዝብ ማዕበል ሊመራ የሚችል ስሜት ነው። እነዚህ ሊሂቃን የሚባሉት ደግሞ ብሄርተኝነትን ተጠቅመው ህዝብን ወደአልሆነ አቅጣጫ የሚመሩት። ለምሳሌ የተዘጋ መንገድ ማስከፈት ያለበት መንግሥት ሆኖ እያለ ይሄ መንገድ የተዘጋው አንተን ለማጥፋት ነው በማለት ህዝቡን ይሰብኩታል። የትግራይም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ አመራው ሲጨቁንህ ነበር እየተባለ ሲነገረው ኖሯል፤ ይህ ለእኔ ዝም ብሎ እብደት ነው። ህዝብ ህዝብን አይጨቁንም።የሚጨቁኑት ፖለቲከኞች ናቸው። እንኳን እዚህ አገር በጣም ሰለጠነች በምትባለው አሜሪካ ብትሄጂ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራንፕ «ስደተኞች ናቸው አሜሪካን እየበጠበጡ ያሉት» ይላሉ። ግን ስደተኛ ባይኖር አሜሪካ አንድ ሌሊት አያድርም ነበር። ስልጣንሽ ላይ ተመችቶሽ ለማቆየት ሁልጊዜም ቢሆን የሆነ ጠላት ማምጣት ወይም መፍጠር አለብሽ። እኔ አውቅልሃለው ማለት ካልቻልሽ መንግሥት ሆነሽ መቆየት አትቺይም። ይሄ ግልፅ ነው። ኢትዮጵያዊነት ግን እነሱ በሚሉት መልኩ የሚገለፅ አይደለም፤ ከየትም ቦታ ተወልደን የትም ተምረን የፈለግንበት የምንኖርባት አገር ነበረች። አሁን ግን ፖለቲከኞች ሆን ብለው የህዝቡን አስተሳሰብ አበላሹትና ነው አሁን የምናየው ነገር የተፈጠረው። ይህም በተወሰነ መልኩ ተሳክቶላቸዋል፤ አሁን ተከፋፍለናል።
አዲስ ዘመን፡-ብሄር ተኮሩ ግጭት ወደ እምነት ተቋማትም እየተሻገረ ነው፤ የዚህ ሁኔታ መጨረሻ ምን ይሆናል ብለው ያምናሉ?
አቶ ሙሉጌታ፡- ይህንን ሁኔታ ካልተቆጣጠርነው ያለምንም ጥርጥር መጨረሻው መጥፎ ነው የሚሆነው። ጥሩው ነገር ግን አሁንም ቢሆን ችግር ያለው በህዝቦች መካከል አለመሆኑ ነው። በታሪካችንም አንድ ህዝብ ሌላውን ህዝብ የጨፈጨበት ሁኔታ የለም። ቀዳማዊ ሃይለስላሴ የትግራይን ህዝብ በአውሮፕላን መደብደባቸው ይታወቃል፤ በወቅቱ ግን ጦርነት ስለነበር ትግራይን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አካባቢዎችንም ደብድበዋል። ያመፀ ሁሉ ተጨፍጭፏል። ደርግ ትግራይ ላይ የዘመተው ትግራይ ስለማፀ እኮ ነው። ዶክተር አብይ ወለጋ ዘምቶ የለ እንዴ? የትኛውን ህዝብ ይዘው ነው በየትኛው ህዝብ ላይ ዘመቱ የሚባለው?። ህዝብ በህዝብ ላይ አይዘምትም። ግን ያመጸ ካለ ማስታገስ የመንግሥት ሥራ ነው። የትግራይ ህዝብ ሕወሃቶች ላይ አኩርፎ የነበረው ስልጣን ሲይዙ ረሱኝ ብሎ ነው። ነፃ እናወጣሃለን ብለው አታግለው ስልጣን ከያዙ በኋላ የራሳቸውን ንግድ ነው የጀመሩት። የሕወሃት መሪዎች ሃብታሞች ናቸው። በውጭ አገር ሳይቀር ደልቷቸው የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። ልጆቻቸው ፈረንጅ አገር ነው የሚማሩት። የትግራይ ህዝብ ይህንን ያውቃል። ግን ብሄርተኝነት የሚባል አስቸጋሪ ነገር ነው ይዞት ያለው።
በነገራችን ላይ ይህ የብሄርተኝነት ችግር በአለም ላይ ያለ ነው። አውሮጳውያን ሳይቀሩ ብሄርተኝነት እያመሳቸው ነው። ብሔርተኝነት የጊዜው ፋሽን ነው፤ ይህ ፋሽን እስኪሚያልፍ ድረስ ዋጋ ያስከፍለናል። ግን ችግሮቻችን ፖለቲከኞች መሆናቸውን ማወቁ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። ህዝብ ላይ የወረደ አይደለም። ግን እንዳልሽው በዚህ ከቀጠለ ወደ ህዝብ ሊወርድ ይችላል። ግን የእኔ ተስፋ ይህንን ችግር ፖለቲከኞች የፈጠሩት ስለሆነ ፖለቲከኞቹ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እየተዳከሙ ሲሄዱ ማሰብ የሚችሉ ሰዎች ወደ መድረክ ይመጡ ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ። አሁን መድረኩን ተቆጣጥረው ያሉት ማሰብ የማይችሉ ናቸው። ለዚህ ነው ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ማዕከላዊ መንግስቱ መጀመሪያ ጠንካራ መሆን አለበት የምልሽ። እኔ ይሄ ምርጫ ቢያመጣ ደስ የሚለኝ ጠንካራ መንግሥትን ነው። ፍትሃዊና ነፃ ምርጫ የሚባለው ነገር አሁን ላይ ለእኔ ዝም ብሎ ጨዋታ ነው። ለዚህች አገር መቀጠል ተጭበርብሮም ቢሆን ዶክተር አብይ ስልጣን ላይ መቆየት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም አሁን ሌላ አማራጭ ሰው አይታየኝም። ሌላ ሰው ቢመጣ የባሳ የሚከፋፈል ሊሆን ይችላል። በአገሪቱን አንድ ማድረግ የሚያስችል ሰው ኢትዮጵያ የላትም። አንድ ሰው ጥቀሺ ብትባይ በጣም ነው የሚጨንቅሽ። ስለዚህ ሰውየው ባሉበት ሆነው ቢያንስ መረጋገት የሚፈጠርበት አምስት ዓመት ያስፈልገናል ብዬ ነው የማስበው።
አዲስ ዘመን፡-አስቀድመው ዶክተር አብይ የአመራር ብቃት እንደሌላቸው ሲገልፁ ነበር፤ ይህ አሁን ከሚሉት ጋር አይጣረስም?
አቶ ሙሉጌታ፡- ቅድም የአመራር ብቃት ያልነው አንድ አገር በሰላም ጊዜ ሊኖረው የሚገባ የመንግሥት አመራር ማለታችን ነው። አሁን ግን እዬዬም ሲደላ ነው እንደሚባለው ሁሉ ጉልበተኛ መሪ ነው የሚያስፈልገን። አዋቂ መሪ ሳይሆን ስርዓት የሚያስጠብቅ፤ ጉልበት ተጠቅሞ በየቦታው ህግ ማስከበር የሚችል ነው። በእርግጥ እሱም እውቀት ይጠይቃል። ግን ያን ያህል አይደለም። ቅድም ዶክተር አብይ እየመሩ አይደለም ካልኩሽ ምክንያቶች አንዱ ለምሳሌ ህውሃቶችን ማራቃቸው ነው። ለሕወሃት መራቅ የእርሳቸውም ድክመት አለበት። ሕወሃት ብቻ አይደለም የሚጠየቀው። እኔ ምንአልባት መደራደር የሚችሉበት እድል ይኖር ነበር ብዬ አስባለሁ። ገና ችግሩ ከመስፋቱ በፊት ቁጭ ብለው እንዲነጋገሩ በገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ገልጫለሁ። ከግብፅ ጋር እንኳን ቁጭ ብለው እየተነጋገሩ አይደለም እንዴ? ይህንንም ስልሽ ዝም ብሎ ማውራት ብቻ ሳይሆን መፍትሄ የሚያመጣ ወሬ ነው መሆን ያለበት። በዚያ ምክንያት ነው ሁሉም የአመራር ብቃት ይጎድላቸዋል ያልኩሽ። በአጠቃላይ እኔ ግን አሁን እየፈለኩኝ ያለሁት የጎበዝ አለቃ ነው። ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሰጥ ለጥ አድርጎ ሰላም ማስከበር የሚችል መሪ ነው ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሙሉጌታ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ማኅሌት አብዱል