ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ባላት የሺህ ዓመታት ታሪክ በርካታ ፍልሰተኞች በአግባቡ የተቀበለች፣ ያስተናገደች፣ የሸኘች፣ የወደዷትም ሲኖሩ ኢትዮጵያዊ ሲሞቱ ኢትዮጵያ ሆነው የኖሩባት ድንቅና ደግ ሀገር ነች። አሁንም ድረስ ሚሊዮኖች ያስጠለለችው ይህች ሀገር፣ ባህር አቋርጠው ከሶሪያና ከየመን ጨምሮ ከጎረቤትና ከሌሎች ሀገራትም የመጡ ፍልሰተኞች ውሎ ማደሪያም ነች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕገ ወጥ ፍልሰት መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የሕገ ወጥ ደላሎች ቅስቀሳ፣ የቤተሰብና የጓደኛ ግፊት፣ ጥቂት ተሳክቶላቸውና ገንዘብ ይዘው የተመለሱ ሰዎችን እንደ ምሳሌ ማየት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ወጣቶችን ለሕገ ፍልሰትን ከሚገፋፉ ምክንያቶች መካከልም የግንዛቤ ማነስ፣ የሀገር ውስጥ የሥራ አማራጮችን ያለ ማየት፣ሥራን ማማረጥ፣ ኑሮን ማሻሻል የሚቻለው በስደት ብቻ ነው ብሎ ማመን፣ ሥራ አጥነትና ድህነት፣ ጎልተው ይጠቀሳሉ።
ሕገ ወጥ ፍልሰት የአንድ ሀገር ብሎም አህጉር ችግር አይደለም። በሁሉም የዓለማችን ክፍል የሚታይ ነው። ይሁንና በታዳጊ ሀገሮች በተለይ ደግሞ ከሳሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ችግሩ ገዝፎ ይታያል። ኢትዮጵያም በሕገ ወጥ ፍልሰት እጅጉን ከሚፈተኑና ከሚሰቃዩ ሀገራት አንዱ ናት።
ሕገ ወጥ ፍልሰትን ምርጫ ያደረጉ በርካታ ኢትዮጵያውያም ተስፋ ያሳደሩበትን ያህል ሕይወታቸውን ሊለውጥ የሚችል ገንዘብ ሊያገኙ ቀርቶ፤ ላልተጠበቀ አደጋ እየተጋለጡ ወደማይወጡት ማህበራዊ ቀውስ ሲገቡ ማየት እጅጉን የተለመደ አሳዛኝ ትዕይንት ነው። እንደዚህ ዓይነቱ የ“አተርፍ ባይ አጉዳይ” ክፉ እጣ የሚገጥማቸውን ኢትዮጵያውን ቤት ይቁጠራቸው ሲሉ የዓይን ምስክርነት የሚሰጡ ወገኖች ጥቂቶች አይደሉም። ቢያንስ ሰብዓዊ መብታቸው እንኳ ሳይከበርላቸው በመከራ የሚሞቱ ደማቸውም ደመ ከልብ ሆኖ የሚቀሩ ሺህዎች ናቸው።
ይህንን መመስከር የሚችሉት ቀይ ባህር፣ ሜዲትራኒያን፣ የሊቢያ በረሀዎች፤ የሱማሊያ፣ የጅቡቲ፣ የየመንና የሳውዲ አሸዋዎች፤ የታንዛኒያና የማላዊ ጫካዎችና ዋሻዎች ብቻ ናቸው። በሀገራቸው ቢሰሩ የሚለወጡበትን ገንዘብ ለደም መጣጮች አውሬ ደላሎችና በሕገ ወጥ ለደለቡ አሳሞች አስረክበው ሥጋቸውንም ነፍሳቸውንም ሸጠው በሞት ሸለቆ ውስጥ አልፈው ወደ ሲኦል ይጓዛሉ።
በሰላም ደረሱ የሚባሉት እንኳ ትንሽ የሰሯትን የደቡብ አፍሪካ ወሮበላ እና የአረብ ፖሊስ ዘርፏቸው ባዶ እጃቸውን ወጥተው ለአካልም ለአእምሮ ህመም የሚጋለጡት የትየሌሌ ናቸው። የቀሩትም እየታፈሱ እንኳን የሰው ልጅ አውሬ እንኳ በማይኖርበት ጭካኔ እጅግ አሰቃቂ ምድራዊ ሲኦልን እንዲኖሩ ይገደዳሉ።
ሁሉም ከቤቱ ሲወጣ ብዙዎቹን በበርሃ በአሽዋ የተዋጡትን፣ በባህር ሰምጠው የቀሩትን ሳይሆን ካዛ መሀል አሰቃቂውን መንገድ አልፈው የተሻለ ኑሮ ያገኙትን ጥቂቶቹን አይቶ እነሱን ሊሆን ተመኝቶ ነው። በዚህ የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ በሚደረግ ሕገ ወጥ ስደት ለቁጥር የሚዳግቱ ኢትዮጵያዊያን በአሰቃቂ ሁኔታ ባህር አሰምጧቸው፣ አውሬ በልቷቸው፣ ሰው ጎድቷቸው ምኞታቸውን ሳያሳኩ ሞት ወስዷቸዋል።
ይህ የብዙ ኢትዮጵያዊያን የጋራ የሰቆቃ ታሪክ ነው። ዛሬም ይህ ሲቃይ መቆሚያ አላገኘም። ዛሬም ኢትዮጵያዊያን ከአካላዊና ሥነ ልቡናዊ ጉዳት አልፈው የበረሀው አውሬና የባህር አሳ ነባሪ ሲሳይ እየሆኑ ነው። በቅጡ እንኳን ስለሞታቸው ያልተነገረላቸው ዜጎችን ቁጥር ቤት ይቁጠራቸው።
እውነታው ይህ ቢሆንም ችግሩን በቅጡ ተረድቶ ከሕገ ወጥ ፍልሰት ራሱን የሚገታ ኢትዮጵያዊ ቁጥር ትንሽ ነው ለማለት ያስደፍራል። ችግሩ ለበርካታ ዓመታት አብሮን ኖሮ ሺህዎች ወንድም እህቶቻችንን ሕይወት ቢነጥቅም አሁንም የሕገ ወጥ ደላሎችን በመከተል ወደ ሞት የሚሄደው ዜጋ ቁጥር በርካታ ነው።
ለዓመታት በዜጎች ላይ ከታየውና ከደረሰው አደጋ ይልቅ ለማይጨበጥና በአጉል ምኞት ለሚያናውዙ ሕገ ወጥ ደላሎች ቀልቡን የሰጠው ብዙ ሆኗል። ለዜጎች አይደለም ለሰው ልጅ ደንታ የሌላቸው፣ በሰው ላብና ደም፣ ሀብትና ንብረት ማካበት የዓለም መጨረሻቸው ያደረጉ ሕገ ወጥ ደላሎች ሃሳብና አካሄድ የሁሉንም ቀልብ በሚስብ መልኩ ነው።
በተለይ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ደላሎች በሚሰጡት የሀሰት ተስፋና መደለያ የመሳሳት እድላቸው የሰፋ ነው። ይህ በመሆኑም ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችንና ለስደት የተለየ አመለካከት ያለበት አካባቢን ኢላማ አድርገው ይንቀሳቀሳሉ። የዘርፉ ምሁራን እንደሚገልፁት በተለምዶ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚባለው በሰው መነገድና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ችግሮችን ያጠቃልላል።
ይህ በተደራጁ ወንበዴዎች የሚፈፀም ሕገ ወጥ ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቀ መጥቷል። ኢትዮጵያዊያንም የዚህ ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ትስስር ያለው ወንጀል ሰለባ መሆናቸውን ቀጥለዋል። በሂደቱ በርካቶች እድል ከእነሱ ጋር ሆና ነፍሳቸውን ይዘው ተመልሰው ዛሬ ያለፉበት ስቃይ እያመማቸውም ቢሆን እንደ ታሪክ ለማውራት የበቁ አሉ። ሕይወት ይህንን ሁለተኛ እድል ያልሰጠቻቸው በቁጥር ይበዛሉ። በየጊዜው የሚሰማው ለጆሮ የሚከብድ የስደተኞች የሞት ዜናንም እየተላመድነው ያለ ክፉ የታሪክ ገጽ ሆኗል።
በይበልጥ ባለፉት ዓመታት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚፈጥረው ስቃይ በዛ ብሎ እያየን ነው። መዳረሻቸውን አውሮፓና ደቡብ አፍሪካ አድርገው ከሀገራቸው የሚነሱ ኢትዮጵያዊያንም በሊቢያና በሌሎችም ሀገራት ስቃይ ላይ ሆነው ፎቶ እየተላከ ከፍተኛ ማህበረሰባዊ ቀውስ ሲፈጥር እያየን ነው።
በርግጥ መንግሥት ችግሩን እስከ ወዲያኛው ለመቅረፍ የሚያደርገውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በሀገርና በዜጎች ላይ ክፉ ጠባሳ እያስቀመጠ የሚገኘውን ይህን ዓለም አቀፍ ችግር ለመፍታት ጥረቶቹ እንደቀጠሉ ናቸው። ችግሩ እንደ ሀገር እያስከተለ ያለውን ቀውስ መንግሥት በአግባቡ ተገንዝቦ የተለያዩ ተግባራትን ከውኗል። ከክውኖቹ መካከል የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀትና ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተጠቃሽ ናቸው።
በሰው መነገድና ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ሰውን ድንበር ማሻገር ወይም በአጠቃላይ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አሉ። የመጀመሪያው የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ ስምምነት ነው። ይህንን ስምምነት ተከትሎም ሁለት አጋዥ ፕሮቶኮሎች ወጥተዋል። እነዚህን ፕሮቶኮሎች ኢትዮጵያ ተቀብላ የሕግ አካል አድርጋለች።
ይህ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ወደ መሬት ለማውረድ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰው መነገድና ሰውን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አላማ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 እንዲወጣ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል። ይህ አዋጅ በ2012 ዓ.ም የወጣ ነው። አዋጁ ከወጣ ጀምሮ ወንጀሎችን ከመከላከል ጀምሮ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሰርተዋል።
ወንጀሎቹ ተፈፅመው ሲገኙ ከመመርመር፣ ከመክሰስ፣ ከማስቀጣት፣ ተጎጂዎችን ከመጠበቅ አንፃር እና በሀገር አቀፍም፣ በዓለም አቀፍም የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ይህንን አላማ ለማሳካትም የተለያዩ አደረጃጀቶች ተፈጥረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ለአዘዋዋሪዎቹ አትራፊ ከሚባሉ የወንጀል ዓይነቶች አንዱ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ወንጀለኞች አቅምም ፈርጣማ ነው። ይህ ወንጀል በባህሪው ከማህበረሰቡ ጀምሮ የብዙ ባለድርሻ አካላትን ትብብርና አስተዋጽኦ ይጠይቃል። ስለዚህ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ፈርጣማ የሆነ መረጃ፣ትብብርና ቅንጅት ይፈልጋል።
በመንግሥት ደረጃ በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 መሰረት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት አለ። ክልሎችና የተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በአባላትነት የሚሳተፉበት አደረጃጀት አለ። ከዚህ አደረጃጀት በታች በፍትህ ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ የፍልሰት የትብብር ጥምረት አለ። ከትብብር ጥምረቱ በታች ስድስት የሥራ ቡድኖች ተደራጅተዋል።
አንደኛው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ የሚሰራ ሲሆን በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ነው። ሁለተኛው ወንጀሎችን ከመከላከልና ከሕግ ማስከበር አንፃር የተደራጀ ሲሆን ከደህንነት ተቋም ጀምሮ ብሔራዊ ባንክ፣ ኢሚግሬሽን፣ጠቅላይ ዓቃቢ ሕግ እና ሌሎች ሕግ አስከባሪ ተቋማት በአባላትነት የሚሳተፉበት የሥራ ቡድን ነው።
በተለይ ከሥራ እድል ፈጠራና ተጎጂዎችን ከመጠበቅ አንፃር ደግሞ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የሥራ ቡድን ተዋቅሯል። የክፍተት መረጃ አስተዳደር የሥራ ቡድን ደግሞ በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሚመራ ሌላኛው ክፍል ነው። እንዲሁም ከፍልሰት ምርምር አንፃር ትምህርት ሚኒስቴር የሚመራው የሥራ ቡድን አለ። ዲያስፖራውን የሚያስተባብርም የሥራ ቡድን አለ። እነዚህ የሥራ ቡድኖች የተለያዩ አባላትን በሥራቸው አቅፈው በተለያዩ ጊዜ እቅዶችን እያቀዱ ሥራዎችን እየፈፀሙ እና እየገመገሙ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየሰሩ ይገኛሉ። ነገር ግን ችግሩን ለመፍታት ዋናው የማህበረሰቡ ተሳትፎ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
መንግሥትም ሕዝባዊ ግዴታ አለበትና በየዓመቱ ሚሊዮን ገንዘብ እየከሰከሰ ቢመልሳቸውም እነሱም ሚሊዮኖችን እየከፈሉ ወደ ሞት ደጋግመው ይጓዛሉ። በዚህ ረገድ የአውሬዎቹ ደላሎች እና ለአንዳንድ ተባባሪዎቻቸው ባለሥልጣናቱ ጭካኔና ስግብግብነት እጅግ የበዛ ነውና መንግሥት ወደ ውሃ ቅዳ፣ ውሃ መልስ አድካሚና አክሳሪ ሥራ ሳይገባ በፊት በሕገ ወጦቹ ላይ የማያዳግም ርምጃ መውሰድን ማስቀደም አለበት።
ከተቀባይ ሀገራት ጋር በስምምነት የሚፈፀም ሕጋዊ አሰራርንም ማጠናከር እንደዚሁ ይገባዋል። መንግሥት ዛሬ የሚመልሳቸው ፍልሰተኞች ነገ ላለመመለሳቸው ዛሬ ላይ ርግጠኛ መሆን አለበት። ለዚህም የሚሆን ጠንካራ አሰራር እና የቁጥጥር ሥርዓት መፍጠር ይጠበቅበታል። በሕገ ወጦች ላይ የሚወስደው ርምጃም ችግሩን በሚመጥን መልኩ ሊቀመርና ተፈፃሚ ሊሆን ይገባል።
ታሪኩ ዘለቀ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም