ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የ2011 በጀት ዓመት የአምስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለ5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ስብሰባ አቅርቧል፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ለዐቃቤ ህግ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬም ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በሰጡት ምላሽም ከአንድ ሺ በላይ ዜጎች ያሉበት አለመታወቁን ገልጸዋል፡፡ የቀድሞውን የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን በህግ ጥላ ስር ማዋልን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየትም ‹‹አንድ ሰው ለመያዝ ብለን ጦርነት አንከፍትም›› ብለዋል፡፡
ከምክር ቤቱ የሕግ፤ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል በውጭ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች በኢንተርፖል እየመጡ በአገር ውስጥ ያሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ለምን አዳጋች ሆነ? በዚህ መንገድ የህዝብ አመኔታ ማግኘት ይቻላል ወይ? ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ አለማድረግስ የችግሩን ዕድሜ አያራዝመውም ወይ? የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪ ክልሎች በወንጀል ተጠርጥሮ ይፈለጋል የተባለ የለም በሚል ካለም አሳልፈው እንደሚሰጡ ሲናገሩ ይሰማል፡፡ በሌላ በኩል የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎችን የደበቁ ክልሎች እንዳሉ ይገልጻል፡፡ ይህ እንዴት ይታያል? ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተደበቁ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በሌሉበት የሚታይበት አግባብ አለ ወይ? የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት_ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ_ ምክትል ለሕግ ቀርበው ጉዳያቸው ሲታይ፤ ግብረአበራቸው በሚል ስማቸው ይነሳልና ያለመከሰስ መብት አላቸው ወይ? ምንም እንኳ በአገሪቱ በነበረው የአሠራር ሂደት አመራሩ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጣ ቢሆንም ተጠርጣሪዎችን የመያዙ ጉዳይ ግን ብሔር ተኮር እንደሆነ ይነሳልና ከዚህ አንፃር በእኩል ደረጃ ተጠያቂ ከማድረግ ጋር ተያይዞ ምን እየተሠራ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ቀርበዋል፡፡
ጥያቄዎቹ ትክክለኛና ተገቢ ናቸው በማለት ምላሽ መስጠት የጀመሩት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ፤መንግሥት ሕግን መሠረት አድርጎ ተጠያቂ የማድረግ ተግባሩን እያከናወነ ነው፡፡ የተሸሸጉ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተም አንዳንዶቹ ቦታቸውን እንደሚለዋውጡ፣ የተወሰኑት ደግሞ ያሉበት እንደማይታወቅ ገለጸው፤ ከአገር ውጭ ያሉትን ግን በመነጋገር ወደ አገር እንዲመጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
«አቶ ጌታቸው ያለመከሰስ መብት አላቸው ወይ?» በሚል ለተነሳው ጥያቄ ግለሰቡ የፌዴራልም ሆነ የክልል ምክር ቤት አባል አለመሆናቸውንና ያለመከሰስ መብት እንደሌላቸው አረጋግጠዋል፡፡ የተሸሸጉት በክልሉ ውስጥ ቢሆንም እርሳቸውን ለመያዝ በተኩስ መሆን አለበት ብሎ መንግሥት አያምንም ብለዋል፡፡ ክልሎች ወንጀለኛ ተብሎ የተጠየቁት እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ካለም አሳልፈው እንደሚሰጡ ያነሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሚያነሱትም ትክክል አይደለም፡፡ በደብዳቤ ጭምር ተጠይቆ ምላሽ አልተገኘም፡፡ ይህ የሚያሳየው ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› ሆኖ ነው ሲሉ ድርጊቱ ሆነ ተብሎ እየተፈፀመ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ተጠያቂነቱ ብሔር ተኮር ተደርጓል በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፤ በከፍተኛ አመራር ቦታዎች ላይ አብላጫውን ቦታ ይዞ የነበረ ብሔር ተጠያቂ ሲደረግ ሊያዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን፤ ይህን ለማሟያ በሚል ሌሎችን የማካተት ሥራ አይሠራም፡፡ ተጠያቂነቱ ወንጀል ተፈጽሟል፤ አልተፈፀመም? በሚለው እንጂ በፖለቲካ አቋምና በብሔር አለመሆኑንም ነው የገለጹት፤ በመሆኑም በሁሉም ክልሎች ወንጀለኞችን የሚሸሽጉ አካላትን አጋልጦ ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ፣ የፖለቲካ አመራርና የምክር ቤቱም ነው፤ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሰላምና የጸጥታ ምሁሩ አቶ ካህሳይ ገብረየሱስ፤ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ አቶ ብርሃኑ ለምክር ቤቱ የሰጡት ማብራሪያ ስሜት የማይሰጥ ነው በማለት ይተቻሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በአገር አቀፍ ደረጃ በተዋረድ የተፈጸመውን ወንጀል አጥንቶ፤ በአሠራር ፈትሾና አረጋግጦ ሳይሆን የመጣለትን ቅሬታ ነው ያቀረበው፡፡ በየትኛው ደረጃ ምን ህግ ተጥሷል የሚለውን አጥንቶ አላቀረበም፡፡ ጉዳዩ ህጋዊ ከመሆን ይልቅ ፖለቲካዊ ተደርጓል፤ ሲሉም ምላሹን ያጣጥሉታል፡፡
በተለይም ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የፌዴራል መንግሥት ተዳክሞ ነበር፡፡ ክልሎች ዜጎችን እንደፈለጉ ሲጨፈጭፉና ሲገረፉ ነበር፡፡ የተፈጸሙ ወንጀሎችም ብዙ ነበሩ፡፡ በእነዚህ ወንጀሎች ኢህአዴግ እንደ ድርጅት በአጠቃላይ የሚጠይቅባቸው ናቸው፡፡ መጠየቅ ካለባቸው ሁሉም የኢህአዴግ አመራሮች መጠየቅ አለባቸው፡፡ የተፈጸመው ወንጀል በአንድ ሰው ስልጣን የተንጠለጠለ ሳይሆን በሁሉም የተፈጸመ ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ሰው የሚጠየቅበትና የሚብጠለ ጠልበት፤ አንዱ የሚነጻ፤ ሌላው የሚቆሽሽበት ሁኔታ ተገቢነት የለውም፡፡ ህገ መንግሥትዊና ህጋዊም አይደለም፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከላይ እስከታች በገለልተኛ አካል በሁሉም ደረጃ አስጠንቶ በእኩል ደረጃ ዕርምጃ መውሰድ እስካልቻለ፤ ግለሰቦችን እየነጠለ መክሰስ አይቻልም፡፡ የግለሰቦችን ስምም መጥራት የለበትም፡፡ በአገር ደረጃ ያለውን ችግርም አይፈታም ይላሉ፡፡
እንደአቶ ካህሳይ ማብራሪያ፤ ጥፋት ያጠፉ ሰዎች በጥፋታቸው ልክ መጠየቃቸው ባያጠያ የቅም፤ ሲጠየቁ ግን የዶክመንተሪ ፕሮፓጋንዳ እየሠሩ፤ ብሄራዊ ማንነታቸውን እየጠሩና እያብጠለጠሉ መሆኑ በራሱ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ወንጀል እየፈጸመ ነው፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ‹‹ለአንድ ሰው ስንል ጦርነት አንከፍትም›› ማለታቸው ከዚያ ህዝብ ጋር ጦርነት የሚያስከፍት ጉዳይ አላቸው ማለት ነው፡፡ እየሄዱበት ያለው መንገድ ህጋዊና ህገ መንግሥታዊ እንዳልሆነም እንደገባቸው ያሳያል፡፡ ህዝቡም ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ ህጉን ማስከበር ያልቻሉት ህግ ስሌላቸውና ኢ-ህገ መንግሥታዊ ስለሆኑ ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የህግ የበላይነት ይፈርሳል፤ በማለትም ይገልጻሉ፡፡
እንደርሳቸው እምነት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ጌታቸውን ለመያዝ ያልቻሉት እርሳቸውን የሚያስይዝ በቂ ማስረጃ ስለሌላቸው ነው፡፡ ከዚህ በፊት በሙስና የተጠርጥረው ጄነራል ክንፈ ዳኘው ስለመያዙ ህዝብ አልጠየቀም፡፡ መያዙ በብሔሩ ያነጣጠረና አያያዙ ተገቢ አለመሆኑ ግን የትግራይን ክልል ህዝብ ብቻ ሳይሆን ሌላውን ህዝብም አስኮርፏል፡፡
የትግራይ ክልል ህዝብ በፌዴራል መንግሥት ማዕቀብ እንደተጣለበት ያውቃል፡፡ በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ስር ያለው መንገድ ተዘግቶበታል፡፡ የአማራ ክልል በግልጽ የማንነት ጥያቄ ሳይሆን የግዛት ማስመለስ በትግራይ ህዘብ ላይ አው ጆበታል፡፡ በዚያ ህዝብ ላይ የሚወርደውን የችግር ዝናብና በረዶ የፌዴራል መንግሥት መከላከል አልቻለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ህዝቡ የወከለውን ሰው ለመያዝ አይችሉም፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉም ይህን ስለሚያውቁ ነው ለአንድ ስው ብለን ጦርነት አንከፍትም ያሉት፡፡ ይህም ህዝቡን አሁንም የሚያስከፋ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት የህግ የበላይነትን ማስከበር የማይችል መሆኑንም የሚያመለክት ነው፡፡ ይህን ህዝብ በህግ ሊያስተዳድሩትና መብቱን ሊያስከብሩ አልቻሉም፤ በማለት የጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ምላሽና ማብራሪያ ውሃ የማይቋጥር መሆኑን ይናገራሉ፡፡
የወለጋ ዩኒቨርሲቲው የስነ ዜጋና የስነምግባር መምህር አቶ ዳባ ዱቤ፤ ከአቶ ካህሳይ ተቃራኒ ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ የጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ምላሽና ማብራሪያ መንግሥት ህግ አክባሪና ለህዝብ ተጠያቂ መሆን መጀመሩን የሚያሳይ ነው፡፡ ጠፉ የተባሉ ዜጎችን ማሳወቁ፤ ስለአቶ ጌታቸውም ያለውን ሁኔታ ለህዝብ ግልጽ ማድረጉ ከአንድ ህዝባዊ መንግሥት የሚጠበቅ ነው፤ ግዴታውን መወጣት መጀመሩንም ያረጋግጣል ይላሉ፡፡
አቶ ዳባ እንደሚሉት፤ ከአንድ ሺህ በላይ የገቡበት ያልታወቁ ዜጎች የተባለውም በአቶ ጌታቸው ይመራ በነበረው የደህንነት መስሪያ ቤት የተሰወሩ እንደሆኑ ጥርጣሪያቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ የተደበቀ ጉዳይም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ገሃድ መውጣቱ አይቀርም፡፡ እናም የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ሲጥሱ የነበሩ ተጠያቂ መሆናቸው እንደማይቀር ይናገራሉ፡፡ አቶ ጌታቸው አሁን ተሸሽጎው ነው ያሉት፤ እርሳቸው ለጊዜው ወደ ህግ እንዳይቀርቡ የትግራይ ክልል ይፈልጋል፡፡ አሳልፎ ለመስጠትም ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እርሳቸውን ለመያዝ ቢሞከር ወደ ግጭት ሊገባም ይቻላል፡፡ በዚህም ንፀሐን ይጎዳሉ፡፡ ንፁሐን እንዳይጎዱ ማድረግ ደግሞ ከአንድ ህዝብን ከሚወክልና ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት የሚጠበቅ ዕርምጃ እንደሆነም ያነሳሉ፡፡
በአቶ ካህሳይ መንግሥት ስለአቶ ጌታቸው መረጃ ያለው አይመስለኝም በሚል የተሰጠው ሃሳብ ትክክል አይደለም፡፡ በእርሳቸው ላይ ማስረጃ ከሌለ ለምን ይሸሸጋሉ፡፡ የፈጸሙት ወንጀል ከሌለ እርሳቸውስ ለምን ይሸሻሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በርካታ ዜጎች ሲገደሉና ሲኮላሹ ነበር፡፡ በዋናነት ይህን ግፍ ሲፈፅም የነበረው በአቶ ጌታቸው ሲመራ የነበረው የደህንነት መስሪያ ቤት ነው፡፡ በመሆኑም፤ ወንጀል አልፈጸሙም፤ መንግሥት ማስረጃ የለውም ማለት ፍጹም ተቀባይነት የለውም፡፡
ጠቅላይ ዐቃቢ ህጉ ‹‹ለአንድ ሰው ስንል ጦርነት አንከፍትም›› ያሉትም ተገቢነት ያለው ነው የሚሉት መምህሩ፤ ምክንያታቸውም ከጦርነት ማንም አያተርፍም፡፡ ለህዝብ ታዛዥ የሆነ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታም ማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ተጠርጣሪዎች ስርዓት ባለው መንገድና ህዝብን በማስተባበር መያዝ አለበት፡፡ በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት እንደተከፈተ አድርጎ ማሰብና ማራገብ ህዝቡን ወዳልሆነ አቅጣጫ ለመምራትና ተጠርጣሪዎች በህዝቡ ወስጥ ለመሸሸግ ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን፤ የድንበርም ሆነ የማንነት ጥያቄ በሌሎች ክልሎች እንደአለው ሁሉ በአማራና በትግራይ ክልልም አለ፡፡ ይህን በአሠራርና በህግ መፍታት እየተቻለ ‹‹ልትወረር ነው›› እያሉ በማራገብ ተጠርጣሪዎች ወንጀለኛን ለመደበቅ መሞከር ተገቢነት የለውም፤ ይላሉ፡፡
አቶ ጌታቸው የትግራይ ክልል ቢፈቀድም ባይፈቀድም ብዙ ንፁሐን ዜጎቸን አስገድለዋልና አስቃይተዋል ተብሎ ስለተጠረጠሩ በህግ ፊት ቀርበው ነፃ እስካልተባሉ ድረስ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ባይጠይቃቸው፤ የትግራይ ክልል አልሰጥም ቢልም እንኳን፤ በዓለም አቀፍ ወንጀለኝነት መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ በመሆኑም፤ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ሸሽጎ ማስቀምጥ ለጊዜው እንጂ በቀጣይ ከተጠያቂነት አያድናቸውም፤ በማለት አቶ ዳባ ይናገራሉ፡፡
አቶ ደባ፤ የቀደመው ህገወጥ አካሄድ ተጠቃሚዎች ወይም አላዋቂዎች ካልሆኑ በስተቀር፤ መስተካከል የሚገባቸው ነገሮች ቢኖሩም እንኳን አሁን ላይ የህግ አካሄድ ከድሮው በእጅጉ የተሻለ ነው ሲሉ፤ አቶ ካህሳይ ‹‹መንግሥት ህግን አላስከበረም›› በማለት የሰጡትን ሃሳብ ይተቻሉ፡፡ በፊት፤ በፊት ዜጎች ለምን ጥያቄ ጠየቃችሁ ተብለው ይገረፉና ይረሸኑ፤ ይታሰሩና ይሰደዱ ነበር፡፡ ይህ አካሄድ ኢ-ዴሞከራሲያዊ ነው፡፡ አገሪቱንም ለችግር የዳረገ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ መንግሥት ከዚህ ችግር ለመውጣት በተግባር እየሠራ ነው፡፡ ምንም እንኳ በርካታ ሥራ ቢቀረውም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ታዲያ፤ ጉድለቶቹን ከማረም ይልቅ ይህን አካሄድ መኮነን ያላዋቂነትና ከድሮ አካሄድ አለመውጣት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ጥቅማቸው የተነካባቸው ወገኖች የመጮህ አባዜ ነው፤ ይላሉ፡፡
የህግ አማካሪው አቶ ተሾመ ወልደ ሐዋርያት በበኩላቸው፤ የፌዴራል ስርዓቱ ግራ እየገባው ነው ይላሉ፡፡ ለክልልና ለፌዴራል መንግሥት የተሰጠ ስልጣን በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ እየሆነ አይደለም፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሰብዓዊ መብትን እንዲያስከበር በህጉ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በየትኛውም ቦታ ሄዶ በወንጀል የተጠረጠረን ሰው የመያዝ ስልጣን አለው፡፡ ነገር ግን፤ አሁን በፌዴራል መንግሥቱ በኩል በህጉ መሰረት ያለመፈጸም ጉድለት እንደ ሚታይ ይናገራሉ፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደረሱ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ይርጋ የላቸውም፡፡ በይቅርታ የሚታለፍም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን እንደመቀበሏ መጠን በዓለም አቀፍ ህግ ጭምር ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ በየትኛውም ቦታ ቢሆኑም ከመያዝ አያመ ልጡም፡፡ ህግን ለማስከበር ህግ መጣስ ባይገባም፤ የፌዴራልም ሆኑ የክልል መንግሥታት ወንጀለ ኞችን በህጉ መሰረት ተጠያቂ ማድረግ ካልቻሉ ራሳቸው ተጠያቂ መሆናቸው እንደማይቀርም ይናገራሉ፡፡
በወንጀል ተጠርጣሪዎች የሚያዙበት ስርዓት አለ፡፡ ይህን የሚተላለፉ ከሆነ በህጉ መሰረት እንዴት መያዝ እንዳለባቸውም ተቀምጧል፡፡ በዚያ ስርዓት ለመያዝ ሲሞከር ጥቂት የሚያፈነግጡ አካላት ይኖራሉ፡፡ እነርሱን ስርዓት ለማስያዝ በሚደረገው ጥረት መጓተት ግን መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማስከበር አቅቶታል ማለት እንደማይቻል ያመላክታሉ፡፡ ሆኖም፤ አሁን ላይ እየታዩ ያሉ የህግ የበላይነትን የሚገዳደሩ ምልክቶች መታረም እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡
የዳኝነት ስርዓቱን ለማስተካከልና ዳኞች በነፃነት እንዲሠሩ መንግሥት ከላይ ጠንካራ ሰዎችን አስቀምጧል የሚሉት አቶ ተሾመ፤ በተዋረድም ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ፍላጎቱና ጥረቱ አለ፡፡ በሂደት ፍርድ ቤቶች እየተስተካከሉ ነው፡፡ ከዚህ ቀደሙ በተሻለ ዳኞች ያለማንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት ለመሥራት እየሞከሩ ነው፡፡ የፖሊስ ምርመራዎችም በአግባቡ ይታያሉ ሲሉ የፍርድ ቤቶች አሠራር እየተሻሻለ መሆኑንም ይመሰክራሉ፡፡
አቶ ዳባ ዱቤ፤ በአገሪቱ የህግ የበላይነትን ለማስፈን የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ክልል በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን እንዲያቀርብ ማድረግ አለበት፤ በትግራይ ብቻ ሳይሆን በየትኛው ክልል ያሉ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ለህግ መቅረብ አለባቸው፡፡ መንግሥት ይህን የማያድርግ ቢሆን እንኳን በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደረሱ ግለሰቦችና ቡድኖች በዓለም አቀፍ ህግ መጠየቃቸው እንደማይቀር ሁሉም ዜጋ ማወቅ ይገባዋል ይላሉ፡፡
አቶ ካህሳይ በበኩላቸው፤ መፍትሔው የፌዴራል መንግሥት የህግ የበላይነትን ሲያስከብር ነው፡፡ አሁን መንግሥት ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን እያስከበረ ስላልሆነ ይህን ማረጋገጥ አለበት፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ ማንነትንና የጆኦግራፊ አቀማመጥን መሰረት አድርጎ ነው የተዘረጋው፤ ይህም በህገ መንግሥቱ መሰረት መከናወን አለበት፡፡ የፌዴራል ስርዓቱ ያስቀመጠውን አወቃቀር አንቀበልም ሲባል አንድም ቃል የማይተነፍስ ከሆነና የግዛት ጥያቄን በጉልበት ማስመለስ ሲነሳ ዝም የሚል ከሆነ ችግሩ ይሰፋል፡፡ ‹‹አንድ አገር፤ አንድ ህዝብ እና አንደ ኢትዮጵያ›› በማለት በስብሰባና በሚዲያ የሚደነፉ እየደነፉ ህገ መንግሥቱን በአደባባይ እየናዱ፤ ህዝብን እንደህዝብ እያዋረዱ የህግ የበላይነት አይኖርም፡፡ በመሆኑም የፌዴራሉ መንግሥት ህገ መንግሥቱን ማክበርና ማስከበር አለበት፡፡ ይህ ከሆነ የህዝቡ ወንጀለኞችን አሳላፎ የመስጠቱ ጉዳይ ቀላል መሆኑን ይናገራሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011
አጎናፍር ገዛኽኝ