ሰው ሲፈጠር በጎነትን ይዞ ነው። በሂደት ግን ከአካባቢው ክፋትን እየተላመደ ይሄዳል። ሆኖም የሚለምደው ክፋት በጎነቱን ይሸፍነው ይሆናል እንጂ ፈጽሞ አያጠፋውም። እናም አንድ አጋጣሚ ተፈጥሯዊ የሆነውን በጎነት ከተዳፈነበት ገለጥ ገለጥ አድርጎ ሊያወጣው ይችላል። ለዚህ አብነት የሚሆኑ በርካታ የሰዋዊ ምግባር ባለቤቶችን መጥቀስ ቢቻልም፤ ለዛሬው ግን ‹‹በጎነት ተፈጥሯዊ ነው›› በሚል መርህ ነድያንን እየረዱና እየደገፉ ያሉትን ‹‹ፍቅር ለነድያን ማህበር›› አባላት የሆኑን ወጣቶች ልናነሳ ወደድን።
ለአንድ ነገር እውን መሆን የግል ስሜትና ፍላጎት እንዳለ ሆኖ አንዳች ቆስቋሽ ምክንያት ማስፈለጉ አይቀሬ ነው። እናም የፍቅር ለነድያን የበጎ አድራጎት ማህበር የተመሰረተው በምክንያት ነው። ይሄንንም የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ወጣት ኪሮስ በላይ፣ ሲያስረዳ፤ ‹‹የታመሙ ሁለት ወንድማማቾች ከቤታችን ስንወጣ በዚሁ በራችን ላይ ተቀምጠው እናያቸዋለን። ሁሌም የእነርሱን ጉዳት እያየን ወደቤታችን እንገባ ነበር። ይህ ሁነት ደግሞ ሰውን ስለመርዳት እንድናስብ አደረገንና ሰው መርዳትን ከእነርሱ ብንጀምር በሚል በራሳችን ልብስ እነርሱን ከመደገፍ በጎ ስራችንን አንድ አልን። ሰውም ይሄን ሲያይ ማገዝ ጀመረ፤ እኛም ደስ ብሎን በዛው ቀጠልንበት፤›› ሲል ገልጸዋል።
በዚህ መልኩ የተመሰረተው ይህ ማህበር ታዲያ በወጣት አባላቱና በተባባሪው ማህበረሰብ አማካኝነት በሁለት ዓመት የበጎነት ጉዞው በርካቶችን ከቆሻሻ ለብሳቸውን አጥቦ አልብሷል፤ ደጋፊ የሌላቸውን ጠይቋል፤ ደካሞችን በበዓላት ቀን ጎብኝቷል፤ የአቅመ ደካሞችን ቤት አድሷል። ከዚህም በላይ ዘወትር እሁድ በጎጃም በረንዳ መንገድ ዳር በሚያከናውኑት የነድያንን ገላ የማጠብ፣ ጸጉር የማስተካከልና የመስራት ብሎም የአልባሳት ልገሳ ተግባራቸው ለበርካታ ነድያን አለኝታም፤ እፎይታም መሆን ችለዋል። ለዚህ ደግሞ ወይዘሮ ፋጡማ አልዪና መሰሎቿ እማኝ ናቸው።
ወይዘሮ ፋጡማ፣ የአዳማ ነዋሪ የነበሩ ቢሆንም፤ እዛ ቤትም ሆነ ስራ ስላልነበራቸው የቤት ኪራይ እንኳን መክፈል ሲያቅታቸው ሶስት ልጆቻቸውን ይዘው የተሻለ ነገር ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ያቀናሉ። ይሁን እንጂ አዲስ አበባም እንዳሰቡት ሳይሆን ቀረ ስራ ሲያገኙ ሰርተው ካጡም ለምነው ያገኙትን ገንዘብ ልጅ ይዞ ከጎዳና ማደር ከባድ ነውና በመጠኑም ቢሆን መብላትና ገላን መሸፈን ከተቻለ በሚል አዳራቸውን በየቀኑ ዝቅተኛ ገንዘብ ተከፍሎባቸው ከሚታደርባቸው የጎጃም በረንዳ ሰፈሮች አድርገዋል። ሆኖም ከዕለት ጉርስና ለዕለት መጠለያ ክፍያ የዘለለ ገቢ ያለማግኘታቸው ሳያንስ፤ የልጆቻቸውን ልብስ መቀየር ቀርቶ ገላቸውን ማጠብና መንከባከብ አልቻሉም።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉም በአካባቢው በተደራጁ ወጣቶች የሚሰጠውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን በመቻላቸው ልጆቻቸውንም ሆነ ለራሳቸው በየሳምንቱ ሰውነታቸውን መታጠብ፤ ጸጉራቸውንም ሹሩባ መሰራትና ቅባትም መቀባት ችለዋል። ይሄም ደስታ የፈጠረባቸው ሲሆን፤ ሁሉም ሰው እንዲህ የወደቁትም መመልከትና እርስ በእርሱም መደጋገፍን ልምዱ ቢያደርግ የሰው ልጆች ተቸግረው መንገድ ላይ ወድቀው አይቀሩም። እናም ሰው በበጎነቱ ለሰው ደራሽነቱን በማሳየት ሰው ሆነው ነገር ግን በተለያየ ምክንያት አቅም በማጣታቸው በጎዳና ላይ የወደቁ ነዳያንን በሳምንት አንዴ እንኳን አለኝታነቱን በማሳየት ተስፋ በመሆን ፍቅርን ሊዛራ ይገባል የሚለው የወይዘሮ ፋጡማ መልዕክት ነው።
የወይዘሮ ፋጡማን ጸጉር ስትሰራ ያገኘናት በጎ ፈቃደኛ ወይዘሮ ሐና ዮሐንስ፣ የልጆች እናት መሆኗ ደጋፊ የሌላቸው ወገኖቿን በሳምንት አንድ ጊዜ ሄዳ ለመጎብኘት እንቅፋት አልሆነባትም። ወጣቶቹ ከሚሰጡት አገልግሎትና ተገልጋዮችም ከሚሰማቸው የደስታ ስሜት ተነስታ ሌላ አቅም ባይኖረኝ እንኳን በጉልበቴ ላገልግል በሚል ሀሳብ ወደዚህ በጎ ፈቃድ ተግባር መቀላቀሏን የምትገልጸው ወይዘሮ ሐና፤ ይሄን በመስራቷና ደካሞችን በማገልገሏ ትልቅ እርካታ እንደተሰማት ትናገራለች። ከአካባቢው ነዋሪዎች ልብስ ከማሰባሰብም ሆነ በራሷ ከመለገስ ባለፈ ከገላ አጠባ እስከ ጸጉር ስራ በበጎ ፈቃደኝነት እንደምትሰራ ትገልጻለች።
ወይዘሮ ሐና እንደምትለው፤ በቦታው ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች በሚያገኙት አገልግሎትና በሚሰጣቸው አልባሳት ደስተኛ ናቸው። ለምሳሌ፣ ጸጉር የሚሰሩ ሴቶች ከመታጠብና ጸጉር ከመሰራት ባለፈ የደረቀ ራሳቸውም ቅባት ይቀቧቸዋል። ለልጆቻቸው ልብስ ይሰጧቸዋል፤ ከህዝብ በሚሰበሰበው ገንዘብም ሳሙናና ቅባት ገዝተው ለጸጉራቸውና ለልብሳቸው ብሎም ለሰውነታቸው ማጠቢያ ያውሉታል፤ በዓል ሲሆንም በግ ወይም በሬ አርደው ጭምር ምሳ ይመግቧቸዋል። በዚህ መልኩ ልጆች፣ ወጣቶች፣ የልጅ እናቶች፣ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፤ እነዚህንም አጥበው፣ ጸጉራቸውን ሰርተው፣ ቀብተውና አልብሰው ይሸኛሉ። እነርሱም ተደስተውና መርቀው ይሄዳሉ።
ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ህዝብ በመንገድ ዳር ያውም ህዝብ በሚበዛበት ቦታ ባልተመቻቸ መልኩ ነው አገልግሎቱ የሚሰጠው። በመሆኑም የሚመለከተው አካል ቢያንስ ተገልጋዮች ሳይሸማቀቁ አገልግሎቱን የሚያገኙበት እድል እንዲያገኙ የሚያስችል ቦታ ቢያዘጋጅላቸው የሚል ምክረ ሀሳብ አላት። ከዚህ ባለፈ ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ መልኩ እንደየአቅሙና አካባቢው ሁኔታ የበጎ አገልግሎት ቢሰጥ ወድቆ የሚቀር ወገን ሳይኖር ሁሉም እጅ ለእጅ ተያይዞ የሚኖርበትን እድል መፍጠር ይገባል ፤ የወይዘሮ ሐና መልዕክት ነው።
የወንዶችን ጸጉር ሲያስተካክል ያገኘነው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ብርሃኑ ዱጋሳ፣ ዘወትር እሁድ በዚሁ ስፍራ ይሄንኑ የበጎ ተግባር ሲከውን ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። ተግባሩም ‹‹ያለውን የሰጠ…›› እንዲሉ ባለው አቅም በሙያው ማገልገልን መርጦ ማህበሩን እያገዘ ያለ ወጣት ነው። የተቸገሩ ወገኖችን በዚህ መልኩ ገላ አጥቦ፣ ልብስ አልብሶና ጸጉራቸውን ጭምር አስተካክሎ መሸኘትን መቻሉ ደስታን የሚፈጥርለት መሆኑን የሚናገረው ወጣት ብርሃኑ፤ በተለይ ተፈናቃዮች፣ ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የአዕምሮ ህመምተኞችና አቅመ ደካሞችን መሰረት አድርገው የሚደግፉ እንደመሆኑ ይሄን ስራ ሰርቶ ውሎ በገባ ቀን ጥሩ እንቅልፍ የሚተኛ መሆኑንም ይናገራል። ይህ ተግባር ግን በተወሰኑ ወገኖች ብቻ ከዳር የሚደርስ ባለመሆኑ መላው ኢትዮጵያውያን በዚህ መልኩ ደጋፊ ያጡ ወገኖቻቸውን ቀርበው ሊደግፉና በፍቅር ዝቅ ብለው ሰዎችን ከፍ ለማድረግ በአንድነት ሊሰሩ ይገባል ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።
‹‹ስራው ደስ የሚል እንደመሆኑ በተቻለን አቅም ተባብረን የምንሰራው ነው፣›› የሚለው ሌላው በጎ ፈቃደኛ ወጣት ሽመልስ ሽፈራው፤ ብዙ ሰዎች ድጋፉን ፈልገው እንደሚመጡ ና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹም በየቦታው እየሄዱ ፈልገው በማምጣት አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ይናገራል። እነዚህን ነድያንም ያለምንም መለያየትና ማዳላት አጥበውና አልብሰው ካገኙም አብልተው እንደሚሸኙ በመጠቆምም፤ እነዚህ ሰዎች ግን አንድም በአእምሮ ህመም፤ ካልሆነም በኑሮ ጉስቁልና የተለያየ ባህሪ ያላቸው እንደመሆኑ ፈልጎ ይዞ ከማምጣት ጀምሮ በማጠብም ሆነ ጸጉር በማስተካከል ሂደት ታግሶ ማለፍን የሚጠይቁ በርካታ አስቸጋሪ ነገሮች እንደሚያጋጥሟቸው ይገልጻል። ወጣቶቹም ይሄን ችለው ለሰው ደራሽነታቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን በማውሳትም፤ ሁሉም ይሄን ማህበር ቢያግዝ እና በየቦታውም መሰል ተግባር መፈጽም ቢቻል በርካታ ነድያንን ማንሳትና አለኝታም፤ ተስፋም መሆን እንደሚቻል ይገልጻል።
ወጣት አቡበከር አክመል፣ ለወጣቶቹ ተግባር አጋዥ በሆነው የገቢ ማሰባሰቢያ ቅርጫት ውስጥ የአቅማቸውን ገንዘብ እያስቀመጡ ከሚያልፉ ወገኖች መካከል አንዱ ነው። የዚሁ ሰፈር ልጅ እንደመሆኑ በአካባቢው ሲያልፍ ዘወትር ወጣቶቹ አቅም የሌላቸውን ወገኖች ሲያጥቡ፣ ልብስ ሲያልብሱ፣ ጸጉር ሲያስተካክሉና ሌላም ድጋፍ ሲያደርጉ በሚያየው ነገር ደስተኛ ነው። ለሁለት ዓመታት ያክል ይሄን ስራ መከወን በራሱ ሊደገፍም ሊበረታታም የሚገባው ተግባር ሲሆን፤ ስራቸውን የበለጠ እንዲያሰፉት ደግሞ የተሻለ የስራ ቦታ ቢያመቻችላቸው ለእነርሱም ሞራል፤ ለሌላውም ተነሳሽነትን የሚፈጥር ይሆናል። ከዚህ ባለፈ ግን ሁሉም እጁን ፈታ አድርጎ አንድም እነርሱን መደገፍ፤ ሌላም በየቦታው መሰል ተግባር መከወን የሚችልበት እድል ቢፈጠር መልካም ስለመሆኑም ነው የሚናገረው።
ወጣቶቹ ስራውን አንድ ብለው ሲጀምሩ በእርሳቸው ደጃፍ ላይ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ለማ፤ ሲጀምሩ እንኳን ፈቃዳቸውን እንዳልጠየቁና እርሳቸውም ስራው በጎ ተግባር መሆኑን ሲገንዘቡ ከመከልከል ይልቅ ደስ ብሏቸው እንዲሰሩ ዝም እንዳሏቸው ይገልጻሉ። ስለ ወጣቶቹ ተግባር ሲያስረዱም ‹‹በዚህ እድሜና ጊዜ ሰውን ሳይጸየፉ ፈልጎ ማምጣትና ማጠብ፣ ሰውን ከሰው ሳይለያዩ ሁሉንም እኩል መርዳት ይከብዳል፤ ሆኖም ልጆቹ ጥሩ በመሆናቸው ይሄን ማድረግ ችለዋል። እኔም ይሄን ተገንዝቤ ነው ዝም ያልኳቸው፤›› ይላሉ። በሂደት ግን የአካባቢውም ሰው እየተገነዘባቸው፤ ቀበሌውም ወደመንገድ ወጣ ብለው እንዲሰሩ ስለፈቀደላቸው ስራቸውን በአግባቡ መስራት እንደቻሉ ነግረውናል። ሆኖም አሁንም የሚሰሩበት ቦታ አመቺ ባለመሆኑ ከቀበሌ ጀምሮ የመንግስት አካል ተመልክቶ ቦታ ሊያመቻችላቸው፤ ህብረተሰቡም በሞራልም በገንዘብም ድጋፍ ሊያደርግና ሊያበረታታቸው እንደሚያስፈልግም ይገልጻሉ።
አንድ ሰው በጎ ሲያደርግ ጥቅሙ ለተደረገለት ሰው ብቻ ሳይሆን በጎ ላደረገው ሰው ጭምር መሆኑን የሚናገረው ወጣት ኪሮስ በበኩሉ፤ በፊት እሁድን የማሳልፈው መጠጥ በመጠጣት ነው፡: ይህ ደግሞ ከንቱ ነገር ነው፤ አይጠቅመኝም ነበር፤ ምክንያቱም ትርፉ ፍቅርን ሳይሆን ከሰው ጋራ ግጭትና ጸብን ማትረፍ ነበር ሲል ይገልጻል። አሁን ግን እሑድን ነድያንን መደገፍና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ በመቻሉ ጸብን ሳይሆን እርካታን ያተረፈበት እንደሆነም ይናገራል።
እናም ሁለት የታመሙ ወንድማማቾችን መነሻ አድርጎ የተመሰረተውና ዛሬ ላይ ሰፊ አገልግሎትን እየሰጠ ባለው ማህበር አማካኝነት ገላ አጥበው፣ ጥፍር ቆርጠው፣ ጸጉር አስተካክለውና ሌሎችም አገልግሎቶችን ሰጥተው ሲጨርሱ በማገልገላቸው በቃላት የማይገለጽ ደስታ እንደሚሰማቸው ያስረዳል። የሚገለገሉ ሰዎችም ደስታቸው በጉልህ የሚነበብ መሆኑ ደግሞ የበለጠ እንዲስሩ ያደረገቸው መሆኑን በመግለጽ፤ አንድ ስራ ሲጀመር ግን ሂደቱ አልጋ በአልጋ ሳይሆን ብዙ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ይናገራል። ለዚህ እንደማሳያም ስራውን ሲጀምሩ የሰዎችን ገላም ሲያጥቡ እንኳን ጓንት( ግላብ) የማይጠቀሙበትን ከባድ ወቅት በማስታወስ፤ ሰዎች ስራውን በጥሩ መልኩ የማይገነዘቡበት ሁኔታ እንደነበርም ይገልጻል።
ነገር ግን የሆነ ነገር ሲጀመር ማቋረጥን ሳይሆነ እስከመጨረሻው መጓዝን ዓላማ በማድረግ እንደመሆኑ፤ በእኛም ጥንካሬ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ያልተቋረጠ እገዛም ዛሬ ላይ መድረስ ተችሏል። ሁሌም እሑድ እሑድ በቋሚነት ከሚሰጠው በጎ አገልግሎት ባለፈም የራሳችን ገቢ ባይኖረንም ህብረተሰቡን በማስተባበር ቤት ለቤት እንክብካቤ እንሰጣለን፤ ደካሞችን እናሳክማለን፤ በዓል ሲኖርም አቅም የሌላቸውን ምግብ እናበላለን። የደካሞችን ቤት የማደስ ስራ እናከናወናለን። አሁን ላይ የማህበረሰቡ ትብብርም የሚያስደስት ነው። ሆኖም አሁን ከአገልግሎት መስጫ ቦታና ቢሮ ጋር በተያያዘ ችግር ያለብን በመሆኑ የመንግስት አካል ቢመለከተን መልካም ነው። ይህ ከሆነ ከወጣቶቹ ብርታት ጋር ተዳምሮ ነገ የተሻለ በጎነትን ማሳየትና አገልግሎትን መስጠት እንደሚችሉ ያለውን እምነት ይገልጻል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 29/2012
ወንድወሰን ሽመልስ