በድርሰት ዓለም የመጨረሻው ስራ የፅህፈት ተግባር ነው። የዚህ ቁልፍ ተግባር መሳሪያ ደግሞ ቋንቋ ነው። ቋንቋ በበኩሉ የራሱ ወሳኝ ወሳኝ ብልቶች አሉትና እነሱን በሚገባ መለየት፣ ማወቅ፣ አውቆም ስራ ላይ ማዋል የደራሲው ተግባር ነው። ድርሰት ከእውቀት ባለፈ የደራሲውን ክህሎትና ቃላት የመምረጥ አቅም ሁሉ ይጠይቃል ።
ሰውና ቋንቋ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች እንደሆኑ ሁሉ ድርሰትና ፅህፈት፤ ፅህፈትና ቋንቋም የዚሁ አይነት ነው ተዛምዷቸው። በተለይ “ድርሰት የተሰራው ከቋንቋ ነው።” ከሚለው አኳያ ስንመለከተው ጉዳዩ ወለል ብሎ ይታየናል። ድርሰት ከተወጠነበት፤ ከተጠነሰሰበትና ከመነጨበት ምናብ ወጥቶ በተገቢው መንገድ አንባቢ ጋር መድረስ አለበት። ይህ ደግሞ ያለ ፅህፈት ተግባርና የቋንቋ መሳሪያነት ዳር አይደርስም።
የፅህፈት ተግባርን ከትምህርት፣ ልምምድ፣ የታወቁ ደራሲያንን ተሞክሮዎች በመቅሰም ወዘተ ማግኘት የሚቻል ሲሆን፤ ተግባሩ በተለይ የፀሀፊውን ልዩ ትኩረት፣ ተሰጥኦና ቃላት እውቀት የሚጠይቅ ነው።
በቋንቋ ውስጥ በርካታ ቃላት አሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም እኩል ውሃ ያነሳሉ ማለት አይደለም። ክብደታቸው ይለያያል፤ ጥቅማቸው ከፍና ዝቅ ያለ ነው። በተለይ በድርሰት ስራ ውስጥ እንደድርሰቱ አጠቃላይ ምንነት የሚወሰን ሲሆን ደራሲው ጉዳዬ ብሎ፣ አስቦና ተጨንቆ ከአንባቢ ጋር የሚገናኝባቸውን ቃላት መርጦ ስራ ላይ ያውላል። ከተሳካ እሰየው፤ ካልሆነ መከነ ማለት ነው።
ኧረ የሰው ያለህ ኧረ የሰው የሰው፣
አይኔን ሰው እራበው አይኔን ሰው ሰው።
ይህ ግጥም ከተመሰረተባቸው ቃላት ሀምሳ በመቶው
አንድ ቃል ነው። ይሁን እንጂ ፈጠራው በተሟላ እውቀት ላይ የተመሰረተ መሆኑ አንድም ቦታ ሲያነቅፍ አይታይም። ስለዚህ የቃላት ድግግሞሽ በራሱ አሰልቺ አይደለም ማለት ነው። ችግሩ እንዴትና ለምን ተደገመ? የሚለው መልስ ማግኘቱ ላይና የገጣሚው የፈጠራ ብቃት ነው።
በድርሰት ዓለም ቋንቋ ወሳኝ እንደመሆኑ ሁሉ፤ ከቋንቋ አካላት መካከል ደግሞ ሰዋሰው፤ ከሰዋሰውም የንግግር ክፍሎቹ የበለጠ የወሳኝነት ሚናን ሲጫወቱ ይታያሉ። እነዚህ ቃላት በተለይ በተካነ ደራሲ እጅ ከገቡ የፈጠራ ስራው ላይ ነፍስ ዘሩበት ማለት ነው። በምሳሌ እንየው:-
“ትልቅ መኪና፣ ትልቅ ቤት፣ ትልቅ ግቢ፣ … ባጠቃላይ ትልልቅ ነገሮችን ይወዳል። […] አህያዋ እጉድባ ትገባና ጠጥታ ትመለሳለች፤ ጠጠር እያነሳ ወደ ኩሬው መወርወር ይጀምራል። — እያረፈ – – – እያረፈ — ዝም ብሎ ይወረውራል፤ — ጠብታ ትንሽ ክብ — ትልቅ ክ— ትልልቅ ክብ — ትልልልቅ ክብ — ትልልልልቅ ክብ — ትልልልልልቅ ክቦች እየሰሩ ይጠፋሉ። […] የሮቢ ፀሀይ ያለወትሮው ያንገበግባል፤ እራስን ፈጥርቆ እየገባ፣ በየዘመኑ ሲንተገተግ፣ ርግብግብግብግብግብ ሲል ሲያዩት አየሩ ላይ ረግቶ ሲያበቃ እየተቆረሰ […]። እየተውረገረገ። ዙሪያ መሬቱም እንዲሁ በርሞጣ፣ በሱፋጭና በባልጩት ይርገበገባል። እግርን በመሞልቀቅ እየሰነጠረ ገብቶ ርግብግቢት ድረስ ሲያጠኸይ ነው የሚሰማው በረገጡት ቁጥር።”
ደራሲው ለርዕሰ ጉዳዩ ማጉያ ይሆነው ዘንድ ይህንን ስልት ከመፅሀፉ መግቢያው ጀምሮ፤ ይሁነኝ ብሎ ሲጠቀም እናገኘዋለን። (ይህንን አንቀፅ በዋናነት ለማስተንተኛነት በመውሰድ በመፅሀፉ ላይ በኤንሽታየን “Theory of Relativity” የተደረገውን ጥናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማየት ይቻላል)። ወደ ሌላው ደራሲ እንሂድ።
“ድንገት ወጣትነት እንደ ከዋክብት ጠዋት ጀምበር የሚሞቅ ፈገግታ እያሳየው እንደ ከዋክብት በሚያብለጨልጩ አይኖቹ እየጠቀሰውና እንደ ፀዳል የሚያበራ ከብሩህ ተስፋ ሌላ ምንም የማይነበብበት፣ ትኩስ ደም የሚተራመስበት፣ ሳቂታ ውብ ፊት እያሳየው፣ ግለት ባለው ጠንካራ እጁ ጨብጦት በመሰናበት ትከሻውን አሳብጦ፣ ደረቱን ነፍቶ፣ ወገቡን እየሰበቀ፣ እንጥር እንጥር እንጥር እያለ፣ እንደቦና ጥጃ እየቧረቀ፣ ሜዳው እስኪጠበው ድረስ እየፈነደቀ እየራቀ፣ እየጨለለ፣ እንደ ጥላ እየኮበለለ ሲለየውና እርጅና መላጣውን፣ ጥጥ የመሰለ ሽበቱን፣ ባዶ ድዱን፣ ብርሀናቸው ደብዝዞ፣ ጭልጭል የሚሉ፣ […] ኩምትር፣ ጭምድድ […]።”
ደራሲው በዚህ አላቆመም። በሌላ ገፁ “ወፎች ዘመሩ። ተራሮች ማህሌት ቆመው ቅዳሴው ሰመረ። የቤተ መቅደስ ጧፍ ተንቀለቀለ። ጉሞች ወደ ከርቤ፣ ወደ ባህረ እጣን ተለውጠው ተነኑ። የባህር ሞገድ ተነስቶ ወደቀ። ስትንሳፈፍ የቆየች ህይወት መልህቅዋን ጣለች። ዝም– ዝምታ።”
ደራሲው በዚህ አይነት የአፃፃፍ ቴክኒኩ የታወቀ ሲሆን የተመራማሪዎችን አድናቆትም አትርፎበታል። አንድ እንጨምርና የበለጠ እንየው።
“የኪሩቤል ዋሽንት – የመላእክት ዜማ፣ የሊቃነ መላእክት ውዝዋዜና ሽብሸባ – የወፎች ዝማሬ – የገነት አየር – የማሪያም መግደላዊት ሽቶ – የኔፈትርቲቲ አንገት – የኪሊዮፓትራ አፍንጫ – የትሮይቱም ሄለን አይን – ዳዊትና መርሳቤህ – ሰለሞንና ሳባ – ከሰማይ ከዋክብት ሲረግፉ – ባህር ሲናወጥ – ሞገድ ሲነሳና ሲወድቅ – የራሄል ጩኸት – አደይ አበባ ሲፈካ – ሲፈነዳ – ምድሪቱን ሲሞላ – ሁለቱም ዝም–ዝምታ።” (ይህንን ደራሲ አለመውደድም ሆነ አለማድነቅ አይቻልም ያለው ማን ነበር?)
ስምን በመጠቀም በኩል “ንጉስ ሆይ! እግዚአብሔር ያሳይዎት፣ ክርስቶስ ያመልክትዎት፣ መላኩ ይንገርዎት፣ ይህ ጥጋበኛ ሰው …”፤ አርእስትን ከመጠቀም አኳያ በ”ጥሬ ጨው” ውስጥ “መፈጨት፣ መደለዝ፣ መወቀጥ፣ መቀየጥ ገና እሚቀራቸው” የሚለው፤ ከቦዝ አንፃር “ለፍቶ ጥሮ ግሮ … የሚኖር ሰው የመንፈስ እርካታን ያገኛል።”፤ ከሳቢ ዘር አኳያ “አረማመድ፣ አቋቋም፣ አለባበስ፣ አቀማመጥ … ማን እንደ ንግስት።”፤ ከሀረጋት አንፃር “አንቺ ያልወለድሽ መካን ሆይ፥ ዘምሪ፤ አንቺ ያላማጥሽ ሆይ፥ ጩኺም፤ ባል ካላት ይልቅ ፈት የሆነችቱ ልጆች በዝተዋልና፥ ይላል እግዚአብሔር።” እና የመሳሰሉትን በመጠቀም የተዋጣለት፤ ቀልብ ሳቢና ተነባቢ ስራዎችን መስራት ይቻላል ማለት ነው።
ከላይ በተመለከትናቸው ቅንጫቢዎች አማካኝነት ለድርሰት ህያውነት ቋንቋ ያለውን ሚና ተመልክተናል። በንባብ ሂደታችንም ንፅፅር አለው? ምን አይነት ዘይቤዎች ስራ ላይ ውለዋል? ዘዬስ አለው? ድርሰትን ለመመዘን ከሚያገለግሉት “ደራሲው ምን አለ? እንዴትስ አለው?” ለሚሉት መልስ መስጠት ይቻላል? ወደ ሩቅ ዘመን የሚወስዱን ቃላት (archaism) አሉ? ካሉስ ለምን ፋይዳ? ቅንብር፣ አቻዊነት፣ ስብጥርነት ወዘተ ይታይባቸዋል?
እነዚህን ለመረዳት ጉዳዩ ቀላል ሲሆን ወሳኝ ካልናቸው የሰዋሰው፤ በተለይም ከስም፣ ግስ/ገላጭ ቃላት፣ ሀረጋት (አቢይ/ንኡስ)፣ አርዕስት አንፃር በመፈተሽ የተፈለገው ጋር መድረስ ይቻላል። በሂደቱም እንደ አይን እየጠፋ ያለውን የፅህፈት ክሂሎት መታደግ ይቻላል።
(በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የመፅሀፍ ቅዱስ ጥቅሶችን፣ ዮፍታሄ ንጉሰ፣ የዳኛቸው ወርቁ፣ የበአሉ ግርማ፣ ደበበ ሰይፉን እና ሌሎች ስራዎች መጠቀማችንን እንገልፃለን።)
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 29/2012 ዓ.ም
ግርማ መንግሥቴ