የሚተቃቀፉ የውሃ ጥቅሎች ከአይን ከራቀው፤ ሰማይና ምድር ከገጠሙበት ማዶ እየተንከባለሉ ከባህር ዳርቻው ከነ ግርማ ሞገሳቸው ይደርሳሉ፤ ደግሞም ባሉበት ይረጋጋሉ። እርስዎ ከባህር ዳርቻው ከአሽዋማው ቦታ ፊትዎትን ወደ ባህሩ መልሰው ተቀምጠዋል። ድንገት አንድ ሰው ከጀርባዎት መጥቶ በሁለት እጆቹ አይኖችዎን ሸፍኖ “እኔ ማን ነኝ?” አለዎት። ለመሆኑ እሱ ማን ነው? ፤ እርስዎስ ማን ነዎት? ይህ ጥያቄን የበለጠ ለመረዳት ቀጥሎ ያለውን አፈ ታሪክ ልብ ብለን እንመልከት።
አንድ ሰው በአስራ ስምንት ዓመቱ ወደ እስር ቤት ገብቶ ከሃያ ዓመት በኋላ ተፈታ። ሆኖም በሃያ ዓመት ጉዞ ውስጥ ብዙ ለውጦች ተፈጥረዋልና ከአዲስ ኑሮን የመጀመር ያህል ከባድ ሆነበት። ስለ ራሱም መጠየቅ ጀመረ፤ ከራሱም፤ ከሌሎችም መልስ አላገኘም። መነሻም መድረሻም ስላጣ ዳግም ቀድሞ ታስሮበት ከነበረበት ማረሚያ ቤት ሄዶ እስከ እለተ ሞቱ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ ተማፀናቸው፤ እኔ ለዚህ ማረሚያ ቤት ማንነቴን ሽጫለሁ አሁን “እኔ” እኔ አይደለሁም፣ እኔነቴ እዚህ ቀርቷል አላቸው።
ከላይ ያለው ባለ ታሪክ ራሱን የገለጸበትን መንገድ በሚገባ ማጤን ይገባል። አንድ ግለሰብ በድርጊቶቹ እና በአስተሳሰቡ ራሱን እና ሌሎችን ይገልጻል። እያንዳንዱ ተግባራችን መገለጫችንም ሲሆን ይስተዋላል። እገሌ እኮ ሳቂታ ነው ሆዱ ቂም የለውም፤ እገሌ እኮ ኮስታራ ነው ኩራቱ መከራ ነው፤ እያልን ከላይ በሚታዩ ድርጊቶቻችን እንገልጻለን። ግለሰቦችንም መልካም፤ ክፉ፤ አስተዋይ፤ ቂመኛ፤ ተንኮለኛ፤…ወዘተ በማለት እንፈርጃለን። ለመሆኑ እኔ ማን ነኝ ብለው አስበው ያውቃሉ?
ከብዙ እይታዎች በአንዱ፤ ግለሰብን የሶስት እውነታዎች ውጤት አድርገን ብንነሳ ግለሰብ ማለት ለራሱ ያለው አመለካከት ሲደመር ሰዎች ስለ እርሱ ያላቸው አመለካከት ሲደመር የግለሰቡ እውነተኛ ማንነት ውጤት ነው ብለን መውሰድ እንችላለን። ይህ ማለት ግለሰቡ ስለ ራሱ፤ እኔ ደግ ነኝ፣ እኔ ሩህሩህ ነኝ፣ እኔ ቁጡ ነኝ ማለቱ፤ እናም ሌሎች ስለ ግለሰቡ፤ እሱ እኮ ጎበዝ ነው፣ ተግባቢና ተሳዳቢ ነው ማለታቸው እና በመጨረሻም እውነተኛው (በትክክል ግለሰቡን የሚገልጸው) የግለሰቡ ማንነት በአንድ ላይ በመሆን የግለሰቡ መገለጫ ሲሆኑ ይታያል።
ሆኖም ግን እውነተኛው ወይም ነባራዊው ማንነታችንን በመረዳት መንገድ ውስጥ ስለራሳችን የምንሰጠው ትርጉምና አመለካከት ወደ አልተፈለገ ቅራኔ እና የተወሳሰበ ችግር ሊያመራን ይችላል። እውነተኛው እኔነታችን ለራሳችን ከሰጠነው ወይም ብንሆን ብለን ከምንመኘው ጋር ሳይስማማ ሲቀር ቅራኔ ይፈጥራል። ይህንን ሀሳብ ለመረዳት በዋናነት ሁለት ነጥቦችን ማስተዋል ያስፈልጋል።
የመጀመሪያው መሰረታዊ ስህተት (False Core) ሲሆን ሌላው ደግሞ ግላዊ ስህተት (False Self ) ነው። መሰረታዊ ስህተቶች ካለፈ ተሞክሮ፣ ከትውስታ፣ ትኩረት ከተሰጠው ነገር፣ ከስሜት፣ ከሚያስተሳስር ድርጊት፣ ሁኔታዎች ከሚተረጎሙበት አንጻር የሚገለጽ “ስለራስ የተሳሳተ አመለካከት” መያዝ ነው። እነዚህን ስህተቶች ተመርኩዞ የሚመጣው የተሳሳተ ድምዳሜ እና የተሳሳተ የመፍትሄ ሀሳብን ግላዊ ስህተት በማለት እንገልጸዋለን። ይህ ማለት አንድም ህመም ሳይኖርብን አመመን ማለት፤ በእዚህ ሳናበቃ ታመናልና እገሌ የተባለን መድሀኒት ካልወሰድን ነው ነገሩ።
እንደ ዩኒቨርሲቲ ተማሪነት ከሚነሱ ተዛማጅ ችግሮች ውስጥ እጅግ ጥቂቶቹን እንይ።
1. መስራት አልችልም
– መሰረታዊው ስህተት አመንጪ:- መወሰን፣ መተግበር አልችልም ማለት
– ግላዊ ስህተት ማስተካከያ:- መስራት፣ መወሰን እንደምችል ከመጠን(ከተገቢው) በላይ በመስራት እና ውጤታማ በመሆን ማሳየት አለብኝ ማለት።
እንዲህ አይነቱ የተሳሳተ አመለካከት በተለይም ከትምህርት ጋር በተያያዘ በስፋት አንዳንዴም ከበድ ባለ ደረጃ ይታያል። ተማሪው በትምህርቱ ላይ ለሚፈጠሩ የተለያዩ ክፍተቶች ራሱን ተጠያቂ በማድረግ እና ካጠናው በላይ ማጥናት ይጠበቅበት እንደነበር በማመን አብዝቶ ይቸክላል።
እንዲሁም አጠቃላይ ድምር ውጤቱ(ጂፒኤው) አስጊ ሁኔታ ላይ ሲወድቅ ከመጠን ያለፈ ጥናት፣ ጭንቀት፣ መረባበሽ በመጨረሻም ለአእምሯዊና አካላዊ ጉዳት ይዳረጋል። በተለያዩ ጊዜያት ራሳቸውን ያጠፉና ሙከራም ያደረጉ ተማሪዎች መኖራቸው ለዚህ ማረጋገጫ ነው። ለዚህም ነው ስናጠናም ሆነ ስንዝናና በመጠኑ መሆን እንዳለበት ሳይኮሎጂስቶች የሚመክሩት።
2. ብቻዬን ነኝ
– መሰረታዊያን ስህተት አመንጪ:- ሰው የለኝም ብሎ ማሰብ
– ግላዊ ስህተት ማስተካከያ:- ብቻዬን መሆን ስለሌለብኝ ከብዙ ስው ጋር(ከመጠን ያለፈ) ግንኙነት (ጓደኝነት መመስረት) ማድረግ አለብኝ ማለት።
በተለይም ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ብቸኝነት መሰረታዊው ችግር ሆኖ ሳለ ይህን በከፍተኛ ደረጃ በማጋነን በጥቂት ሳምንታት እና ወራት ውስጥ በርከት ያሉ ጓደኞችን በማፍራት ረጃጅም ሰዓቶችን በግቢው ውስጥ እና ውጪ በመዟዟር ያባክናሉ። ከማን ጋር መሆን እንደለባቸው መወሰን እስኪያቅታቸው ይቸገራሉም።
ብዙ ጓደኛ ማፍራት ሰዓት ከማጥፋቱም በተጨማሪ አንዳንዴም ወደ አልተፈለገ ከአንድ በላይ የግብረ-ስጋ ግንኙነት ጓደኛ መያዝም ያመራል። የአገራችን ሰው ሲተርት “ዘጠኝ ዳቦ ከመላስ አንዱን መግመጥ” ይላል። ብዙ ከመያዝ አንድ የልብ ወይም የፍቅር ጓደኛ ማፍራት ጤናማ ነው እላችኋለሁ።
3. ፍቅር የለኝም
እንዲህ አይነት ተማሪዎች በአብዛኛው እንደ መፈክር አፍቃሪ እና ተፈቃሪ መሆን አለብኝ ብለው ስለሚነሱ ያዩትን፣ የተዋወቁትን፣ አብሮአቸው የሚማረውን፣ በአጠቃላይ የተገኘውን በማፍቀር ላይ ይጠመዳሉ። ማፍቀሩ ግን ጤናማ ስለማይሆን አፈቀርኩህ ያሉት ላይ ጉዳት ሊያደርሱም ይችላሉ። የሚያፈቅራቸው ከሌለም ራሳቸውን ወደ መጥላት ይሄዳሉ። መቼም አቅዳችሁና አልማችሁ አፍቅሩ ቢባል ለአንዳንድ ሰው ከባድ ሊሆን ይችላል!
ነገር ግን የማያፈቅረንን እንዲያፈቅረን ማስገደድ የለብንም። ምክንያቱም አፍቃሪውም፣ ተፈቃሪውም ላይ የስሜት፣ የአካል፣ የአእምሮ፣ እና የሞራል ጉዳት ይደርሳልና። እራሳችንን እስካላወቅን ድረስ የሌለን ማንነት ለራሳችን ልንሰጥ እንችላለን። ከዚህም አስከትሎ ከፍ ወዳለ የአእምሮ ህመም እንደርሳለን።
ኳንተም ሳይኮሎጂ እንዲህ አይነቱን ርዕሰ ጉዳይ እያነሳ የሚፈትሽ ስለሆነ የጎደለውን በበለጠ ንባብ እንድታዳብሩት እጋብዛለሁ። ለንባባችሁ ይረዳችሁ ዘንድ “The Beginner’s Guide to Quantum Psychology” የተሰኘውን መጽሐፍ ጀባ አልኳችሁ። ወደ መዝጊያችን ስንደርስ እንዲህ እንላለን፡- እኔ ማን ነኝ ብለን እንጠይቅ ስለሌሎች አብዝተን ከመጠየቃችን ቀድመን ደጋግመን እኔ ማን ነኝ እንበል ጤና ይስጥልኝ! ቸር ያገናኘን።
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 29/2012 ዓ.ም
ኖኅ ውብሸት