ቡና ተፈጥሮ ለሰው ልጅ ያበረከተችው ፀጋ/ሀብት ሲሆን፤ ይህንን እፁብ ድንቅ በረከት ከታደሉት ጥቂት አገራት ደግሞ ኢትዮጵያ አንዷ፤ ምናልባትም ቀዳሚዋ ነች።
ቡና ባህላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ ወዘተ ፋይዳዎችንና እርካታዎችን የሚያስገኝ የግብርና ምርት ሲሆን ከሁሉም ጎልቶ የሚነገርለት ግን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ነው። በመሆኑም “አረንጓዴ ወርቅ”፣ “የኢኮኖሚ ዋልታ” እና መሰል ማእረጎችን ሊያገኝ ችሏል። “ሻይ ቡና”፣ “ቡና እንጠጣ”፤ “ቡና ጠጡ” . . . አይነቶቹም በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በቀላሉ የሚታለፉ ሳይሆኑ ከፍተኛ ባህላዊ እሴት ያላቸው መሰረታዊ ፅንሰ ሀሳቦች ናቸው።
ከእነዚህ ቀዳሚ ፋይዳዎቹ መካከል ምንም ያልተነገረለት ቢኖር ሥነልቦናዊ ፋይዳው ሲሆን አሁንም ድረስ በዘርፉ በረባ ደረጃ “ይኸው” ያለ አጥኝም ሆነ ጥናት አልተገኘም።
ወደ ባህር ማዶዎቹ ስንሄድ ግን ቢያንስ አንድ ሰው (ብዙ እንደሚሆኑ ቢታወቅም) እናገኛለን። ከሶስት ዓመት አይበልጥም። አንዲት የውጪ ተመራማሪ ሰው የኛን ቡና ከጥሬው እስከ መጨረሻው፤ እስከ ተጠጣበት (ከአቦል እስከ ቶና) ድረስ ያለውን ሂደት አጥንተው “የኢትዮጵያ የቡና፣ የአፈላል ስርአቱና መጠጣቱ አምስቱን የስሜት ህዋሳት – መቅመስ፣ ማሽተት፣ መንካት፣ መስማት እና ማየት – በትክክል ያሟላል። እርካታውም በዚሁ ደረጃና ከፍታ ነው መገለፅ ያለበት።” በማለት የደመደሙት ለተገቢ ጥቅስነት የሚበቃ ነውና አጥኚዋ ሊመሰገኑ ይገባል።
ይህን እንደ እግረ መንገድ አነሳን እንጂ የዚህ አስተያየት ቁም ነገር የምድሩ የቡና ማህበራዊ ፋይዳ አይደለም፤ የዚህ ፅሁፍ ቀጥተኛ አላማ የሰሞኑን የቡናችንን ወደ ጠፈር ማቅናት አስመልክተው የተነገሩ ዜናዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ሲሰጡ የነበሩ ማብራሪያዎች ናቸው። ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት የተገኘውን መረጃ እንመልከት።
በቴክኖሎጂውና ህዋ ሳይንሱ ዘርፍ እያሳያችው ባለው ተሳትፎና እያስመዘገበች ባለችው ውጤት ሳቢያ የዓለም አቀፉ የአስትርኖሚካል ህብረት አባል በመሆን የተለያዩ ሳይንሳዊ ክንውኖችን ከህብረቱ ጋር በመሆን ስታከናውን ቆይታለች። ይህንኑ ተከትሎም የዓለም አቀፉ አስትሮኖ ሚካል ህብረት (IAU) የተመሰረተበትን የመቶኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ ባደረገው የህዋ አካላትን የመሰየም ንቅናቄ የ”IAU 100 NameExoWorlds” ኢትዮጵያም በዚሁ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንድትሆን በተደረገው
መሰረት በአንድሮሜዳ ህብረ ኮከብ ውስጥ የምትገኘውን በሳይንሳዊ አጠራሯ HD-16175 የተባለች አንድ ኮከብና ይህችን ኮከብ የምትዞራት HD-16175-b የተባለች ዓለምን ያካተተውን ስርአት እንድትሰይም እድሉን አግኝታለች።
በመሆኑም ዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ህብረት ባወጣው የስም መረጣ ደንብና መመሪያ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟሉ ስሞችን የመምረጥ ተግባር በብሄራዊ ኮሚቴው አማካኝነት በማከናወን 10 የመጨረሻ ጥንድ ስሞችን በመምረጥ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ይፋ አደረገ። የስም መረጣውም በድረ-ገፅና በ920 ነፃ መልእክት መቀበያ መስመር ህዝቡን በማሳተፍ ምርጫው እንዲካሄድ ተደረገ። በዚሁ መሰረት የብሄራዊ የስም አሰያየም ኮሚቴ ባደረገው የድምፅ ስብሰባ መሰረት የህዝቡን ምርጫና የኮሚቴውን የውሳኔ ሀሳብ በማገናዘብ ሶስት ጥንድ ስሞችን መርጦ የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚካል ህብረት የህዋ አሰያየም ኮሚቴ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጡባቸው ሶስት ጥንድ ስሞችን ላከ።
በዚሁ መሰረትም ለህዋ አካላቱ ስያሜ ለመስጠት የመጨረሻ ደረጃ የደረሱትን ሶስት ጥንድ ስሞች የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት የስም አሰያየም አቢይ ኮሚቴ ባደረገው ግምገማ መሰረት ለኢትዮጵያ እንድትሰይም የተሰጣትን ኮከብና ፕላኔት የመጨረሻ ስያሜ ውጤት ለብሄራዊ ኮሚቴው አሳወቀ። ሶስት ስያሜዎች ቢላኩም ቡና (Bunna) የኮከቡ ስያሜ፤ አቦል (Abol) የፕላኔቱ ስያሜ (Exo-planet Name) እንዲሆን ተመረጠ።
ይህ የሚያመለክተን አንዳች ፍሬ ጉዳይ ቢኖር ቡናችን ከምድራዊ በረከትነቱ አልፎ ወደ ሰማያ ሰማያት-ጠፈር ድረስ መዝለቁን ነው። ይህ ለኛ ለአሁኖቹ ብዙም ብርቅ ወይም አስገራሚ ላይሆንብን ይችላል፤ ከመጪው በበለጠ ከሱ ቀጥሎ የሚመጡ ትውልዶችን ግን ምን ያህል የኩራት ምንጭ፤ የማንነት መገለጫ እና የሀብት ምንጭ እንደሚሆን ከወዲሁ ለመገመት ምንም መሆን አያስፈልግም።
እንደሚታወቀው የአንድ አገርና ህዝቦቿ የማንነት መገለጫዎች በርካታ ናቸው። አንዳንዶቻችን አጥበን እንደምናየውና እንደምንረዳው አይደለም ማንነት። ዛፍ ቅጠሉ፤ አራዊት እንስሳው፤ ወንዝ ፏፏቴው፤ ጋራ ሸንተረሩ፤ ወርቃማው የአየር ፀባይ፤ . . . ሁሉ የማንነት መገለጫዎችና ኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ውስጥ ያሉ ናቸው። ባይሆንማ ኖሮ ዋሊያ፣ ቀይ ቀበሮ፣ አክሱንም ሀውልት፣ የአባይ ስልጣኔ፣ . . . መለያችን ባልሆኑና በኢትዮጵያዊነታቸው ባልነገሱ ነበር።
ሌላም መጨመር ይቻላል። የኢትዮጵያን የመልክአ ምድር አቀማመጥ ሲያዩ አስቸጋሪና የማይጠቅም ይመስላል። እውነታው ግን እሱ አይደለም። እውነታው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ላይ እንድትገኝና በዓለም በጂኦ- ፖለቲካዊ አቀማመጧ የዓለም ስትራተጂክ እንድትሆን ማድረጉ ነው። አልተጠቀምንበትም እንጂ ይህም የት ባደረሰን ነበር። ማለት የተፈለገው ወደፊት እነዚህ ሁሉ ልክ እንደ ቡናችን የሚጠብቃቸው ወርቃማ እድል አለ ለማለት ነው።
ከላይ እንደተመለከትነው ከእንግዲህ ቡና ምርታችን ብቻ አይደለም። በጠፈር አደባባይ ላይ ተለይተን የምንታወቅበት መታወቂያችን እና ማንነታችን ጭምር እንጂ። ቡና ከላይ በመግቢያችን ከጠቀስንለት ፋይዳዎቹ አልፎ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ከነማህበረ-ባህላዊ ስርአቱ (“አቦል”ን) ይዞ ሰማየ ሰማያት መጥቋል። ሌሎች የማንነት መገለጫዎቻችንና የተፈጥረና ሰው ሰራሽ ሀብቶቻችን፤ ቁሳዊና መንፈሳውዊ ቅርሶቻችንም ይህንኑ የቡናን ፈለግ እንደሚከተሉ መጠራጠር አይቻልም፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሁሉም ይሆናል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነችውንና መረጃን ከምድር ወደ ህዋ ከህዋም ወደ ምድር የምትልከውን 70 ኪሎ ግራም ክብደት ያላትን ETRSS-1 “የመሬት ምልከታ ሳተላይት” (Earth Observation Satellite) ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ከንጋቱ 12፡21 ላይ ከምድረ ቻይና (ከቤጂንግ 400 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው ታዩዋን ከተማ ባለው የማምጠቂያ ጣቢያ) ማምጠቋ የሚታወሰ ሲሆን፤ በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ኢትዮጵያ 10 ሳተላይት እንደሚኖራት፤ በሶስት ዓመት ውስጥ ደግሞ ከተያዙት ፕሮጀክቶች በዋንኛነት የኮሙዩኒኬሽንና ብሮድካስት ሳተላይ ፕሮጀክት፣ የከፍተኛ መሬት ምልከታ ሳተላይት ፕሮጀክት፤ እንዲሁም የሳተላይት መገጣጠሚያ ፋብረካና ፍተሻ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደሚጠናቀቁ መገለፁ ይታወሳል። ይህ ፅሁፍም ይህንኑ ከማበረታታት አኳይ ሊታይ የሚችል ይሆናል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 29/2012 ዓ.ም
ግርማ መንግሥቴ