አዲስ አበባ፡- የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ዕጣ ለማውጣት መረጃውን/ዳታ/ የማስገባት ሥራ በገለልተኛ አካል እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽሕፈት ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ ሂደት መሪ አቶ ጋሻው ተፈራ፣ ቀደም ሲል ዕጣ የማውጣቱ ሥራ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ(ኢንሳ)ይሠራ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን የግንባታው ባለቤት የሆነው የአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ሥራውን ተረክቦ እየሠራ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል ሱቆችን ጨምሮ 22 ሺ 863 ቤቶችን ለማስተላለፍ ቃል የተገባ ቢሆንም እስካሁን ግን አልተቻለም፡፡ ለዚህም የመሰረተ ልማት ያለመሟላት ችግር እንዳለ ሆኖ ዕጣውን የማውጣት ሥልጣን ያለው አካል ሥራውን ከማይመለከተው ከኢንሳ ተረክቦ እንዲሠራ በሚደረገው የሽግግር ሂደት መዘግየት ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በሌላም በኩል፤ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የቤቶች ግንባታ የሚያስፈልጉ ከአምስት መቶ በላይ ግብአቶች በመንግሥት በኩል የሚፈጸሙ በመሆናቸው፤ የኮንትራክተሮች የአቅም ውስንነት፤ የአማካሪዎች ክትትል ማነስና ሥራቸውን በቦታው ላይ ተገኝተው በሙሉ አቅማቸው ያለመሥራት ቤቶቹን በተባለው ጊዜ ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ያልተቻለባቸው ችግሮች መሆናቸውን አቶ ጋሻው አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም፤ አሁን ያለው አሠራር የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ቤቶቹን ገንብቶ እያንዳንዱ ቤት ምን ያህል ወጪ እንደወጣበት ከሚገልጽ ሰነድ ጋር በማያያዝ ለቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ያስረክባል፡፡ ኤጀንሲውም ከቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ያገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ የቤቱን ዋጋ በመተመን ለተጠቃሚዎች ያስተላልፋል፡፡ እነዚህና መሰል ችግሮች ቢያደናቅፉትም የቤቶቹ አፈጻጸም በአሁን ሰዓት ከ80 በመቶ በላይ መሆኑንና ከግንባታ አንጻርም የተሻለ በሚባል ደረጃ ቤቶቹ እየተገነቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ሲታሰብ ቤት መገንባት ብቻ ሳይሆን ከተማ የመገንባት ሥራ ነው ያሉት አቶ ጋሻው፤ አሁን እየተሠሩ ያሉት አብዛኞቹ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከከተማው ወጣ ያሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ጽህፈት ቤቱ ለተለያዩ ማህበራዊ ተቋማት ግንባታ የሚውሉ ቦታዎችን በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ አካባቢ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡
መንግሥት በተለያዩ አማራጮች የህብረተሰቡን የቤት ፍላጎት አይቶ አማራጭ እያስቀመጠ በመሆኑ ማህበረሰቡ ተስፋ ሳይቆርጥ ቁጠባውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት፤ የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህል ካልዳበረ የቤት ልማትን ማሳካት አይቻልም ያሉት አቶ ጋሻው፣ በአሁን ወቅት የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም አጠቃላይ ከ94 ሺህ ቤቶች በላይ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011
በፍሬህይወት አወቀ