በመላው ዓለም የምንኖር ድሆች ከበለጸጉት አገራት በአብዛኛው ከምዕራባውያን እርዳታ እንቀበላለን። ለአብነት ታዋቂው የአሜሪካ ባለ ሃብት ቢል ጌትስና ባለቤታቸው ሚሌንዳ ጌትስ አፍሪካ ውስጥ የብዙዎችን ሕይዎት እያሻሻለ የሚገኝ ትልቅ የእርዳታ ፕሮጀክት አላቸው። ታዲያ ከአሜሪካ ድረስ እዚህ ያስመጣቸው ምን ይመስላችኋል? የትውልድ ቦታቸው ስለሆነ ወይም አፍሪካዊ፣ ኬንያዊ፣ ጋናዊ፣ ኢትዮጵያዊ… ስለሆኑ እንዳትሉኝ። የተወለዱት አሜሪካ ዜግነታቸውም አሜሪካዊ ነው። “ጥቁሮች” ስለሆኑ አፍሪካ ደግሞ የጥቁሮች አህጉር ስለሆነች እንዳይባልም እነርሱ “ነጮች” ናቸው። መቼም እንደ እኛ መስሏችሁ ለ “ብሔራቸው” ሲሉ ነው አፍሪካውያንን የሚረዱት ብላችሁ እንዳታስቁኝ።
አፍሪካ የሚባል ብሔር የለም፤ አሜሪካውያን ደግሞ እንደምታውቁት ከፍ ሲል ሃገር ዝቅ ሲል ደግሞ “ስቴት” ወይም “ክፍለ ሃገር” ነው ያላቸው። ማንን ብለው እዚህ ይመጣሉ? አሁን ማንን ብለው እንደመጡ ትገምታላችሁ ብዬ አስባለሁ። የተቸገረን “ጥቁር”፣ የተቸገረን “ብሔር”፣ የተቸገረን “ሃገር” ሊረዱ አይደለም ወደ አፍሪካ የሚመጡት፣ ሰዎች የሚመጡት እነዚህን ሰው ሰራሽ እውነታዎች ለመርዳት ሳይሆን ሰዎችን ለመርዳት ነው። ሁሉንም የሚያስተሳስረው ብቸኛው ተፈጥሯዊ እውነታ ሰውነት ወይም በመጀመሪያው ቋንቋ- በግዕዝ ሰብዓዊነት ነውና!
ሰውነት ወይስ ብሔርነት?
እኛስ? እኛማ እንኳንስ ድንበር ተሻግረን ሰውን ልንረዳ(ሰውን መርዳት እንደነ ቢል ጌትስ በገንዘብ ብቻ አለመሆኑን ልብ ይሏል) አንድ አገር ላይ ተቀምጠንም እንደ ሰው በጋራ መቆም አቅቶናል። ይማራሉ፤ ሰው ይሆናሉ ብለን ወደ መካነ አዕምሮ የላክናቸው ልጆቻችን በጉልበተኛ ወንጀለኞች ታግተው ጫካ ውስጥ ሲቀሩ፣ ሰው የመሆን ነጻነታቸው ተገፍፎ በፍጡር እጅ ታፍነው በባርነት ውለው ሲያድሩ እንደ ሰው በጋራ መጮህ አቅቶናል። ለታገቱት የሰው ልጆች ይፈቱ ብለው ሰልፍ የወጡት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። የታገቱት ልጆች የወጡበት “ብሔር” ወይም ልጆቹ የሚኖሩበት “ክልል” ነው ሰልፍ የወጣው። የታገቱት ግን በፍጥረታቸው ሰዎች፣ በጾታቸው አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው።
ስለሆነም ሰው የሆነ ሁሉ(ሴትና ወንድ አድርጎ ፈጠራቸው) ስለሚል መጽሃፉ ሰልፍ መውጣት ያለበት የተማሪዎቹን ሰውነት የሚጋራ ሰው ሆኑ የተፈጠረ ሁሉ መሆን ነበረበት። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች “ካሉ” ልጆቼ ታገቱብኝ ብሎ ሰልፍ የሚወጣው ግን ልጆቹ በሥጋ የተገኙበት አካባቢ ብቻ ሰው ከሆነ በሌላው አካባቢ የሚገኘው ሰው ግን ዝም የሚል ከሆነ ሰውነት የት አለ? ብሔር ሰው አይደለም ወይ? ሰማንያ ብሔር አለ ማለት ሰማንያ ዓይነት ሰውነት አለ ማለት ነው ወይስ ሰው ሰራሽ እውነታው(ብሔር) ከመጠን በላይ ገዝፎ ተፈጥሯዊ ዕውነታውን(ሰውነትን) እንዳናይ ጥላውን አጥልቶብናል ማለት ነው? እውነታው ይኼው ነው፡፡
ሰው አልባ ፖለቲካ
ታዋቂው የግሪክ ፈላስፋ አርስቶትል “ሰው ፖለቲካዊ እንስሳ ነው” ይላል። ፖለቲካ የሚለው ቃል ራሱ “politiko” ከሚል የላቲን ቃል የመጣ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም “የህዝብ አስተዳደር” መሆኑን የቃሉን አመጣጥ አስመልክቶ በእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላቶች ላይ የተሰጡ ማብራሪያዎች ያመላክታሉ። ልብ በሉ እንግዲህ፣ ፖለቲካ ህዝብ አስተዳደር ነው፤ ህዝብ ደግሞ “ሰው” የሚለው ቃል ብዜት ነው። ማለትም ብዙ ዛፎች አንድ ላይ “ደን” የሚል መጠሪያ እንዳላቸው ሁሉ “ህዝብ” የሚለው ቃልም ብዙ ሰዎች አንድ ላይ የሚጠሩበት የወል ስም ነው። ስለዚህ ፖለቲካ የህዝብ አስተዳደር እንደመሆኑ መጠን ዋነኛ መሰረቱም ሰው ነው።
ሰውን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ደግሞ መነሻውና መድረሻው ሰውነት ስለሆነ ሰው ሁሉ በሰውነቱ ይተሳሰርበታል እንጅ አይለያይበትም። ከዚህ በተቃራኒው ፖለቲካ ከትክክለኛ ተፈጥሮው ሲወጣ፣ መሰረቱን ሰው ላይ ማድረግ ሲገባው የራስን ፍላጎት ለማስፈጸም ታስቦ የተመሰረተን አንዳች “ቡድን” ማገልገል ሲጀምር ከእውነታው ይወጣል። ቋሚውን እውነታ (Natural Reality) ትቶ “ሰው ሰራሽ እውነታ”ን(Constructed Reality) ማገልገል ይጀምራል። በእኛም ሃገር የገጠመን መሰረታዊ ችግር ይኸው ነው፤ ፖለቲካው መሰረቱን ሰው ላይ ሳይሆን ብሔር ላይ አድርጓል። የህዝብ አስተዳደር የሆነው ፖለቲካ የብሔር(የቡድን) አስተዳደር ሆኗል፣ በሰዎች የሚመራው ፖለቲካ የሚያስተዳድረው ሰዎችን ሳይሆን ብሔሮችን ነው።
በአጠቃላይ ፖለቲካው ሰውን አግልሏል፣ ሰው አልባ ሆኗል! ለዚህም ነው እንደ ብሔር እንጅ እንደ ሰው መቆም ያልቻልነው፤ በሰውነት ሳይሆን በሰፈር የምንሰባሰበው። እንደ ሰው መቆም ካልተቻለ ደግሞ ችግር ነው። እንደ ሰው መቆም ባልቻለ ማህበረሰብ ውስጥ ደግሞ እንደ ሰው እኩል ለመሆን ያስቸግራል፣ ሰዎችን በእኩልነትና በፍትሃዊነት ለማስተዳደር የማይቻል ይሆናል። በውጤቱም ሰብዓዊነት ይመነምናል፣ ቡድንተኝነት ይገነግናል።
ሞትን ያልተቃወመ ከሞት አያመልጥም
እናም ከ1960ዎቹ ጀምሮ ቀስ በቀስ ሥሩን ሲሰድ ቆይቶ ባለፉት ሃያ ዘጠኝ ዓመታት ደግሞ መንግስታዊ ድጋፍ አግኝቶ በከፍተኛ ደረጃ እንዲንሰራፋ የተደረገው ሰው አልባ ፖለቲካ አሁን ላይ ፍሬው በስፋት እየታጨደ በመሆኑ አገሪቱ በክፉ ችግር ውስጥ የምትገኘው። ይህም ከሰብዓዊነት እንድንወርድና በጋራ ቆመን አንድ ላይ ከመዳን ይልቅ ከሰውነት ባነሰ መደብ ተቧድነን ተከፋፍለን እንድንጠፋ እያደረገን ይገኛል። ለዚህ ነው በሰው አልባው ፖለቲካችን ተከፋፍለን በመቆማችን በሰውነት እና በሰብዓዊነት ላይ ዘግናኝ ወንጀል የፈጸሙ አጥፊዎችን ለህግ ማቅረብና ፍትሕን ማስፈን ያልቻልነው። ለዚህ ነው ደፋ ቀና ብለው በላባቸውን ኑሯቸውን አሸንፈው ከመኖር በቀር ምንም የማያውቁ የንጹሃንን ህይወት በግፍ ከሚቀጥፉ ጉልበተኞች መታደግ ያልተቻለው። ፖለቲካው የቡድን በመሆኑ ነው የደቦ ፍርድ የተስፋፋው።
ፖለቲካው እንደ ቡድን እንጂ እንደ ሰው በጋራ የማያቆም በመሆኑ ነው አጥፊዎችን ለመጠየቅ በጋራ መቆም ያልተቻለው። የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለማስቆም፣ ፍትህን ለመጠየቅ በጋራ መቆም ያልተቻለው የጋራ መሰረት በሆነው ሰውነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ስለሌለ ነው። እንደ ሰው በጋራ መቆም ያለመቻልን መርገምት ደራሲ ዓለማየሁ ገላጋይ የገለጸበት መንገድ ሁኔታውን የበለጠ እንድንረዳው ያስችላል የሚል ዕምነት ስላለኝ እዚህ ጋር ብጠቅሰው ተገቢ ይመስለኛል።
ፍትህ መጽሄት ላይ ባስነበበው አንድ መጣጥፉ ላይ ዓለማየሁ ገላጋይ ሁለት ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃዎችን አጣቅሶ ከሰብዓዊነት የመውረድን ሸክም እንዲህ ያሳየናል፡-
“…ኦስትሪያዊው ደራሲ ፍራንዝ ካፍካ በጻፈው “The Penal Colony” በሚል አጭር ልብ ወለዱ ውስጥ እንደተረከልን አንድ አገር አሳሽ ከአንድ የሞት ቅጣት ማስፈጸሚያ ጣቢያ የጉብኝት ግብዣ ይደርሰዋል። ደስ እያለው ይሄዳል፤ ፍርደኞቹ በስቃይ ባዝነው እንዲሞቱ የሚደረግበት ትልቅ መንኮራኩር አለ። አስጎብኝው መኮንን መንኮራኩሩ እንዴት እንደተፈለሰፈና በምን ዓይነት ስቃይ እንደሚገድል ያብራራል፡-
“መንኮራኩሩ የተፈበረከው በቀድሞው አስተዳዳሪ ነው ይባል እንጂ አብዛኛው ፈጠራና ግንባታ የእኔ አንጡራ ሃሳብ ተካትቶበታል” ይላል መኮንኑ በኩራት፤
“ጥሩ” ይላል አሳሹ
“እንደምታው መንኮራኮሩ አልጋ መከስከሻና የአፍ መጠቅጠቂያ አለው። ሞት ፍርደኛው…”
አሳሹ ሳይሰቀጥጠው ይሰማል። ትንሽ ቆይቶም የፍርደኛውን ሞት በመመልከት እንደተባለው መሆኑን ለማረጋገጥ ቸኩሏል። የታሪኩ አንኳር መልዕክት ያለውም እዚህ ላይ ነው። አንድ ሰው ከትርክት እስከ ድርጊት ሰቅጣጭ ሁኔታን ለመከታተል እንደምን ፈቃዱን ይሰጣል? ዘግናኝ ድርጊቶችን ለመስማትና ለማየት ያልሰቀጠጠው በሰው ስቃይ ከሚደሰተው ወገን አይደለምን?…
…ካፍካ ትረካውን የሚያጠናቅቀው አሳሹን የጨካኙ መንኮራኩር ጭዳ በማድረግ ነው። ሳይሰቀጥጠው የሰማውን ጭካኔ በገዛ አካሉ ላይ ተከናውኖ አረጋገጠው። ከልብ የሞላው በአፍ ሲፈስ፤ ሌላ ተመሳሳይ ልብ ያለው ባለጆሮ አቆላምጦ ይሰማዋል…
ይህን የሚመስል አንድ የራሳችን ታሪክም አለ፡- …“…አጼ ቴዎድሮስ የተናደዱባቸውን እስረኞች በዘበኞች እያስያዙ ወደ ገደል ሲሰዱ ሁለት መነኮሳት ቆመው በግርምት ያዩ ነበር። አጼ ቴዎድሮስ ወደ መነኮሳቱ ተጠግተው፡-
“አባቶቼ ምን እያደረጋችሁ ነው? ሲሉ ጠየቁ፡-
“ሰው ወደ ገደል ሲወረወር እያየን” መነኩሴዎቹ መለሱ፡- “እንግዲያውስ በደንብ እዩት” ብለው እነርሱንም ወደ ገደል አስጣሏቸው።
የካፍካና አጼ ቴዎድሮስ ፍርድ አንድ ነው። ሰብዓዊነት ለሰው ፍጡር ሰቅጣጭ ከማየት ራሱን ሊከላከል በድርጊቱ ሊሳብ አይገባውም። በተለይ መነኮሳት ሲሆኑ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠውም ቢሆን አጼውን በመገዘት ድርጊቱን ሊያስቆሙ ሲገባቸው እነርሱ ግን ጭካኔ የተሞላች የጭካኔ ሥራ በመጋበዝ ይዝናኑ ነበር።
በመጨረሻም “የዚች ሃገር፣ የዚህ ዘመን ሰዎችም እዚህ ደርሰናል፤ የግፍ ሥራ ጆሯችንን ሞልቶ ሰብዓዊ የመሰቅጠጥ ፀጋችንን ተገፈናል። ሃፍረት ማጣት ብሔራችን፣ ነውር ድንበራችን ሆኗል” በማለት የደረስንበትን የሰብዓዊነት ቁልቁለት ያመላክተናል።
እኔ ደግሞ ዛሬ በዛሬው ትዝብቴ በዋነኝነት ለማሳየት እየጣርኩ ያለሁት ከዚህ ቁልቁለት ጀርባ ያለውን ገፊ የሰብዓዊነት ጠላት ነው። እርሱም ተፈጥሯዊ መሰረቱን- ሰብዓዊነትን የጣለው፣ ሰውነትን በቡድንተኝነት የተካው፣ ሰው አልባው የጎጥ ፖለቲካችን ነው።
መውጫው መንገድ
መፍትሔው አንድና አንድ ነው፣ እርሱም ከሁሉም በላይ ሰው መሆን ይቀድማል፣ “ሰውነት ይቅደም፣ ቡድንተኝነት ይውደም” የሚል ነው። እዚህ ጋር ግልጽ መሆን ያለበት ነገር ከሰውነት ለመውረዳችን፣ ከሰብዓዊነት ለመውጣታችን ዋነኛው ምክንያት ቅድሚያ ለሰውነት ሳይሆን ቅድሚያ ለቡድን ማለትም ለብሔር የሚሰጠው የፖለቲካ ሥርዓታችን ነው ብለናል። ይሁን እንጅ ቡድንተኝነት ወይም የብሔር ፖለቲካ እንጅ ብሔር አይኑር አላልኩም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፣ ይህንን መካድም ጤናማነት አይደለም፣ መካድም አይቻልም፣ እውነታ ስለሆነ። ብሔርማ ትናንትናም ነበረ፣ ዛሬም አለ፣ ነገም ይኖራል።
ይህ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ መልክ ነው፤ አይቀየርም ሊቀየርም አይችልም። “ነብር ዥንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን አይለውጥምና!” ብሔር ወይም ብሔረሰብ መሆንም ችግር ሆኖ አያውቅም፤ ብሔር ሆነን ሦስት ሺህ ዓመታት ኖረናል። እናም አሁን ዘመን አመጣሽ በሽታ ሆኖ ችግር እየፈጠረብን ያለው ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት አገር መሆኗ ሳይሆን ብሔር፣ ብሔረሰቦች ሰው ያልሆኑ ይመስል ሰውነትን ከብሔር ብሔረሰቦች አውጥቶ፣ በብሔር ሥም ብቻ የሚነግደው “ሰው አልባው የብሔር ፖለቲካ ነው”።
ምክንያቱም በሃይማኖቱ ሰው ሁሉ እኩል ነው። ጥቁሩም፣ ነጩም፣ ቻይናውም አረቡም በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ፤ ከአንድ አባትና እናት ከአዳምና ከሔዋን የተገኘ ነው። ይህ የሰው ልጅ አፈጣጠርን በተመለከተ ሃይማኖታዊው ዕይታ ሲሆን አስተምሮው የሚመሰረተውም በዚሁ መሰረታዊ አስተሳሰብ ላይ ነው። እናም በሃይማኖታዊው እሳቤ መሰረት ዘር፣ ብሔር፣ ጎሳ የሚባል ነገር የለም፤ ሰው ሰው ነው። ዘረኝነትም የተወገዘ ነው። በሳይንስም “ዘረኞች” እንጅ ዘር የሚባል ነገር አለመኖሩ ተረጋግጧል። እናም ታላቋ እንስት አሳቢ አያን ራንድ እንዳለችው ብሔርን ጨምሮ በማንኛውም ቡድን ላይ የተመሰረተ ቡድንተኝነት ተፈጥሯዊ ሳይሆን የጭፍንነትና የመንጋነት አስተሳሰብ ውጤት ነው።
ታላቋ አሳቢ አያን ራንድ እንዳለችው ብሔርን ጨምሮ ማንኛውም ቡድንተኝነት ክፉና በጎውን ማመዛዘን የማይችል ምክንያታዊነት የጎደለው የጭፍን አስተሳሰብና በመንጋ ማመን የፈጠረው ነው። ለዚህም ዋነኛው ምክንያቱ በቡድን ካልሆነ በቀር ግለሰቦች በራሳቸው ምንም ማድረግ አይችሉም የሚለው የዘመናዊ ፍልስፍና አስተሳሰብ ነው። ይህ አስተሳሰብ በሂደት በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ሰርፆ በመግባት ተቀባይነትን ማግኘት ሲጀምር ግለሰቦች ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ ይመጣል፤ የሚጠቅማቸውን ነገር ለመምረጥና ትክክለኛ ውሳኔ ለመወሰን የራስ መተማመን ያጣሉ።
ይህም በበኩሉ ምክንያታዊ ዕምነት እንዳይኖራቸው ስለሚያደርጋቸው ሰዎች በአስተሳሰብ ሳይሆን በሥጋ የሚቀርባቸውን ቡድን እንዲቀላቀሉ ያስገድዳቸዋል። ይህ በአስተሳሰብ ሳይሆን በሥጋ ዝምድና የሚመሰረት “በምክንያት ያልተመረጠ ቡድን” ነው እንግዲህ “ብሔር” የሚል ታርጋ የሚለጠፍለት። በዚህ የተነሳም ቡድንተኛ ብሔርተኞች በዕውቀትና በምክንያት ላይ ተመስርተው የሃሳቡን ጥቅምና ጉዳት መዝነው ሳይሆን አጥንታቸውን ቆጥረው ለተሰባሰቡበት ግዑዛዊ ቡድን “በማንኛውም ጊዜ ያለ ቅድመ ሁኔታ ለቡድንህ ታመን” ከሚለው ከሁሉም አስበልጠው ከሚያዩት የመንጋ መርሃቸው በቀር ሌላ ህግና መርህ አያውቁም።
ማንኛውም ቡድንተኝነት ፀረ ዕውቀት፣ ፀረ ምክንያታዊነትና ፀረ ሞራል የሆነ፣ ልፋት የማይጠይቅ የደካሞችና የሰነፎች ሥራ ነው። እናም በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከራሳቸው ጠባብ የአጥር ክልል ውጭ ስላለው ዓለም ዴንታ የሌላቸው እንዲያውም ከእነርሱ ውጭ ያለውን፣ በእነርሱ አገላለጽ “መጤ” የሚሉትን ሁሉ የሚጠራጠሩና በስጋትነት የሚመለከቱ፣ በራስ ወዳድነት ታስረው የተቀመጡ ድኩማን ፍጥረቶች ናቸው። ቡድንተኞች ክፉውን ከበጎው የሚለዩበት ማመዛዘኛ ህሊና እና እውነቱን እውነት፣ ሃሰቱን ሃሰት፣ ትክክሉን ትክክል፣ ስህተቱን ስህተት የሚሉበት ሞራል የላቸውም።
ታዲያ ሰውን በብሔር ከፋፍሎ በዚህ ዓይነት የተዋረደና የሞተ ፍጹም ከሰውነት ውጭ የሆነ ሰው አልባ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ከመምራት የበለጠ ሰውን የሚጎዳ ሌላ ምን የከበደ ጥፋት አለ! ፖለቲካ ማለት በዋነኝነት የመንግስትን ስልጣን ይዞ በሃገርና ህዝብ ጉዳይ ላይ መወሰን ማለት ነው። ይህም ከሚያስገኘው ጥቅም እኩል የሚያስጠይቅ ታላቅ ኃላፊነት ያለበት ነውና ራሱን ስልጣን ላይ ማቆየትን ብቻ ዓላማና ግቡ ያደረገው፣ በቡድንተኝነት እንጅ ሰውነት ላይ መሰረት ያላደረገው ኋላቀሩ የቡድን ፖለቲካ ግን ሰዎችን እኩል ማስተናገድና መምራት ስለማይችል ኃላፊነቱን መወጣት ሲከብደው ከተጠያቂነት ለመራቅ መሰረቱን ትቶ ቡድን ውስጥ ይደበቃል።
በዚህም ፖለቲካው ራሱን በትክክል መምራት ሲያቅተው ሰዎችን አንድ አድርጎና አስተባብሮ ለመምራት ሳይሆን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው በአፍራሽ መንገድ በእያንዳንዱ የሰዎች ሕይወት ውስጥ ጣልቃ እየገባ ሰውን ከማንነቱ እንዲለይ ያሴራል፣ ባህላዊ ጉዳዮች ውስጥ ይገባል፣ ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ ይወሸቃል። ምን ይሄ ብቻ አሁን ላይ በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች እንደምናየው ፍጹም ወደማያገባው መስጊድና ቤተ ክርስቲያናት ውስጥም እየገባ ሰዎች የሚለያዩበትን መንገድ ይፈጥራል፣ ሰዎችን ከሰውነት ባህርይ ያስወጣቸዋል። ያኔ አንድ የሚያደርገው ሰውነት ቀርቶ ሁሉም ነገር ቡድን ይሆናል። ሰውነት እንደ ጭራ ይመነምን እና እንደ ሰው በጋራ መቆም ያቅታል፣ ሰብዓዊነትም ይረሳል።
ስለሆነም ከላይ በደራሲ ካፍካና በአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ ውስጥ እንዳየነው በሰውነት በጋራ መቆም ቀርቶ፣ ሰብዓዊነት ተረስቶ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን በመቃወም ፋንታ እርሱም ተራው ደርሶ የመጥፋት ጽዋውን እስኪጎነጭ ድረስ ቆሞ መመልከት ይጀምራል። እናም ሰብዓዊነትን ከሚነጥቅ ከዚህ የዘመናችን መርገምት ለመዳን ሰውነትን ክዶ በግዑዝ መንጋ የሚያምነው “ሰው አልባው” ን እና ስሁቱን የቡድን ፖለቲካ “ሰው መር” ማድረግ ፍቱን መፍትሔ ነው እላለሁ። ይኸው ነው። በእኔ ዕምነት ሕዝቦቿ የተባረኩ ናቸው፤ ከቻለ(ደግሞ ይችላል!) እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ፖለቲካዋን ይባርክ!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 27/2012
ይበል ካሳ