የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ወራት ብቻ ለሚቀሩት የሪዮ ኦሊምፒክ በአፋጣኝ ወደ ስልጠና ለመግባት ሁኔታዎች እንደሚመቻቹ አመለከተ፡፡ ፌዴሬሽኑ በዝግጅቱ ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል፡፡
ጃፓን አስተናጋጅ የሆነችበት የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ሊካሄዱ የቀሩት ከስድስት ወራት ያነሰ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ካለፉት የሪዮ ኦሊምፒክና የዶሃው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተሞክሮ በመውሰድ ስልጠና እንዲታቀድና በአፋጣኝ ወደ ትግበራ እንዲገባ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ለተግባራዊነቱም ፌዴሬሽኑ ለሚያወጣው የምልመላና የስልጠና ዝግጅት ሚናውን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡ ለውድድሩ ታስበው የሚከናወኑ እንዲሁም ታቅደው የሚመሩና የሚፈጸሙ እንዲሆኑ ጥብቅ ክትትልና የድጋፍ ስርዓት ተዘርግቶ ችግሮች ሲያጋጥሙ በወቅቱ ተቀራርቦና ተረባርቦ መፍታት የሚያስችል ቀልጣፋ ስርዓት እንዲዘረጋና እንዲተገበርም ፌዴሬሽኑ አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ጋር በተያያዘ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ትናንት ባደረገው የምክክር መድረክ ላይ ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ፌዴሬሽኖች፣ አንጋፋ አትሌቶችና የሙያ ማህበራት፣ ክለቦች፣ ማሰልጠኛ ተቋማት፣ አሰልጣኞች፣ ማናጀሮች እንዲሁም የማናጀር ተወካዮችና ሌሎችም ባለሙያዎች ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በውይይቱም ላይ አገሪቷ በተለይ በኦሊምፒክ ውጤታማ በሆነችበት የአትሌቲክስ ስፖርት እንደተለመደው ውጤት በማስመዝገብና የአገርን መልካም ገጽታ በመገንባት ላይ ያጠነጠኑ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡
የምልመላ፣ የስልጠና የአሰራር፣ ቅንጅት፣ ተግባቦት፣ ትብብር፣ ተፈጥሯዊና ንጹህ ውድድር ማድረግ እንዲሁም ከግል ፍላጎት ይልቅ የአገርን ክብር ማስቀደም የሚሉ ሃሳቦችም ጎልተው ተንጸባርቀዋል፡፡ ትግበራውም በፌዴሬሽኑ መሪነትና አስተባባሪነት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተግባብቶና ተቀናጅቶ በመስራት ረገድ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ የአቋም መግለጫ በማውጣት የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡
በአቋም መግለጫው የአትሌቶችና አሰልጣኞች ምላመላ በተሻሻለው የፌዴሬሽኑ የውስጥ አሰራር መመሪያ መሰረት ግልጽ፣ ፍትሃዊና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ተጠቁሟል፡፡ አትሌቶች ዘመናዊና ሳይንሳዊ ስልጠና ከመስጠት አንጻር የሚመረጡ አሰልጣኞች ወቅቱንና ሁኔታው የሚጠይቀውን የስልጠና ዕቅድ እንዲዘጋጅ፣ በአፈጻጸሙም ላይ በተገቢው መንገድ ክትትል እንዲደረግበትና የማስተካከያ እርምጃዎችም በወቅቱ እንዲወሰዱ እንዲሁም የቶኪዮን የአየር ሁኔታን ያገናዘበ ስልጠና እንደሚካሄድም ቃል ተገብቷል፡፡
ፌዴሬሽኑ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በመተባበር የገንዘብና የግብዓት አቅርቦት ወቅቱን ጠብቆ እንዲቀርብና በሥራ ላይ እንዲውልም ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ስለ አበረታች ቅመሞች ግንዛቤ ያለውና ንጹህ የሆነ አትሌት እንዲሁም በዓለም አቀፉ ጸረ አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ መመሪያ መሰረት ምርመራ ሂደቱን በአግባቡ የሚያልፉ አትሌቶች በመድረኩ እንደሚካፈሉም ተረጋግቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለውጤታማነት እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፣
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 27/2012
ብርሃን ፈይሳ