– የ100 ቀናት እቅዱን 60 በመቶ አከናወነ
አዲስ አበባ፡- ከአገራዊ የ100 ቀናት ዕቅድ ውስጥ 60 በመቶ ያህል ሥራውን ማከናወን እንደቻለ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ተቋሙ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል፣ በማዘመንና ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑም ጠቁሟል፡፡
ኮሚሽነሩ አቶ በዛብህ ገብረየስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ቀልጣፋና ውጤታማ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት በመዘርጋት አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል የመጀመሪያው ቁልፍ ሥራው ነው፡፡ ይህን ለማድረግም ቀደም ሲል የነበረው የሲቪል ሰርቪስ አሠራርና አካሄድ በመልካም ገጽታው የሚታወቅበትን ሁኔታ ማስተካከል መነሻ ሥራ ሲሆን፤ በቀሪ ቀናትም አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና የተሳለጠ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
ቀደም ሲል የነበረውን የውጤት ተኮር መመዘኛ ስርዓት በተለይም አብዛኞቹ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ወረቀት የሚበዛባቸው፣ ለመረዳት ግልጽ አይደሉም፣ ሥራዎቹ ውስብስብ ናቸው፣ የሚሉና መሠል ችግሮች ይነሱ እንደነበር ኮሚሽነሩ አስታውሰው፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም ቀላል የአሠራር ስርዓቶችን ለመዘርጋት የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት ፕሮጀክት ላይ የሚሠሩ ፓኬጆች በየተቋማቱ ላይ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም100 በሚሆኑ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ እየተተገበሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ ቀርፆ መተግበር ሌላው ተግባር ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ይህ ቁልፍ ተግባር ከዓለም ባንክና ከእንግሊዝ ተቋም ጋር ግንኙነት በመፍጠር የውጭ አገር ባለሙያዎችን በማምጣት የፍኖተ ካርታ ምሰሶዎች ላይ ያተኮረ መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡ ከ60 በላይ ባለሙያዎች፣ የቢሮ ኃላፊዎች፣ በሥራው ላይ ከፍተኛ ዕውቀት አላቸው የሚባሉ አካላት ከዓለም ባንክ ባለሙያዎች ጋር በመሆን መነሻ እያዘጋጁ እንደሆነና የጥራት ማረጋገጥና ተገቢ ግብዓቶችን ሰጥቶ ወደ ተግባር የማስገቢያ ዐውደ ጥናት ለአንድ ቀን እንደሚካድ ጠቁመዋል፡፡ ፍኖተ ካርታውም ረቂቅ ተዘጋጅቶ በቀሪ አንድ ወር ውስጥ ተጠናቅቆ የሕዝብ ውይይት ይደረግበታል፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ የሰው ሀብት ልማትና አመራር ስርዓትን ማዘመን ሌላው ተግባር ሲሆን፤ በዚህም አገር አቀፍ የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ስትራተጂ ሰነድ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ የሚወጡ መመሪያዎች፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ሁሉ የነበረውን ችግር በሚቀርፍና በአሁኑ ወቅት የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ በሚደግፍ አግባብ እየተሠራ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
በተለይም የመንግሥት አሠራር በግልጽነት፣ ተጠያቂነትና በፍትሐዊነት ላይ እንዲሆንና የእነዚህ ድምር ውጤትም ሰላምን ያሰፍናል በሚል እየተሠራም ነው ያሉት ኮሚሽነር በዛብህ በዚህም አዳዲስ ምሩቃንን ወደ ሲቪል ሰርቪሱ የሚገቡበት የምልመላ ስርዓት መዘርጋት በመቶ ቀናት ውስጥ በትኩረት የሚሠራበት ነው ብለዋል፡፡ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ ወደ ሲቪል ሰርቪሱ የሚገቡበት ሁኔታ የሚመቻችበትና ተማሪዎቹ ገና በትምህርት ቤት ሳሉ ቀድመው ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ለማከናወን ልምዱ ካላቸው ተቋማት ጋር ትስስር መፈጠሩን አብራርተዋል፡፡
የሥራ ምዘናና ደረጃ አሰጣጥ (ጂኤጂ) በሁሉም የአገሪቱ ተቋማት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር ማድረግ በመቶ ቀናት ውስጥ የታቀደ ሲሆን፤ 99 በመቶ ያህል መጠናቀቁን አቶ በዛብህ ጠቁመዋል፡፡ አገር አቀፍ የሰው ሀብት ልማትና ሥራ አመራር ማደራጀት ጋር ተያይዞም ለረጅም ዓመታት በተቋሙ ያሉ የሌሎች መስሪያ ቤቶች መረጃዎችንም የማጠናቀር ሥራ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የመያዝና የወረቀት ሰነዶችን ቦታ በማስለቀቅ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የመተካት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ እስከአሁን 12 ሺህ 800 ሰነዶች በዚህ መልኩ ተስተናግደዋል፡፡ ይህም በዕቅድ የተያዘው በመቶ ቀናት ውስጥ ካሉት 100 ሺህ በላይ ሰነዶች 25 ሺህ የሚሆነውን መሥራት ነበር፡፡ ከኦዲት ጋር ተያይዞ ያሉ ሥራዎችን ደግሞ ያሉትን ሥራዎች በመቶ ቀናት ውስጥ ሊያልቅ የማይችል መሆኑ በመገምገሙ ይህን የሚሠራ የፕሮጀከት ጽህፈት ቤት ሊከፈት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በሥራው ላይ ያጋጠሙ ችግሮች እንዳሉም ኮሚሽነሩ አልሸሸጉም፡፡ ከተቋማት በተለይም ከዩኒቨርሲቲዎች የሚመጡ በርካታ ቅሬታዎችን ማድመጥ በርካታ ስትራተጂካዊ ጉዳዮችን በሚፈለገው ደረጃ ላለማየት ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ እንደ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ያሉ የፈረሱ ተቋማት ሥራዎች ማጠናቀቅ፣ ተጠሪ ተቋማት በተለይ የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ነበር በሚል የሠራተኛውና የአመራሩ መስተጋብር ጥሩ አለመሆንና መሰል ችግሮች በሥራው ያጋጠሙና ጎታች የነበሩ ምክንያቶች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ለችግሮች መፍትሔ በማስቀመጥ በመሠራቱ ተጨባጭ ውጤት መጥቷል በማለት ሥራዎችንም በቀሪ ቀናት ለመተግበር በትኩረት እተሠራ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 1/2011
በፍዮሪ ተወልደ