የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አልጋ ወራሽ የነበሩትና ኢትዮጵያን ከ1903-1909 ዓ.ም ‹‹ያስተዳደሩት›› ልጅ ኢያሱ ሚካኤል የተወለዱት የዛሬ 127 ዓመት ( ጥር 25 ቀን 1885 ዓ.ም) ሲሆን ዕለቱ በቤተዘመድ እና አድናቂዎቻቸው ታስቧል።
በተለይ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሒደት ተከትሎ እየታዩ ያሉ ግጭቶች፣ አለመረጋጋቶችና የአክራሪ ብሔርተኝነት እና ሃይማኖት አካሄዶች… ያስተዋሉ አንዳንድ ወገኖች 127 ወደኋላ ተመልሰው በሴራ የጨነገፈውን የልጅ ኢያሱን የሥልጣን ዘመን በማስታወስ ታሪክ ራሱን ሊደግም ይሆን? በሚል ሥጋታቸውን ይገልጻሉ።
ልጅ ኢያሱ ሚካኤል፣ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ የልጅ ልጅ፣ ንጉሠ ነገሥት ባይባሉም ከ1903 እስከ 1909 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሥልጣን ጨብጠው ያስተዳደሩ መሪ ነበሩ።
የታሪክ ፕሮፌሰሩ ባሕሩ ዘውዴ እንደጻፉት፣ የኢያሱ ዘመነ መንግሥት በእንቆቅልሽ የተሞላ ዘመን ነው። አፍ ሞልቶ በክፉም በበጎም ማውሳቱ ያዳግታልና። ‹‹አቤቶ›› እየተባሉም ይጠሩ የነበሩት ልጅ ኢያሱ፣ በአጭር የሥልጣን ዘመናቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለኝታን በማጠናከራቸው፣ ተራማጅ ሊባሉ የሚችሉ አንዳንድ እርምጃዎችን ወስደዋል።
የግል ንብረትን የማስከበርና ዐሥራትን በወቅቱ ከመሰብሰብ ደንብ በተጨማሪ፣ ከሳሽና ተከሳሽ አብረው እንዲማቅቁ ያደርግ የነበረውን የቁራኛ ሥርዓት ለመሻር፣ እርምጃ ወስደዋል። እንዲሁም ከፍትሕ ይልቅ ለቂም መወጫና ደካማ ማጥቂያነት የሚያገለግለውን የሌባ ሻይ ሥርዓት መልክ ለማስያዝ ሞክረዋል። የመንግሥት ገንዘብን ባባከኑት ላይ እርምጃ በመውሰድም ልጅ ኢያሱ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ ሳይሆኑ አይቀርም።
በ1884 ዓ.ም. የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጅ የሆነችው ሸዋረጋ ከወሎው ገዢ ራስ ሚካኤል ጋር በተደረገ ትስስር የሰመረው ጋብቻ፣ ልጅ ኢያሱን አስገኘ። ኢያሱ ያደጉት አያታቸው ከመጡበት የአንኮበር ከተማ ነበር። ልዑሉ በዚህ ቦታ ተገልለው ቢቀመጡም የትምህርታቸው ክትትል መረጃ ግን በፎቶ ግራፍ አንሺዎች ይመዘገብ እንደነበር ይነገራል።
ከዚህ በተጨማሪም ልዑሉን በአእምሮና በአካል የጠነከሩ አድርጐ ለማብቃት መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ፣ ዳዊት ሲደግሙ፣ ፈረስ ሲጋልቡ፣ እንዲሁም የእጅ ጽሕፈት ሲማሩ መቆየታቸውን የሚያሳዩት ፎቶግራፎች ያነሷቸው ከዳግማዊ ምኒልክ በተላኩ የፎቶ ግራፍ አንሺዎች አማካይነት ነው።
ከሕፃንነት ዘመናቸው ጀምሮ ፎቶግራፍ የተነሡት ልጅ ኢያሱ፣ በፎቶግራፍ ጥበብ ተገልጸዋል። ዘውድ ባይጭኑም የሥልጣን ተምሣሌቶችን ለራሳቸው መጠቀማቸው የቀረቡት ፎቶ ግራፎች ያመለክታሉ።
ይኸውም እንደ ጦረኛ፣ እንደ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ እንደ ዲፕሎማት ሆነው ከመስቀል፣ ከአንበሳ፣ ከጦር መሣሪያ ጋር፣ ሜዳሊያ በማጥለቅም ተነሥተዋል። ለብቻ ወይም በቡድን በመሆን በሚነሷቸው ፎቶግራፎቻቸው አማካይነትም ፖለቲካዊና ቤተሰባዊ ትስስርንና ጥምረትን ያሳዩ ነበር።
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ከተከፈቱት ሁለት የፎቶ ስቱዲዮዎች ባለቤቶች ለኢያሱ ቅርብ ነበሩ። በተለይ ቤድሮስ ቦያጂያን፣ ልጅ ኢያሱ በመላ ሀገሪቱ በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ሁሉ አብሮ የመሆን (የማጀብ) ልዩ መብት ነበረው።
ከቀረቡት ፎቶ ግራፎች መካከል አንዱ የልጅ ኢያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤል ዘውድ ደፍተው የተነሱት ፎቶ ነው።
ንጉሡን ያነገሷቸው ልጃቸው ልጅ ኢያሱ ናቸው። ስለዚሁ ታሪክ ከቀረቡት ልዩ ልዩ መጻሕፍትና መዛግብት አንዱ የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ “የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በአቤቶ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት” ነው፤ ስለ ንግሥናው የሚከተለውን ተርኳል።
“ከአፄ ምኒልክ ሞት በኋላ በ1906 ዓ.ም. ሚኒስትሮችና መኳንንት በቆይታ ተመካክረው ለአቤቶ ኢያሱ የምክር ቃል አቀረቡ፤ ሲባል ተሰማ። የምክሩም ቃል ፣ጃንሆይ አፄ ምኒልክ በሕይወታቸው ሳሉ አልጋ ወራሼ ኢያሱ ነው ብለው አስታወቁን፤ አሁን እሳቸው ዐረፉ፤ እንግዲህ ምን እስቲሆን እንጠብቃለን፤ የዘውድ በዓልዎ የሚደረግበትን ቀን እንወስንና ዘውድ ደፍተው በአባትዎ መንበረ ዳዊት ይቀመጡልን፣ የሚል ነው።
አቤቶ ኢያሱም፣ “ምክራችሁ መልካም ነው፣ እኔም ሳላስብበት አልቀረሁም፤ ነገር ግን አባቴን ራስ ሚካኤልን በፊት ንጉሥ አሰኝቼ፣ በኋላ ንጉሠ ነገሥት መሆን ይገባኛል” ብለው መለሱላቸው። ሐሳባቸውን የፈጸሙት በዚያው ዓመት ከአዲስ አበባ ከአፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ዘውድና ሉል፣ ልብሰ መንግሥት ወደ ደሴ በመላክ ራስ ሚካኤልን “ንጉሠ ወሎ ወ ትግሬ” አሰኝተው፣ በግንቦት 23 ቀን 1906 ዓ.ም. በዕለተ እሑድ ደሴ ላይ አንግሠዋቸዋል።
ቅብዐ መንግሥት ከአራት ዓይነት ሽቶና ከአምስተኛ ዘይት ተዘጋጅቶ በጸሎት የሚቀደስ፣ ነገሥታት ዘውድ በሚቀዳጁበት ዕለት የሚቀቡት ቅብዐት ነውሪ የቀቡዋቸው ከአፄ ዮሐንስ ጋር ትግሬ ላይ የነበሩት ግብፃዊ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው። የንጉሥ ሚካኤል ማኅተምም በግእዝና በዐረብኛ ተጽፎበታል።
በአዲስ አበባ በጥንቱ የቅድስት (መካነ) ሥላሴ (ያሁኑ በዓለ ወልድ) ቤተ ክርስቲያን ምሥራቃዊ ግድግዳ ላይ በ1901 ዓ.ም. በካሣ አረጋኸኝ የተሣለው ዳግማዊ ምኒልክና ልጅ ኢያሱን ከአቡነ ማቴዎስ ጋር በአንድነት ያሳያል።
ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ ዘውድና በትረ መንግሥት፣ ልጅ ኢያሱ ጎራዴ፣ አቡነ ማቴዎስ መጽሐፍ ቅዱስ መያዛቸው፣ እንደ ርእሰ ብሔር ያላቸውን ሚና የሚያመለክቱ ናቸው። በመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ልጅ ኢያሱ ቆመው የሚያሳዩ ሦስት የግድግዳ ሥዕሎችም ተሥለው ይታያሉ።
በመስከረም 1909 ዓ.ም. የነበረው ፎቶግራፍ፣ የልጅ ኢያሱን አጭር የሥልጣን ዘመን እንዲያበቃ ያደረገውን መፈንቅለ መንግሥት ያረጋገጠ መሆኑ በዐውደ ርዕዩ ተመልክቷል።
ከዚያ ቀን ጀምሮ ልዑሉ ከአደባባይ ሕይወት ተገልለው ነበር። በመጨረሻዎቹ የልጅ ኢያሱ ዓመታት ጥቂት ፎቶግራፎችና አንድ የቤተ ክርስቲያን ሥዕል ብቻ ተገኝቷል።
ልጅ ኢያሱ የጀርመን መልክተኛ በተቀበሉበት ጊዜ የአውሮጳውያን ልብስ ለብሰው የተነሡት ፎቶግራፍም አለባበሳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ የኢትዮጵያ መሪ ዘመናዊ ልብስ ለብሶ የሚያሳይ መሆኑም ተመዝግቧል።
ኢያሱ ከሐረሩ መሪ አብዱላሂ ሳዲቅ አጠገብ ተቀምጠው የተነሱት ፎቶግራፍ ላይ የሚታየው አለባበስ የሐረሮቹን ባህል የተከተለ መሆኑ የሚከተሉትን የፖለቲካ ስትራቴጂና አጋርነት የሚያሳይ ነው።
75 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። የልጅ ኢያሱ እስር ቤትም የሚገኘው እዚሁ ነው። ልጅ ኢያሱ በጋራሙለታ ግራዋ ወረዳ እስር ቤት የቆዩት ከ1925 እስከ 1927 ዓ.ም እንደነበረ ይነገራል።
ልጅ ኢያሱ ከሥልጣናቸው በተቀነባበረ ሴራ ከተወገዱ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ ሕይወታቸውን ያሳለፉት ከአንዱ ቦታ ወደሌላው በመዘዋወር ነበር ማለት ይቻላል።ተክለ ፃድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ልጅ ኢያሱ እንዴት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ እንደሚከተለው ይገልጹታል፡-
‹‹…የልጅ ኢያሱ ያሉበትም አገር ጠፍቶ ሲኖር በ1913 ዓመተ ምሕረት በትግሬ ውስጥ ግብፅያ በሚባለው ገዳም ተገኙ። ወደዚያም የሄዱበት ምክንያት የልዑል ራስ ሥዩም ባለቤት ወይዘሮ ተዋበች እህታቸው ስለነበሩ በዚያ ለመሸሸግ ብለው ነው ይባላል። በኋላ ግን በዚሁ ግብፅያ በሚባለው ገዳም የራስ ጉግሳ አርአያ ሰዎች አግኝተው ማረኳቸው።›› (ሁለተኛ እትም 2000፤ ገጽ 166)
ይህንንም ተከትሎ ልዑል ራስ ጉግሳ የአቤቶ ኢያሱን በቁጥጥር ሥር መዋል ለአልጋ ወራሹ ራስ ተፈሪ አበሰሯቸው።
‹‹…ልዑል አልጋ ወራሽም በ1913 ዓ.ም. በፋሲካው ወራት ወደ ደሴ ሄደው ሳሉ ራስ ጉግሳ እስረኛውን አቤቶ ኢያሱን በታማኝነት አስረከቡ። ከዚያም አቤቶ ኢያሱ ወዳዲስ አበባ መጥተው ሰላሌ ፍቼ በልዑል ራስ ካሳ እጅ እሥረኛ ሆነው መኖሪያ የሚሆን ልዩ ቤት ተሠርቶላቸው ተቀመጡ።›› (ተክለ ፃድቅ መኩሪያ፤ ገጽ 117)
‹‹ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ አጭር የሕይወቱና የጽሑፉ ታሪክ›› በሚል ዮሐንስ አድማሱ በፃፈውና ዮናስ አድማሱ ባሰናኘው መጽሐፍ በወቅቱ ስለነበረው ኹነት ሲገልጽ፡-
‹‹…ከዚያም በኋላ ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ የጦር ሚኒስትሩን ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስንና ከጎጃም ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖትን አስከትለው ወደ ትግሬ ዘመቻ ተጉዘው ደሴ ላይ ሲደርሱ፣ ራስ ጉግሳ ልጅ ኢያሱን ይዘው መጥተው የጁ ላይ ከሸዋ ለተላከው ጦር ስላስረከቡ ዘመቻው ደሴ ድረስ ሆኖ ከደሴ ጦሩ ወደ የሀገሩ እንዲመለስ ተደረገ።… [ልጅ ኢያሱ] እንዲታሰር ተወስኖ የነበረውም ኰላሽ በተባለው አምባ ስለነበር ልጅ ኢያሱ በዚህ ሥፍራ አልታሠር በማለት ቅሬታቸውን ስለገለጡ መኳንንቶቹ ለንግሥትና ለአልጋ ወራሽም አመልክተው ኮረማሽ እንዲታሠሩ ተደረገ። አልጋ ወራሽም ከደሴ ሲመለሱ ኮራማሽ ደርሰው ቦታውን አይተው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።…›› (2004 ዓ.ም.፤ ገጽ 18-19)
የሸዋ መኳንንት ሴራ
አጥናፍ ሰገድ ይልማ “አቤቶ ኢያሱ አነሳስና አወዳደቅ” በሚለው መጽሐፋቸው ልጅ ኢያሱ በሸዋ መኳንንት ሴራ እንዴት እንደተጠለፉ ጽፈዋል። “….ንጉሥ ሚካኤል፤ አጅባር ሚካኤልን፣ ደሴ መድኃኒዓለምንና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን ያሰሩ ትልቅ ክርስቲያን ተብለው የሚጠቀሱ ናቸው። ልጃቸው ኢያሱም በክርስቲያን ወግ ተኮትኩተው ስላደጉ ነው፤ አጤ ምኒልክ የአልጋወራሽነቱን ክብር ያጐናፀፏቸው። … ምንም ተባለ ምን ኢያሱ ክርስቲያን ነበሩ። የሸዋ መኳንንት ልጅ ኢያሱን “ሰልሟል፣ ቀበጥና ያያትን ሴት ሁሉ ቀሚስ ገፋፊ ሆኗል” የሚል ታርጋ መለጠፍ የጀመሩት ኢያሱ ወደተለያዩ የጠረፍ ግዛቶቻቸው በመዘዋወር ህዝብን በማረጋጋት፣ ችግሩን በማዳመጥና መፍትሔ በማፈላለግ ላይ ሳሉ ነው። በተለይ የደጃዝማች ተፈሪ ግዛት ወደነበረው የሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ሄደው፣ ለረጅም ወራት ከሶማሌዎች፣ ከአፋሮችና ከሐረሬዎች ጋር መቆየታቸው ለሥልጣን ተቀናቃኞቻቸው ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል።
የደጃዝማች ተፈሪ (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ) የልብ ወዳጅ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለ ማርያም፤ “በዓይኔ አየሁት” ያሉትን በአግባቡ መመርመር ኢያሱ ሰልመዋል? ወይስ የሸዋ መኳንንት የፈጠራ ክስ ነው? የሚለውን ጥያቄ በወጉ ይመልስልናል። ፊታውራሪው ኢያሱ እንደሚጠረጥሩዋቸው፣ ለተፈሪ ለመሰለል ይሁን ወይም ራሳቸው እንደሚሉት ለሀገራቸው በቅንነት ለማገልገል ከኢያሱ ጋር በሐረር፣ በጅጅጋ፣ በሐረማያ፣ በጅቡቲና በሌሎችም ቦታዎች ተዘዋውረው የኢያሱን “ገመና” ያሉትን ታዝበዋል ወይም መታዘባቸውን ገልጠዋል። ፊታውራሪ “አቶ ባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ)” በሚል ርዕስ ጽፈው ቤተሰባቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ጋር በመተባበር በ1998 ዓ.ም ባሳተመው ግለታሪካቸው (ገፅ 245-285) ኢያሱ ተፈሪን እንደሚፈሩ፣ በዚህ የተነሳ ከሐረር ሊነቅሏቸው፣ ከተቻለም ከማንኛውም ፖለቲካዊ ሥልጣን ሊያስወግዷቸው ማቀዳቸውን፣ የኢያሱ ቅብጠት ከልክ ያለፈ መሆኑን እንዲያውም “ኢዲልቢ” የሚባል የውጭ አገር ዜጋ፣ ሚስትና ልጁን እያቀረበላቸው እንደሚማግጡ፣ ሃፍረተቢስ ሴሰኛ መሆናቸውን፣ ከሙስሊሞች ጋር ጫት ሲቅሙ ማየታቸውን፣ የግመል ስጋ እንደሚወዱ… ከሁለት ሰዎች ጠይቀው ማረጋገጣቸውን፣ ሲጋራ እንደሚያጨሱ፣ ቀልድ እንጂ ቁምነገር የሚባል ነገር እንደማያውቁ ዘርዝረዋል።
ከሁሉም በላይ የሸዋን መኳንንት አድማ ሲሰሙ በብስጭት “…እንዲያውም ኢትዮጵያን በሙሉ አሰልማታለሁ። ይህን ያላደረግሁ እንደሆነ እኔ አቤቶ ኢያሱ ሰው አይደለሁም (ገፅ 275) አሉና ፈከሩ” ብለው ከመጻፋቸው በተጨማሪ፣ ጅጅጋ ውስጥ እንደ አደሬ (ሐረሪ) ሙስሊሞች ለብሰው ራሳቸው ላይም የሙስሊም ጥምጣም አድርገው ማየታቸውን ገልጠዋል። ሆኖም በገፅ 277 ላይ “ልጅ ኢያሱ ቀንና ሌሊት ከአደሬ እስላሞች ጋር ከተማውን እየዞሩ ያዳርሳሉ። በየመስጊዱ እየገቡ ጫት ይበላሉ። ይሰግዳሉም እየተባለ ይወራል። ግን ለማረጋገጥ አልተቻለም” ብለዋል።
…በነገራችን ላይ በርኖስ ተገልብጦ የሚለበሰው በሐዘን ጊዜ ብቻ ነው፤ የቅርብ ዘመድ ሲሞት የሚደረግ። ፀጋዬ ገ/መድኅን “የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ” በሚለው ግጥሙ ውስጥ “እውነትን ሲገድሉ እንዲህ ነው ፈገግታውን አጨልመው…” ይላል፤ ልክ እንደ ንጉሡ ማለት ነው። በግፍ ለገደሉት፤ በረሃ ለበረሃ እንደ ዱር አውሬ ሲያሳድዱት ለኖሩት ኢያሱ ሐዘን ሲቀመጡ ይታያችሁ። እናም ኢያሱ ሃይማኖታቸውን አልካዱም፤ መጀመሪያ የምኒልክን አደራ፣ ቀጥሎም የገቡትን ቃልና የሊቀጳጳሱን ግዝት በማፍረስ ለሥልጣን ሲሉ እምነታቸውን የካዱ የወቅቱ የሸዋ መኳንንት ናቸው። እምነታቸውን ክደው፣ ለተፈሪ በማበራቸውና ተፈሪም እየተከታተሉ በሠሩት ግፍ የኢትዮጵያ መኳንንት እና ህዝብ በእጅጉ ተቀየመ፤ በውጤቱም የማይጨው ውርደት ተከተለ። ልጅ ኢያሱን የሸዋ መኳንንት የወነጀሉበት ሌላው ነጥብ “ኢያሱ ሴሰኛ ነው” የሚል ነው።”
ልጅ ኢያሱ በፍቼ እስር ቤት
ልጅ ኢያሱ በፍቼ እስር ቤት ከ1923 እስከ 1925 እንደቆዩ ይነገራል። ከኢያሱ ጋር ፊታውራሪ ተሰማ ቡኔና ቴዎድሮስ ኢያሱ አብረው ታስረው ነበር የሚለውን መረጃ አግኝቻለሁ። (ልጅ ኢያሱ ወደ ጋራሙለታ እስር ቤት ሲዘዋወርም አብረውት እንደነበሩ ይነገራል።)
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ልጅ ኢያሱ በፍቼ የነበረው የእስር ቆይታቸው በአንፃራዊነት በምቾት የተሞላ ነበር። ዘመዳቸው በነበሩት ካሳ ኃይሉ ቁጥጥር ሥር ነበሩ። ይሁንና እ.ኤ.አ. በ1931 ኢያሱ ከፍቼ እስር ቤት አመለጡ። ከእስር ለማምለጣቸው የተለያዩ ምክንያቶች ይሰነዘራሉ። ኃይለ ሥላሴ እጃቸውን ጣሊያኖች ላይ ሲቀስሩ፣ ሌሎች ደግሞ ተጠያቂው የጎጃሙ ራስ ተክለ ሃይማኖት ናቸው ብለው ይከራከራሉ። እንደምክንያትም የሚያነሱት ለከፈልኩት መስዋዕትነት ምንም ሥልጣን አልተሰጠኝም ማለታቸውን ነው።
የተክለ ፃድቅ መኩሪያ መጽሐፍ ላይ እንደተመለከተው፣ ‹‹…ልዑል ራስ ካሳ የልዑል መርድ አዝማች አስፋው ወሰንን ሠርግ ለማክበር ወደአዲስ አበባ በመጡበት ሰዓት በ1924 ዓ.ም. በግንቦት ወር አቤቶ ኢያሱ ከልዑል ራስ ኃይሉ በተላከላቸው ገንዘብ ጠባቂዎቻቸውን አባብለው ከእስር ቤት አመለጡ።…›› (ገጽ 192 – 200)
የልጅ ኢያሱን ከፍቼ እስር ቤት አመላለጥ አስመልክቶ ጎርሀም ሲ. በኃይለ ሥላሴ ሕይወት ዙሪያ ባሳተመው መጽሐፍ አንድ ‹ታሪክ አቅርቦ ነበር፤ እንደ ጎርሀም ገለፃ ከሆነ ልጅ ኢያሱ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ወዲያ በአንገታቸው ዙሪያ የወርቅ ሰንሰለት ታስሮ ወደ ጋራ ሙለታ ተራራ አጠገብ ገራዋ እስር ቤት ተወረወሩ። በዚያም የኃይለ ሥላሴ የአካባቢው ታማኝ ሰዎች ጥብቅ ቁጥጥር ሥር ወደቁ። በዚህ እስር ቤት ሁኔታዎች የከፉ እንጂ እንደፍቼው ተድላና ምቾት አልነበሩም። ይሁንና አንዳንድ ጸሐፍት እንዳስቀመጡት ሴቶች በእስር ቤቱ እየመጡ ይጎበኟቸው ነበር።
በዚህም የተነሳ ራስ ኃይሉ በክህደት ወንጀል ተከሰው ሞት ቢፈረድባቸውም፣ ንጉሡ ቅጣቱን ወደ ዕድሜ ልክ እስራት ቀይረውላቸው ዋና ዋና ሀብታቸውም እንዲወረስ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የልጅ ኢያሱ ሞት
የልጅ ኢያሱ አሟሟትና የቀብር ቦታ እስካሁንም ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነና በተለያዩ መላምቶች የተሞላ ነው። በተፈጥሮ ነው ሕይወታቸው ያለፈው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ተመርዞ፣ ታንቆ ወዘተ. ነው የሞተው የሚሉም በርካቶች ናቸው። ማርክ አር. ሊፕስቹትዝና አር. ኬንት ራስሙሰን የተባሉ ጸሐፊያን ‹‹Dictionary of African Historical Biography›› (1989) በተሰኘው መጽሐፋቸው የልጅ ኢያሱን የሞት መንስኤ ከታይፎይድ ጋር ያያይዙታል። ጎርሀም የተባለው ጸሐፊ ደግሞ ልጅ ኢያሱ በ37 ዓመታቸው ቀውሰው እንደሞቱ ያስረዳል። ልጅ ኢያሱ ልክ የዛሬ 80 አመት ህዳር 12 ቀን 1928 ህይወታቸው አለፈች።
ለልጅ ኢያሱ በዘመናቸው ከተገጠሙላቸው ግጥሞች መካከል …
ወዴት ነው ያለኸው ኢያሱ አባ ጤና፣
ችጋር ሊገድለን ነው እባክህ ቶሎ ና። (በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ የአስተዳደር ዘመን ረሀብ ተከስቶባቸው የነበሩ አካባቢዎች ሰዎች የገጠሙት)
…
መቅደላ አፋፉ ላይ ያስካካል ፈረሱ፣
የዘጠኝ ንጉሥ ልጅ አስረኛው እሱ፣
እንኳን ሴቶቹና ወንዶቹ ቢነግሱ፣
አልጋውን አይለቅም አባጤና ኢያሱ። (ልጅ ኢያሱ ዙፋናቸውን ለማስመለስ መቅደላ ላይ ከማዕከላዊው መንግሥት ጦር ጋር በተዋጉበት ጊዜ የተገጠመ ነው።) (ማጣቀሻዎች፡- አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ ድሬቲዩብ፣ ልዑል ዐምደፅዮን ሠርፀድንግል ድረገጽ…)
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 27/2012
ፍሬው አበበ