መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የስጋ ደዌ በሽታ በአብዛኛው ቆዳንና የነርቭ ህዋሳትን ያጠቃል፤ የህመሙ መንስኤም ማይኮባክቴሪያ ሌፕሬ (Mycobacteria leprae) የተባለ ባክቴሪያ ዝርያ ነው። ባክቴሪያው የበሽታው መሰንኤ መሆኑም እኤአ በ1873 በኖርዌይ ተወላጁ ጌርሃርድ አርማወር ሃንሰን መታወቁን መረጃው ይጠቁማል። የበሽታው አምጪ ተህዋስ ቢታወቅም፣ በሳይንሳዊ ፍኖት ዘመናዊ መድኃኒት የተገኘለት ግን እ.ኤ.አ በ1941 በአሜሪካዊው ባይ ፈጌት ነው።
በሽታ አምጪ ተህዋሱ ደካማና ለመረባት የሚወስደው ጊዜም ረጅም ነው፤ በተህዋሱ በተጠቃ ሰው ውስጥ ምንም ዓይነት ምልክት ሳያሳይ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ሊቆይ እንደሚችል መረጃዎች ጠቁመው፣ ባክቴሪያው በ100 ሰዎች ቢገባ አምስቱ ብቻ ሊጠቁ እንደሚችሉ፣ 95ቱ የመከላከል አቅም እንዳላቸው ያመለክታሉ።
በሁሉም የኑሮ ደረጃና የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንዶችንና ሴቶችን ሊያጠቃ ይችላል። ለህመሙ የሚያጋልጡትና መተላለፊያዎቹ ድህነት እና በስጋ ደዌ ታሞ ካልታከመ ሰው ጋር አየር በበቂ ሁኔታ በማይዘዋወርበት ቤት ተፋፍጎ መኖር ናቸው። ይህም ያልታከሙ ህሙማን ባሉበት ክፍል አየሩ እንዲታመቅና ባክቴሪያው በአንድ አካባቢ ለረጅም ጊዜ ተከማችቶ ለስጋደዌ ህመም ያጋልጣል።
የስጋ ደዌ ታማሚ መሆኑ ከተረጋገጠ ሁለት ወይም ሦስት ፀረ ተህዋስ (ባክቴሪያ) እንደ በሽታው ዓይነት ለስድስት ወርና ለአንድ ዓመት ይሰጣል። መከላከያው የታመመውን ሰው ተገቢውን ህክምና እንዲያገኝ እና ህፃናት ክትባት እንዲከተቡ ማድረግ ነው።
በኢትዮጵያ የስጋ ደዌ ዘመናዊ ህክምና የተጀመረው በ1942 ዓ.ም በዘነበወርቅ ህክምና ማዕከል ነው። ማዕከሉም ከ30 ዓመት በኋላ አድማሱን አስፍቶ ወደ መላው አፍሪካ የስጋ ደዌ ትምህርትና ህክምና ማዕከልነት (አለርት) አድጓል። የበሽታው ስርጭትም ከ10ሺ ህዝብ 0.4 የደረሰ ሲሆን፣ አንድ ሀገር የስጋ ደዌን አጥፍታለች ተብሎ የሚታመነው ደግሞ ከ10ሺ ህዝብ 1.0 የሚለውን ግብ ሲያሳካ ነው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ይህን ግብ ማሳካቱዋን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ከግንዛቤ አኳያም ከፊቱ አኳያ ሲታይ ለውጦች መታየታቸውም ይገለጻል። የአዲስ አበባ ስጋ ደዌ አካል ጉዳተኞች ተጠቂዎች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ከበደ አዲስ ከ30 ዓመት በፊት ኅብረተሰቡ ለስጋ ደዌ ተጠቂዎች የነበረውን ግንዛቤና አመለካከት ከአሁኑ ጋር በማነጻጸር የሰማይና የምድር ያህል ይለያያል ይላሉ። ታክሲና አውቶብስ ለመሳፈር ትራንስፖርት ለመጠቀም ይቸገሩ እንደነበርም በማስታወስ፣ አሽከርካሪዎችም ለማሳፈር ደስተኛ እንዳልነበሩ ይናገራሉ። እሳቸውም በአዲስ አበባ የተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት ሲማሩ ተማሪዎች ሲያደርሱባቸው በነበረው ማግለል ሳቢያ ትምህርታቸውን ከጓደኞቻቸው ጋር ማቋረጣቸውንም ያብራራሉ። አሁን ግን እነዚህ ችግሮች እንደሌሉም ነው ያመለከቱት።
አቶ ከበደ አሁንም ግን አንዳንድ ክፍተቶች እንዳሉ ይጠቁማሉ። የስጋ ደዌ አካል ጉዳተኞች ተምረው ሥራ ለመቀጠር እንደሚቸገሩ ጠቅሰው፣ የዜጎች እኩልነትን ለማረጋገጥ የፍትህ አካላት የተጠቂዎቹን መብት ለማስጠበቅ መሥራት፣ ጤና ሚኒስቴርም የስጋ ደዌን ጉዳይ በፖሊሲው ማካተት አለበት ይላሉ። ተጠቂዎቹ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳይፈፀምባቸው እንዲሁም ትምህርትና ሥራ ቅጥር ላይ ትኩረት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ።
በአለርት ሆስፒታል የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ባለሙያ ዶክተር አታክልቲ ባራኪ፣ ሰዎች በስጋ ደዌ የሚጠቁት ተህዋሱ ካለባቸውና ተገቢውን ህክምና በወቅቱ ካልወሰደ ሰው ጋር ለረጅም ጊዜ አብረው ከኖሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ ታማሚዎች ህክምና ከጀመሩና ታክመው ከዳኑ ወደ ጤነኛ ሰው ሊተላለፍ አይችልም ይላሉ።
እንደ ዶክተር አታክልቲ ገለጻ፤ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች በቶሎ ህክምና ካላገኙ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል። ይህም በዋናነት ቆዳንና እና ነርቭን በማጥቃት የሚመጣ ነው። በተለይም የተጠቃው ነርቭ አካባቢ የሚኖረውን ክፍል ስሜት አልባ በማድረግ ለተለያዩ ጉዳቶች ይዳርጋል። ሰውነታቸው ላብ ወይም ወዝ እንዳይኖረው፣ ቆዳም እንዲደርቅና እንዲሰነጣጠቅ ያደርጋል። በዚህም ታማሚዎች በእጃቸው፣ በእግራቸውና በዓይናቸውና በፊታቸው በአፍንጫቸው ላይ የተለያየ ጉዳት ያደርስባቸዋል። ቆዳ ላይ ነጣ ነጣ ብለው የሚታዩ ስሜት አልባ ምልክቶች፣ በፊትና በጆሮ ላይ ብጉር መሳይ ጉብታዎች፣ የእጅና እግር መደንዘዝና ስሜት አልባ ቁስል፣ ቆዳን የማቃጠል ስሜት ምልክቶቹ ሲሆኑ ቶሎ ህክምና ካልተደረገም የከፋ አካል ጉዳት ያስከትላል።
ተገቢውን ህክምና መውሰድ ከተቻለ መዳን እንደሚቻል የሚናገሩት ዶክተር አታክልቲ፣ ሰዎች ተመርምረው በቶሎ መድኃኒቱን ከወሰዱ በአካል ላይ የሚደርሰው ጉዳት ሳይከሰት መከላከል እንደሚቻሉ ይገልጻሉ። አዳዲስ የመከላከያ ዘዴዎች በመምጣታቸው የስጋ ደዌን ብዙ ሀገሮች በማጥፋት ከስጋ ደዌ ጉዳትና ስጋት ነፃ የሆነ ርቀት ላይ ደርሰዋል ሲሉ ያመለክታሉ።
በጤና ሚኒስቴር የቲቢና ስጋ ደዌ መከላከልና መቆጣጠር አስተባባሪ አቶ ታዬ ለታ እንዳሉት፤ የስጋ ደዌ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ በሚገኝባቸው 93 ወረዳዎች በሁሉም ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች አገልግሎቱ ይሰጣል፤ መድኃኒቶቹም በነፃ ነው ለህሙማኑ የሚሰጡት።
ዝቅተኛ የስጋ ደዌ ጫና አለባቸው ተብሎ በሚታመንባቸውና በዓመት ውስጥ አንድ ኬዝ በሚገኝባቸው ቦታዎች በወረዳው ውስጥ አንድ ጤና ድርጅት መድኃኒቱ ተቀምጦ በዙሪያው ያሉ አራትና አምስት ጤና ጣቢያዎች ከጤና ድርጅቱ እንዲወስዱ እንደሚደረግ በአጠቃላይ በሁሉም ማዕከላት አገልግሎቱ እንደሚሰጥ ያብራራሉ።
ቤተሰብ በታማሚ የደረሰው ችግር የጋራ ነው ብሎ ያለ ድካምና መሰልቸት መንከባከብ ማኅበረሰቡም በስጋ ደዌ የተጠቃን ሰው መርዳት ሰብአዊ ውዴታና ግዴታ መሆኑን በመረዳት ለተጎጂዎችና ቤተሰባቸው ሁሉ ፍቅርና አክብሮት ማሳየት በተጨማሪም ተጠቂዎች ከደረሰባቸው ችግር እንዲወጡ ማገዝ እንጂ አድሏዊ አለመሆንና አለማግለል ይገባል። ኅብረተሰቡ ለስጋ ደዌ የተዛባ ያለውን አመለካከትን ለመግራት መገናኛ ብዙሃን በትኩረት መሥራት ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሚረዳ የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በአጠቃላይ ብሔራዊ ማኅበሩና የእርዳታ ድርጅቶች የመንግሥት አካላት ማኅበረሰቡ የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ለመርዳት መጣር አለባቸው ማግለልና መድልዎን ማስወገድ የተዛባ አመለካከትን መግራት ብሎም ከስጋ ደዌ ጉዳትና ስጋት ነፃ የሆነ ርቀት ላይ ለመድረስ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 26/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ