በጌዲዮ ዞን በዲላ ከተማ ውስጥ ተገኝተናል። አመጣጣችን በዞኑ ውስጥ የሚኖረው ማህበረሰብ በየ ዓመቱ የሚከበረውን የደራሮ አዲስ ዘመን መለወጫ በዓልና ስነ ስርዓት ለመታደም ነበር። ባሳለፍነው ሳምንት እንዳስነበብናችሁም ባህላዊ ዝግጅቱ በልዩ ሁኔታ ተከብሮ አልፏል። በዚህኛው ሳምንት ደግሞ በቆይታችን ወቅት በዲላ ከተማ ውስጥ ዞር ዞር ብለን ከቃረምናቸው አዳዲስ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ወደሆነው ስፍራ በምናብ ወስደን ልናስቃኛችሁ ወደናል። ይህ ስፍራ “ዋለሜ” የሚል ስያሜ ሲኖረው የዲላ ዩኒቨርሲቲ በበላይነት የሚያስተዳድረው የእፅዋት ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ማዓከል ነው።
እጅግ ማራኪ የሆኑ አገር በቀል እፅዋት፣አእዋፋትሠ እንዲሁም የዱር እንስሳት የሚገኙበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ የጌዲዮን ማህበረሰብ ከተፈጥሮ ጋር እንዴት እራሱን አዛምዶ መኖር እንደሚችል በጉልህ የሚያሳይ ስፍራም ሆኖ እናገኘዋለን። ይህን ስፍራ ተዘዋውረን በተመለከትንበት ወቅት የእፅዋት ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ሞነንዳ ይህ ማራኪ ስፍራ የያዛቸውን ተፈጥሯዊ መስህቦ ችከዚህ እንደሚከተለው አስረድተውናል።
በቦታው ተገኝቶ ለሚመለከተው መንፈስ የሚያድስ እና ለእይታ ሳቢ የሆነ መልከአ ምድርን ከመመልከቱ ባለፈ ከከተማው ውክቢያ ለጊዜው ወጥቶ አይምሮውን ማሳረፍና ማደስ ያስችለዋል። ማዕከሉ የተቋቋመው በ2009 ዓ.ም ነው። አራት ዓላማዎችን ታሳቢ አድርጎ አዳዲስ መስህቦችን የማበልፀግና ነባር ተፈጥሮዎችን የመጠበቅ ሥራ ይሠራል።
ከአራቱ ዓላማዎች ውስጥ አንዱ ጥበቃ ሲሆን የእፅዋት ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ማዕከሉ የተፈጥሮ ጥበቃ ያደርጋል። በውስጡ እጅግ በርካታ አገር በቀል እፅዋቶች እና ብርቅዬ እንስሳቶች ይገኙበታል። እነዚህን በተለያየ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የመከላከል ሥራ ይሠራል። ሁለተኛው ደግሞ ተፈጥሮን መሰረት በማድረግ ቦታው የቱሪስት መዳረሺያ እንዲሆን ይሠራል። በዚህም የአካባቢው ማህበረሰብ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል መሰረት በመጣል ላይ ይገኛል። በሦስተኛ ደረጃ ምርምርና ጥናት ይደረጋል። አራተኛው ዓላማው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ማህበረሰቡ በስፍራው በመገኘት በቀጥታ የተግባር ትምህርት የሚያገኙበት እንዲሆን ተደርጎ እንዲዋቀር መደረጉ ነው።
ማዕከሉ ለምን ተመረጠ
ዲላ ዩኒቨርሲቲ ዋና መለያ አረንጓዴ ምድር የሚገልጽ ነው። ይሄ የሆነውም የጌዲዮ ዞን እና አጠቃላይ መልከዓ ምድሩ በልምላሜ የተሞላ በመሆኑ ነው። በዚህ መነሻ ይህን አረንጓዴ ስፍራ የመጠበቅና ይበልጥ የማበልፀጉን ሥራ የመሥራት የተጣለበት ኃላፊነት ከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ነው።
ዋለሜ የእፅዋት ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ማዕከል የሚገኘው ከአራቱ ካምፓሶች ውስጥ ዋነኛው በሆነው ግቢ እና ኦዳያ የሚል ስም በተሰጠው የመማሪያ ግቢ መካከል ነው። አሁን ያለው ስፋት 40 ሄክታር ሲሆን በቀጣይ ከሚረከበው 90 ሄክታር ጋር ተደምሮ 130 ሄክታር ስፋት ይይዛል። ልዩ ተፈጥሯዊ መስህቦችን ከመያዙም በላይ ለእይታ ሳቢ የሆነ መልካ ምድር ያለው ነው። በዚህ መነሻ ስፍራውን የመጠበቅ፣ የማልማት፣ ለቱሪዝም ተመራጭ የማድረግና ለምርምርና ጥናት ማከናወኛ እንዲሆን ተለይቷል። ከዲላ ከተማም የአንድ ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር የቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑ ተመራጭነቱን አጉልቶታል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች ነች። ከዚህ ውስጥ አንዱ የአካባቢው ስነምህዳር ውብ መሆኑና ለመስህብነት ተመራጭ መሆኑ ነው። በተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎችም ይህንኑ እውነት ስንገልፅና ስናወድስ ኖረናል። ሆኖም ግን ይህን ፀጋ ይበልጥ ከማልማት፣ ከማስተዋወቅ እንዲሁም ከመጠበቅ አንፃር ድክመት ይታያል። ይህንን ለመቀየር ደግሞ መሰል ማዕከሎችን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የጌዲዮ ዞን አስተዳደር የተረዳው ይመስላል።
የጌዲዮ ዞን ዋንኛው ውበት በስምጥ ሸለቆ ከሚገኙ ስፍራዎች ማራኪ መልካ ምድር ያለው መሆኑ ነው። ለዚህም ነው ማዕከሉ በዚሁ በዋለሜ እንዲሆን ሃሳቡን መጠንሰስ ያስፈለገው። በተለይ በስፍራው በርካታ ተራሮች እና ለአይን ሳቢ ገደላ ገደሎች ከእፅዋቱ ጋር ተዛምደው ልዩ ገፅታ አላብሰውታል። የአእዋፋቱ ዝማሬና የዱር እንስሳቱ መገኘት ሲጨመርበት ደግሞ ቀልብን ከመያዝ አልፎ ልዩ የሆነ ስሜት የመፍጠር አቅም አላብሶታል። እነዚህን ጥምር ውበቶች መንከባከብ እና መጠበቅ ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ምን እየተሠራ ነው?
በመግቢያችን ላይ ለማንሳት እንደሞከርነው የዋለኔ የእፅዋትና የኢኮ ቱሪዝም ማዕከል አራት ዓላማዎችን ሰንቆ ሥራዎቹን እየተገበረ ነው። ከዚህ ውስጥ በልዩ መልኩ የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች እና መሰል አካላት ከማዕከሉ ውጪ ባለው የጌዲዮ ዞን እና አጎራባች ዞኖች በመዘዋወር ሊጠፉ የተቃረቡ እፅዋትን በመሰብሰብ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ ሌላ በዚያው ስፍራ ላይ የሚገኙትን እፅዋት፣ አእዋፋት እና ሌሎች የዱር እንስሳቶችን በልዩ ሁኔታ ለመለየትና ጥበቃ ለማድረግ ጥናቶች እየተሰተሩ ነው። ይህን ለማገዝ ደግሞ የላብራቶሪ ማዕከል የማደራጀት እቅዶች አሉ።
ከዚህ በተለየ መልኩ መስህቡ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ሳይለቅ ለመዝናኛነት እንዲውል ተጨማሪ የማልማት እና ለጎብኚዎች ክፍት የማድረግ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። በዚህ ምክንያትባህላዊ የሠርግ ስነስርዓቶች እንዲከወኑበት እና የተለያዩ ዝግጅቶች እንዲደረጉበት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ተችሏል። ይህም በዞኑ ውስጥ እና ከዞኑ ውጪ ያሉ ሁሉም ማህበረሰቦች በባህላዊ መንገድ የተፈጥሮ አጠባበቅንና መስህብን እየቃኘ የደስታ ጊዜውን እንዲያደርግ ልዩ አማራጭ የሚሰጥ ነው። ልዩ ድባብ ለመፍጠርም ባህላዊ ጎጆዎች ከመሠራታቸውም በላይ አዳራሾችም እየተገነቡ ነው። ከዚህ ሌላ የጉዞ ስፍራዎችና ተንጠልጣይ ልዩ ድልድይም ለመሥራት እቅድ መያዙን ሰምተናል። በረጅም ጊዜ እቅዳቸውም ባህላዊ ሎጅ የመገንባትና ዓለም አቀፍ ይዘቱን የጠበቀ የምግብ አዳራሽ የመሥራት ዓላማን ሰንቀዋል።
ጎብኚዎች ምን ያገኛሉ
ከአገር ውስጥና ከመላው ዓለም ለቱሪዝም የሚመጡ ጎብኚዎች በዚህ ስፍራ ምን የተለየ ነገር ያገኛሉ የሚለው ዋንኛው ነው። ማዕከሉም ይህን ታሳቢ ያደረገ ይመስላል። ጌዲዮ በአግሮ ፎረስትሪ በተለይም ከይርጋ ጨፌ የተፈጥሮ ቡና ጋር የተያያዘ እምቅ ሀብት ያለው መሆኑ ይታወቃል። ማህበረሰቡም ተፈጥሮን በባህላዊ መንገድ የመጠበቅ ልምዱ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። በቀላሉ ይህን ስጦታ አጉልቶ በማሳየት ከመላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎችን መሳብ ይቻላል።
ከዚህ ባሻገር ዞኑ የልዩ ልዩ ቅርሶች መገኛ ነው። በተለይ የትክል ድንጋይ ከመላው ምሥራቅ አፍሪካ በላይ በብዛት የሚገኝበት ነው። ከዚህ ባለፈ በድንጋይ ላይ የተቀረፁ ስእሎችም ባለቤት ነው። ይህን ለማስተዋወቅ ደግሞ በማዕከሉ ሙዚየም ለመገንባት እንቅስቃሴ መኖሩን ለማወቅ ችለናል። ስፍራው የጌዲዮ ዞንን ብቻ ሳይሆን ሲዳማን እና ጉጂ ዞኖችን የሚያገናኝ ከመሆኑ አኳያ የነዚህን ማህበረሰቦች ባህል እና ተፈጥሯዊ ስፍራዎችን እንዲይዝ እንደሚደረግም ተገንዝበናል። ይህም የኢትዮጵያ ባህላዊ የቤት አሠራር እንዲሁም አልባሳትን ከመስህቡ ጋር አዛምዶ እንዲይዝ ያስችለዋል። በዚህ መልክ እንዲዋቀር መደረጉም የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር የማድረግ አቅሙ ከፍ ያለ ነው።
የማዕከሉ መቀነት
በዚህ ማዕከል ውስጥ ተጨማሪ መስህብ የሆነው ተፈጥሮ እንደመቀነት ከቦት ቁልቁል የሚፈሱት ረጅም ሦስት ወንዝ ናቸው። በተለይ እነዚህን ወንዞች ከከፍታ ላይ መመልከቱ ማራኪነቱን ይጨምራል። ከድንጋዮቹ ጋር ተጋጭተው የሚያወጡት ዜማም ለጆሮ ምግብ ነው። ከወፎቹ ዝማሬና ዛፎቹ ከንፋሱ ጋር እያወጉ ከሚያወጡት ድምፅ ጋር ስሜትን ጨምድዶ የመያዝ ኃይሉ መንፈስን ያድሳል።
ሦስቱ ወንዞች እና ሁለቱ ምንጮቹ ተደምረው የአባያ ሀይቅን ይገብራሉ። መነሻው ሳላን ወንዝ ሲሆን ሲዳማን እና ጌዲዮን የሚለየው ለገራራ ወንዝ እንዲሁም መጀጌ ወንዝ ኦሮሚያንና ጌዲዮን አዋስነው ቁልቁል እየነጎዱ መዳረሻቸውን አባያ ያደርጋሉ። በዚያ ከመድረሳቸው አስቀድሞ ደግሞ ጊዳዎ ግድብን በማልማት ውለታ ሠርተው የሚያልፉ ናቸው።
ሦስት ምንጮችም በዚሁ ማዕከል ላይ ማግኘት ይቻላል። ምንጮቹ የተፈጥሮ ፍል ውሃ ናቸው። ይህን የተፈጥሮ ዕድል በመጠቀምም ማዕከሉ የተለያዩ የመዋኛ ገንዳዎችን የመገንባት እና ለጎብኚዎች ተጨማሪ አገልግሎት የመስጠት ትልም ሰንቋል።
የማዕከሉ አጋዦች
ማዕከሉ በሚገኝበት አካባቢ በርካታ ነዋሪዎች ይገኛሉ። የተፈጥሮ ስፍራውን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ የማልማትና የመጠበቅ ቁርጠኝነት አላቸው። ይህ ፍላጎታቸው አሁን የመጣ ሳይሆን በረጅም ዘመናት ውስጥ የተቆራኛቸው ማንነታቸውና ባህላቸው ነው። ህይወት እና ልምድም በርካታ እውቀቶችን አስጨብጧቸዋል። ይሄን ልምድም ለዩኒቨርሲቲው ተራማሪዎችና የበላይ ጠባቂዎች ለማሸጋገር ፍላጎት አላቸው። እነርሱም ሳይንሳዊ ዘዴዎችን በተቃራኒው በመገንዘብ ስፍራውን የመጠበቅ ቁርጠኝነት አላቸው።
የማዕከሉ ማነቆዎች
ይህን ስፍራ ለማልማት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋል። ሆኖም በልዩ ሁኔታ ማዕከሉን ለመንከባከብ፣ባህላዊ የተፈጥሮ ጥበቃውን ለማስቀጠል እንዲሁም ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን በስፋት ለመሥራት የፋይናንስ አቅም እንደማነቆ ይታያል።
በተለይ መደበኛ በጀት አለመያዙ ማዕከሉ በሚፈልገው መንገድ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎታል። ይህን እንቅፋት መቅረፍ ቢቻል ለአካባቢው ማህበረሰብና ለዩኒቨርሲቲው ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭና ኩራት መሆን የሚችል ነው።
ሌላው ከፋይናንሱ ጋር በተያያዘ የሥራ መከወኛ ቁሶች ችግርም አለበት። በተለይ ዋንኛ ችግሩ የመጓጓዣ ነው። ሠራተኞቹ በዚህ ምክንያት እንደልባቸው እየተንቀሳቀሱ ሥራቸውን እንዳይከውኑ እንቅፋት ገጥሟቸዋል። በተጨማሪም ከማዕከሉ ስፋት አንፃር የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮችም ይጠቀሳሉ። እነዚህ መሰናክሎች ማዕከሉ በሚፈልገው ፍጥነት እና እርቀት እንዳይጓዝ የሚገዳደሩት ናቸው። ሆኖም መስህብነቱን እና ያለውን ውብ ተፈጥሯዊ ይዘት የሚያደበዝዙት አይደሉም። ግንጥል ጌጥ እንዳይሆን ግን እነዚህም ቢሆኑ መሟላት ይኖርባቸዋል።
መሰናበቻ
በቆይታችን በዲላ ከተማ ውስጥ ዞር ዞር ብለን ከቃረምናቸው አዳዲስ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሆነውን ስፍራ በምናብ አስቃኝተናችኋል። ዋለሜን የዲላ ዩኒቨርሲቲ በበላይነት የሚያስተዳድረው የእፅዋት ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ማዕከል ይሁን እንጂ የአገር ሀብት እንደሆነም መገንዘብ አስችሎናል። ይህን የምድር ላይ የተፈጥሮ ገነት ሙሉ ለማድረግ በመጨረሻዎቹ ሃሳቦቻችን ላይ የተነሱት መሰናክሎች በዞኑ፣ በክልሉና በፌዴራል መንግሥት ጥረት መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል። ይህ የዝግጅት ክፍላችን ጠንካራ እምነት ነው። ሰላም!!
አዲስ ዘመን ጥር 24/2012
ዳግም ከበደ