በአዲስ አበባ መሬት መቀራመት ትልቅ በሽታ ሆኖ ቆይቷል፡፡ መሬት ለግንባታ በሚል ወስዶ ለዓመታት የማጠር በሽታም የአልሚ ነን ባዮች ስር የሰደደ ደዊ ነው፡፡ አልሚ ነን ባዮቹ መሬት ይዘው ነው ገንዘብ የሚሠሩት፡፡ ገንዘብ ይዘው አይደለም መሬቱን የሚይዙት፡፡
ቦታዎቹ ባለመልማታቸው ሳቢያ ለአልሚዎቹ እና ለከተማዋ ያስገኙት የነበረው ጥቅም ቀርቷል፡፡ እንደሚታወቀው በከተማ መሬት ወደ ልማት ሲገባ በቅድሚያ ተጠቃሚ የሚሆኑት ባለሀብቶች አይደሉም፡፡ ከተሞች፣ የቀን ሠራተኞች፣ የግንባታ ተቋራጮችና ሌሎች ባለሙያዎች እንዲሁም ግንባታው በሚካሄድበት አካባቢ የሚገኘው ህዝብ ነው ተጠቃሚ የሚሆነው፡፡ ቦታዎቹ ወደ ልማት ባለመግባታቸው ሳቢያ እነዚህ ወገኖች ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡
ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ባለቤቶቻቸው፣ ተከራዮች፣ መንግሥት ተቀጥረው የሚሠሩ ወገኖች ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ አካባቢው በከፍተኛ ደረጃ እየተነቃቃ ስለሚመጣም ተጠቃሚው እየበዛ ይመጣል፡፡ ግንባታው ባለመካሄዱ የተነሳ ግን ይህ ሁሉ ቀርቷል፡፡
አብዛኞቹ ቦታዎች በመልሶ ልማት የተገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ከነዋሪዎች እንዲጸዱ ከተደረጉ በኋላ ከመታጠር ውጪ እንዲገነቡ አልተደረገም፡፡ በዚህ የተነሳም በፍርስራሽ የተሞሉ፣ በእዚህ ላይ የተለያዩ ተክሎች ስለበቀሉባ ቸውም ዳዋ ለብሰው ነው የቆዩት። ነዋሪዎችና መንገደኞች ቆሻሻ መጠያ ፣መጸዳጃ አድርገዋቸው ኖረዋል፡፡ እንደ ውሻ ያሉ የሞቱ እንስሳት መጣያ፣ በአካባቢው ማንም ዝር የማይል በመሆኑ በአጋጣሚ የሚተላለፉ ወገኖች የዘራፊዎች እና የወንጀለኞች ሲሳይ ሆነውባቸው ቆይተዋል፡፡ ከአካባቢዎቹ የሚወጣው መጥፎ ጠረን አላፊ አግዳሚውን የማያሳልፍ እና የጤና ጠንቅ ነበር፡፡
ቦታዎቹ ሳይለሙ ታጥረው ብቻ የመቆየታቸው ችግር በእዚህ አያበቃም፡፡ የከተማዋ ገጽታም ቢሆን ተባላሽቷል፡፡ በቦታዎቹ ላይ የነበሩ የደከሙ ግንባታዎች መነሳታቸው ጥሩ ነገር ሆኖ ሳለ ቦታዎቹ ቶሎ ወደ አልሚዎች ሲተላለፉ አይስተዋልም። ከተላለፉም በኋላ ግንባታቸው ቶሎ ሲጀመርም አይታይም፡፡ በእዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ አጥራቸው ከሁለት ጊዜ በላይ እስከመታደስ የሚዘልቁ ቦታዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ አጥራቸው ሲፈራርስ ገበናቸው እየተጋለጠ የከተማዋን ገጽታ እያበላሹ ቆይተዋል፡፡
የቦታዎቹ ከአልሚዎቹ መወሰድ ይህን ሁሉ ችግር እየፈታው መጥቷል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በቅድሚያ ከወጣቶች ጋር በመከረበት ወቅት ቦታዎቹ በጊዜያዊነት ወደ ሥራ እንዲገቡ የቀረበው ጥያቄ ምላሽ እያገኘ መጥቷል፡፡ አስተዳደሩ በቦታዎቹ ላይ ሰፍረው የነበሩ ንብረቶችና አጥሮች ጭምር መነሳታቸው የከተማ አስተዳደሩ ምን ያህል ቁርጠኛ አቋም እንደያዘ ማረጋገጫ ነው፡፡ ቦታዎቹን ለመጥረግ ፣ለመደልደልና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውሉ ያደረገበት ፍጥነትም አድናቆት ሊቸረው የሚገባው ተግባር ነው፡፡
አንዳንዶቹ ቦታዎች ለከተማዋ ለሚያስፈልጉ ሥራዎች እንደሚወሉም እየተጠቆመ ነው፡፡ ይህ ዕርምጃም ከተማዋ ባለፉት አስተዳደሮች ትኩረት ተነፍገው የነበሩ ለከተማዋ አስፈላጊ የሆኑ የመዝናኛ መሠረተ ልማቶች፣ የመኪና ፓርኪንግ ስፍራዎች ትኩረት መስጠት የሚያስችል ሁኔታ እንዲፈጠር እያደረጉም ይገኛሉ፡፡ ሸራተን አዲስ ፊት ለፊት የታጠረው ቦታ ለአረንጓዴ ስፍራነት እንዲውል ይደረጋል የተባለውም ለእዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ይህም ከተማ የተጠማችውን የአረንጓዴ ስፍራ እንድታገኝ ያስችላል፡፡
በቦታዎቹ ላይ የሚፈለገው ግንባታ እስከሚደረግ ድረስ ቦታዎቹ ለአንዳንድ አስፈላጊ ሥራዎች በጊዜያዊነት እንዲውሉ መደረጉም ሌላው ብልህነት የተሞላበት ሥራ ነው፡፡ ይህ ተግባር የሚፈታው ችግር በርካታ መሆኑን ቦታዎቹ የቆዩባቸው እነዚህ አጠቃላይ ሁኔታዎች ያስገነዝባሉ፡፡
በርካታ ቦታዎች እንዲጸዱ እና በሚገባ እንዲደለደሉ እየተደረገ ወጣቶች ለፓርኪንግ አገልግሎት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በዚህም በቦሌ፣ በካዛንችስ፣ በሜክሲኮ፣ ሰንጋ ተራ በፊት በር ወዘተ አካባቢ በርካታ ቦታዎች ለፓርኪንግ አገልግሎት እየዋሉ ናቸው፡፡
ቦታዎቹን ወጣቶች እየተደራጁ የፓርኪንግ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ያለበት ሁኔታ በከተማዋ የተንሰራፋውን የወጣቶች ሥራ አጥነት ለመፍታት የራሱ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ቦታዎቹ በርካታና ሰፋፊ መሆናቸው እንዲሁም በከተማዋ እምብርት እንደመገኘታቸው በርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ያስችላሉ፡፡
ይህ ሥራ በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፍ እንደማለትም ነው፡፡ እንደ ተባለው ወጣቶች ተጠቃሚ እየሆኑ ሲሆን፣በቦታዎቹ ላይ መኪናቸውን የሚያቆሙ ወገኖችን ብዛት ስንመለከት ደግሞ በከተማዋ ምን ያህል የመኪና ቦታ ማቆሚያ እጥረት እንደነበረ ያሳያል፡፡
የፓርኪንክ ሥራው ምን ያህል የወጣቶችን፣ የአሽከርካሪዎችን እንዲሁም በየአካባቢው የሚገኙ የዋና ዋና እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ችግር እንደፈታ መረዳት አያዳግትም፡፡ አሽከርካሪዎች ደህንነቱ ባልተጠበቀ ስፍራ በማቆም ሳቢያ ይደርስባቸው የነበረውን የመኪና ዕቃና የመሳሰሉት ስርቆትም ያስቀራል ፡፡
በተለይ በቦሌ ዓለም ሕንፃ አካባቢ ከሳውዲ አረቢያ ኤምባሲ ላይ በተወሰደው ቦታ ላይ የተዘጋጀው የመኪና ማቆሚያ ቦታ እያስተናገደ የሚገኘው መኪና ብዛት አካባቢው ምን ያህል በመኪና ማቆሚያ እጥረት ውስጥ እንደነበር ያስገነዝባል፡፡
በቦሌ መንገድ መኪና አቁሞ መሄድ የማይቻል በመሆኑ ባለመኪናዎች መኪናቸውን በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለማቆም ይገደዳሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ በጣም ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ በየሕንፃዎች ስር ለመኪና ማቆሚያ የተገነቡት በአብዛኛው ሥራ ላይ ያልዋሉ እንደመሆናቸው በእዚህ መንገድ የመኪና ማቆሚያ ችግር ከፍተኛ ነው፡፡ በቦታዎቹ ላይ ለወጣቶች የተዘጋጁት የመኪና ማቆሚያ ለአካባቢው ትልቅ እፎይታ ሰጥቷል፡፡
በዚህ ጎዳና ላይ ለፓርኪንግ አገልግሎት በሚል የሚገነባ ሕንፃ የሌለ እንደመሆኑ ችግሩ በቀጣይም አሳሳቢ ነው፡፡ እዚያው ድረስ ግን ክፍት ቦታዎችን ለመጠቀም የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሊበረታታ ይገባል፡፡
በከተማዋ በቀጣይም መንገድ ላይ መኪና ማቆም እየተከለከለ የሚሄድ እንደመሆኑ እነዚህን መሰል ቦታዎች በዘላቂነት ለፓርኪንግ አገልግሎት የሚውሉበት ሁኔታ ቢፈጠር ከተማዋ ሕንፃ ስትል ያጣቻቸውን የመኪና ማቆሚያ መሰረተ ልማት እንድታገኝ የሚያስችላትም ይሆናል፡፡
አንዳንዶቹ ቦታዎች ኤግዚቢሽን እየተካሄደ ባቸውም ይገኛል፡፡ በሜክስኮ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው ባዶ ስፍራ በጥቂት ቀናት ውስጥ ተደልድሎ ለፓርኪንግ ዝግጁ ተደርጓል፡፡ ቦታው ለሸገር አውቶቡስ ማቆሚያና ማሳደሪያ እንደሚውል የሚጠበቅ ሲሆን፤ እዚያው ድረስ በሚል ይሆናል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኢግዚቢሽንና ባዛር እየተካሄደበት ነው፡፡ ይህም በአካባቢው የሚካሄዱ ባዛሮች በእግረኞች መንገድ ላይ ያስከትሉ የነበረውን መጨናነቅ የሚያስቀር ከመሆኑም በተጨማሪ ለአደጋ ተጋላጭነታቸውን ያስቀራል፡፡
የቦታዎቹ መጠረግና በሚገባ መደልደል በራሱ በቦታዎቹ ላይ ቆሻሻ እንዳይጣል በማድረግም አካባቢው ንጽህናው እንዲጠበቅ ፣ እያስቻለ ነው፡፡ ቦታዎቹ በፍርስራሽ፣ በግንባታ ተረፈ ምርትና ሌሎች ቆሻሻዎች ክፉኛ የቆሸሹ እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ አሁን ይህ አይታይም፡፡ በሚገባ ተጠርገው ተደልድለዋል፡፡ ይህም በማስተር ፕላኑ መሰረት ግንባታው እስከሚጀመር ድረስ በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንዲቆዩ መደረጉ ለከተማዋ ገጽታም ቢሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡
በቀጣይ ደግሞ ልጆች ኳስ እንዲጫወቱባቸው በማድረግም የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች እጥረትን መፍታትም ይገባል፡፡ ከተማዋ የመኪና ማቆሚያ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልጋት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም ናቸው፡፡ ይህም በየሰፈሩ ለስፖርት ማዘውተሪያ ሲውሉ የነበሩ ቦታዎች በሙሉ በካርታ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው በመሆኑ ብቻ ለሕንፃ መገንቢያ እንዲውሉ በመደረጉ ወጣቶች ራሳቸውን የሚያፍታቱባቸው የማዘውተሪያ ስፍራዎች አጥተዋል እየተባለ ቅሬታ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
አሁንም ከባለሀብቶቹ ከተወሰዱት ቦታዎች ውስጥ የተወሰኑትን ለስፖርት ማዘውተሪያነት በጊዜያዊነት እንዲውሉ ማድረግ ይገባል፡፡ የሚመለከታቸው አካላትም ይሁኑ ወጣቶች ቦታዎቹን ለስፖርት ማዘውተሪያነት በሚል ቢጠይቁ ማን ያውቃል ሊያገኙ ይችላሉና መጠየቁ መልካም ነው፡፡ አንድ እናት ልጃቸውን መልዕክት አድርስ እያሉ ሁሌም ይጠይቁታል፤ እሱ ግን መልዕክቱ እየቀለለበት ይሁን በፍራቻ ለማድረስ እንደማይችል ይገልጽላቸዋል፡፡ እሳቸው ግን ልጄ መልዕክተኛ አጼ ቤት ይገባል እባክህን እያሉ ያስገነዘቡት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ወጣቶች ግድ የላችሁም ጥያቄያችሁን ለሚመለከተው አካል ሰብሰብ ብላችሁ /እየተደራጃችሁ/አቅርቡ፡፡
እንዲያውም ልክ እንደ ሸራተን ፊት ለፊቱ ቦታ አንዳንዶቹን ቦታዎች ለእዚህ አገልግሎት እንዲውሉ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ስፖርቱን የሚመሩ አካላትም ይህ እንዲሆን ጥያቄ ማቅረብ የሚችሉበት ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ለእዚህ አገልግሎት ቢውሉ ብለው የሚያስቧቸውን ቦታዎች ቢጠይቁ መልካም ይሆናል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችን ወደ ሥራ እንዳሰማራ ሁሉ መደገፍና ለጥሪት ማብቃት ይጠበቅበታል፡፡ ቦታዎቹ ለሥራ ሲፈለጉ ማስለቀቅም ሊኖር እንደሚችል ማስገንዘብ እስከዚያው ድረስ ግን ሀብት እንዲያፈሩና ሌላ ሥራ እንዲዘጋጁ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
አሁን በፓርኪንግ አገልግሎት የተሰማሩት ወጣቶች በቀጣይም ከዚህ በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን ከመደጎም አልፈው ጥሪት እንዲያፈሩ በማድረግ በፓርኪንግ ሥራም ይሁን በሌላ የሚሰማሩበትን ሁኔታም አያይዞ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ወጣቶቹ እንዲቆጥቡ ማድረግ ይገባል፡፡ ሥራው ዘላቂ እንዳልሆነ በማስገንዘብም ለሌላ ሥራ ራሳቸውን እያዘጋጁ እንዲቆዩ ማድረግም ይኖርበታል፡፡
አሁን ቦታዎቹ በጊዜያዊነት ሥራ ላይ እንዲውሉ እየተደረገበት ያለው ሁኔታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በባለሀብቶችና በመንግሥት ተቋማት ጭምር ለልማት በሚለው ተወሰደው ለዓመታት ታጥረው የቆዩ ቦታዎችን ለመውሰድ ሲንቀሳቀስ ያስተዋሉ አንድ ፀሐፊ በእዚህ ገጽ ላይ በአንድ ወቅት ‹‹ካላየሁ አላምንም›› በሚል የጻፉት አጀንዳ ታወሰኝ፡፡
ፀሐፊው የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ባለሀብቶች በተደጋጋሚ ሲያስፈራራ አስተውለዋል፤ዕርምጃ ለመውሰድ የተንቀሳቀሰባቸው አጋጣሚዎች እንደነበሩም በማስታወስ ዕርምጃ የተወሰደባቸው ቦታዎች ግን ለባለሀብቶቹ መመለሳቸውን በመጥቀስ አስተዳደሩ በቅርቡ እወስዳለሁ ያለውና እየወሰደ የሚገኘው ዕርምጃ በተጨባጭ ልማት ካልተረጋገጠ አላምንም ብለው ነበር፡፡
አሁን በጊዜያዊነትም ቢሆን ቦታዎቹ እንዲለሙ እየተደረገ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ቦታዎችም ለታላቅ አገልግሎት እንደሚውሉ እየተገለጸ ነው፡፡ የሸራተን አካባቢ ቦታ ለአረንጓዴ ስፍራ ታስቧል፡፡ የዋቢ ሸበሌ አጠገቡ ቦታ ደግሞ ለትራፊክ ማኔጀመንት መስሪያ ቤት ሕንፃ መስሪያ ታስቧል፡፡ ይህም ካለየሁ አላምንም ያሉት ፀሐፊ ‹‹ማመን ጀመርኩ፤ እንዲሉ ያስችላ ቸዋል፡፡ በእርግጥም እኔም ማመን ጀመርኩ፡፡ መልካም ልማት ይሁን፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011
በአንተነህ ቸሬ