ለብዙ ሰዎች “ዓላማ” ከቃልነቱ ያለፈ በሕይወት ጉዞአቸው የተገናዘበ ትርጉም የለውም። የአንዳንዶቻችን የሕይወት ጉዞ ከተራራ አናት ላይ እንደተፈነቀለ አለት ከዕለት ወደ ዕለት ቁልቁል የሚምዘገዘግ ሆኖ ይገኛል።
አንዳንዶች ደግሞ እንኖርበታለን ያሉትን ዓላማ እያሳኩ
፤ በጸጋ ላይ ጸጋ እየጨመሩ ኑሮ “አልጋ በአልጋ” ሲሆንላች ይታያል። ዓላማቸው እና ግባቸው አድሮ መገኘት ከሆነው በየምዕራፉ ተግዳሮት
ሲገጥማቸው ጎመን በጤና እያሉ መንገድ ከሚቀያይሩት ባሻገር ለየት ባለ መልኩ ለዓላማቸው የጨከነ ማንነት ያላቸው ጥቂት ሰዎች አሉ።
እንዲህ ያሉት ማድረግ የሚፈልጉትን ከማድረግ የማይቆጠቡ ፤ለተፈጥሮአዊም ሆነ ለሰው ሰራሽ ምክንያቶች ወገቤን የማይሉ ጀግኖች! ናቸው።
በኑሮ ዑደት ውስጥ ደግሞ ይመሻል ይነጋል፤ ክረምት ይሄዳል በጋ ይመጣል። የጊዜን ሂደት ማን ሊገታ ይቻለዋል? በዚህ ሂደት ውስጥ የአንድን ስጋ ለባሽ ሕይወት የሚያስጨንቅ ከቋጥኝ በላይ የከበደ ሸክም ድህነት ይሉት የሰው ጠላት አለ። ድህነት ቢያጎብጣቸውም ሰርክ እጅ ላለመስጠት ከሚፍጨረጨሩና ከድህነት በላይ ነግሰው ለመገኘት የሚታትሩ ሰዎች ጥቂት የዚህች ዓለም ፈርጦች አሉ። ከእነዚህ ጥቂት ፈርጦች ውስጥ ደግሞ ወይዘሮ አስራት አዳሌ ወይም እማማ ገንፎ አንዷ ናቸው።
ወይዘሮ አስራት አዳሌ ወይም እማማ ገንፎ ዘምሞ ሊወድቅ በደረሰው የቀበሌ ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት፤ ሳሪስ በልዩ ስሙ በርበሬ ሰፈር ስድስት አባወራዎች ከሚኖሩበት የቀበሌ ቤቶች ተያይዘው ከተሠሩት እና ከተከፋፈሉት አንዱ ውስጥ ነው የወይዘሮ አስራት አዳሌ “እማማ ገንፎ” መገኛቸው።
ባለ ትልቅ ልብ የሆኑት “እማማ ገንፎ” ሲናገሩ “በደህናው ጊዜ ጉልበቴም ደህና ስለነበር እንጀራ ጋግሮ በመሸጥ ወላጅ አልባ ፣አሳዳጊ የሌላቸውን እንዲሁም የዘመድ ልጆችን ሰብስቤ አሳድግ ነበር ፤” በኋላ ግን ይላሉ “እማማ ገንፎ” “አቅም እያነሰኝ እየደከምኩ ስሄድ የቀድሞውን እንጀራ መጋገሩም ተሳነኝ፤ ታዲያ ቤት ውስጥ ሆኜ ልሰራው የምችለው ስራ ብዬ አስብኩ ፤ አሁን የምስራው ስራ መጣልኝ እጄ ላይ ባለችኝ አንድ መቶ ብር በማትሞላ ጥሪት ስራውን ጀመርኩኝ።”
ገንፎና አጥሚት እየሠሩ በመሸጥ የሚተዳደሩት ወይዘሮ አስራት፣ የሥራ ዘርፋቸው የእሳቸው መጠሪያ ሆኖ ዓመታት አስቆጥሯል። የአካባቢው ነዋሪም ሆነ የሚያውቃቸው እንዲሁም ቤቱ ውስጥ ቁጭ ብለው በሚመገቡት ዘንድ ወይዘሮ አስራት ‹‹እማማ ገንፎ›› በመባል ነው የሚጠሩት።
ከዚህ ከተጨናነቀ ሠፈር የሚኖሩት እማማ ገንፎ፣ ቤታቸው መጥተው ለሚመገቡ ብቻ ሳይሆን፣ በሆስፒታልና ጤና ጣቢያ ተኝተው ለሚታከሙ ደራሽ ናቸው። ሰው የታመመባቸው፣ ሐኪም ቤት አስተኝተው አጥሚት ለመሥራት የተቸገሩ እማማ ገንፎ ጋር ጎራ ብለው ከአጥሚቱ ሆነ ከገንፎ የፍላጎታቸውን ገዝተው ይወጣሉ።
“እማማ ገንፎ” የሚለውን ታፔላ ተከትለን፣ እማማ ገንፎ ቤት ስንደርስ፣ እማማ ገንፎን ያገኘናቸው እንደ ወትሮው ገንፎ እያገነፉ ወይም አጥሚት እያሞቁ አልነበረም። ይልቁንም ያረጀ ሶፋቸው ላይ ጋደም ብለዋል። በዕለቱ አሟቸው ነበር። አቅማቸውን ያሳጣቸውን ድህነት ለመወጣትና ቤተሰቦቻቸውን ለማኖር ሌት ተቀን ደፋ ቀና የሚሉት እማማ ገንፎ፣ በዚህ እድሜያቸው ጎንበስ ቀና ብለው የገንፎና አጥሚት እህል ለማዘጋጀት መታተራቸውና በየጊዜው ወፍጮ ቤት መመላለሳቸው ጉልበታቸውን አሟጦት ለበሽታ እንደዳረጋቸው ይገምታሉ።
የ65 ዓመቷ እማማ ገንፎ እርጅና የተጫጫነውን ፊታቸውን ወደ እኛ መለስ አድርገው ባለቤታቸው ጡረታ ከወጡ በኋላ የቤቱ ቀንበር እሳቸው ላይ እንደተጫነ አጫወቱን። ሌሎች እናቶች እንደሚሠሩት ጠላ፣ እንጀራ፣ ወይም ቆሎ ለመሥራት ቢያስቡም ብዙ አዋጭ እንዳልሆነ በመገመታቸው በሰዎች ዘንድ እምብዛም ያልተለመደውን ገንፎ አገንፍቶ የመሸጥ ሐሳባቸውን ዕውን አድርገው መሥራት ከጀመሩ ሦስት ዓመታት አስቆጥረዋል።
ታዲያ በዚህ ሥራ ከሁለት ዓይነት የገንፎ እህል ያዘጋጃሉ። የቡላና የገብስ ገንፎ። የቡላውን ገንፎ እሳቸው በሚለኩበት ሳህን አንዱን በ50 ብር ይሸጣሉ። የገብስገንፎ ሲሆን ደግሞ አንዱ ሳህን 60 ብር ነው።
ሥራቸው ከቅፅል ስማቸው ውጪ ያተረፈላቸው ነገር እንደሌለ የሚናገሩት እማማ ገንፎ፣ ከቀን ወደ ቀን የበሽታቸው መፈራረቅ ኑሯቸውን ይበልጥ አስቸጋሪና አዳጋች ቢያደርገውም በዚህ ሥራ ራሳቸውን ጨምሮ ስድስት ቤተሰብ እንደሚያስተዳድሩ ይገልጻሉ።
የልጅ ልጃቸው ቦታ እስኪይዝላቸው በሽታቸውን ተቋቁመው እየሠሩ እንደሆነ፣ ሁለት የወንድማቸውን ልጆች፣ ሦስት የልጅ ልጆቻቸውን ማስተማር እሳቸው ትከሻ ላይ መውደቁ ብዙም አላሳሰባቸውም። የእሳቸው ሐሳብ ከቀን ወደ ቀን የጠነከረው ሕመማቸው ከሥራ አግዷቸው የቤተሰቦቻቸው ሆድ ፆም እንዳያድር ነው።
ሥራውን የማስፋት ሕልም እንዳላቸው የሚናገሩት እማማ ገንፎ፣ ከደንበኞቻቸው የሚሰጣቸው አስተያያየት ጥሩ ቢሆንም፣ የቦታው ማነስና የጤናቸው መታወክ በሥራቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ይገልጻሉ። የብዙ እናቶች ተምሳሌት የሆኑት እማማ ገንፎ አሁን የሚኖሩበት የቀበሌ ቤት እፍንፍን ያለና ከጎረቤትም በጣም የተጠጋጋ በመሆኑ፣ ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይሠሩ አድርጓቸዋል።
ሠፈራቸውን፣ ‹‹መሸት ሲል የቀዬውን ልጆች ለማሳደግ ቀርቶ ለእኛ ለአዋቂዎች አስቸጋሪ ነው›› የሚሉት እኚህ እናት፣ ብጡል ሆቴልና ቱሪዝም አማካሪ ባሰናዳው የእናቶች ምሥጋና ዝግጅት ከተመስጋኞቹ አንዷ ነበሩ።
«የገብስ ገንፎ 60፣ የቡላ ገንፎ 50፣ የፊኖ ገንፎ 40 ብር ነው የምሸጠው። የገብስ ገንፎ ከ 15-20 ደቂቃ፣ ቡላ 10 ደቂቃ፣ ለመብሰል ይወስዳል። ፊኖውን በምጣድ ነው የማበስለው።» የሰው እጅ ከማይ እና ከመለመን በሚል ገንፎ እና አጥሚት በመስራት እና በመሸጥ ኑሯቸውን የሚግገፉት የ65 አመት እናት አስራት አዳል- የገንፎ እህሉን በእጃቸው በመፈተግ እና በማዘጋጀት ያስፈጫሉ። እማማ ከአጃ፣ ቡላ እና ገብስ አጥሚት እና ገንፎ ያዘጋጃሉ።
‹‹እናቶችን በጋራ እናመስግን›› በሚል መሪ ቃል የእናቶች ቀን ሲከበርም በፆታ እኩልነት፣ በባህል በአጠቃላይ በነበራቸው በጎ ተፅዕኖ በሕይወት ያሉ 60፣ በሕይወት የሌሉ 34፣ በሕይወት ያሉ ጠንካራ እናቶች በሚል ስምንት እናቶች ተሸልመዋል። በሕይወት ከሌሉት መካከል የሲዳማዋ ንግሥት ፍራ በጊዜው በሠራችው ሴቶችን የማንቃት ሥራ እንዲሁም እቴጌ ምንትዋብ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ እቴጌ መነን አስፋውና ሌሎችም በመድረኩ መዘከሩ የሚታወስ ነው።
እናም እንደ ወይዘሮ አስራት ወይም እማማ ገንፎ አይነት ሰዎች ማበረታታት ብቻ ሳይሆን በሚያስፈልጋቸው ነገር ከጎናቸው መቆም ያስፈልጋል። እንግዳችን እንደ ፋና ፣ ብስራት፣ ሪፖርተር … በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የህይወት ተሞክሮአቸውን አካፍለዋል ፤ የእንግዳችን ህይወት አስተማሪ ነው። ነገር ግን የየትኛው መገናኛ ብዙሃን ፕሮግራም ሟሟያ ከመሆን ባለፈ ከጎናቸው የቆመ አንድም በጎ አድራጊ የለም። እማማ ገንፎ ሊደገፉ የሚገባቸው የትውልዱ ማስተማሪያ እናት ናቸው።
የእማማ ገንፎ ህይወት ለብዙ ወጣቶች ስራ የለም፤ ስራ አጣን ፤ተመርቀን ድንጋይ ላይ ተቀመጥን ለሚሉ ሁሉ ማስተማሪያ ህይወት ያላቸው ከራሳቸው አልፈው ሰባት ሰዎችን የሚያስተዳድሩ ብርቱ እናት ናቸው።
የወይዘሮ አስራት “እማማ ገንፎ” ህይወት በአንድ በኩል ግልጽ የሚታይ የሚጨበጥ ነው፤ በሌላ በኩል ረቂቅ የህይወት ቀለማት ውሕድ ነው፤ ለሁሉም እንደ ዓይነ ልቡናው አቅም መጠን የሚገለጥና የሚሰወር ነው። የታመቀም፣ የተዘረዘረም ነው። ስለሆነም ልክ እንደ ቀስተዳመና “የማሪያም መቀነት” ያለ ምንም ጥያቄ ጠቅልለው ወይም የደመቀላቸውን ያህል መርጠው ሊላበሱት የሚወዱት የመኖራቸውን ያህል አከራካሪ ውህዱ እየፈተናቸው በሩቁ ቆመው ብቻ እንዲታዘቡት ያደረጋቸው አይጠፉም። ነገር ግን ጠጋ ብለው ሲመረምሩት የወይዘሮ አስራት “እማማ ገንፎ” የሕይወት ጉዞ ዘርፈ ብዙ ቀለማት ያሉት ቢሆንም ህብሩ አንድ ወጥ ነው። እምነት ፣ መስጠት ፣ ቀጥተኛነት እና ትጋት ነው። ልባምነት ፣ ምልስነት ፣ባለአዕምሮአዊነትም የእማማ ገንፎ መለያ ነው፤ ይህም ደንበኞቻቸውን ሲያስተናግዱ ታይቶባቸዋል።
የዓላማ ቁርጠኝነት፣ የጥንቁቅነትና ርኅራኄ እና የታታሪነት ተምሳሌት ናቸው። የወይዘሮ አስራት “እማማ ገንፎ” የህይወት ጉዞ እንደ ብዙነቱ የተበታተነ አይደለም ፤ የወይዘሮ አስራት የህይወት ትጋት እና የአኗኗር ሥርዓት የሚያሳዝንም የሚያስተምርም በተለያዩ እውነቶችም የተደራጀ ነው። ስለሆነም መዝገቡን ከፍቶ ቅጠሎቹን ሳይሆን አንጓዎችን መርጦ ማገጣጠም ከወይዘሮ አስራት “እማማ ገንፎ” የህይወት ጉዞ ጥንካሬ እና መማር ተገቢ ነው። የአዲስ ዘመን ጋዜጣም ለወይዘሮ አስራት “እማማ ገንፎ” በቀሪ ህይወትዎ ረጅም ዕድሜ እና ጤና መልካም የስራ እና ስኬት ዘመን እንዲሆንልዎ ይመኛል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
አብረሃም ተከስተ