የተወለዱት በድሮው ሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ይርጋለም ከተማ ነው። ይሁንና በተወለዱ በሶስት ወራቸው አባታቸው በወንጌል አገልግሎት ምክንያት ወደ ኩየራ በመቀየራቸው ኩየራ ከተማ ለማደግና እስከ ሶስተኛ ክፍል ለመማር ተገደዱ ። ከሶስተኛ ክፍል በኋላ ግን ወላጅ አባታቸው የወንጌል አገልግሎታቸውን ትተው በንግድ ስራ ተሰማሩና በሃዋሳ ከተማ ከተሙ። ልጅም እስከ ስምንተኛ ክፍል ሃዋሳ ከተማ በሚገኘው ኮምቦኒ ሚሽን ተማሩ። ስምንተኛ ክፍልን ሲጨርሱም ደብረዘይት በሚገኘው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን ኮሌጅ ስር በነበረው አዳሪ ትምህርት ቤት ነፃ ትምህርት እድል አገኙና በዚያ ኮሌጅ ከዘጠነኛ ክፍል እስከ 11ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታተሉ። 12ኛ ክፍል ሲደርሱ ግን አብዮቱ በመፈንዳቱ እድገት በህብረት ለመዝመት ተገደዱ። ከዘመቻ መልስም ሃዋሳ ተመልሰው 12ኛ ክፍልን አገባደዱ።አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተውም በኢኮኖሚክስ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ።
ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም ማዕከላዊ ፕላን በሚባል መንግስታዊ ተቋም ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ፤ በዚህ መስሪያ ቤት እያሉም አስመራና የተለየዩ የአገሩቱ አካባቢዎች ተዘዋውረው ሰርተዋል። በኋላም የአገራቸውን ድንበር ጥሰው ኬኒያ ገቡ፤ ከአንድ አመት ቆይታ በኋላም ወደ አሜሪካዋ ቨርጂኒያ ግዛት ተሸጋገሩ። ይህ ከሆነ እንግዲህ 28 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በአሜሪካ ቆይታቸው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሌላ ዲግሪ እንዲሁም በሲስተም ኢንጅነሪንግ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል። በፔንታጎንና በሌሎችም የአሜሪካ መንግስት መስሪያቤቶች በተማሩበት ሙያ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። እንሰት በሚባልም ማህበራዊ ድረገፅ ብሎገር ሆነው ሰርተዋል። ይሁንና በ1997ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ የቅንጅት አባላት መታሰራቸውን ተከትሎ በአገሪቱ እየተፈፀመ ያለው ኢ ዲሞክራሲያዊ ተግባር ያሳዝናቸውና ያስቆጫቸው ስለነበር ገዢውን ፓርቲ ባላቸው አቅም ሁሉ ለመታገል ቆርጠው ተነሱ።
ልክ በዚህ ወቅት ታዲያ ምስረታቸውን አውሮፓ ካደረጉት ግንቦት ሰባቶች ወደ አሜሪካ በመምጣት የፓርቲያቸው አባል እንዲሆኑ ጥሪ ይቀርብላቸዋል። ከዚያ ወዲህም የሞቀውን የአሜሪካ ኑሮና ደመወዝ ርግፍ አድርገው በመተው ኤርትራ በርሃ ድረስ በመምጣት የትግሉ አጋር ሆነዋል። በአገሪቱ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎም በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ አገራቸው ገብተዋል። በአሁኑ ወቅት በዜግነት ጉዳይ ምክንያት ፓርቲ ውስጥ ገብተው በምርጫ ለመሳተፍ ባይችሉም ያላቸውን እውቀትና ልምድ ለፖለቲካ ሃይሎች በማካፈል ፖለቲካ ትንታኔ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። አዲስዘመን ጋዜጣ ከቀድሞው የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባልና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
ፎቶ – በሐዱሽ አብርሃ
አዲስ ዘመን፡- ከአገር ለመውጣት የተገደዱ በትን አጋጣሚና የአሜሪካ ቆይታዎ ምን ይመ ስል እንደነበር ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ኤፍሬም፡- የመጀመሪያ ዲግሪዬን እንዳጠናቀ ቅሁኝ ማዕከላዊ ፕላን ተመደብኩና ኤርትራ የመሄድ እድሉን አገኘሁ። እዚያ በነበርኩበት ወቅትም ከእኔ ጋር የተማሩ ጓደኞቼ በውትድርና መስክ ተሰማርተው አገኝ ነበር። እነዚያ ጓደኞቼን በየሶስት ወሩ ባገኘኋቸው ቁጥር በጦርነቱ እየሞቱ ቁጥራቸው ከ15 ወደ አምስት ወረደ። ይህም ሁኔታ ታዲያ የአገሬን ነባራዊ ሁኔታ በደንብ እንድርዳ አደረገኝ። በጦርነቱ የአገራችን መንግስት በምንም መልኩ ሊያሸንፍ እንደማይችል ተገነዘብኩኝ። በሌላ በኩልም እዛው እያለሁ ነፃ የትምህርት እድል በሄግ፥ በኢንግላንድና በሜልቦርን በተለያየ ጊዜ እድል ባገኝም ሁሉንም ዝግጅት ካጠናቀኩኝ በኋላ በተደጋጋሚ አንተ የእኛ ሰው አይደለህም ብለው የትምህርት እድሉን እንዳላገኝ ከለከሉኝ። ይሄን ጊዜ እኔ አገሬ ነው ብልም ሌሎች ግን አገሬ እንዳልሆነ እየነገሩኝ በመሆኑ አገሬን ጥዬ መውጣት እንዳለብኝ አመንኩኝና ድንበር ጥሼ ኬንያ ሄድኩኝ። ኬንያ ለአንድ አመት ብቻ ነው የተቀመጥኩት። በአመቱ አሜሪካ ቨርጅኒያ ስቴት ታናሽ ወንድሜ ይኖር ስለነበር እሱ ጋር ሄድኩኝ።
አሜሪካ እንደገባሁ ወንድሜ የሚሰራበት ሬስትሮራንት ውስጥ ሰሃን አጣቢ ሆኜ ተቀጠርኩ። በእቃ አጣቢነት ስድስት ወር ከሰራሁ በኋላ የመጋዘን ስራ አገኘሁ። እዚያ እየሰራሁ ያለው ማስተርሴን መማር ብፈልግም ትራንስክሪብት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማግኘት ባለመቻሌ መማር ሳልችል ቀረሁ። አንድ ጊዜ ዋሽንግተን ዲሲ ለግል ጉዳዬ ሄጄ እያለሁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስተማረኝ መምህር አግኝቼው ስለሁኔታው አጫወትኩት። ያ መምህር ተባበረኝና ትራንስክርቢቴን አስመጣልኝ፤ ከዚያም በኢኮኖሚክስ ማስተርሴን ጀመርኩ። ይሁንና ትምህርቱን ከጀመርኩት ከአንድ ሴሜስተር በኋላ አስጠላኝና አቋረጥኩት። ዳግመኛ ኮሚኒቲ ኮሌጅ ገብቼ የመጀመሪያ ዲግሪ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሰራሁ። ትምህርቱን ከማጠናቀቄ ከሶስት ወር በፊት ግን ሆራይዘን የተባለ ትልቅ የአሜሪካ የኮምዩኒኬሽን ኩባንያ ቀጠረኝ። በኩባንያው አንድ አመት እንደሰራሁ የማስተርስ ትምህርት ለመማር አመለከትኩኝና ገባሁ። ኩባንያው በሲስተም ኢንጅነሪንግ አስተማረኝ። በመቀጠልም የዶክትሬት ዲግሪዬን ትምህርት ለማመር ዳግመኛ ወደ ዩኒቨርሲቲ ተመለስኩኝ።አንድ አመት ከተማርኩኝ በኋላ ልጄ ትምህርት ቤት መግባት ሲጀምር ልጄን መከታተል እንደሚገባኝ አመንኩ። ስለዚህ የራሴን ትምህርት አቋረጥኩና ሙሉ ትኩረቴን ወደ ልጄ አዞርኩኝ።
አዲስ ዘመን፡- ታዲያ የፖለቲካውን መስመር ለመቀላቀል የተገደዱበት ምክንያት ምን ነበር?
አቶ ኤፍሬም፡- እኔ በተለይም የቅንጅት አመራሮች ከታሰሩ በኋላ የነበረውን መንግስት በፅኑ እቃወም ጀመርኩ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አመራር ዘር ላይ የተመሰረተ ነው። በሃይል ካልተወገደ በስተቀር ዝም ብሎ በምርጫ ማስወገድ የማይሆን ነገር እንደሆነ ተገንዝቤ ለመታገል በወሰንኩበት ጊዜ ግንቦት ሰባቶችም ተመሳሳይ ሃሳብ ይዘውልኝ መጡ። ግንቦት ሰባት አውሮፓ ውስጥ ሲፈጠር በምን እንደመረጡኝ አላውቅም ግን ወደ አሜሪካ ሊመጡ ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደወለልኝ። ከዚህ ቀደም ግን ፕሮፌሰር ብርሃኑን በቅርበት አላውቀውም ነበር። ስለፓርቲው ሁኔታ አጫወተኝ። ግንቦት ሰባት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ ሲገባ አባላቸው ሳልሆን የመክፈቻ ንግግር እንዳደርግ ጠየቁኝ። ንግግር ካደረኩኝ በኋላ አባል ሆንኩኝ።
ከዚያም እ.ኤ.አ 2014 ዓ.ም አንዳርጋቸው ፅጌን ሲያስሩት ሁላችንም እልህ ውስጥ ገባን። የእኛን ድርጅት ለማድከም ከሆነ ሃሳባቸው እንዳውም ታጠናክሩታላችሁ የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩኝ። በወቅቱ ለአሜሪካ መንግስት ፔንታጎን ድርጅት ውስጥ ነበር የምሰራው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ነገር በተለይ ሳይማር ያስተማረኝ ህዝብ ለችግር እየተደረገ መሆኑን ሳስብ ደመወዙም ሆነ የአሜሪካ ኑሮ አልታይህ አለኝ። ደግሞም ልጄ ደግሞ 12ኛ ክፍል የሚገባ በመሆኑ ብዙም የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ አሰብኩኝ።ህወሃቶችም ቢሆኑ ኢትዮጵያን የተቆጣጠሩት የእነሱን ትላልቅ ሰዎች ሰውተው በመሆኑ የአገሬ ህዝብም ነፃነቱን እንዲያገኝ ቢያንስ ጥቂት ልጆቹን ማጣት አለበት የሚል ቆራጥ ውሳኔ ላይ ደረሰን። በዚህ መሰረት ወደ ኤርትራ ገባን።
ኤርትራ ከገባን በኋላ ብዙ ውጣ ውረድ ነበረው። እዛ ጉዳይ ውስጥ መግባት አልፈልግም። ግን እዚያ እያለን ከአርበኞች ግንባር ጋር ተዋሃድን። በእርግጥ አሁን ላይ ሳስበው መዋሃድ ካልነበረብን ድርጅት ጋር ነው የተዋሃድነው የሚል እምነት አለኝ። በባህልም አንገናኝም። ግን ኤርትራ ውስጥ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በደንብ እናውቅ ነበር። ከየብሄሩ የመጡ ታጋዮችና ቡድኖች ነበሩ። ስለዚህ አንድ ላይ ሆነን ካልታገልን በስተቀር በሌሎች የአፍሪካ አገራት እንዳየነው ሁሉ ድል እንኳን ብናገኝ ተግባብተን ልሰራ አንችልም ነበር። ስለዚህ በባህል ባንገናኝም ለአገራችን አስበን አንድ ላይ ሆነን የቻልነውን ያህል ደከምን።ይህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ በእኛ ብቻ ይመጣል ብለን አስበንም አናውቅም። ግን የእኛን ሚና መጫወት አለብን ብለን ነው ስንታገል የነበረው። ባላሰብነው መንገድ ይሄ ለውጥ መጣ። በኋላም የእንገናኝ ግብዣ ከለውጡ መሪ መጣልንና ወደ ዋሽንግተን ተመለስኩኝ። ከዶክተር አብይ ጋር ባደረግነው ውይይት መሰረትም ኢትዮጵያ ውስጥ መቼና እንዴት እንደምንገባ፤ እኛም ሆነ እነሱ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ተነጋገርን፤ ተግባባን፤ የምንገባበትን ቆርጠን ወደዚህ መጣን።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በምን ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት?
አቶ ኤፍሬም፡- አሁን ኢዜማን ፓርቲ ከታች ጀምሮ ሲመሰረት ትልቅ ሚና ነበረኝ። የደቡብ ኢትዮጵያ የፓርቲው መሰረት ሲጣል ያንን ክንፍ የምመራው እኔ ነበርኩኝ። ፓርቲዎች ሲፈጠሩ ግን ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌለኝ በመሆኑ በአባልነት መቀጠል አልቻልኩም። ይሁንና በአንዳንድ ቴክኒካል ጉዳዮች ላይ የበኩሌን ድጋፍ አደርግላቸዋለው። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ምርጫ ውስጥ ሊገቡ ነው፤ በምን መልኩ መደራጀት አለበት? በከተማ ደረጃ ለወጣቶች ምንአይነት ቅስቀሳ ቢያደርጉ ነው ወደ ፓርቲው ማምጣት የሚችሉት? የሚሉትን ነገሮች አማክራቸዋለሁ። በነገራችን ላይ የማማክረው
ኢዜማን ብቻ ሳይሆን በዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱትን ሁሉ ነው። በተጨማሪም ከ27 አመታት በላይ ችግር ውስጥ የከተተንን የዘር ፖለቲካ እንዴት መውጣት እንደሚችል ግንዛቤ አስጨብጣለሁ። ምክንያቱም በአገራችን ውስጥ ወደድንም ጠላንም የዘር ፖለቲካ ተገንብቶ ቁጭ ብሏል። በሱ ዙሪያ ብቻ የሚታገሉ ሃይሎች አሉ።
ይህንን ሁኔታ እንዴት እናሸንፋለን በሚሉ እውቀት ተኮር ስትራቴጂዎች አቅጣጫዎች ላይ ከየትኛውም ፓርቲ ጋር አብሬ እሰራለሁ። በጠየቁኝ ሁሉ ለመደገፍ ፍቃደኛ ነኝ። ምክንያቱም የእኔ ትልቁ ፍላጎት ወደአገር ውስጥም የገባሁበት ዋነኛ አላማ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ ሲካሄድ ማየት ነው። ምክንያቱም ከ16 ዓመቴ ጀምሮ የኖርኩበት ህይወት ነውና እሱን ማየት እፈልጋለሁ። አሜሪካ ውስጥ ብዙ ምርጫዎችን አይቻለሁ። በመጀመሪያው የኦባማ ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ተካፍያለሁና ልምዱ አለኝ። ስለዚህ ምንም እንኳ የአሜሪካንን ምርጫ ሙሉ ለሙሉ ማምጣት ባንችልም የተሻለ ምርጫ ግን ማካሄድ እንችላለን። ከአደጉት ሀገራት የምርጫ ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሊተረጎም የሚችል ነገር አለ። በዚህ መሰረት በቀጣዩ ምርጫ በኢዜማ በኩል ዘመናዊና ዴሞክራሲያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ምን እንደሚመስል ለማሳየት ጥረት ይደረጋል ብዬ አምናለሁ ።
አዲስ ዘመን፡- አባል መሆን ያልቻሉት ዜግነቶትን መቀየር ስላልፈለጉ ነው?
አቶ ኤፍሬም፡- ዜግነቴን ብቀይርም በፍፁም በህይወቴ ከማልፈልጋቸው ነገሮች ውስጥ በፖለቲካ ስልጣን ይዞ መስራት ነው። በእውነት ነው የምልሽ መመረጥ አልፈልግም። ይሄ ጉዳይ የአሁን ውሳኔዬ አይደለም። ወደዚህ ስመጣ የነበረ እንጂ። እውነቱን ለመናገር ደግሞ በአለም ላይ ለመምራት አስቸጋሪ ከሆኑት አገራት ኢትዮጵያ ዋነኛዋ ናት። ታዲያ ለምን እያየሁ እገባለው። ደግሞም ከልጅነቴ ጀምሮ የተማርኩት ነገር ቢኖር እሱን ነው። ለምንድን ነው እዛ ውስጥ የምገባው?። የኢትዮጵያ ስልጣን የሚያዝበት መንገድ በህዝብ ፍቃድ ብቻ እንዲሆን የሚችልበት ሁኔታ ከፈጠርኩ በራሱ ለእኔ በቂ ነው። ስለዚህ ለእኔ የዜግነቱን ጉዳይ ብለውጥም ባልለውጥም ምንም ትርጉም የለውም ።
አዲስ ዘመን፡- ግን እርሶ የደቡብ ክልል ተወላጅ እንደመሆንዎ የክልሉ ህዝብ እንደእርሶ ያለ በፖለቲካ ልምድ ያለው አመራር ያስፈልገዋል ብለው አያምኑም?
አቶ ኤፍሬም፡- ተቋም ግንባታ ላይ ኢትዮጵያ ገና ብዙ ሊሰራላት የሚገባት ጉዳይ አላት። እነዚያ ተቋም ግንባታዎች ላይ አስተዋፅኦ ባደርግ ደስ ይለኛል። ኢትዮጵያ ውስጥ በአግባቡ መገንባት ካለባቸው ተቋማት መካከል አንዱ ሚዲያ ነው። ዘግቡ ሲባሉ የሚዘግቡ፣ አትዘግቡ ሲባሉ የማይዘግቡ ሚዲያዎች መሆናቸው ቀርቶ በራሳቸው ውሳኔ ማስተላለፍ የሚችሉበትን አቅም ሊፈጠርላቸው ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ ያሉት ሚዲያዎች መንግስት ተጠያቂ የማድረግ አቅም የላቸውም። ለምሳሌ በቅርቡ ደንቢዶሎ ውስጥ በታገቱት ተማሪያዎች ዙሪያ ሚዲያው በሚፈለገው ደረጃ እየሰራ አይደለም። አንደኛ ነገር የረጅም ጊዜ ዝምታው፤ ሁለተኛ ተፈቱ መባሉ፤ ተፈቱ ተብሎ ግን ለሳምንታት ወላጆች ልጆቻቸው የትእንዳሉ አለማወቃቸው በጣም ነበር ያናደደኝ። ይህንን የማጣራትና ይፋ የማድረግ ስራ የሚዲያ ነበር። ልጆቹ የትገቡ ብሎ ሚዲያው መጠየቅ ሲገባው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተከሉትን ዛፍ ውሃ አጠጡ ይል ነበር። ይህ ለእኔ ጥቅም አልባ ጉዳይ ነው። ይሄ ለእኔ ሚዲያ አይደለም። ስለሆነም እነዚህ ሚዲያዎች እንዴት ይገነባሉ? እንዴት አድርገው መንግስትን ተጠያቂ ያደርጉታል? በህዝብና በመንግስት መካከል ሆነው ሃላፊነቱን ያልተወጣ ባለስልጣን እንዴት ያነቁታል?። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የምርመራ ዘጋቢዎች የሉንም። ስለዚህ እነዚህ ተቋማትን በማደረጃት ሂደት ውስጥ የራሴን ሚና መጫወት እፈልጋለው።
አዲስ ዘመን፡- ወደዚህ አገር ከመምጣቶ በፊት እንደተቃዋሚ ፓርቲ ቃል የተገባላችሁ ነገር ተፈፅሟል ብለው ያምናሉ?
አቶ ኤፍሬም፡- እኛ ወደዚህ አገር ከመግባታችን በፊት ለብዙዎቻችን ክብር ነበራቸው። እነሱ እንዳውም ለተወሰነ ጊዜ ሆቴልም ሊያስቀምጡን ፈልገው ነበር። እኛ ግን አልፈለግንም። ከደህንነት ጋር ተያይዞ አሁን ልነግርሽ የማልችላቸውን ብዙ ነገሮች ፈፅመዋል። ለውጡ ከመጣ በኋላ በርካታ ችግሮች ተፈጥረው አይተናል። በእርግጥ መንግስት ከወሰዳቸውና ከሚያስመሰግናቸው እርምጃዎች አንዱ የሱማሌ ክልል የነበረውን ችግር መፍታት መቻሉ ነው። ይህንንም አሁን በክልሉ የምናየው ነገር ያመላክተናል። አንድ መልካም ወይም መጥፎ ሰው በአንድ ክልል ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖዎች በሱማሌ ክልል ማየት ይቻላል። አንዳንድ ችግሮች ምንአልባት ከመንግስትም አቅም በላይ የሆኑበት ሁኔታ ነበር። መንግስት ችግር ውስጥ እንዲገባ ሆን ብሎ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች አሉ። እነዚህ ሃይሎች ከፊሎቹ ከውጭ የመጡ ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ናቸው። የዜና ማሰራጫ ማዕከል ያላቸውም ጭምር ናቸው፤በገንዘብም ይደጎማሉ።
ይህ ወጣት የሆነው አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ እነዚህን ነገሮች አንድ አድርገው ለማቆየት የሚያደርጉት ጥረት ጥሩ ነው። በእርግጥ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ዶክተር አብይ አህመድ ከሚታማባቸው ችግሮች አንዱ እርምጃ አለመውሰዱ ነው። በግሌ በአንዳንድ አባባሎች ላይ አልስማማም። ብዙ ጊዜ እኛ ኋላቀሮች አይደለንም፤ አንገድልም የሚል አስተያየት ይሰጣሉ፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ኤፍሬም የሚለው ዝም ብለህ ግደል አይደለም። እኛ ያልነው ፍትህን አስፈጽም ነው። የህግ የበላይነትን ማስፈንና መግደል የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ባደኩባት ሃዋሳ የተፈፀመው ወንጀል አንዳንዱ በቪዲዮም ጭምር የተቀዳ ማስረጃ ያለው ነው። ነፍሰገዳይን ለፍትህ አለማምጣት ከእነሱ ጋር ከመተባበር አይለይም። እነዚያ ሰዎች በጊዜ ተይዘው ለፍርድ ቀርበው በሚዲያ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ቢነገር ኖሮ ሻሸመኔ ላይ ሰው ተዘቅዝቆ አይገደልም ነበር። እነዚህን ወንጀለኞች አንነካም ማለት ለእኔ ፍቅር አይደለም። እንደዚህ አይነት ፍቅር የለም። እንደዚህ አይነት ፍቅር ወደ ሃይማኖቱ ጋር ወስደን እናስቀምጠው። እያወራን ያለነው ስለፖለቲካ ነው። ፖለቲካ ላይ ትልቁ ነገር ፍቅር ሳይሆን ስምምነት ነው። ያ ስምምነት እንዲመጣ ማድረግ አለብን። ስምምነት እንዳይመጣ የሚያውኩ፤ ህዝብን የሚገድሉ፤ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የጠቀሷቸው ችግሮች ለቀጣዩ ምርጫ ስጋት አይሆንም ብለው ያምናሉ?
አቶ ኤፍሬም፡- ልክ ነሽ። የእኔም ትልቁ ፍርሃት እሱ ነው። እንኳን ትልቅ ምርጫ ትልቅ የእግር ኳስ ውድድር ለማካሄድ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባል። የሃይማኖት በዓል ላይ እንደዚህ የጥይት ድምፅ ከተሰማ ምርጫው ሲካሄድ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ፈጣሪ ነው የሚያውቀው። አሁንም የፍትህ ተቋማት፣ ሚዲያዎች በእርግጥ ለእውነት ይቆማሉ ወይ? የሚለው ነገረ አጠያያቂ ነው። ለምሳሌ መከላከያው በአሁኑ ወቅት የት እንደቆመም አናውቅም። እናም የፖሊስና የደህንነት ሃይሉ በእርግጥ ለህዝብ ጥቅም ይቆማሉ ወይ? የሚለው ነገር አጠያያቂ ነው። ምርጫው የኢትዮጵያ ሃይሎች ቁጭ ብለው ተደራድረው የሚወስኑት ውሳኔ ውጤት መሆን ነበረበት። ግን እሱ ሊሆን አልቻለም። ምርጫው ነሃሴ ነው ተብሏል፤ እሱ ራሱ ትልቅ ጥያቄ ፈጥሯል። ምርጫ ቦርድ ከዚያ ጊዜ ብናልፍ ህገመንግስቱን መጣስ ይሆንብናል ይላል። ለእኔ የሚያስፈራኝ ግን ዝናብ ከዘነበ ሰዎች ወንዝ መሸገር የማይችሉበት ሁኔታ እንዳይፈጠር ነው። ይህ ደግሞ ይመርጣል ተብሎ ከታሰበው በግማሽ ያህል እንኳ እንዳይሳተፍ ሊያደርግ ይችላል። እናም ይህን የሚያክል ህዝብ በህይወታችን ውስጥ በጣም ወሳኝ ከሆነ ምርጫ ልናወጣው ነው?። ደግሞ ከተጠበቀው ከፊሉ ብቻ እንኳ ቢመርጥ ውጤቱን መቀያየሩ አይቀሬ ነው። ይህንን ሁኔታ ተዲያ ህገመንግስታዊ ነው ብለን ልንቀበል ነው? እንዳውም ይህ ሁኔታ ይበልጥ አገሪቱን የሚያጠፋበት ሁኔታ ይበልጣል ባይ ነኝ።
በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ህገመንግስት የሚኖረው ለኢትዮጵያ ነው። ኢትዮጵያ ለህገመንግስቱ አትኖርም። ደግሞም አቅሙ የሌለን በመሆኑ በግንቦት ወር ምርጫውን ማድረግ አንችልም። ተስማምተን በፈለግንበት ጊዜ ምርጫውን ብናደርገው ህገመንግስቱ ተነስቶ ሊከሰን ነው እንዴ? ወረቀት እኮ ነው!። ይህን ማድረግ እየተገባን እንደፈለጉ 30 ዓመት ሲጥሱት የኖሩትን ህገመንግስት ይጣሳል ይሉናል!። እናም እኔ እንዲህ ብለው የሚያመጡብን ችግር ይብሳል የሚል ስጋት አለኝ።እንዳውም ይህችን አገር እንደአገር ማቆም ሊያቅተን ይችላል የሚል ፍርሃት አለኝ። ችግሩ ሲመጣ እኮ ህገመንግስቱ አይከላከልልንም። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ ምርጫ ቦርድም፤ መንግስትም አሁንም እንደገና ቢያስቡበበት ደስ ይለኛል። በእኔ እምነት ግን ይህችን የተለየች ምርጫ ዝናቡ ሙሉ ለሙሉ በሚያቆምበት በጥቅምት ወር ላይ ብናደርገው የተሻለ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይህን ቢሉም ያልተመረጠ መንግስት ለጥቂት ወራትም ቢሆን ሊመራን አይገባም የሚሉ ወገኖች አሉ?
አቶ ኤፍሬም፡- እሱን እኮ ነው የምልሽ! ሁላችንም ተስማምተን ያለው መንግስት ሃላፊነቱን ወስዶ እስከምርጫ ሊያደርሰን ይችላል። ይህ አይነት ተሞክሮ በየትኛውም አገር አለ። ለምሳሌ እስራኤልን ወስደሽ ብታይ ቤንጃሚን ኔትናያሆ ምርጫ ሳይካሄድ ሃላፊነቱን ወስደው ነው እየመሩ ያሉት። በየትኛው የፓርላማ አገር ውስጥ ምርጫ የሚስተጓጎል ከሆነ ያለው መንግስት ሃላፊነቱን ይረከባል። ይሄ ያልተመረጠ የሚለው ሃሳብ ለእኔ ብዙም ተቀባይነት የለውም። ትልቅ የብሄር ፣ የጥቅም ግጭት ስላለበት ግን ደግሞ በታሪክ ውስጥ የመጀመሪያውን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂዳለው ስለሚል አገር እኮ ነው የምናወራው። በታሪካችን ሺ ዓመታት በንጉስ እየተቀጠቀጠ የኖረ አገር አሁን ለሁለትና ሶስት ወራት በነባሩ መንግስት ባላደራነት አንመራም ማለት ለእኔ ተቀባይነት የለውም። ይህ ሃሳብ በአብዛኛው የመጣው የሚመስለኝ ራሳቸውን ፌደራሊስቶች ነን ከሚሉ ሃይሎች ነው። በነገራችን ላይ ለምሳሌ የኦፌኮ መሪ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ሁልጊዜም ቢሆን ያልተመረጠ መንግስት እያሉ አልነበረም እንዴ ሲከራከሩ የነበሩት? አሁን ላይ ምን የተለየ ነገር መጣ? እናም አሁንም ቢሆን ይህ መንግስት ተመርጧል ማለት አይደለም። ይልቁኑ ይህን የረጅም ታሪካችንን ለመቋጨት አንድ እድል አግኝተናል፤ እንጠቀምበት።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ ያሉት የፖለቲካ ሃይሎች ከምርጫ በኋላ የምርጫውን ውጤት በፀጋ ተቀብለው የመሄድ አዝማሚያቸው ምን ይመስላል?
አቶ ኤፍሬም፡- በግሌም ሆነ ባለፉት 12 ዓመታት አብሬያቸው እንደሰራኋቸው የፖለቲካ ሃይሎች ከምርጫው በላይ ኢትዮጵያን ያያሉ። በዚህ ምርጫ ውስጥ እኛ አሸንፈን ሂደቱ ጠማማ ከሚሆን፤ እኛ ተሸንፈን ሂደቱ ትክክለኛ ቢሆን እንመርጣለን። በሚቀጥለው ምርጫ ላይ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ ከሆነ ብንሸነፍ ለመቀበል ሙሉ ፍላጎት አለን። ኢትዮጵያ
ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ሂደት ተጀመረ የሚባለው እኛ ስናሸንፍ አይደለም። ተሸንፈንም ውጤቱን በፀጋ ስንቀበል ነው። ከታሪክ ስናይ የምርጫ ውጤትን የማይቀበሉት በብሄር የተደራጁ ሃይሎች ናቸው። ምክንያቱም ሲደራጁም ዋና አላማቸው የራሳቸውን የፖለቲካ ስልጣንና ጥቅም ለማስጠበቅ በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ህውሃቶች የአገሪቱን ስልጣን ተቀብለው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን እንደሆነ ይታወቃል። የአገሪቱን ስልጣን ሲረከቡ ኢኮኖሚውን ተቆጣጠሩት፤ በዚህ ምክንያት እንደፈለጉ አደጉ፤ ሃብት መዘበሩ። ስለዚህ የብሄር ሃይሎች ይህንን ስለሚያውቁ የፖለቲካ ስልጣን ላይ መሸነፍ ማለት ይህንን ሁሉ ጥቅም እንደማጣት አድርገው ነው የሚወስዱት።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27ዓመታት የብሄር ተኮር ፖለቲካ ተግባራዊ ሲሆን በቆየበት ሁኔታ እርሶ የሚሉት አስተሳሰብ በአንድ ምርጫ እንዴት ይመጣል ተብሎ ይታመናል?
አቶ ኤፍሬም፡- ልክ ነሽ፤ የብሄር ፖለቲካ በአንድ ጊዜ አይጠፋም። ጊዜ ይፈልጋል። ግን አንድ ነገር ልብ እንድትይልኝ የምፈልገው እኛ የማንፈልገው ፖለቲካውን እንጂ የሚወክሉትን ብሄረሰብ አይደለም። ነገር ግን እነዚያ ማንነቶች የቡድን መብታቸው ተከብሮላቸው ነገር ግን ፖለቲካውን ሁላችንም ሊያግባባን በሚችለው በዜግነት ላይ የተመሰረተ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ አሁን ያሉት በርካታ የፖለቲካ ሃይሎች ወደአንድ መምጣት ይገባቸዋል። በነገራችን ላይ የማንነት ችግር የነበረባት ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም። ስፔን ፣ ሲሪላንካ፣ ናይጄሪያ ተመሳሳይ ችግር ነበር። አራት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን ብናቋቁምና ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ እንኳን የጥምር መንግስት ማቋቋም ቢችሉ የቡድንና የግለሰብን መብት እኩል ማክበር መቻል አለባቸው። ይህ ሲሆንም ሁሉም ዜጋ በተመረጠው መንግስት ላይ እምነት ይኖራቸዋል። ያን ሲያደርጉ ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከብሄር ፖለቲካ መሰረት ተላቆ በዜግነት ላይ የተመሰረተ የሚሆነው። ይህም አንድ አራት ምርጫ ይፈልጋል። በቀላሉ አይሆንም። ግን ካልጀመርነው አይሄድም። ወደዚያ በምንሄድበት ሂደት ውስጥ ግን የግድ የብሄር ሃይሎችን ማጥፋት የለብንም።
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን እየተፈጠሩ ባሉት ችግሮች ምክንያት ኢትዮጵያ የምትባል አገር በቀጣይ ስለመኖርዋ ስጋት እንደሆነባቸው አንዳንድ አካላት ያነሳሉ። እርሶ ይህ ስጋት አያሰጋዎትም?
አቶ ኤፍሬም፡- በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በተለይ ሰዎችን ወደ ማዕከል በማምጣት የሚታወቁ የፖለቲካ ሃይሎች ወይም መሪዎች አሁን ከዚያ ፀባያቸው ወጥተው ማህበረሰቡን የሚያራርቅ ንግግር መናገር ጀምረዋል። እነዚህ ንግግሮች በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ቅሬታዎችን ፈጥረዋል። ለምሳሌ ልዩነቶቻችን እየሰፉ ካሉ ጉዳዮች አንዱ የባንዲራ ጉዳይ ነው። አገሪቱ ውስጥ ህጋዊ ባንዲራ እያለ የፌዴራል ሃይልም ሆነ የክልል ሃይል ህጋዊ ያልሆነ ባንዲራ ማውለብለብ የለበትም። አሁን በሁሉም በኩል እልህ እናያለን። በተለይ 60 በመቶው ህዝብ ወጣት በሆነበት አገር ወጣቱ በእልህ ሲነሳሳ ማድረግ የማይፈልገው ነገር ውስጥ ይገባል። ለዚህ ነው አዳማ ላይ በዚህ ምክንያት ግጭት ተፈጥሮ ሰዎች የሞቱት። እናም አንዱ ይህ አይነት ችግር የሚመጣው ከክልል ነው።
ለዚህ ችግር መባባስ ዋነኛው ምክንያትነው ብዬ የምወስደው የፖለቲካ ሃይሎች የሚናገሩት ከፋፋይ የሆነ ሃሳብ ነው። ይህንን ጉዳይ በእርግጥ ምርጫ ቦርድም ሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ሊያየው ይገባል። ቄሮ ተዘጋጅ የሚል መልዕክት ከመሪ ሲተላለፍ ምን ማለት ነው? እኔም ዛሬ ተነስቼ ወጣት ተዘጋጅ ልበል? ስለዚህ እደዚህ አይነት ሃላፊነት የጎደላቸው ሃይሎችን ማስታገስ ይገባል። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ይህ ችግር ሁልጊዜ የሚፈጠረው በብሄር የተደራጀ ሊሂቅ ሃይል ነው። ይህ ሃይል አድርግ የሚለውን በስሜት የሚነዳው ወጣት ያደርጋል። አታድርግ ቢለውም አያደርግም። የፖለቲካው ሊሂቅ የሚያመጣውን ቀውስ ለማየት ሩቅ መሄድ የለብንም። ደቡብ ሱዳንን ማየት እንችላለን። ደቡብ ሱዳናውያን ነፃ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በሁለቱ ሃይሎች ምክንያት ሲተላለቁ አልነበረም እንዴ? ልክ ሁለቱ ሃይሎች ሲስማሙ ግጭቱ አበቃ።በኢትዮጵያ ውስጥም ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው። የፖለቲካ መሪዎች ማህበረሰባቸውን ለክፋት ከመቀስቀስ ይልቅ ለጥሩ ነገር መቀስቀስ አለባቸው። ይህንንም ከሱማሌ ክልሉ መሪ ከሙስጠፌ ሊማሩ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ በሐረር ተከስቶ ከነበረው ጋር ተያይዞ ጉዳዩን የሃይማኖት ግጭት እንደተከሰተ የሚቆጥሩ አካላት አሉ፤ በሌላ በኩል የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተከታዮች እየተጠቃን ያለነው አገራችንን ስለምንወድ ነው በማለት ቅሬታቸውን ያነሳሉ።ሙስሊሞችም በማንታችን እየተጠቃን ነው እያሉ ነው። እርሶ እነዚህን ሁለት ነገሮች እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ኤፍሪም፡- እኔ በእውነት ኢትዮጵያዊነትንና ኦርቶዶክሳዊነትን ማያያዝ አስፋላጊ ነው ብዬ አላምንም። ኢትዮጵያ የኦርቶዶክሶች አገር ናት። ደግሞም የፕሮቴስታንት፣ የካቶሊክ ፣ የሙስሊሙ፣ የዋቄፈታውም እምነት ተከታዮች አገር ናት። ይህ ብቻ አይደለም፤ ሃይማኖት ደንታዬ አይደለም የሚለውም ሰው አገር ናት። ኢትዮጵያዊነትንና ኦርቶዶክሳዊነትን ስናገናኝ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር እንጣላለን። ኢትዮጵያ በርከት ያለ የሙስሊም ማህበረሰብ አለ። ይህ የሙስሊም ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ እምነቱን የማራመድ መብቱ ከኦርቶዶክስ መብት ጋር እኩል ነው። የማንም ከማንም አያንስም፤ አይበልጥም። ይህንን ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። ይህንን ባልተገነዘብን ቁጥር አንዳንዴ አውቀንም ሳናውቅም የምንተቻቸው ትችቶች ወደአልተፈለገ ነገር ሊመራን ይችላል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት ይባላል፤ ግን አይደለችም። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ደሴት ናት። እናም ይህንን ነገር በአግባቡ መገንዘብ ይገባናል።
እንደኢትዮጵያውያን መኖር የምንችለው ሁላችንም ተከባብረን ተቻችለን ስንኖር ነው። አንዱ የሌላውን ቤተ እምነት ከማፅዳት በላይም መብለጥ አለበት። ከዚያ ባለፈ እያንዳንዱ ክርስቲያን ሙስሊም ወንድሙን ከልቡ ማክበር አለበት። እኔ ለምሳሌ ምንም እንኳ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ብሆንም ለ12 ዓመታት ስሰራ የቆየሁት መሰረታቸው የኦርቶዶክስ እምነት የሆነ ነገር ግን ስለሃይማኖት ደንታ ከሌላቸው ከእነአንዳርጋቸው ጽጌ ጋር ነው። አንድም ቀን ችግር ፈጥሮብኝ አያውቅም። ምክንያቱየም ሃይማኖት የግላችን ነው። ያገናኘን ፖለቲካው ነው። በሃይማኖት የሚነሱ ግጭቶች አንድን ማህበረሰብ ምን ማድረግ እንደሚችሉ አይተናል። በእርግጥ አንድ መርሳት የሌለብን ነገር አለ፤ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ በቆየችባቸው ዓመታት ህዝቡን ለአገሩ እንዲሰለፍ የመቀስቀሻ ዋነኛ መንገድ የነበረው ቤተክርስቲያን ነው። ከሌሎች አፍሪካውያኖች በተለየ የተደራጀ የእምነት ተቋም የነበረን በመሆኑ ነው በቅኝ ያልተያዝነውም። ኢትዮጵያ ውስጥ የተደራጀ የእምነት ተቋም መኖሩ ህዝቡ በጋራ ጠላቱን እንዲከላከል አድርጎታል። ይህንን የቤተክርስቲያንን ሚና ልንረሳ አንችልም። ለሁለት ሺ ለሚጠጋ አመታት የእኔ እምነት ነው ብሎ የሚቀበል ማህበረሰብ መኖሩንም ልንዘነጋም አይገባም።
በሌላ በኩል አሁን ከዚህ ተቋም ጋር ፊት ለፊት የሚጋጩ ሃይሎች ተፈጥረዋል። እንደሚመስለኝ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያለ ቤተእምነት በቋንቋ መሰበክና መገልገል እንዳለበት አምናለሁ፤ ነገር ግን በመግባባት ነው መሆን ያለበት ።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን ሕወሃት በክልሉ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተቃውሞ እየገጠመው ነው፤ ይህ ሁኔታ የትግራይ ህዝብ ልክ እንደሌላው ህዝብ አማራጭ ፓርቲዎችን ለማየት እድሉን ለማግኘት ያስችለዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ኤፍሬም፡- ህውሃት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ስልጣን ከተነሳ ወዲህ በአብዛኞቹ ክልሎች የሚታዩ ነገሮች አሉ። እኔ ሕወሃቶች ይህንን አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚል ከአለም ላይ የጠፋውን የሌኒን ፍልስፍና ይዘው መቀጠል አይችሉም። ህውሃት 19 67 ዓ.ም ሲመሰረት የቀሩ ሰዎች ያሉበት ድርጅት ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎች ባሉበት ድርጅት አመራር ትግራይ ውስጥ ፍትህና ነፃነት ይኖራል ብዬ አላስብም። ፍትህና ነፃነት የራቀው ህዝብ ትንሽ ጊዜ ሊፈጅበት ይችላል እንጂ ግን ታግሎ የጨቆነውን አካል ገርስሶ ይጥላል። የትም አገር ውስጥ የህዝብን መሰረታዊ መብት ቀምቶ የሚኖር ሃይል አይኖርም። የትግራይ ህዝብ አሁን ተይዞ ሊሆን ይችላል። የተደቀነበትን አደጋ ጥሶ የሚወጣ ሃይል ደግሞ መምጣቱ አይቀርም። ይህ እንዲሆን ግን የሌሎች የኢትዮጵያኖች እርዳታ ያሻዋል። በተለይም ደግሞ የትግራይ ህዝብ ራሱ ይህንን የሕወሃትን ዘመን አበቃ ማለት አለበት።
በእርግጥ ትግራይ ውስጥ ቀርቶ በሌላውም አካባቢ ነፃ ምርጫ ይካሄዳል የሚለው ነገር አሁንም ለእኔ ትልቅ ጥያቄ ነው። ክልል የራሱ ልዩ ሃይል አለው። የክልል ልዩ ሃይል ባለበት ቦታ ላይ ከክልል ውጭ የመጣ ሃይል ማሸነፍ ይችላል? ክልሉ የራሱ ሚዲያ አለው። ያ ሚዲያ ከሌላ ክልል በመጣ ፓርቲ የክልሉ መንግስት ተሸነፈ ብሎ ያወራል? አሁን እዛ ጋር ደርሰናል ወይ? ትግራይ ውስጥ ደግሞ የባሰ ነው። አሁን ላይ ትግራይ ከፌዴራል መንግስት እጅ የወጣ ነው የሚመስለው። ሲናገሩም፤ ሲሳደቡም፤ ሲያስጠነቅቁም፤ ሲዝቱም የዓለም ጦር ሁሉ እነሱ ጋር ያለነው የሚመስለው። «በፋሲካ የተዳረች ሁሌ ፋሲካ ይመስላታል» እንደሚባለው ማለት ነው። ደርግን ስላሸነፉ ሁሉም ነገር ደርግ ይመስላቸዋል። እንደዚህ አይነቱን ጡሩንባ እንሰማለን ግን የፌዴራል መንግስቱም ቢሆን የትግራይ ህዝብ መብት ሲጣስ ዝም ይላል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ሃላፊነት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ኤፍሬም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
ማኅሌት አብዱል