የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቻይና የሚካሄደውን የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ማራዘሙን አስታወቀ። እአአ ከመጋቢት 13 እስከ 15 ቀን 2020 በቻይና ናጂንግ ከተማ ሊካሄድ የነበረው 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክውድድር ለ12 ወራት ያህል እንዲራዘም መደረጉን የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ዋቤ አድርጎ ቢቢሲ ዘግቧል።
የዓለም አትሌቲክስ የጤና ቡድን ከዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ጋር በቻይናና ከቻይና ውጪ በሌሎች አገራት የኮሮኖ ቫይረስን አስመልክቶ በቅርበት መረጃዎችን በመለዋወጥ ባገኘው መረጃ ኮሮና ቫይረስ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደሆነ ለመረዳት መቻሉን ዘገባው አመልክቷል። በቻይና መነሻውን ያደረገው ኮሮና ቫይረስ 130 ሰዎችን የገደለ ሲሆን፤ በ16 ሀገራት ተስፋፍቷል። ከስድስት ሺህ ሰዎች በላይም በቫይረሱ መጠቃታቸውን ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ በመነሳት የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቻይና በተስፋፋው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት ውድድሩን በተባለለት ጊዜ ማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑን በማመን ውድድሩ እንዲራዘም ውሳኔ አሳልፏል። በመሆኑም እ.አ.አ በ2021 ውድድሩ እንዲካሄድ አማራጭ መቅረቡን አስታውቋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሩን በሌሎች አገራት ለማድረግ አስቦ እንደነበር ያስታወቀው ፌዴሬሽኑ ቫይረሱ ከቻይና ውጪ ወደ ሌሎች አገራት የመሰራጨቱ ጉዳይ አሳሳቢ ስለሚሆን አገር የመቀየር ምርጫውን መሰረዙን አመልክቷል። ብዙ አትሌቶች ውድድሩ እንዲካሄድ ካላቸው ፍላጎት አንጻርም የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሩን ሙሉ ለመሉ የመሰረዝ ምርጫውንም እንደተወውም ነው ተጠቀሰው። ይህ በመሆኑ ምክንያት ናንጂንግ እ.አ.አ በ2021 ውድድሩን የሚካሄድበት ምቹ ጊዜ ማግኘት እንደምትችል የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል። የዓለም አትሌቲክስ ከአትሌቶች፣ ከናንጂንግ የውድድር አዘጋጅ ኮሚቴና ከአጋሮች ጋር የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር እ.አ.አ 2021 የሚካሄድበት ቀን ለመወሰን በቅርበት እንደሚሰራም አስታውቋል።
የዓለም አትሌቲክስ ቻይና የኮሮኖ ቫይረስን ለመከላከል እያደረገች ያለችውን ጥረት እየተከታተለ እንደሆነና ተቋሙ አገሪቷ እያከናወነች ላለው ሥራ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል መግባቱንም አስፍሯል። ቫይረሱን አስመልክቶ ለአትሌቶች፣ ለብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖችና አጋሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ ያሉ ጉዳዮችን ማሳወቅ ተገቢ እንደሆነም ማመልክቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
የእስያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም በቻይና ሀንግዙ ግዛት ሊካሄድ የነበረውን ዘጠነኛው የእስያ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር መሰረዙን ከአራት ቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
ዳነኤል ዘነበ