የስፖርት ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በእጅጉ እየጨመረ እንደመጣ ይታወቃል። የዓለም አገራት የስፖርት ሴክተሩን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በመረዳት ብቻ የሚቆሙ እንዳልሆኑ በዘርፉ ያስመዘገቡት ውጤት ማሳያ ነው። በዓለማችን በበርካታ አገራት ከሌሎች ሴክተሮች ባልተናነሰ መልኩ ለስፖርት ልማቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን በማፍሰስ ስማቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ከማድረግ አልፈው ብዙ ማትረፍ ችለዋል፡፡
ለስፖርት ሴክተሩ ትልቅ ትኩረት መስጠት በማህበራዊ ፋይዳው አምራችና ጤናማ ዜጋን በማፍራት ረገድ ያለውን ውጤት ከመረዳት ይመነጫል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ትላልቅ ውድድሮች በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከሚገኘው ድል ጀርባ ለአገር ፖለቲካዊ ትርፍ ማጣጣም ማስቻሉንም መታዘብ ይቻላል፡፡ ስፖርተኞች ከውድድር ድል በኋላ የሚያገኙት ረብጣ የሽልማት ገንዘብና የአገር ኢኮኖሚን በማንቀሳቀስ የሚገኘው ትርፍም ቀላል አይደለም፡፡ የስፖርቱን ዘርፈ ብዙ ፋይዳን በጥልቅ በመረዳት የስኬት ማማ ላይ የወጡ እንደ ጀርመን ያሉ አገራትን ማንሳት ይቻላል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለስፖርት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ረገድ ጀርመን በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ ናት። ይህች አገር ስፖርቱ በጠንካራ የፋይናንስ መሠረት ላይ ማቆም መቻሏ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ መሠረቱን ሳይለቅ መጓዝ የቻለ አደረጃጀት መፍጠሯ ለስኬቷ ምክንያት ተደርጎ ይነሳል፡፡ የጀርመን መንግሥት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ከሚያፈስባቸው ዘርፎች ዋነኛው ስፖርት ሊሆን የቻለውም ለዚህ ነው፡፡
ስፖርት በጀርመን ኢኮኖሚ ውስጥ 2 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ ይይዛል። ስፖርቱን በፋይናንስ አቅም እንዲጎለብት ከማድረግ በተጓዳኝ፤ ጠንካራ አደረጃጀት የተዘረጋለት ነው። በጀርመን የስፖርት ዘርፍ ይህን መልክ መላበሱ ከዘርፉ የሚገኘው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዲጎላ ማድረጉ ይነሳል። በኢትዮጵያ ለስፖርቱ ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረትና ውጤት ከሌሎች አገራት አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በቀደሙት ጥቂት ዓመታት ለስፖርቱ ቅርብ ከሆኑ ሰዎች፣ ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በኩል ኢትዮጵያ ለስፖርቱ ዘርፍ ተገቢ ትኩረት መስጠቷ ይነገራል፡፡ ለስፖርት ዘርፍ በተገቢው ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ አለመሆኑንና የዘርፉ እድገት በቁልቁለት ጉዞ ውስጥ መሆኑም በሌላ ወገን ይነሳል። የስፖርት ሴክተሩ ውጤት አልባ መሆኑ ግን ሁለቱንም ወገኖች እንደሚያስማማ ለመታዘብ ይቻላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በመንግሥት ደረጃ ይኸው እውነታ ታምኖበት እየተሰራ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ እየተነገረ ይገኛል።
በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የዕቅድ በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንድሪስ አብዱ፤ በአገሪቱ ባለፉት ሁለት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመናት ዘርፉ ለአገሪቱ ማበርከት ካለበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታዎች አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ላይ አለመገኘቱና ውጤቱም በመላ አገሪቱ ተደራሽነት ላይ ክፍተቶች መኖራቸው እንደታመነበት ይናገራሉ:: ለዚህም የስፖርት ሴክተሩን መሠረታዊ ችግር በተረዳ መልኩ የ10 ዓመት የስፖርት ሴክተር ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንዲሆን በኮሚሽኑ በኩል እንቅስቃሴ ከተጀመረ መሰንበቱን ያስረዳሉ፡፡
ስፖርቱን ወደፊት ለማራመድ እንቅፋት ከሆኑ መሠረታዊ ምክንያቶች መካከል በዋነኛነት ከአደረ ጃጀት፣ ከፋይናንስ፣ ከሰው ኃይል ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች መሆናቸውን የጠቆሙት የኮሚሽኑ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ እንየው አሊ፤ የ10 ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ የተጠቀሱትን ክፍተቶች በጥናት እንዲመልስ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ያስቀምጣሉ፡፡ ስትራቴጂክ ዕቅዱ አገራዊ የስፖርት ሪፎርምን መነሻ በማድረግ በስፋት የተዘጋጀ መሆኑንም ይገልፃሉ። በመሆኑም በአገሪቷ ቀጣይ የስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ለውጥና ውጤት ማምጣት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡ የስፖርት ሴክተሩ ሪፎርም ፕሮግራም ዘርፍን መለወጥ የሚችሉ ብዙ ያመላከታቸው ነጥቦች እንዳሉም ያስረዳሉ። በዚህም ከአደረጃጀት ፣ ከፋይናንስ፣ ከሰው ኃይልና ሌሎችም ጉዳዮች አንፃር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚቻል ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በሪፎርሙ ላይ የሴክተሩ ችግሮች የተለዩ ሲሆን በተመሳሳይ መፍትሄዎች መመላከታቸውንም ያክላሉ። ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውና ከስፖርት ሪፎርሙ የሚቀዳው የ10 ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅድ ዘርፍን የተሻለ እንደሚያደርገውም ያላቸውን እምነት ይገልፃሉ፡፡
አቶ እንድሪስ በበኩላቸው፤ በቀጣይ ዓመት ተግባራዊ የሚደረገው ስትራቴጂክ ዕቅድ ትኩረት ያደረጋቸው አንኳር ጉዳዮች መኖራቸውን በመጥቀስ በሴክተሩ በቀጣይ 10 ዓመታት በትኩረት የሚሰራባቸው ተብለው የቀረቡት ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች እንዳሉ ይናገራሉ:: በመጀመሪያ መንግሥታዊ የስፖርት አደረጃጀቶችን የመፈፀም እና የማስፈፀም አቅም በማጎልበት፤ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን እና የአሠራር ሥርዓቶችን ተግባር ላይ ማዋል ፤ ሕዝባዊ የስፖርት አደረጃጀቶችን በዓለም አቀፍ እና በአገር አቀፍ መስፈርቶች መሠረት ማደራጀት የስትራቴጂክ እቅዱ ትኩረት መሆናቸውን ያስቀምጣሉ:: በሁለተኛ ደረጃ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የማሰልጠኛ ማዕከላት ተደራሽነት፣ ሕጋዊነት እና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ በጥራት የሚገነቡበትን ስልት ሥራ ላይ ማዋል ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ያስረዳሉ። በአህጉር እና ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች በተፈጥሮ ብቃታቸውን መሠረት በማድረግ አገራችንን የሚወክሉ እና ውጤታማ የሆኑ ተተኪ ስፖርተኞችን በሳይንሳዊ ስልጠናዎች ማፍራት ትኩረት ተደርጎ የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑንም ያብራራሉ፡፡ ስፖርት ለማህበራዊ ልማትና ለአገር ብልፅግና ፣ ለሕዝቦች መቀራረብ ፣ ለገፅታ ግንባታ እና ለቱሪዝም ዕድገት መሣሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ትኩረት ሰጥቶ መስራትም የስትራቴጂክ እቅዱ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው። በስትራቴጂክ ዕቅዱ የተጠቀሱትን አንኳር ጉዳዮች መሠረት አድርጎ የተዘጋጀው ግብ ወደ ተግባር መቀየር ከተቻለም የስፖርት ሴክተሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ፤ በአገር አቀፍ የስፖርት ፖሊሲ ባለፉት ሁለት አስር ዓመታት የተመዘገቡ በርካታ አበረታች ውጤቶች ቢኖሩም የአገራችን የስፖርት ዕድገት ከዕድሜው አኳያ ሲመዘን በሚፈለገው ደረጃ ባለማደጉ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ያመላክታሉ። በአሁኑ ወቅት መንግሥት ስፖርቱን እንደ አንድ የልማትና ብልፅግና መሣሪያ አድርጎ በመውሰድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየሰራ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ ሃብታሙ ፤ የስፖርት ዘርፍ በታሪኩ በዚህ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እንደማያውቅ ያብራራሉ:: የብሔራዊ የስፖርት ምክር ቤት በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነትና የበላይ ጠባቂነት መመራቱ መንግሥት ለስፖርቱ ሴክተር የሰጠውን ትኩረት እንደሚያሳይም ያስቀምጣሉ፡፡ በመሆኑም የስፖርት ዘርፍን ከትናንት በተሻለ መልኩ ዛሬ ትኩረት በማግኘቱ ዕድሉን በአግባቡ በመጠቀም ጠንክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
ዳንኤል ዘነበ