በምድር ላይ ህጎች በአራቱም አቅጣጫ ይወጣሉ፤ ህግ አውጪ፣ ህግ ተንታኝ፣ ህግ አስፈጻሚ፣ ህግ ፈፃሚ፣ ዳኛ፣ ዐቃቢ ህግ፣ ጠበቃ፣ ከሳሽ፣ ተከሳሽ፣ ምስክር፣ዋስ፣ … ወዘተ ይኖሩታል። ከህገ ልቡና ዛሬ በየመንደሩ እና በየቤቱ በየፌስቡኩ እስከሚወጡት ህጎች እንሰማለን፤ እናያለን፤ እንተዳደርበታለን፣ እናስተዳድርበታለን፤ ሌሎችን እንዳኝበታለን፤ ራሳችንም እንዳኝበታለን። ከሚሻር ህግ እስከማይሻርና ለዘለዓለም የሚፀና ህግ ባለቤቶችም ነን። ኢትዮጵያውያን የህግን መሰረት ያልለቀቁ ዘመናትን ያስቆጠሩ በህብረተሰብ ዘንድ የተከበሩ ብዙ ስርዓቶች አሉን። ነገር ግን ከሚወጡት ህጎችና መመሪያዎች ብዛት ያልተናነሰ የማይተገበሩና በቸልተኝነት የሚታዩትም በርካታ ናቸው።
ለዛሬ በኢትዮጵያ ህግ ወጥቶለት በመተግበርና ባለመተግበር፣ በመቀጣትና ባለመቀጣት እንዲሁም ላለመማር በማስተባበል ውስጥ የዘለቀውን የደህንነት ቀበቶ (ሴፍቲ ቤልት) ጉዳይ እንመልከት።
ዳራ
የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ በህዝብ ትራንስፖርት አማካኝነት የሚንቀሳቀሱ አካላት በጉዞ ወቅት የደህንነት ቀበቶ በአግባቡ ቢጠቀሙ አደጋ በሚያጋጥማቸው ወቅት አሽከርካሪውንና ከፊት የሚቀመጡ ሰዎችን ከ45 በመቶ እስከ 50 በመቶ ለሞት ተጋላጭነታቸውን እንደሚቀንስና ከኋላ የሚቀመጡ ተጓዦችን ደግሞ ከ25 በመቶ እስከ 35 በመቶ ከሞት ሊታደገቸው እንደሚችል ያሳያል።
የመንገድ ትራፊክን ለመቆጣጠር የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 208/2003 ላይ እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ማንኛውም አሽከርካሪ ከሞተር ብስክሌት በቀር የደህንነት ቀበቶ ሳያስር ማንኛውንም ተሽከርካሪ ማሽከርከር እንደሌለበት እና በተሽከርካሪ ውስጥ የተሳፈረው ሰው የደህንነት ቀበቶ ማሠሩን ማረጋገጥ እንዳለበት ተደንግጓል።
አስገዳጅ መመሪያ
የተጠቀሰውን ድንጋጌ ተግባራዊ ለማድረግና የተሽከርካሪ ደህንነት ቀበቶ ባለማሰር ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ እና ለመከላከል የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የደህንነት ቀበቶ ባለማሰር ምክንያት የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እና ለመከላከል የደህንነት ቀበቶ አተገባበር አስገዳጅ መመሪያ ማውጣቱ ይታወቃል። በኢፌዴሪ ትራንስፖርት ሚኒስቴር የትራንስፖርት ባለስልጣን የወጣው የተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ መመሪያ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ጉዳት 50 በመቶ ለመቀነስ የሚያስችል ነው።
የመመሪያው ዓላማ
የመመሪያው ዓላማ የተሳፋሪዎችን ደህንነት ቀበቶ አጠቃቀም ስርዓት በማሳደግ በአደጋ ወቅት በተሳፋሪዎች ላይ የሚደርሰውን የአደጋ ተጋላጭነት መጠን መቀነስ ሲሆን፤ በተለይ ተሳፋሪው የትራፊክ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት በፊተኛው ወይም በጎን ባሉ የተሽከርካሪው መስታወቶች ተስፈንጥረው እንዳይወጡና የጉዳት መጠናቸው እንዳይባባስ እንዲሁም የአደጋ ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
በተሽከርካሪዎች ላይ የደህንነት ቀበቶ እንዲኖር በማድረግ አሽከርካሪው እና ተሳፋሪዎቹ ቀበቶ እንዲያሥሩ በማድረግ በጉዞ ወቅት አደጋ ቢከሰት የሚደርሰውን የከፋ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መቀነስ ሌላኛው የዚህ መመሪያ ዓላማ ነው።
ተግባራዊነትና ክትትል
የመመሪያው ተግባራዊነት እና ክትትል የሚደረግባቸው ተሽከርካሪዎች፤ የመንግሥት፣ የግል፣የጭነት እና ህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ሲሆኑ፤ ከ5 እስከ 8 መቀመጫ ያላቸው ተሽከርካሪዎች ሁሉም ተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ ማሰር ይጠበቅባቸዋል።
እስከ 150 ኪሎ ሜትር የሚጓዙ ሚኒባሶች እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ልዩ ባሶችና ሀገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻዎች፣ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ ከ12 እስከ 15 ሰው የሚጭኑና በከተማ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ በከተማ አውቶቡሶች እና የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት ሰጭዎች ከፊት የሚቀመጡ ተሳፋሪዎች ሲሆኑ በመመሪያው አንቀፅ 5 ንዑስ አንቀፅ 6 ነጥብ 5 መሰረት ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች መመሪያውን በራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ተፈቅዷል።
መመሪያውም ተቋሙ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በመንግሥት፣ በኤምባሲዎች፣ በግል የንግድ ድርጅት፣ ለግል አገልግሎት በሚውሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ተፈጻሚ ነው በማለት በያዝነው ዓመት ከጥር ወር መጀመሪያ አካባቢ ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል።
ከጥር 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግራዊ የሆነው መመሪያው በተሽከርካሪዎች ላይ በሚደረገው ቁጥጥር ከአሽከርካሪው አጠገብ ወይም ገቢና የሚቀመጡ ተሳፋሪዎች መቀመጫ የደህንነት ቀበቶ ያሌላቸው ተሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ ርምጃ የሚወሰድ ሲሆን፤ በአግባቡ የማይሠራ የደህንነት ቀበቶ ያላቸው ተሽከርካሪዎች የደህንነት ቀበቶ እንደሌላቸው ተቆጥሮ ርምጃ እንደሚወሰድባቸውም ነው የተቀመጠው።
የደህንነት ቀበቶ ማሰር አሽከርካሪው ወይም ተሳፋሪው አደጋ በሚከሰት ወቅት በፊተኛው ወይም በጎን ባሉ የተሽከርካሪው መስተዋት ተስፈንጥረው እንዳይወጡ በማድረግ በዚህ ምክንያት ይደርስ የነበረውን ከፍተኛ አደጋ ለመቀነስ እና አሽከርካሪዎች በአደጋ ወቅት ተሽከርካሪውን ለመቆጣጠር እንዲችሉ ያግዛል።
በዚሁ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ከከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር መመሪያው ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ ቁጥጥር በማድረግ ወደ ህጋዊ ርምጃ የሚገባው ከአሽከርካሪው አጠገብ (ጋቢና) የሚቀመጡ ተሳፋሪዎች ላይ ብቻ ሆኖ በቀጣይ በሂደት በመመሪያው የተቀመጡት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆኑ አስታውቋል። በከተማዋ በሁሉም ተሽከርካሪዎች ከአሽከርካሪው አጠገብ ወይም ጋቢና የሚቀመጡ ተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶን መጠቀም ግዴታንም አስቀምጧል።
መመሪያና ቁጥጥር-ሆድና ጀርባ
በእርግጥ የደህንነት ቀበቶ በሌላቸው ተሽክርካሪዎች ላይ ቅጣት የሚጥለው መመሪያ የተሽከርካሪውን ዕድሜና የአሽከርካሪውን የኑሮ ደረጃ ያገናዘበ አይመስልም። ቀድሞውኑም ከሹፌሩ በስተቀር መች ቀበቶ አላቸውና። አንዳንድ ተሳፋሪን እያገለገሉበት ያሉት መኪናዎች በጣም የቆዩና ያረጁ በመሆናቸው ቀበቶ ቀርቶ ፍሬን የሚይዙት እንኳን ‹‹በፈጣሪ ቸርነት›› ነው። ስለሆነም ብዙዎቹ የተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ መመሪያ አሽከርካሪዎች ምንም ዝግጅት ያደረጉ አይመስሉም። ቀበቶ አላቸው የሚባሉ መኪኖች እንኳን የደህንነቱን ቀበቶው ያዘጋጁት ለይስሙላና እንዳይቀጡ ብለው እንጂ ውስጡ ቢፈተሽ ብዙ ጉድ ይወጣዋል።
ቀበቶ የማድረግ ጥቅሙ በዋናነት ለባለቤቱ ሲሆን ለሌላውም እግረኛ መንገደኛም ሆነ አሽከርካሪ ጥቅሙ አንድ እና ሁለት የሚባል አይደለም። የደህንነት ቀበቶ ያላጠለቀ አሽከርካሪ አለማጥለቁን ባወቀበት ቅፅበት ከጉዞዉ ተገቶ ቀበቶውን ለማድረግ ይገደዳል፤ ነፍሱን/አካሉን እና ንብረቱን ከአደጋ ለመታደግ ፣ ንብረት ከማውደም እና አካልን/ነፍስን ከማጥፋት ሌላውን ለመታደግ ፣ አልፎ ተርፎም ከመቀጣት እና የቅጣት ቁጥሩን ላለማብዛት እና ለመቀነስ ነው። የተሽከርካሪ መቀመጫ ቀበቶ ማሰር በትንሹ በአደጋ ጊዜ በቀላሉ ከተሽከርካሪው ጋር ከተቀመጡበት ተስፈንጥረው እንዳይጎዱ እዚያው ወንበሩ ጋር ደግፎ በመያዝ አደጋን ለመቀነስም ጭምር ነው።
ነገር ግን እዚህ ደርሰናል። የህግ መብራቶችን እንደ ጭፈራ ቤት መብራት ማየቱ ሳያንሰን የወጣውን መመሪያ ወደ ጎን በማለት ቀበቶ ይሁን ቡቱቶ፤ ብቻ ምንነቱ ያልታወቀ ነገር ለይስሙላ በማሰር ነፍስን ለህልፈት ሰጥቶ ከቀጪ አካል ለማምለጥ ብቻ ሙከራ የማድረግ አባዜ። በነገራችን ላይ ለተሳፋሪ ቀበቶ ባለመስጠት የትራፊኩን ፊሽካ ሰምቶ እንዳልሰማ የሚያደርግ ወረርሽኝም መጥቷል። የፊሽካው ድምፅ በጨመረ ቁጥር የመኪናውም ፍጥነት የዚያኑ ያህል ይንራል።
ከቤታችን ወጣ ስንል እኮ ከህግ ወጣ ያሉ ድርጊቶችን በአይነት በአይነት ነው የምንኮመኩመው። ብዙ ሹፌሮቻችን ተሽከርካሪው አጠገቡ ከሚርመሰመሰው እግረኛና አጠገቡ ላለው ተሳፋሪ ቀበቶ እንዲጠቀም ከማድረግ ይልቅ ከሩቅ የቆመ ትራፊክ ፖሊስ ጎልቶ ይታየዋል። የአደጋ መከላከያ ቀበቶውን ለይምሰል ደረታቸው ላይ እንደ ከረባት ጣል የሚያደርጉ፤ የተከለከለ ቦታን ለራሳቸው የፈቀዱ ፤ ትርፍ የጫኑትን፤ መብራት እንዳይዛቸው እንደ ቀስት የሚወረወሩትን፤ መብራት ሲለቃቸው እንደ ተወዳዳሪ መኪና ተፈናጥረው የሚነሱትን፤ ዜብራ ላይ በቀደመ የሚጫወቱትን ሳንታዘብ ወደ ቤታችን አንመለስም። ትራፊክ ፖሊስ ይዞት መንጃ ፍቃድ ሲጠየቅ ገንዘብ የሚያወጡትንማ መኪናቸው ይቁጠራቸው።
በአሽከርካሪው ቸልታም ሆነ በሌላ ምክንያት፣ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ተሽከርካሪ የሚያደርሰውን የንብረትና አሠቃቂ የሕይወት ጥፋት ሁላችንም እናውቀዋለን። ለራሱ የደኅንነት ቀበቶ ያሠረ ሹፌርና ተሳፋሪ ግን በአመዛኙ ከሚደርስበት የአደጋው ጉዳት ሊያመልጥ ወይም ጉዳቱን ሊቀንስ እንደሚችልም እናውቃለን። አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሳያደርግ (ለራሱም ሆነ ለተሳፋሪ) ቀበቶ ሳያስር የሚያሽከረክር ሾፌርን አይቶ ባላየ የሚያልፍ ትራፊክ ፖሊስም ያጋጥመናል። ዓላማው ጉዳትን በመከላከል የተሳፋሪዎችን ደኅንነት መጠበቅ ነውና መቅጣት ቢያቅተው ምክርና ማስጠንቀቂያ መስጠት እንዴት አይቻለውም?
ለመመሪያው ተግባራዊነት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም ክፍተቱ ግን በስፋት ይስተዋላል። በተለይ የተሽከርካሪ ባለቤቶች፣ አሽከርካሪዎች፣ የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት እና ተሳፋሪዎች ነገሩን በቸልታ ያለፉት ይመስላል። የተሽከርካሪ ባለቤቶች በአግባቡ የሚሠራ የደህንነት ቀበቶ በተሽከርካሪው ላይ እንዲሟላ ማድረግ እና የደህንነት ቀበቶው በተገቢው ሁኔታ የሚያገለግል መሆኑን በየጊዜው የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ዘንግተውታል። የሚጨነቁት ከቅጣት ማለፍን እንጂ ነፍስ ማዳን ላይ አይደለም።
በአግባቡ የሚሠራ የደህንነት ቀበቶ የሌላቸው በርካታ ተሽርካሪዎች አሉ። ከዚህ አንጻር ማንኛውም የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት በዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ወቅት የአሽከርካሪውና የተሳፋሪዎች የደህንነት ቀበቶ መኖሩን እና በአግባቡ የሚያገለግሉ መሆኑን በትክክል እያረጋገጠ ነው ለማለት አያስደፍርም።
አሽከርካሪውም የደህንነት ቀበቶን በአግባቡ በማድረግ ተሳፋሪዎች በአግባቡ ማድረጋቸውን በራሱ ወይም በረዳቱ በኩል ማረጋገጥ ኃላፊነቱን የሚወጣው ለይስሙላ ብቻ ነው። በየታክሲዎቹ ውስጥ ፊት ለፊት ባሉት መቀመጫዎች ሁለት ተሳፋሪ አስቀምጠው ‹‹ፍቅር ካለ አንድ ቀበቶ ለሁለት ተሳፋሪ በቂ ነው›› የሚሉ አሽከርካሪዎችም አልጠፉም። እያንዳንዱን ተሳፋሪ ተሽከርካሪው ከመነሳቱ በፊት የደህንነት ቀበቶ ማሠሩን ማረጋገጥ ስለሚኖርበት ‹‹እርሷን ነገር ዝም ብለህ ጣል አድርጋት ይላል›› ላለመከሰስ ብቻ። ታዲያ ጣል የምትደረገዋ ቀበቶ መሳይ ጨርቅ ከትራፊክ ፖሊስ እጅ እንጂ ከትራፊክ አደጋ አታስጥልም።
ተሳፋሪዎችም የደህንነት ቀበቶን በአግባቡ በማሰር የራሳቸውን ህይወት ከትራፊክ አደጋ መታደግ ሲኖርባቸው ለተሽከርካሪው በማዘን ይሁን አሊያም ችግሩን ለማባበስ በማይታወቅ ምክንያት ነገሩን ቸል ሲሉት ይታያል።
እንደ መውጫ
ዞሮ ዞሮ ላለብን ችግር የመፍትሔ አካል ካልሆንን እራሳችን የችግሩ ተባባሪ ነን። እናም የችግሩ አምራችም ሸማችም የሆነው እኛ ለችግራችን የመፍትሔ አካል የማንሆነው እስከ መቼ ነው? ህግን ሳይሆን ህግ አስከባሪውን የምንፈራው እስከ መቼ ነው? እስከ መቼ ነው ለወጡት ህጎች ተገዥ ባለመሆን ደም እና እንባስ መፍሰስ የሚቆመው?
የትራፊክ ሕግን ማክበር፣ የደኅንነት ቀበቶ ማሰር፣ መኪናን ጥሩ አድርጎ መያዝና የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ አለማሽከርከር የአሽከርካሪውንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ሊያድን ይችላል። እነዚህ ምክሮች ከአደጋ ሊያድኑ የሚችሉ ቢሆኑም ሊያድኑ የሚችሉት ተግባራዊ ካደረግናቸው ብቻ ነው። በመሆኑም መመሪያውን ያወጣው አካልም ሆነ ሌሎችም ባላድርሻ አካላት ተግባራዊነቱን በደንብ ሊፈትሹት ይገባል። ይህ ሲባል ተሳፋሪ ቀበቶ ማሠሩን ብቻ ሳይሆን ‹‹እውነት ያሰረው ነገር ትክክለኛ የመኪና ቀበቶ ነው ወይ›› ብሎ መመርመር ይገባል።
ዛሬም ለሚያሽከረክሩትም ሆነ ለማናሽከረክረው፣ ቀበቶ ለምናስረውም ሆነ ለማናስረው፣ ህጉን ጠብቀን በእግረኛ መንገድ ለምንጓዘውም ሆነ ለማንጓዘው፣ የእግረኛ ማቋረጫ (ዜብራ) ለምንጠቀመውም ሆነ ለማንጠቀመው ሁሉን በአንድ ስለሚገዛ እና ልብ ልንለው ስለሚገባ ነገር እየጋለብን ካለንበት ከአውሎ ንፋስ ከፈጠነ ዝቅጠታችን ማንሳት ወደድኩ፤ ሁላችንም ቆም ብለን የደህንነት ቀበቷችንን ጠበቅ እንድናደርግ አደራዬ የበረታ ነው።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
አዲሱ ገረመው