አዲስ አበባ፡- ለፓርኪንሰን ሁሙማን የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ውስን መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን መሪ አቶ አበባው አየለ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ፤የፓርኪንሰን ህሙማን ህክምና የሚያገኙት በሆስፒታሎች ውስጥ ቢሆንም፣ አገልግሎት አሰጣጡ ግን ውስን ሆኗል፡፡
የፓርኪንሰን ህመም ህክምና በባህሪው አስቸጋሪ መሆኑን አቶ አበባው ጠቅሰው፣ የበሽታውን ምልክቶች በማየት ካልሆነ በስተቀር በህክምና መሳሪያዎች ብቻ በመመርመርና ውጤቱን በማወቅ ህክምና መስጠት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ይህም የህክምና አገልግሎት አሰጣጡን ውስን እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡
በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆንና በተለይም የነርቭ ህክምና ባለሙያዎች ቁጥር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘት በሆስፒታል ደረጃ ህክምናውን በተሟላ መልኩ ለመስጠት ችግር መፍጠሩን ቡድን መሪው ገልፀው፤ ህክምናው በሚሰጥባቸው ሆስፒታሎች ውስጥ ለሚገኙ ሃኪሞች በህመሙ ዙሪያ አጫጭር ስልጠናዎች አለማግኘታቸውና የግብአት አቅርቦት እጥረት መኖር አገልግሎት አሰጣጡን እንደገደበው አስታውቀዋል፡፡
ቡድን መሪው ህመሙ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም፣ በትምህርት ቤት ጤናና ስርአተ ምግብ ፕሮግራምና በአእምሮ ጤና ስትራቴጂ እቅድ ውስጥ ተካቶ እየተሰራበት እንደሆነ ጠቅሰው፣አገልግሎቱን ለማስፋት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሁለንተናዊ እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስባዋል፡፡ ከህክምና አገልግሎቱ ባሻገር ታማሚዎች በማህበረሰቡ የሚደርስባቸውን አድሎና መገለል ብሎም ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታትም በአጋርነት መስራት እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡
ከህሙማን ማህበሩ ጋር በመተባበር አጫጭር ስልጠናዎችን ለሃኪሞች በመስጠት የህክምና አገልግሎቱን ለህሙማን የበለጠ ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻልም ቡድን መሪው ተናግረው፣ በሃገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ጤና ነክ ዩኒቨርሲቲዎች ህመሙን በስርአተ ትምህርታቸው ውስጥ በማካተት የሚያስተምሩበት ከሆነ በዘርፉ የሚታየውን የባለሙያዎች እጥረት መፍታት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
ፓርኪንሰን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰ የሚሄድ እንቅስቃሴን የሚያውክና በአእምሮ ህመም ስር የሚካተት የስነ ነርቭ ህመም መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ በጥናት የተረጋገጠ መረጃ ባይኖርም በኢትዮጵያ የፓርኪንሰን ህሙማን ቁጥር ከ200 እስከ 300 ሺ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011
በአስናቀ ፀጋዬ