አቶ አበራ ደበበ ይባላሉ። በሰባት ቤት ጉራጌ እነሞር ጉንችሌ አካባቢ ተወልደው አደጉ፤ በልጅነታቸውም የቀለም ትምህርታቸውን ጀምረው እስከ ስምንተኛ በዚሁ አካባቢ ተማሩ። ከዚህ በላይ ለመቀጠል ግን በወቅቱ ያስተምሯቸው የነበሩ አያታቸው በሁለት ነገር ተፈተኑ። በአንድ በኩል አበራን ከዚህ በላይ ማስቀጠል ያለመቻል አቅም ወሰናቸው። በሌላ በኩል የወቅቱ ተማሪ የአቶ አበራ የስምንተኛ ክፍል ያስመዘገቡት ጥሩ ውጤት አሳሳቸው። እናም አዲስ አበባ መርካቶ አካባቢ ወደሚኖሩ እህታቸው ዘንድ እንዲማሩ በ1964 ዓ.ም አካባቢ ወደ አዲስ አበባ አድርሰዋቸው ይመለሳሉ። አቶ አበራ ግን የታሰበው ቀርቶ ያልታሰበ ገጠማቸው። የወቅቱን የቀለም ቀንድ አቶ አበራ እድላቸው ከአክስታቸው ልጆች ጋር የመማር ሳይሆን የቤት ጠባቂነት ሆነ።
ይህ ያልተዋጠላቸው አቶ አበራም በዚህ መልኩ ከመቀጠል ይልቅ የአክስታቸውን ቤት ትተው በወቅቱ ልደታ ፍርድ ቤቱ አካባቢ ሊስትሮ ይሰራ የነበረ ወንድማቸው ጋ መሄድን መረጡ። ይሄም አልተሳካም። ምክንያቱም ወንድማቸው በወቅቱ እርሳቸውን ጨምሮ የማኖር አቅም ስላልነበረው በዛው አከባቢ ሜዳ ላይ የነበሩ ልጆች ጋ ተጠግተው እርሳቸውም የሊስትሮ ስራ ጀመሩ። በዚህ መልኩ ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ የትምህርት ጥማታቸውን ለማስታገስ ሲሉ ስምንተኛ ክፍልን ድጋሚ ተፈትነው 98 ነጥብ በማስመዝገብ ወደዘጠነኛ ክፍል ማለፍ ቻሉ።
ይሁን እንጂ በድጋሚ አቅም ፈትኗቸው የጓጉለትን ትምህርት ማጠናቀቅ ስላልቻሉ ወታደር ቤት ይገባሉ። በውትድርና ዘመናቸውም በሶማሌ አካባቢ በታንከኝነት አገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተው በ1983 ዓ.ም በነበረው የስርዓት ለውጥ ምክንያት ከውትድርናው ዓለምም ይለያያሉ። እናም ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ራሳቸውን ደጉመው ለመኖር ይወስናሉ። ይሁን እንጂ ነገሮች አሁንም እንደጠበቁት አልሆነም፤ ይልቁንም ቤታቸው ተወርሶ ስለጠበቃቸው ማረፊያ አልባ ውጪ አዳሪ ሆኑ። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም በግ ተራ አካባቢ ገመድ እየሸጡ ራሳቸውን መደጎምና ከጎዳና ወደ ኪራይ ቤት መሸጋገር ቻሉ።
ሆኖም እድል ሆነና ከደጅ ወደቤት በገቡ በ27 ቀናቸው በስራ ላይ እያሉ በመውደቃቸው ተሰብረው የአልጋ ቁራኛ ይሆናሉ። በዚህ ሁኔታ ያለ ጠያቂና ደጋፊ ዓመት ያሳልፋሉ። በዚህ መሃል የቶሎሳ ሰፈር ያፈራቸው አዳነ ያገኟቸዋል። በአንዲት ምንጣፍ ላይ ኮሪደር በምታክል በቆርቆሮ በተከበበች ቤት ቤት መሰል ነገር ውስጥ አቅንተው፣ የቆሸሸ ገላቸውን አጥበውና ጸጉራቸውን አስተካክለው ያነሷቸዋል። በምግብ የተጎዳ ሰውነታቸው በአልሚ ምግብ እንዲጠገን፤ በህመም የተጎሳቆለ አካላቸው ህክምና እንዲያገኝ፤ ቤት የናፈቀ ማንነታቸው በቀበሌ ቤት እንዲያርፍ ያደርጉላቸዋል።
የዚህ ታሪክ ባለቤት አቶ አበራ እንደሚሉት፤ የቶሎሳ ሰፈር የወለዳቸው እንደ አባይነህ ደምሴ ያሉ ወጣቶች ተረስተው ከወደቁበት አንስተው እንደሰው እንዲኖሩ አስችለዋቸዋል። አሁንም እንደልብ ወጥተው መስራት የሚችሉበት ደረጃ ባለመድረሳቸው በእነርሱው ድጋፍ ስር ናቸው። ሆኖም የህመማቸው ጉዳይ ከአገር ውጪ መፍትሄ የሚያገኝ በመሆኑ በእነዚህ ወጣቶች አቅም የሚከወን አይደለም። እርሳቸው ግን አሁንም መዳንን ተስፋ በማድረግ ከቶሎሳ ሰፈር ወጣቶችና ወጣቶቹ ከመሰረቱት እድሮች ህብረት በወሰዱት የበጎነት አስተምህሮ ነገ ራሳቸውን ችለው ሌሎችን ስለመርዳት ያልማሉ። ለዚህ ግን አገር ሰላም ሊሆን፤ እንደነዚህ ወጣች ያሉ የበጎ ተግባር ወጣቶችና ማህበራት ሊታገዙ፤ መንግስትና ሌሎችም አካላት መልካምነትን ሊደግፉ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን እርሳቸውና እርሳቸውን መሰል ተስፈኞች ችግሮቻቸውን ተሻግረው ከተስፋቸው ጫፍ ይደርሳሉ።
አቶ አለማየሁ ደርሶ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ተወልደው ያደጉና እየኖሩም ያሉ የቶሎሳ ሰፈር ልጆች አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ይሄን ማህበርና እድር በመጀመሪያ ሲያቋቁሙ አብሯደግ በሚል ነው የቶሎሳ ሰፈር ልጆች በአንድ ላይ የተደራጁት። ይህን ያደረጉት ደግሞ ትናንት እነርሱን ያሳደጉ እናትና አባቶች ያለ ጧሪና ደጋፊ የአረጋዊነታቸውን ጊዜ መግፋትን ምክንያት በማድረግ እነዚህን አረጋውያን ለመደገፍ ሲሆን፤ ይሄን ሀሳባቸውን ይዘውም ወደ ሻምበል መኳንንት ይሄዳሉ። የሀሳቡ ጠንሳሾች አብሮ አደጎችና ሌሎች በውጭ ካሉ አብሮአደጎቻቸው ጋር ቢተባበሩ ለእነዚህ አረጋውያንና ሌሎች ደጋፊ ያጡ ሰዎችን ከመርዳት አኳያ ምን መስራት እንደሚችሉም ያማክሯቸዋል። እርሳቸውም በሚችሉት ሁሉ እንደሚያግዟቸው በመግለጽ ስላበረታቷቸው አብሮ አደጎቹ ወጣቶች ሶስት(ቶሎሳ ሰፈር ቁጥር አንድ፣ ቶሎሳ ሰፈር ቁጥር ሁለት እና የአዲስ ምዕራፍ የቁም መረዳጃ) ወንድማማች የህብረት የመረዳጃ እድሮችን መፍጠር ቻሉ።
ከዚህ በኋላ የሚረዷቸውን ሰዎች እየዞሩ በመመልመል በትክክል እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች እና በምን መልኩ ሊረዱ እንደሚችሉ የመለየት ስራን ጀመሩ። ሂደቱ አድካሚ ቢሆንም ዛሬ ላይ ከ200 ያላነሱ ሰዎችን ለመርዳት በቅተዋል። አቅመ ደካሞችን በገንዘብም ለበዓል የሚሆን ተጨማሪ ድጋፍም የፈረሰ ቤት የመስራትና የመጠገን ተግባርም ሲያከናውኑ፤ በከተማ አስተዳደሩ እስኪጀመር ድረስም የተማሪዎች ምገባ ሲያደርጉም ቆይተዋል። በሳምንት ሁለትና ሶስት ጊዜ የኩላሊት ዕጥበት ለሚያከናውን ወጣትም የመኖር ተስፋ ለመሆን ችለዋል። እስካሁንም መልካም የሚባል ተግባርን እያከናወኑ ይገኛል። ሆኖም በሽታም ሆነ ከአቅም ማጣት ጋር የተያያዘ ሌላ ችግር ቀጠሮ ይዞ አይመጣምና የእነርሱን እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ከዚህ የበለጠ መስራትና መደገፍ ይፈልጋሉ። ለዚህ ደግሞ መንግስት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ ሀሳባቸውን ሊያጤንና ሊደግፍ ይገባል። ምክንያቱም ዛሬም ችግር ደብቋቸው በዓልን በራቸውን ዘግተው የሚውሉ አዛውንቶች፤ በጉብዝናቸው ወቅት ያለጠያቂ በአልጋ የዋሉ ወንድምና እህቶች በርካታ ናቸው። እናም በመንግስት በኩል መጠነኛ ድጋፍ ቢደረግላቸው ከዚህ የላቀ መስራት እና ከሰፈር አልፈው በወረዳ፣ ከወረዳም አልፈው በክፍለ ከተማና በከተማ ደረጃ በመድረስ አርዓያነት ያለው ተግባር ለማከናወን አስበዋል።
አቶ አባይነህ ደምሴ፣ በዚሁ በቶሎሳ ሰፈር ተወልዶ ያደገ ነው። እርሱም እንደሚለው፤ የተሰራው ስራ በጣም ብዙ ነው። እርካታውም የዛኑ ያክል ነው። ይሄን የማድረግ ሀሳቡ በእነርሱ ውስጥ የነበረ ቢሆንም ቶሎሳ ቁጥር አንድ እና ሁለት እንዲሁም አዲስ ምዕራፍ መረዳጃ እድሮችን በአንድ በማድረግም በሻምበል መኳንንት በኩል ሀሳባቸው ቀንቶ ወደተግባር እንዲገቡ ሆነዋል። በእስካሁን ሂደታቸውም ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች እያደረጉ ሲሆን፤ በዚሁ ቀበሌ ወጣቶች ሆያሆዬ ጭምር ጨፍረው በሚያገኙት ገንዘብ በመታገዝ ወደ አራት ቤቶች አድሰው መስራት ችለዋል።፡ አበራን ጨምሮ ሌሎች ወገኖችንም በመደገፍ ትልቅ እርካታን ማትረፍ ችለዋል።
ይህ ደግሞ ሰፈር ውስጥ ሊረዱ የሚገባቸው ነገር ግን ተረድተው የነበሩና ሊታዩ ያልቻሉ እናትና አባቶች እንደእግዚአብሔር ፈቃድ ሄደው የማየታቸው ውጤት ሲሆን፤ አቅም በፈቀደና ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው አግባብ በርካቶችን መደገፍ የሚችሉበት ደረጃም ደርሰዋል። ብዙ አይነት ተረጂዎች ያሏቸው እንደመሆኑም ድጋፉንም ምን አይነት ተረጂ እንዳለና በምን መልኩ ሊረዱ እንደሚገባ በመለየት ያከናውናሉ። በዚህም ኮሚቴው ተነጋግሮ ገንዘብ ለሚገባው ገንዘብ፤ ቤት ለሚሰራለት ቤት፤ አቅም ላጠራቸው ደግሞ ለበዓል መዋያ የሚሆን ስጋም ሆነ እንርሱ የሚፈልጉትን እንዲያደርጉ ገንዘብ እንዲሰጣቸው ይሆናል።
‹‹አበራን ያገኘሁት እኔ ነኝ። ያገኘሁትም ሰፈር ባለ ጓደኛዬ አማካኝነት ሲሆን፤ ስናገኘው የነበረበት ሁኔታ ከአዕምሮ በላይ ነበር፤›› የሚለው አቶ አባይነህ፤ ሲያገኘውም በቆርቆሮና ማዳበሪያ ከታጠረች በጣም ጠባብ ቤት ውስጥ መሬት ተኝቶ እንደነበር ያስታውሳል። በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ሆኖ ግን በተጎሳቆለ ፊቱም ላይ ቢሆን የተስፋ ድባብ እንደነበር በመጠቆምም፤ ከዚህ በኋላ ነው ከምግብና አልባሳት ጀምሮ አልጋና ቤትም እንዲያገኝ ከእድር ማህበራቱ ጋር ተሰርቶ ለዚህ ደረጃ እንደደረሰ ይገልጻል። ሆኖም እነርሱ የሚያደርጉት የተወሰነ እርዳታ እንደመሆኑ መንግስት ከጎናቸው ሆኖ እንዲህ አይነት ሰዎች ተንቀሳቅሰው ራሳቸውን የሚችሉበት ነገር ቢደረግ ምኞታቸውም፤ ፍላጎታቸውም መሆኑን ይገልጻሉ።
አቶ አባይነህ እንደሚለው፤ የታመሙ እናትና አባቶቻችንን ለማሳከምም ጤና ጣቢያ በመሄድ የጤና መድን ፈንድ ካርድ እንዲወጣላቸውና ህክምናውን እንዲከታተሉ እያደረጉ ነው። ከህክምናው ባለፈም ከጎናችሁ አለን እያሉ ብዙ ስራ እየሰሩ ነው። ይሄን ስራ ለማከናወን በሁለት መልኩ የገቢ ምንጭ ያላቸው ሲሆን፤ አንደኛ፣ ከሶስቱም ማህበር በየወሩ ከሚዋጣ ብር ነው። ሁለተኛውም በቶሎሳ ሰፈር ያደጉና በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያኖች በሚልኩት ገንዘብ ነው። እነዚህ ሁለቱ አንድ ላይ ተሰባስበው ነው እርዳታው የሚከናወነው። አሁንም ይሄው ድጋፍ የሚቀጥል ሲሆን፤ በውጭ ያሉትን በማቀናጀትና ቀሪ እድሮችንም በማስተባበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል። በቀጣይም መንግስት ከጎናቸው ከሆነ ከዚህ የተሻለና የሰፋ ጥሩ ስራ የመስራት ተስፋን ሰንቀዋል። ለዚህም ህዝቡም በሞራል፤ መንግስትም በድጋፍ ከጎናቸው እንዲሆን የእነዚህ ወጣቶች መልዕክት ነው።
ሻምበል መኳንንት ነጋሽ፣ የወረዳ እድር ምክር ቤት ሰብሳቢ ናቸው። ስለ አካባቢው እድሮችና ወጣቶች ሲያብራሩም፤ በወረዳው 24 እድሮች አሉ፤ እነዚህን እድሮች በማሰባሰብ የእድሮች ምክር ቤት አቋቁመን ነው በመስራት ላይ የምንገኘው። የእድር ምክር ቤቱ እንዲቋቋም ያስፈለገበት ዋናው ምክንያትም በዚህ ሰፈር ውስጥ ከ1985 ጀምሮ በመፈናቀልና መሰል ምክንያት አደጋ ላይ የነበሩ ብዙ ወንድምና እህቶቻችን ስለነበሩ እየተለመነ ነበር ቀብር የሚካሄደው። ይሄን ነገር ለማቆም ምን ማድረግ አለብን በሚል ዓላማ ተነሳስተን ከዚህ በኋላ ልመና መቆም አለበት ብለን አንድ በቁምም ጭምር መረዳዳት የሚችል እድር አቆምን። እድሩም በአምስት ብር የተጀመረ ሲሆን፤ ዓላማውም ሰዎች በህይወት እያሉ መረዳዳት የሚቻልበትን እድል መፍጠር ነው። ይሄንንም በመተዳደሪያ ደንባችን ለተወሰኑ መንግስታዊ ላልሆኑ ውጭ እርዳታ ድርጅቶች ጭምር በማሳየታችን ከእኛጋር ለመስራት መጡ። በዚህም ወላጅ አልባ ህጻናትን፣ በኤች.አይ.ቪ የተጠቁ እህቶችና ወንድሞቻችንን በመርዳት ሂደት ‹‹ፍቅር ለህጻናት›› የሚል ድርጅት ከጎናችን ሆኖ መስራት ጀመርን። በዚህም 865 ህጻናትን እንረዳ ነበር።
በዚህ ጊዜ ግን ከመንግስትም ከሌላም አካል ብዙ ጥያቄዎች የመጡብን ሲሆን፤ ይሄ የእርዳታ ድርጅት ወይስ እድር ወይስ ሌላ የፖለቲካ ድርጅት ነው በሚል ብዙ ጥያቄዎች ቢቀርቡብንም እኛ ግን ባለመፍራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ስላደረግን ሌሎችም እድሮች ይሄኛው እድር ከሰራ ለምን ሌሎቻችንስ አንቀየርም የሚል ጥያቄ በማንሳት መቀየር ጀመሩ። ከዛ በኋላ ሰፈር ውስጥ ያለን አራት እድሮች አንድ ላይ ሆነን መስራት ጀመርን፤ በሂደት ወደሰባት አደግን። እያለም አሁን ላይ 26 ደርሰናል። ይላሉ።
ሰዎች የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖራቸውም የእኛ ስራ ዓላማ ግን ሰው ከመሞቱ በፊት እንዴት ሊረዳ ይገባዋል፤ በሰፈራችን ውስጥ ያሉ ችግሮችንስ እንዴት እንፍታ የሚል ነው። በዚህም ብዙዎችን ከህመም ማዳን፣ ብዙዎችን ከወደቁበት ማንሳት፣ ብዙዎችን ለችግራቸው መድረስ ተችሏል። በዚህ ሂደት ውስጥ እያለን ነው የቶሎሳ ሰረፍ ልጆቻችን ይሄን ስራ ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚወስድ ሀሳብ ይዘው የቀረቡት። እኛ ደግሞ የምንፈልገው ይሄን ነበር። ምክንያቱም እኛ አሁን በእድሜም እየገፋን በመሆኑ ነገ ትተነው ስንሄድ የእኛን ታሪክ ተከትለው መሄድ የሚችሉ ወጣቶችን ማየት እንፈልግ ነበር። በመሆኑም እነዚህ ወጣቶች በሶስት የእድር ማህበራት ተዋቅረው ወጡ። ይህ ደግሞ ለእኛ ለአንጋፋዎቹ ትልቅ የምስራችና እድል ነበር።
ከዚህ በኋላ በየቦታው እየዞሩ የምናውቃቸውን ነገር ግን መርዳት ሳንችል የተረሱትን እናትና አባቶች ነው እያወጡ መደገፍ የጀመሩት። እነዚህ አዛውንቶች ደግሞ አይደለም አንድ ሺ ብርና አምስት መቶ ብር ቀርቶ 50 ብር ሲሰጣቸው ትልቅ ነገር ሆኖባቸው ምን እናድርገው የሚሉ እናትና አባቶችን መርጠው ነው ያመጡት። እነዚህ ወጣቶች ዛሬ ደርሰው የእናትና አባቶቻቸውን ጓደኞች ሲረዱ ማየት ያስደስታል። ወጣቶቹ ቤት ማደስን ከመስራትም ባለፈ በትምህርት ቤት ምገባ 164 ህጻናትን በትምህርት ቤታቸው ሁሉን ነገር አሟልተው መመገብ ጀምረው ነበር።
የሻምበል መኳንንት እንደገለፀው፤ ይህ ስራቸው ሲታይ እነዚህ ወጣቶች ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባ ነበር። በዚህ ረገድ እንደ መንግስትም ድጋፍ አልተደረገላቸውም። እነርሱ ግን ይሄንን በመስራታቸው ሰዎችን ከሞት አድነዋል፤ ደካሞችን መደገፍ ቤት የወደቀባቸውን አቅንተው ማደስና ከቤት ማሳደር፤ የተቸገሩትን ማገዝና የታመሙ በአልጋ ቁራኛ ወድቀው ጭምር የተረሱትን አስታውሰው መደገፍ አችለዋል። በዚህም ደካሞችና አዛውንቶች ወገን አለኝ፣ ልጆቼ ረዱኝ የሚሉበት፤ በችግራቸው ፈጣሪን እያማረሩና ሞትን እየተመኙ ትውልድን ከመውቀስ ይልቅ ፈጣሪን አመስግነውና ወጣቶቹን መርቀው የሚኖሩበት እድሜ የሚለምኑበት እድል ተፈጥሯል። ይሄም ለእነዚህ ወጣቶች ይሄን ሲያዩ ደስታና እርካታን ተላብሰው የበለጠ የተነሳሱበት፤ በቀጣይም እንዴት ተጠናክረው የበለጠ እንርዳ በሚለው ላይ እንዲያተኩሩ አድርጓቸዋል። በመሆኑም በመንግስትም ሆነ በአካባቢው አመራር ሊታዩና ሊደገፉ ይገባል።
ምክንያቱም እንደ ወጣቶቹም ሆነ እድር አባላት በቀጣይ የታቀዱ በርካታ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ፣ የከተማ ውስጥ ግብርና አንዱ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ቦታ ሁሉ ተለይቶ እንዲሰጥና አቅመ ደካሞችም ባቅማቸው ሰርተው ራሳቸውን የሚደጉሙበት እድል እንዲፈጠር እየጣርን ነው። ሆኖም አመራሩ ይሄን ባለመረዳት እያገዘ አይደለም። በመሆኑም ቦታም አለ፤ ሀሳብም አለ፤ የሚያግዝ ወጣትም አለ። ሆኖም ይሄን ተረድቶ የሚያግዝ የአካባቢ አመራር ሊፈጠር ይገባል። ምክንያቱም እንደ አበራ አይነት ከወደቁበት የተነሱ ሰዎች ሌላው ቢቀር ትንሽ ሱቅ ብትከፍትላቸው በእርሷ ራሳቸውን መደጎምና ከእርዳታ መላቀቅ የሚችሉበት እድል አለ። የከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት ለስራችን እውቅናና የዋንጫ ሽልማት ሰጥቶናል። በዚህ ልክ ግን የአካባቢው አመራር ሊያግዛቸው ይገባል። ይህ ከሆነ እነዚህ ወጣቶች ከሰፈር አልፈው ክፍለ ከተማና ከተማ ደረጃ ድጋፍ ማድረግ የሚችሉበትን እድል ይፈጥርላቸዋል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
ወንድወሰን ሽመልስ