ባህላዊ መድሀኒት/ህክምና ለሰው ልጅ እንግዳ አይደለም። በተለይ ለአፍሪካዊያን፤ በተለይ በተለይ ለኢትዮጵያዊያን ፍፁም የታወቀ፣ የተዘወተረ፣ ተፈትኖም የተመሰከረለት አገር በቀል እውቀት አፈራሽ ባህላዊ እሴት ነው።
ይህን እውነት፤ እድሜ ጠገብ ታሪክ አሳምረን ስለማወቃችን ምንም ጥርጥር ባይኖርም በማንኛውም የአገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የህመም መፈወሻ ብልሀቶች እና ህክምናዎችን ጠጋ ብሎ መመልከት፤ መመርመር ይገባል። ይህ ካልሆነም አለም በልዩ ፍቅርና በስስት አይኑ የሚመለከተውን “መጽሐፈ ሄኖክ”ን እና ሌሎችንም መመልከት ተገቢ ነው።
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በዚሁ ጉዳይ ላይ ሰፋ አድርገው ካጠኑት አንዱና ቀዳሚው ናቸው። በጥናቶቻቸውም ቱባ አገር በቀል እውቀት እንዳለን፣ ከእነዚህ መካከልም አንዱ ይሄው ባህላዊ መድሀኒት/ህክምና መሆኑን፤ በመሆኑም ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ የውጪ ሰዎች አይናቸውን እንደጣሉበትና ተደጋጋሚ ጥናቶችን ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። መፍትሄውንም “ኢትዮጵያ በፍጥነት ወደዚህ ዘርፍ ጥናት እንድትገባ”፣ ለጥናቱም የተለያዩ ዘዴዎችን እንድትጠቀም፣ ለጥናቱ “መረጃ ምንጭነት ከሚያገለግሉት አንዱ ቃላዊ ሥነጽሁፍ (ሥነቃል)” እንዲሆን፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በተለይም በግእዝ የተፃፉና የተነገሩ ሀሳቦች በአግባቡ እንዲመረመሩ፣ ከሁሉም በላይ በባህላዊ መድሀኒት/ህክምናና አገር በቀል እውቀት ላይ ብቻ ያተኮረ ሙያዊ ህትመት “Journal of traditional Ethiopian Medicine” እንዲዘጋጅ አበክረው አሳስበዋል። እንደ ፕሮፌሰሩ ጥናት ከሆነ ስንዘረፍ ኖረናል፤ አገር በቀል እውቀታችን ከስሩ ተመንግሎ እየጠፋ ነው፤ ስለዚህ ፈጥነን ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብቶቻችንን ለራሳችን ጥቅም ልናውለው ይገባል።
ወደ ጉዳያችን እንምጣ። ይህ እየተነጋገርንበት ያለው አገር በቀል እውቀት ያፈራው ባህላዊ መድሀኒት/ህክምና በቱባው እሴታችን በሆነው ሥነቃል እንዴት ተገልጿል የሚለውን እንመልከት። ይህ በበኩሉ የሚናገረው የራሱ ታሪክ፣ ጊዜና ቦታ፤ እንዲሁም የሚያሳየው የስነ-ቃላችንን ጥልቀት፤ ፍልስፍና፣ የፈጣሪ-ተናጋሪውን ማህበረሰብ ከፍታ አለውና ጠቃሚ ነው።
ከአንድ በአዳኝ-ፈዋሽነቱ የታወቀና የተመሰከረለት የምድር ዛፍ አለ። የማያድነው የህመም አይነት እንደሌለ ይነገርለታል። ይህ እፅዋት በአንዳንድ የኮንዶሚኒየም አካባቢዎች እንዳለ ተነግሮኝ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ አግኝቼው ለማየት ችያለሁ (ወዲያው አንድ እናት ጓሯቸው ለመትከል ነቅለው ወሰዱት)። ይህ ከምድር ከአንድ ሜትር በላይ የማይርቅ የምድር ዛፍ በማህበረሰቡ ዘንድ ወሳኝ ጥቅሙ ታውቆለት ገና ጥንት እንዲህ ተብሎለታል፤
ግዚያዋ ካለ ደጅሽ፤ (“ግዚያዋ” የዛፉ ስም ሲሆን “..ያዋ” ይባላል)
ለምን ሞተብሽ ልጅሽ።?
ኮሶ አንደኛው ባህላዊ መድሀኒት መሆኑ ይታወቃል። መራር መሆኑም እንደዛው። በመሆኑም በምሬቱ ምክንያት ታማሚው/ታካሚው ይህንን ፍቱን መድሀኒት ሳይወስድ እንዳይቀር በማሰብ (ሰው ሆዱን ይወዳል የሚለውን ያስታውሳል)፤ “ዶሮ ማታ፤ ዶሮ ማታ” (እስኪጨርሰው ድረስ) ይባልለታል። ከጨረሰው በኋላ ደግሞ – ሰራንልህ እንደማለት ፤
እንኳን ዶሮ፤
የለም ሽሮ።
ተብሎ እቅጩን፤ ቁርጡ ይነገረዋል። በዚህችኛዋ ኮሶ ጠጪና አጣጪ (ፈዋሽና ተፈዋሽ)ን በተመለከተ ቃል ግጥም ብዙ ማለት ይቻላል። (እዚህ ላይ መች ስለኮሶ ያወራል፤ ስለዶሮ እንጂ የሚል አንባቢ እንደማያጋጥም ታስቦ ነው በሌላኛው ገፅታው ቃል ግጥሙን እዚህ ማስቀመጥ የተቻለው።)
ከዚሁ ከኮሶ ጋር በተያያዘ በጣእምና ፈዋሽነቱ አቻው የሆነውን ግራዋ ከፍቅር ጋር ለውሶ ይዞ የቀረበውን ቃል ግጥም እንጥቀስ፤
ቁጭ ብዬ ግራዋ
ቆሜ ኮሶ ጠጣሁ፤
እንዳንቺ መለየት
የመረረኝ አጣሁ።
ቃል ግጥሙ የሆድ ውስጥ ምናምንን ጥርግርግ አድርገው የሚያወጡትን የግራዋንና ኮሶን መራራነት ከእሷ መለየት ጋር በማነፃፀር (“እንደ”) የቀረበ ሲሆን በማንፀሪያነት የቀረቡት ሁለቱ ባህላዊ መድሀኒቶች መራራነት ከሷ ፍቅር ጋር ሲነፃፀሩ ምንም ማለት እንዳልሆኑና የእሷ ግን እንደሚበረታ ያወሳል።
ከኮሶ ህክምና ጋር በተያያዘ የ”ኮሶ ሻጭ”ነት ጉዳይ ይነሳል። የአፄ ቴዎድሮስ እናት በዚህ ሙያ ይተዳደሩ እንደነበር ታሪክ ይናገራል። ይሁን እንጂ ዘመኑ ዘመነ መሳፍንት በመሆኑና የኮሶ ሻጯ ልጅም የዚሁ ዘመነ መሳፍንት ተቀናቃኝ በመሆኑ ይህ የእናትየዋ ሙያ እንደ ስድብ ሆኖ አገልግሏል። ጉዳዩን ዛሬ ላይ ሆነን ስናስበውና ኮሶ መድሀኒት መሆንን ከተቀበልን መባል የነበረባቸው “ኮሶ ሻጭ” ሳይሆን “መድሀኒት ሻጭ” ነበር ማለት ነው። ለነገሩ ሙያን መናቅ ስራችን አልነበር እንዴ? ስያሜያችን ሁሉ አንጥረኛ፣ ቀጥቃጭ፣ ፉጋ፣ ጠይብ … ነበር እኮ። እንደ “መጽሀፈ ቡዳ” ደራሲ አገራችንን እንዲህ ወደ ኋላ ያስቀራት ይህ አይነቱ ከፍና ዝቅ አተያይ ነው።
የሰው ልጅ ሰው ከሆነና ማሰብ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የባህላዊ ህክምና (እራስን በራስ የማከም ብቃት) አለም የዚሁ መድሀኒት ተጠቃሚ ሆኖ ኖሯል የሚሉ የስነ-እፅዋት ተመራማሪዎች (ቦታኒስት) በብዛት ያሉ ሲሆን፤ በተለይ ጥንታዊ ስልጣኔ ባለባቸው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ፣ ግብፅ፣ ሜሶፖታሚያ፣ ህንድ እና ቻይናን የመሳሰሉ አገራት በዋናነት በዚህ የሚታወቁ ናቸው። ከእነዚህ አገራት መካከል ይህንኑ አገር በቀል እውቀት ሳይለቁና የትም ሳይጥሉት እዚህ ዘመን ላይ በማድረስ አዘምነው ከራሳቸውም አለፈው፤ ለአለም መድህን ይሆን ዘንድ እየሰሩበት ያሉ አሉ። የቻይናውን አኩፓንክቸር እዚህ ጠቅሶ ማለፉ ብቻ በቂ ማስረጃና መረጃ ነው።
“ምንም ይሁን ምን፤ ፌጦ መድኃኒት ነው።” የሚል አባባልም አለ። እኛ ዘመንኞቹ የፌጦ ጥቅም የገባን አሁን ነው መሰል ውድነቱ ጣራ ዘሏል፤ “ለአንዳንድ ነገር” በሚል በኪስ ቋጥሮ መሄድ ሁሉ እየተለመደ ነው።
ከላይ በጥቂት ማስተንተኛ ቃል ግጥሞች ይህን አልን እንጂ፤ እንደ ግዚያዋ፣ ኮሶና ግራዋ ሁሉ ስለምች መድኃኒት፣ ዝንጅብልን፣ ሰሊጥና ሌሎች የተባሉትን ሁሉ እያነሳን ብንነጋገር ብዙ ሚስጢራት አሉ።
የአገር በቀል እውቀት ጎልቶ ከሚታይባቸው ዘርፎች አንዱ የህክምናው ዘርፍ ነው። ይህ ከሚገለፅባቸው፣ እውቀቱና ፋይዳውም ለህዝንብና መጪው ትውልድ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች ደግሞ አንዱና ዋናው (የጽሁፍ ጥበብ ባለመኖሩ ነው) በጥቅል ስሙ ሥነ-ቃል እና የዚሁ ንኡስ ዘውግ የሆነው ቃል-ግጥም ነው።
ባጠቃላይ፤ በቃል ግጥም ያልተገለፀ ነገር የለም። መመርመርና መመራመር የባለቤቱ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ሁሉንም በእቅፉ ይዟል። አገር በቀል እውቀቱም ሆነ ኢትዮጵያዊ ጥበቡ እዚያ አለ። በመሆኑም በዋዛ ፈዛዛ ያመለጡንን ሁሉ አስበን አሁንም ጊዜው አለና ሪቻርድ ፓንክረስት እንዳሉት ፈጥነን ወደ ስራ ልንገባ ይገባል።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
ግርማ መንግሥቴ