ሦስተኛ ወገን በፍቅር ወይም በትዳር ሕይወት ላይ ላሉ ጥንዶች ለሚፈጠሩ የዕለት ተዕለት ግጭቶች ማርገቢያ መሣሪያ ነው። ይህም ጥንዶች በሚገጥማቸው ግጭቶች በራሳቸው መፍታት ሲከብዳቸው ሦስተኛ ወገን አስፈላጊ ይሆናል። ለዚህም የቅርብ ጓደኛ፣ ዘመድ፣ የሥራ ባልደረባ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በሳል ሰዎችና የሃይማኖት አባቶች አስታራቂ ሦስተኛ ወገኖች ሆነው ይገኛሉ። አስታራቂ ሦስተኛ ወገኖች የጥንዶችን ግጭት በሰላ መንፈስ በማዳመጥና በመመርመር ለግጭቱ ተጠያቂ መቀጮ እንዲከፍል ወይም ከልብ ይቅርታ እንዲጠይቅ በማድረግ ግጭቱን ይፈቱታል። ወደፊትም ተመሣሣይ ግጭት እንዳይነሳ ጥንዶችን ቃል ያስገባሉ።
ሦስተኛ ወገን አወንታዊ ጎኖች ቢኖሩትም እንደዛው ሁሉ አሉታዊ ጎኖች አሉት። አንዳንዴ ሦስተኛ ወገኖች የግጭትን ይዘት ሊያከብዱና ግጭቱ የማይፈታበት ደረጃ ላይ ሊያደርሱ ይችላሉ። ይህ ሲሆን ሦስተኛ ወገን ማካተት ከባድ ሆኖ ይገኛል።
ለሦስተኛ ወገን አሉታዊ ጎን እንደማሳያ የበላይነህ ገለታና የሺመቤት መስፍን የፍቅር ሕይወት ጠቃሚ ተሞክሮ ነው። በላይነህ የጂንካ ከተማ ተወልዶ ያደገ ሲሆን የሺመቤት የአርባ ምንጭ ከተማ ተወላጅ ናት። በአንድ ወቅት በላይና የሺ በአርባ ምንጭ ከተማ በታክሲ ውስጥ አጠገብ ለአጠገብ ተቀምጠው ሳለ ነበር የተዋወቁት። ከታክሲ ከወረዱ በኋላም በጋራ በእግር ጉዞ ወደየመኖሪያ ሰፈራቸው እያቀኑ ሳለ አንድ ካፌ ሻይ ቡና ለመባባል ተነጋገሩና ወደዚያው አቀኑ። በዚህም አጋጣሚ ስለማንነታቸው፣ ባህሪያቸው፣ የሥራ ሁኔታና የመሳሰሉትን ተነጋግረውና የስልክ ቁጥር ተቀያይረው ተለያዩ።
ከዚያ ትውውቅ ጊዜ ጀምሮ በስልክ መደዋወል ጀመሩ። መደዋወሉ እየጠነከረ ሲሄድ በደንብ መግባባት ጀመሩ። መግባባታቸው ዳግም እንዲገናኙ አደረጋቸው። መገናኘታቸው እየጠነከረ ሲሄድ መነፋፈቅና መዋደድ ጀመሩ። ይሄም የመዋደድ አጋጣሚ ወደ ፍቅር ተቀየረና በላይነህ ቀድሞ የፍቅር ጥያቄ ሲያቀርብላት የሺ ስትጠብቀው የነበረው አጋጣሚ ስለነበር በደስታ ተቀበለችው። ከዚህ አጋጣሚ ጀምሮም ፍቅራቸው ደርቶ ወደ ፍቅረ-ገነት አቀኑ።
በላይነህና የሺ በፍቅር ሕይወት በሰላም ሁለት ዓመታት አሳለፉ። በዚህ ሁለት ዓመታት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ስላልነበር ፍቅራቸው እጅግ ሰላማዊ ነበር። በአንድ ወቅት በላይነህ አንድ ማቲዎስ የሚባል ጓደኛውን ለየሺ ሲያስተዋውቃት የሺ ደግሞ ሰላማዊት የምትባል ጓደኛዋን ለበላይነህ አስተዋውቃ ነበር። ይህ የማስተዋወቅ አጋጣሚ በመርህ ደረጃ መልካም ነገሮችን እንዲፈጥር ነበር። ማለትም የሺና በላይነህ ጊዜያዊ ግጭት ውስጥ ቢገቡ የቅርብና ውስጥ አወቅ አስታራቂ ጓደኞች እንዲሆኑ ነበር። የየሺና የበላይነህ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር የምክር አገልግሎት እንዲለግሷቸውም ጭምር ነበር። ግንኙነቱም ወደ ትዳር የሚያድግ ከሆነም የጋብቻ ጊዜ ሚዜዎች እንዲሆኑም ነበር።
የበላይነህና የየሺ ግንኑነት እጅግ በጣም መተሳሰብ የበዛበት ለብዙዎች ተምሳሌት የሚሆን በመሆኑ ሰላምና ማቲዎስ በዚህ ግንኙነት የሰይጣን ቅናት አደረባቸው። ቅናታቸው እያደገ ሲመጣ የበላይነህንና የየሺን ግንኙነት ለመመረዝ አሰቡ። ሀሳባቸውም የበላይነህና የየሺን መፃዒ ሕይወት ገደል ለመክተት ነበር።
በዚህም የተነሳ ሰላምና ማቲዎስ የበላይነህን ስም በሆነው ባልሆነው በማጥፋት የሺ እንድትሰማና እንድታውቅ አደረጉ። የሺ ስለበላይነህ መጥፎ ነገሮችን መስማት ስትጀምርና ነገሮች እየተካበዱ ሲመጡ የሺ መጠራጠር ጀመረች። ከሚወሩ ወሬዎች አንደኛው እጅግ ከባድ ነበር። በላይነህ ኤችአይቪ/ኤድስ በደሟ ውስጥ ካለባት ወጣት ሴት ጋር በድብቅ ይገናኛል የሚል ወሬ ነበር። ወሬው ይዘቱ ከባድ ስለነበር የሺ ስሜቷን ነክቶ ነበር። በዚህም የተነሳ የሺ የፍቅር ግንኙነቱን ለማቋረጥ አሰበች። ከቤተሰቦቿ ጋርም ተመካከረች። ነገር ግን ለበላይነህ ሀሳቧን አላሳወቀችውም ነበር። የሺ በባህሪዋ ስሜታዊ ስለነበረች ጉዳዩን ለማጣራት እንኳን ጊዜ ለመውሰድ አልቻለችም ነበር። ለሁለት ዓመታት ታምና ለቆየችው የሺ ነገሩ ከባድ ስለነበረ ታማኝነቷን ወደ መቀመቅ የሚከት ሁኔታ ሲከሰት የሺ በስሜት ያላትን ግንኙነት ለማቋረጥ የበላይነህን ስልክ ብላክ-ሊስት ውስጥ በማስገባት እንቅስቃሴዋን ጀመረች።
በላይነህ ምንም የሰራው ጥፋት ስላልነበርና የሰማው ነገር ስለሌለ ከጨዋታው ውጪ ነበር። የሺ የበላይነህን የስልክ ቁጥር ብላክ-ሊስት ውስጥ ስታስገባ በላይነህ ሲደውል ግራ ተጋብቶ ነበር። ወደ የሺ ስልክ በተደጋጋሚ ቢሞክርም ሊሰራለት አልቻለም። ሲቸግረው በመልዕክት ሲሞክር ሰራለትና መልዕክቱ ገባ። በዚህም እጅግ ግራ ተጋባና በሌላ ሰው ስልክ ደወለላት። የሺ ስልኩን አነሳችና በላይነህ መሆኑን ስታውቅ ጆሮው ላይ ዘጋችበት። ደጋግሞ ሲሞክርም ተመሳሳይ ምላሽ አገኘ። በዚህም ጊዜ አንድ አደጋ እንዳለ ገባው። ግራ ተጋባም። ያልጠበቀው ነገርም ሆነበት። ወደ ሀሳብ ባህር ባለበት ቦታ ነጎደ።
ይህ በሆነ በሁለተኛው ቀን ወደ የሺ ሰፈር አቀናና ሊያዋራት ቢሞክርም ፍቃደኛ ልትሆን ስላልቻለች ትቶ ተመለሰ። ከሥራ ስትመለስ በተደጋጋሚ እየጠበቀ ቢሞክርም ፈፅሞ ፍቃደኛ ልትሆን አልቻለችም። በሰፈር ጓደኞቿ ሊያናግራት ሲሞክር ጓደኞቿ በተወራው ወሬ ደስተኛ ስላልሆኑ ፍቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም። የሚይዘውና የሚጨብጠው ጠፋው። ያጠፋውን ነገር የሚያውቀው ባለመኖሩ ምክንያቱ አልገባውም ነበር። በስሜቱ ከመጠን በላይ ተጎዳ። ሕይወት ምስቅልቅል ሆነችበት። ሞትን መናፈቅ ጀመረ። ሀሳብ በዝቶበት የምግብ አፒታይቱ በመውረዱ በጠና ታመመ። ቤተሰቦች መታመሙን ሰምተው ለህክምና ወደ ሆስፒታል ወስደው ሲያሳክሙት የጭንቀት ችግር ስለሆነ የምክር አገልግሎት ስለሚያስፈልገው የሥነ-አዕምሮ ሐኪም ጋር እንዲወስዱ ተነገራቸው። ቤተሰቦቹም የቻሉትን አደረጉ።
በላይነህ ከ6 ወር በኋላ አገግሞ ወደ ጤናው ተመለሰ። ነገሮችን ሁሉ ረሳ። በዓለም ላይ ማጣትና ማግኘት ያለ ነው ብሎ ኑሮውን ጀመረ። ሰውን ማመን ቀብሮ ነው የሚለውን አባባል ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ በብቸኝነት ኑሮውን መግፋት ጀመረ። ፍቅር መልካም ነገርን ብቻ ሳይሆን አደጋንም እንደምታመጣ ተቀበለ።
ከተለያዩ ስድስተኛ ወር ላይ የሺ የበላይነህን መጎዳትና ማገገም ሰምታ ነገሮችን ከስሜት ወጥታ ማጣራት ስትጀምር የተባሉት ወሬዎች ሁሉ መሰረተ-ቢስ እንደነበሩ ተረዳች። ሰላምና ማቲዎስ በፈጠሩት አሻጥር ነገሮች እንደተበላሹ ገባት። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ፀፀት ገባት። ነገሮችን ወደነበረበት ለመመለስ እንዳትሞክር የበላይነህን ስሜት ባለማወቅ ጎድታ ስለነበር ከበዳት። በላይነህ ስላመረረ ነገሮች እንደማይሆኑ ስለገባት ሌላ ፍቅረኛ ያዘች። ከአዲሱ ፍቅረኛዋ ጋርም ኑሮዋን ቀጠለች። ከበላይነህ ጋር የነበራት ግንኙነት ተፅዕኖ ስላሳደረባት ከአራት ወራት በኋላ ለመለያየት በቃች። በዚህም በብቸኝነት ኑሮዋን መግፋት ጀመረች።
ሦስተኛ ወገን አንዳንዴ እንዲህ ያለ የከፋ አሉታዊ ጎን አለው። ለበላይነህና ለየሺ የፍቅር ሕይወት መቀመቅ መውረድ ሦስተኛ ወገን ተጠያቂ ነው። መጥፎ ሦስተኛ ወገኖች ከአስታራቂነት ይልቅ የሚያጣሉ ይሆናሉ። ለበላይነህና ለየሺ ከፍቅር ሕይወታቸው በላይ የጤና መታወክ፣ የአስተሳሰብ መበላሸትና ቂም እንዲያረግዙ ዳርጓቸዋል። የበዛ ማህበራዊ ሕይወትም ተመሳሳይ ሦስተኛ ወገኖች እንዲፈሩ ይዳርጋል። ለዚህም ከበዛ ማህበራዊ ሕይወትና ተገቢ ካልሆነ ከሦስተኛ ወገን ጣልቃገብነት ፍቅራችንና ትዳራችንን እንጠብቅ እላለሁ። አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
በላይ አበራ (ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኝ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ)