የስፖርት ውድድሮችን በመመልከት አሸናፊውን ቀድሞ የመገመት የውርርድ ጨዋታ እንደ አንድ መዝናኛ የሚወሰድ ቢሆንም፣ መጨረሻው ግን ገንዘብ ማግኘት ነው፡፡ ‹ጨዋታው መሸነፍም ማሸነፍም ያለበት በመሆኑ ያጓጓል፤ በተለይም ወጣቶችን፡፡ ጨዋታው ህጋዊ ፈቃድ ባላቸው ሰዎች የሚከናወን ቢሆንም ከማዝናናቱ በላይ አገራዊ ጉዳቱ ጎልቶ እየተነገረ ነው፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ አንዳንድ ወጣቶች ሃሳባቸውን አካፍለውናል፡፡
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ ብሩህ ተስፋ፤ የውርርድ የስፖርት ጨዋታ ብዙ ወጣቶችን እያሳሳተ እንደሆነ ይናገራል፡፡ አርሱም አንዴ ሞክሯል። ጓደኛውና እርሱ ለአንድ ጉዳይ ገንዘብ ፈልገው አማራጭ ያደረጉት በቅድመ ግምት ስፖርት ውርርድ የሚፈልጉትን ገንዘብ ማግኘት ነበር። ውርርዱን ለማሸነፍም እያንዳንዳቸው 25 ብር ነበር ያዋጡት፡፡ ለሁለት ያዋጡት 50 ብር ያሰቡትን ብር አላስገኘላቸውም፡፡ እርሱም ከዚያ በኋላ በጨዋታው አልቀጠለም፡፡
ተማሪ ብሩህ በአንድ ጓደኛው አማካኝነትም የመጫወቻ ትኬት በመቁረጥ ገንዘብ እንዲያገኝም ተጠይቆ እንደነበርና ጥያቄውን እንዳልተቀበለው ነግሮኛል፡፡ እርሱ እንዳለው ይህን ሥራ መስራት ለሀገርም ሆነ ለግለሰብ አይጠቅምም፡፡ እውቀት የሚጨምር ሥራ አይደለም ብሏል፡፡ ያለእውቀት ገንዘብ ማግኘት ተገቢ ነው ብሎም አያምንም፡፡ በድካሙ ገንዘብ ማግኘት የማይፈልግ ሰው ሥራ ነው ብሎ ያምናል፡፡
ተማሪው ብዙ ተማሪዎች የሚጫወቱት ለአንድ ነገር ገንዘብ ሲፈልጉ እንደሆነ ከብዙዎቹ ተገንዝቧል። ጨዋታውን የማሸነፍ ዕድሉ ጠባብ እንደሆነና ከሚገኝበት የማይገኝበት ጊዜ እንደሚበልጥም ተናግሯል፡፡ በመንግሥት ፈቃድ ተሰጥቶ መስፋፋቱ ደግሞ ተማሪውን ገርሞታል፡፡ መንግሥት ሊዘጋው እንደሚገባም አስተያየት ሰጥቷል፡፡
ፒያሳ አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት ዳንኤል በቀለ፣ በሚኖርበት አካባቢ ለጨዋታው ትኬት የሚቆርጡ እና የሚጫወቱ ብዙ ወጣቶችን ያውቃል፡፡ ጓደኞችም አሉት፡፡ ከሚሰማው እና ከሚያየው ውጭ አርሱ በጨዋታው ተሳትፎ አያውቅም፡፡
የቅድመ ስፖርት ውርርድ ጨዋታ ከገቡበት ሱስ የሚያስይዝ መሆኑን ቀድሞ በመረዳቱ አልሞከረውም። እራሱን መግዛት በመቻሉም ጨዋታውን በመጫወት ችግር ውስጥ ከወደቁት እንደአንዳንዶቹ ከመሆን ተርፏል፡፡ በጊዜ ሂደትም ጨዋታው ከማዛናናቱ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ከጓደኞቹ ተረድቷል፡፡
ወጣት ዳንኤል እንዳለው በጨዋታው የሚሳተፉት ሁለት አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ለጨዋታው በቀን 20 ብር መመደብ የማይቸገሩ የሀብታም ልጆች እና በሚገዙት ትኬት ከፍተኛ ገንዘብ ለማግኘት የሚመኙ ገቢ የሌላቸው ናቸው፡፡ ገንዘቡ ያላቸው ለሚያወጡት ብር አይጨነቁም፡፡ የሌላቸው ደግሞ ትርፍ ለማግኘት ስለሆነ ለመወራረጃ ገንዘብ ለማግኘትም በውርርዱም አሸናፊ አለመሆናቸው ያስጨንቃቸዋል፡፡ በተለይ ተማሪዎች በሳምንቱ መጨረሻ አርብ ውርርዱን ሥራቸው አድርገውታል። ሱሰኝነቱ ደግሞ ወደ ስርቆት ያመራል፡፡ ውርርዱን ለማሸነፍ ውጤቱን መከታተል የግድ ስለሆነ በቤተሰብ ግንኙነትና በማህበራዊ ትስስር ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡
በጨዋታው የሚያሸንፉ ጥቂት እንደሆኑና ያሸነፉ ቢኖሩ እንኳን ገንዘቡን ቁምነገር ላይ አያውሉትም። ጓደኞቻቸውን በመጋበዝ እና በአልባሌ ነገር ነው የሚያጠፉት፡፡ ጨዋታው ጉዳት እንጂ ጥቅም አለው ብሎ አያስብም፡፡ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ጨዋታውን ማስቆም እንደሚገባም ሃሳብ ሰጥቷል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት አራት ዓመታት በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ውስጥ እየሰራ እንደሆነና በአባቱ የመናዊ በአያቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ የነገረኝ ወጣት አህመድ አሊ ኢትዮጵያን እንደሁለተኛ ሀገሩ ያያታል፡፡ በስፖርት ጨዋታ ውርርድ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎችን እንደሚያውቅና አብዛኞቹ ተሳታፊዎች በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ ታዝቧል፡፡
እርሱም ጨዋታው መፈቀድ የለበትም ብሎ ያምናል፡፡ ሰው የገንዘብ ሱስ ውስጥ ከገባ ወንጀል ውስጥ እንዲገባ መንገድ ይከፍታል ይላል፡፡ ለጨዋታው ትኬት የሚቆርጡትም ሆኑ የሚጫወቱት በዚህ ከቀጠሎ የተለየ ሥራ ልምድ እንዳይኖራቸው እንደሚያደርጋቸውና በወደፊት ዕድገታቸው ላይም ተጽዕኖ እንደሚኖረው ይገልጻል፡፡
ወጣቱ እንደሚለው፤ ጨዋታውን በማየት ብቻ መዝናናት ይችሉ ነበር፡፡ በውርርድ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉት ግን ግባቸው ገንዘብ ማግኘት እንደሆነ ከድርጊታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ወጣቶች ቆም ብለው እንዲያስቡና የሚዝናኑበትንም እንዲመርጡ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ሌላዋ ያነጋገርኳት ወጣት ነጻነት ብዙነህ ትባላለች፡፡ በልጅነቷ ኳስ መጫወት ያስደስታት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ የሰፈሯ ወንዶች ልጆች ኳስ ሲጫወቱ ከመካከላቸው ነጻነት አትጠፋም፡፡ ከፍ ካለች በኋላ ደግሞ ኳስ ሜዳ እየገባች ትመለከትም እንደነበር አጫውታኛለች። እርሷ እንዳለችው ከሀገር ውስጥም ከውጭም የምትደግፋቸው ቡድኖችም ነበሩ፡፡ ከድጋፍ ባለፈ ወደጸብና ውርርድ በሚከት መልኩ ጽንፍ የወጣ እንደ አንዳንድ ደጋፊዎች አይነት ግን ይደለችም፡፡
ወጣት ነጻነት የስፖርት ውርርድ ጨዋታውን አትደግፍም፡፡ በጨዋታው የሚከስሩ እንጂ ተጠቃሚ የሆኑም አላጋጠሟትም፡፡ በተለይ ወጣቶች ነገ ሀገር ተረካቢ ይሆናሉ ተብለው ተስፋ ሲጣልባቸው ትርፍ በሌላው ነገር ውስጥ መሳተፋቸው አበሳጭቷታል። ወጣት ነጻነት እንዳለችው በጨዋታው ለመሳተፍ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች ደግሞ ገንዘብ የላቸውም፡፡ በጨዋታ ውርርዱ ሱስ ውስጥ ሲገቡ የት እንደሚሄዱ መገመት አያዳግትም ትላለች፡፡ ከዚህ ሁሉ በጊዜ ከማይጠቅም ነገር ውስጥ መውጣት እንደሚያስፈልግ መክራለች፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት ጨዋታው በአንድ ነገር ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ የሚያደርግ በመሆኑ የውርርድ ጨዋታው ሰዎችን ከተለያዩ ተሳትፎዎች ይገድባል፡፡ በተለይም ወጣቱ ፈጠራ እንዳይኖረው ያደርገዋል፡፡ ጉዳዩ በብዙዎች ዘንድ እያነጋገረ በመሆኑ በመንግሥትም ትኩረት ተሰጥቶት በተለያየ ጊዜ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2012
ለምለም መንግሥቱ