ምግብ፣ የህክምና መሳሪያ፣ የጤና ግብዓቶችና የውበት መጠበቂያን አስመልክቶ፤ ደህንነት፣ ፈዋሽነት፣ ጥራትን የማስጠበቅ ሃላፊነት በአዋጅ ቁጥር 1112/2011 ለኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ተሰጥቷል። ለጤና ጎጂ የሆኑ አልኮልና ትምባሆን የመቆጣጠር ጉዳይም የተቋሙ ኋላፊነት ሆኗል። ተቋሙ የተለያዩ ጥናቶችን ካስጠና በኃላ ምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ግብአቶች ላይ ቢያተኩር የተሻለ ውጤት ያመጣል በሚል እሳቤ ወደምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንነት እየተሸጋገረ ይገኛል። በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን (የኢትዮጵያ የምግብ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን) በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ የሚገኙትና በፋርማሲቲካል አናሊሲስና ኳሊቲ አሹራንስ ሁለተኛ ዲግሪ የሰሩት የፋርማሲስት ባለሙያዋ ወ/ሪት ሔራን ገርባ የዛሬው የተጠየቅ እንግዳችን ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልል ከተሞች በየጎዳናውና በመንገድ ዳሮች ተዘጋጅተው የሚቀርቡትን ምግቦች ደህንነትን ለማስጠበቅ በመቆጣጠር ረገድ ክፍተት እንዳለባችሁ ይታያል ምን ይላሉ?
ወ/ሪት ሔራን፡- እንደአገር ካለንበት የለውጥ ሂደት ጋር ተያይዞ ተቋሙ በጤና ቁጥጥር መስክ በሶስት ዘርፎች ላይ ለውጥ እናመጣለን ብለን እየሰራን ነው። አንደኛ የተቋሙን አወቃቀር ማዕቀፍ ማስተካከልና መከለስ ነው። ሌላው ከክልሎች ጋር ያለንን መስተጋብር በተሻለ መንገድ የህብረተሰቡን ጤና ለማስተግበር በሚያስችል መንገድ ለመፈጸም እንዲቻል ጥናቶችን እያካሄድን ነው። ከምግብ ቁጥጥርና ከሌሎች ግብዓቶች ጋርም የምግብ ቁጥጥር ስራን የምናዘምንበትን መንገድ እየሰራን እንገኛለን።
የፌዴራል ተቋሙ በዋነኝነት ከተቻለ ክልሎችን በገንዘብ አቅም ካልተቻለ ደግሞ በስልጠናና በሌሎችም ነገሮች የመደገፍ ስራ እንድንሰራ ሃላፊነት ሰጥቶናል። ባለፈው ዓመት ወደአምስት ሺ ለሚጠጉ የቁጥጥር ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥተናል። ሁለት ሺ 500 በመድሃኒት፣ ገሚሶቹ ደግሞ በምግብ ዘርፍ ሰልጥነዋል። በተለይም በምግብ ተቋማት ምግብን ከባእድ ነገር ጋር የመቀላቀል ጉዳይ እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል እውቀት ገብይተዋል።
መንገድ ላይ ምግቦችን ማብሰል በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራት የተለመደ ነው። ግን ትልቁ ችግር ከንጽህናና ከተላላፊ በሽታዎች ጋር ተያይዞ ያለው ነው። በእዚህ ላይም ሰፊ ስልጠናዎችን ለመስጠት ሞክረናል። በሂደቱ ትልቁ ችግር ያለው ከሰው ሃይል አቅም፣ ከአደረጃጀትና ከበጀት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ሲሆን፤ በቁጥጥሩ ክልሎችም እኛም የምንፈተንባቸው ጉዳዮች ናቸው።
በተለይ ደግሞ ወደክልልና ወረዳ ሲወርድ ለቁጥጥር ስራው የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ነው። ይህ ማለት ጉዳዩ ህብረተሰቡ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ ካለመገንዘብም ሊሆን ይቻላል።
ሌሎች ደግሞ በጣም ብዙ ችግሮችም ኖረው ቅድሚያ የመስጠት ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ። ከእዚህ ጋር ተያይዞ ከአደረጃጀት አንጻር እኛ በምናደርጋቸው የተለያዩ ውይይቶች የቁጥጥር ስራው ይገመገማል። ከክልል ተቆጣጣሪ ሃላፊዎች ጋርም በየጊዜው የምንገናኝባቸው ፎረሞች አሉ። እስከ አሁን በጋራ የማቀድና እቅድን መገምገም ላይ ደርሰናል። በጀትን በጋራ የማስተዳደር ጉዳይ ግን ከአቅም ጋርም ተያይዞ አልደረስንም። ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ያለነው የተቆጣጣሪዎቹን አቅም ማጎልበትና በየጊዜው የሚሰሩትን የቁጥጥር ስራ የመደገፍና የመቆጣጠር ስራ ነው። ባለፈው ዓመት በሰፊው የሰራነውና አሁንም የቀጠልነው የክፍለ ከተማ፣ የወረዳና የዞን ተቆጣጣሪዎች ስራ ቢሆንም ድህረ ቁጥጥር ስናደርግ ወደ ፋብሪካ የምንሄደው ክፍተቶችን ማሳየት ስላላስቻለ የገበያ ጥናት ብለን ወደ ችርቻሮ እየሄድን ነው።
በተለይ አዲስ አበባ ከተማ ባለፈው ዓመት እንኳን ወደ100 የሚጠጉ ምግቦች ህብረተሰቡ እንዳይጠቀምባቸው በብዙሃን መገናኛ አሳውቀናል። በእዚህ ሩብ ዓመትም 28 የምግብ አይነቶች ገበያ ላይ እንዳይቀርቡ አድርገናል። በሌላ በኩልም አገር ውስጥ የሚመረቱ እንደ ዘይት፣ ኦቾሎኒ ቅቤ፣ ጨውና የመሳሰሉት ነገሮች በትክክል ሳይመረቱ፣ የገላጭ ጽሁፍ ሳይኖራቸው ቀርቶ በመገኘቱ ከገበያ እንዲሰበሰቡ አድርገናል።
ይህም ህብረተሰቡ ጥራቱና ደህንነቱ ያልተረጋገጠ ምግብ እንዳይጠቀም ማድረግ ያስቻለ፤ ሲሆን በዘርፉ ፍቃድ እንዴት መመታት እንዳለበት ሳያውቁም እያመረቱ ገበያ ላይ የሚያቀርቡም ወደ ስርዓቱ ገብተው ምርቶቻቸው በላቦራቶሪ በማስመርመር በዘርፉ እንዲቀጥሉ አስችሏል። አንዳንዶቹ በእህቶቻችንና በእናቶቻችን ተደራጅተው በስራ ፈጠራ የሚሰራ ነው። አንዳንዱ ደግሞ እያወቀም የሚያጠፋ አለ። ሁሉም ወደ ህጋዊ መስመሩ እንዲገባ አስችሏል። ግን ይህንን ጉዳይ እያወቁ ከቀጠሉ በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን፦ ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀል የአንድ ወቅት የብዙሃን መገናኛ መነጋገሪያ ይሆናል ግን የድርጊቱ ፈጻሚዎችም በህግ ተጠያቂ ሲሆኑ አይሰማም ለምን ?
ወ/ሪት ሔራን፦ ምግብን ከባዕድ ነገር ከመቀላቀል ጋር ተያይዞ ያለው ችግር ዓመታትን የተሻገረ ነው። ግን አሁን ህብረተሰቡ በአግባቡ እያወቀው፣ እየጠቆመም፣ እርምጃዎችም እየተወሰዱ ይገኛሉ። አሁን ባለን መረጃ መሰረት አራት የምግብ አይነቶችን ማለትም ጤፍ (እንጀራ)፣ ቅቤ፣ ማር እና በርበሬ ላይ መሰረት ተደርጎ የሚሰራ ነው። እነዚህ ማንኛውም ማህበረሰብ የሚጠቀማቸው ምግቦች ናቸው።
ባለፈው ዓመት እንደትኩረት አቅጣጫ ወስደነው በተለያየ መንገድ በስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክተር ውስጥ ስውር ጥናቶችን የሚያጠና የስራ ክፍል አደራጅተናል። በእነርሱ አማካኝነትና በሌሎችም አካላት እገዛ ጥናቶች ከተሰሩ በኋላ ባለፈው ዓመት በተለያዩ ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ በ10 ሩም ክፍለ ከተሞች ስራዎች ለመስራት ተሞክሯል።
እንጀራና ሰጋቱራን አስመልክቶ አንዳንድ ቦታዎች እጅ ከፍንጅ የተያዙበት፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ምልክቶች የተገኙበት ነው። ለምሳሌ እንጀራ መጋገሪያ ቤት ተፈጭቶ የተቀመጠ ሰጋቱራ አጋጥሟል። በእዛ ሁኔታ ሰጋቱራ ተፈጭቶ ተቀምጦ ከተገኘ ከጤፍ ጋር ሊቀላቀል መሆኑን ያሳያል። በእዚህ በኩል የክፍለ ከተማ፣የወረዳ፣ የክልልና የፌዴራል ተቆጣጣሪዎች ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተን ብዙ ስራዎችን ለመስራት ሞክረናል።
እንጀራን ከጀሶ ጋር መቀላቀል በመሰረታዊነት ብዙ የሚታየው በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች ነው። የክልል ከተሞች ባደረግነው ጥናት ያልደረስንባቸው ቦታዎች ሊኖሩ ይችላሉ ግን በእዚህ ደረጃ ሰፊ ነገር አላየንም።
አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ማርን ከስኳር ጋር፣ ከተፈጨ ብርጭቆ፣ ከመኪና ዘይት ጋር የመቀላቀል ብዙ ነገር አይተናል። በእሩብ አመቱም በተለይ በኮምቦልቻና ደሴ አካባቢ ግኝቶች አሉ። ቅቤንም ከሙዝ፣ ከሸኖ ለጋና ከሌሎች ጋር በመቀላቀል መጠኑን ቀንሶ ለማሳደግ የሚደረጉ አዝማሚያዎች አሉ። በርበሬንም ከሻክላና ከመሰል ባዕድ ነገሮች ጋር እየቀላቀሉ የመሸጥ ሁኔታዎች አሉ። በሂደቱ ጠንካራ ስራ የተሰራውን ያህል ክፍተቶችም አሉ። የተሻለ አቅም ኖሮ በላቦራቶሪ ምርመራ ጀሶ መኖርና አለመኖሩን የማረጋገጥ፣ በርበሬ፣ ማርና ቅቤ ምግቦች ላይም ያሉትን ነገሮች ከመለየት አንጻር አገራዊ አቅም ካለመኖር ጋር የተፈጠሩ ችግሮች ነበሩ።
ጉዳዮቹ ወደ ፍርድ ቤትም ሲሄዱ ከላቦራቶሪ ጋር የተያያዙ ማስረጃዎች ያስፈልጋሉ። ጀሶና እንጀራን ብንወስድ የጀሶ ጉዳይ በጤና ላይ ምን ጉዳት እንዲሚያደርስ ገና በጥናት የተረጋገጠ ነገር የለም። ግን ጀሶ የግንባታ ግብዓት እንጂ ምግብ እንዳልሆነ ይታወቃል።
ስራው በጥበብ ነው የሚሰራው። ሕብረተሰቡ እኛንም፣ የክልል ተቆጣጣሪ አካላትንም እንዲያግዝ የምንፈልገው ይህንን ነው። ጉዳዩ ፊት ለፊት ሳይሆን መኖሪያ ቤት ውስጥ በሌሊት የሚሰራ ነው። ስራዎቹ የሚያሰሩት በዘመድ አዝማድ በመሆኑና ራሳቸውን የቻሉ ወፍጮ ቤቶች ስላሏቸው ከህብረተሰቡ ዓይን የተሰወሩ ናቸው። ሆኖም በአጋጣሚ እንዲህ አይነት ነገር ሲታይ ማህበረሰቡ ጥቆማ እያቀረበ ይገኛል። በእኛ እይታም አሁን ጀሶን ከጤፍ ጋር መቀላቀል በአዲስ አበባ ከተማ እየቀነሰ መጥቷል። ግን ከአዲስ አበባ እየሸሹ በሌሎች ከተሞች ስውር ቦታዎች ጀሶን ከጤፍ ጋር አይቀላቅሉም ማለት አይደለም። ለእዚህ ሰፊ ጥናት ያስፈልገዋል። በእኛ ኢንተለጀንስ ክፍል ከጸጥታ አካላት ጋር በመታገዝ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሰፊ ጥናት መሰራት አለበት እርምጃዎችም መወሰድ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፦ አንዳንድ ሆቴሎች/ ምግብ ቤቶች የምግብ ማብሰያ ክፍሎቻቸው ጥራት የጎደላቸው ሆነው ይታያሉ፤ በህግ ስልጣን የተሰጣቸው ተቆጣጣሪ አካላት ለምን ጉዳዩን ችላ ይሉታል?
ወ/ሪት ሔራን፦ በኮከብ ደረጃ የሚገኙትም ሆኑ ታች ምግብ ቤት ለሚባሉት ከፍቃድ አሰጣጥ አንጻር የብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጥ ኃላፊነት የተሰጠው ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በተዋረድ ለባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ነው። ትልቁ ክፍተት ያለው እዛ ላይ ነው። የጤና ተቆጣጣሪ አካላት የጤና ቁጥጥር ቢያደርጉም እርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ ይሆናል። ምክንያቱም ለሃላፊነት የብቃት አረጋጋጭ አይደሉም። ቁጥጥር ሲያደርጉም ተቋማቱም የመዝጋት እርምጃ የመውሰድ ስልጣን የላቸውም። በእዚህ ላይ በተለያየ መንገድም አስተያየት ለመስጠት ሞክረናል። ግን አሁንም በእዚሁ መንገድ ቀጥሏል። በፊት ከሶስት ኮከብ በላይ ያሉ ሆቴሎች ላይ ቁጥጥር እናደርግ ነበር። በተለይ የክልል ተቆጣጣሪ አካላት ጤና ነክ ጉዳዮችን የሆቴሎች ኩሽና ጉዳይን ተቆጣጥረው ግብረ መልስ ሰጥተው እንዲስተካከል የተደረገበት ሂደት ነበረ። አሁን ስራው ወደጤና ሚኒስቴር ሄዷል።
አብዛኞቹ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ግን የክልል ተቆጣጣሪ አካላት የሚከታተሏቸው ናቸው። ከእዚህ በፊት ከባህልና ቱሪዝም ጋር በጋራ ሆነን ሆቴሎች ሲመዘኑና የኮከብ ደረጃ ሲሰጣቸው አገልግሎት ለመስጠት ማሟላት ያለባቸውን ነገር የሚገመግም 40 የሚጠጉ መስፈርቶች ተዘጋጅተው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። ግን የተግባርና ሃላፊነት መደራረብ በባህልና ቱሪዝም ደረጃ ቁጥጥር የሚያደርግባቸው ጤና ተቆጣጣሪ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጋር የሚጣጣም አይደለም። የጤና ተቆጣጣሪ ሆቴሎች ላይ የብቃት ማረጋገጫ ለመስጠት ሃላፊነት ቢሰጠው ከኩሽና ባሻገር የተለያዩ መመዘኛዎች አሉ። የአንሶላ፣የአልጋና መሰል ንጽናዎች ከዚህ ጋር የሚታዩ ናቸው። በእዚህ ረገድ በእኛ በኩል የምናደርጋቸው የአቅም ግንባታዎች ላይ ይሄንን ሁሉ አካተን ነው የምንሰራው። በእኛ በኩል ሁል ጊዜም አስተያየት የምንሰጠው በጋራ ሆኖ ከጤና ተቆጣጣሪዎች ጋር ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን፦ ወደ አገር የሚገቡ መድሃኒቶችን ጥራት እና ደህንነትን የመቆጣጠር ሂደቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው ?
ወ/ሪት ሔራን፦ አንድ መድሃኒት ለሕብረተሰቡ ለጤና አገልግሎት ከመቅረቡ በፊት ሶስት ጉዳዮች ቁጥጥር ይደረግባቸዋል። አምራች፣ የመልካም አመራረት ስርዓት ስለመተግበሩና የብቃት ማረጋገጫ። መድሃኒት የኬሚካልና የመረጃ ዘርፍ አለው። በጣም ብዙ ሳይንሳዊ ሂደቶችን ያልፋል። ከጥሬ ዕቃው ጀምሮ የአመራረት ሂደቱን፣ ጥሬ እቃው ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች በአግባቡ ስለመለየታቸውና መድሃኒቱ ላይ የተጨመሩ ነገሮችን በአግባቡና ሳይንሳዊ ሂደቱን መከተሉ ይረጋገጣል። የመጠቀሚያ ጊዜውን አስመልክቶም የሚቀርቡ ማስረጃዎች አሉ። ክሊኒካል የሆኑ በሰዎች ላይ የተሞከሩ ማስረጃዎች ሲያስፈልጉም ይቀርቡና ይገመገማል። ከእዚህ ቀደም እናደርግ የነበረው ለምዝገባ የገበያ ፍቃድ ለመስጠት ናሙና እራሳቸው አምጥተው ምርመራ እናደርግ ነበር። የምዝገባ ሰርተፍኬቱን ለማግኘት ሲባል ጥሩ ነገር ይመጣል። ውጤቱም ሁሌ ጥሩ ይሆናል። ይሄንን አቁመን ሁለቱን ሂደት ካለፈ የገበያ ፍቃድ
እንሰጥና ምርቱን ወደአገር ሲያመጣ ከኤርፖርት ወይም ከሚገባበት ኬላ ናሙና ይወሰዳል። በ11 መስፈርቶች የአለም አቀፍ እውቅና ያለው የመድሃኒት ምርመራ ላብራቶሪያችን ይመረመራል።
የኮንዶም መመርመሪያ ላብራቶሪያችንም በአምስት ሜካኒካል መስፈርቶች ISO 17025 እውቅና ባለው ይመረመራል። ወደእዛ ላቦራቶሪ መጥቶ ይፈተሽና ካለፈ በኋላ ለገበያ እንዲቀርብ ይደረጋል። ይህ የገበያ ፍቃድ በአዲሱ አዋጅ ቁጥር 1112/2011 መሰረት ለአምስት ዓመታት ይቆያል። ማንኛውም በመንግስትም በግልም የሚገባ መድሃኒት በእዚህ ሂደት ያልፋል።
ይህ በቅድመ ፍቃድ የሚሰሩ ስራዎች ናቸው። በድህረ ፍቃድ የሚሰሩ ደግሞ መድሃኒቱ ገበያ ላይ ከዋለ በኋላ ከአገሪቱ የበሽታ ስርጭት አንጻር (በርግጥ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችም ቁጥራቸው እየጨመረ ቢሆንም) ኤች አይቪ፣ ቲቢ፣ ማላሪያ፣ ከእናቶችና ህጻናት ጋር ተያይዘው ያሉ መድሃኒቶች ናቸው። ለአንድ መድሃኒት የማምረቻ ሂደት ብቻ ሳይሆን የማከማቻና የስርጭት ሂደትም ለመድሃኒቱ ጥራትና ደህንነት ውጤት ስላለው አገር ውስጥ ከገባ በኃላም የጉዞ፣ የማከማቸት ሂደቱ እንደመድሃኒቱ ባህሪ መሆን አለበት። መድሃኒት በአንዴ ፍቃድ ብቻ የማያልቅ በመሆኑም የደህንነትና የጥራት ሁኔታ በየጊዜው ክትትል ይደረጋል።
በማከማቸት ሂደትም የሚፈጠር ነገር ሊኖር ስለሚችል የመድሃኒት አስመጪ፣ አከፋፋይና አከማች ፍቃድ ይሰጣል። የድህረ ፍቃድ ጥራት ምርመራ ናሙናዎችን በመውሰድም ይሰራል። እነዚህ መድሃኒቶች ችግር ካለባቸውም ከገበያ እንዲሰበሰቡ እናደርጋለን። ለምሳሌ በእሩብ ዓመቱ ሁለት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር የሚያወጡ መድሃኒቶች ጥራትና ደህንነታቸው ተረጋግጦ ወደሃገር እንዲገቡ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፦ህገወጥ የመድሃኒት ዝውውርና ስርጭት ስርዓት ማስያዝ አልቻላችሁም፤ መንግስት በሚቆጣጠራቸው የሆስፒታል ፋርማሲዎችም በርካሽ ዋጋ ተገዝተው የሚገቡ መድሃኒቶች በተለያየ መንገድ እየወጡ ይሸጣሉና ለምን መቆጣጠር አልቻላችሁም?
ወ/ሪት ሔራን፦ ህገወጥ መድሃኒት ስርጭት ሁለት አይነት ማሳያዎች አሉት። እንደአገር ከሌሎች አገራት ጋር በሚያዋስኑን ወሰኖች ላይ በጣም ሰፊ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ ከሶማሌ ጋር በሚያዋስነን ቶጎ ጫሌን ጨምሮ ሌሎች ወሰኖች ላይ ወደአንድ ሺ ኪሎ ሜት የሚጠጋ ቦታ አለ። በደቡብ ክልልም በሞያሌ በኩል እንደዚሁ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ይታያሉ። ከእዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ኤርፖርትን ጨምሮ በ17 ኬላዎች ተቆጣጣሪ አካላት መድበናል። በአገር አቀፍ ደረጃም የሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቆጣጠር የተደራጀ ግብረ ሃይልም አለ። በሚገርም ሁኔታ ትልቁ የህገወጥ ዝውውር መግቢያ ነው ተብሎ የሚታሰበው ቶጎ ጫሌም ሆነ ሞያሌ የበለጠ አዲስ አበባ ኤርፖርት ነው። በምግብ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ በመሆኑም ብዙ ግኝቶች አሉ።
ሁለተኛው ገጽታ ከመንግስት ሆስፒታል ፋርማሲዎችና በርካሽ ዋጋ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት በተለያየ መንገድ እየወጡ የሚሸጡ መድሀኒቶች አሉ። ይህንን ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በየጊዜው ጥናቶችን አጥንተን ለመንግስት አቅርበናል። በእዚህ መሰረትም አሰራሮች እንዲሻሻሉ ተደርጓል። እጥረት አለ የሚባለውም በእዚህ መንገድ ስለሚወጣና ሕዝቡ ስለማያገኘው ነው። ይህንን የየሆስፒታሎቹ አስተዳደሮች ይመለከታቸዋል። የፋርማሲ አሰራሩን በስርዓት ቁጥጥር የሚደረግበት ሁኔታ ሊዘረጋ ይገባዋል። ሆኖም በጤና ተቆጣጣሪ የሚደረገውን ስርቆት የመቆጣጠር ተግባርና ሃላፊነታችን አይደለም። በእዛ ደረጃም የሚፈታ ጉዳይ አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ የውበት መጠበቂያ ምርቶች ላይ የተመለከታችሁት ችግሮች ምንድን ናቸው?
ወ/ሪት ሔራን፦ የውበት መጠበቂያ ምርቶች የሚመረቱና መጥተው የሚከፋፈሉ አሉ። በመድሃኒትም በውበት መጠበቂያ የማይመደቡ ምርቶችም አሉ። የተቀመጠው አቅጣጫ ከሰው ጤና ጋር የሚገናኝ፣ ሰውነትን የሚቀይር፣ የሚፈውስና በሽታን የሚከላከል ከሆነ ወደ መድሃኒትነት ይገባል። ከእዛ ውጭ ከሆነ ውበት መጠበቂያ ይባላሉ። ውበት መጠበቂያ ብዙ ኬሚካሎችና ንጥረ ነገሮች አሉበት። በስጋት ደረጃቸው መከፈል አለባቸው። እየሰራንበት ያለነው መመሪያ አንዳንድ የውበት መጠበቂያዎች ውስጥ መገኘት የሌለባቸው ኬሚካሎች ስላሉ አስመጪዎች እነዚህ ነገሮች እንደሌሉበት የማሳወቅ፣ መግለጫዎቹ አይቶ የመቆጣጠር ስራ ይሰራል። ቆዳን እንዳያሳክክና እንዳያቃጥል በላቦራቶሪ ከሰው ሰውነት ጋር የሚገናኝ ባህሪ ባላቸው እንስሳቶች የጥራት ምርመራ ይደረጋል። ለእዚህ ምርመራ አይጦችና ሌሎች እንስሳቶች አሉ ቆዳቸው ይላጥና ይቀባሉ። ችግር ከሌለው ወደ ገበያ እንዲቀርብ ይደረጋል።
በአገር ውስጥ በከፍተኛና በአነስተኛ ደረጃ የሚመረቱ የውበት መጠበቂያ ምርቶች አሉ። ፍቃድ ሳይወስዱ የውበት መጠበቂያ የሚያመርቱ አሉ። አንድ የውበት መጠበቂያ ምርት ለማምረት አዋጁም እንደደነገገው የብቃት ማረጋገጫ ማውጣት ያስፈልጋል ። በክልሎች ላይ የሚሸጡ ከሆነ ከክልል ተቆጣጣሪ አካላት ከአንድ ክልል ወደሌላ ክልል የሚዘዋወር ከሆነ ደግሞ ከፌዴራል ተቋሙ የብቃት ማረጋገጫ መውሰድ ይኖርባቸዋል። ለእዚህም የሚፈለጉ መስፈርቶች አሉ።
ለውበት መጠበቂያ ማስመጣት ማከፋፈል ላይም የብቃት ማረጋገጫ መውሰድ ይጠየቃል። መስፈርቶቹ ላይ ወጥ የሆነ ነገር ስለሌለ በየክልሎቹ የሚሰጥበት መስፈርት መለያየት፣ በዘርፉ የሚሰማሩ አካላት ያለምንም ብቃት ማረጋገጫ መግባትና ፣ የሌሎች ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ የሚውል ምልክትን በማጭበርበር ቀድቶ የመጠቀም ሁኔታ አለ። በጣም ብዙ ቦታዎች ላይ የታየው ጥሬ ዕቃው ከየት እንደሚመጣና እንደሚሰራ ምንም የማይታወቅ ሻምፖ፣ ኮንዲሽነር ቅባቶች በጣም በብዙ ሁኔታ ይመረታሉ። ባለፈው 60 የሚጠጉ ችርቻሮ ድርጅቶች ስራ እንዲያቆሙ ተደርጎ ነበር። ከእዚህ በኋላም ምርቶቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ወስደው በማስመርመር ዋና ዋና መስፈርቶችን አሟልተው ወደስራ እንዲገቡ ተደርጓል። አንዳንዶቹም የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ብቁ ስላልነበሩ ስራቸውን ያቆሙ አሉ። መመሪያዎችን እየከለስን እንገኛለን። በአነስተኛ ደረጃ የውበት መጠበቂያ ለሚያመርቱ ሕጋዊ አሰራር ተከትለው እንዲተገብሩ የማስተካያ ስራ እንሰራለን።
አዲስ ዘመን፦ የትምባሆ ምርቶችን ከመቆጣጠር አንጻር እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ እንደሆነ ይታወቃል። ምን ውጤት አለ?
ወ/ሪት ሔራን፦ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ 2016 አለም አቀፍ ደረጃ በአዋቂዎች በተደረገ ጥናት አነስተኛ የአጫሾች ቁጥር ካሉባት አገር አንዷ ናት፤ (የአጫሾች ቁጥር አምስት በመቶ ብቻ ነው) ግን ይሄ ቁጥር ቀላል አይደለም። 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ 15 ዓመትና ከዛ በታች ያለ ማህበረሰብ እንደመሆኑ ብዙ ስራ ካልተሰራ ለማጨስ ተጋላጭ ነው። ስለዚህ በእዚህ አግባብ የአለም አቀፍ ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ 2003 (FRAMEWORK CONVENTION ON TOBACCO CONTROL) የሚባል አለም አቀፍ ስምምነት ፈርመናል። ሕግ ለማድረግ ግን ረጅም ጊዜ ፈጅቷል። በ 2006 ዓ.ም አዋጅ ቁጥር 822 ሲወጣ የትምባሆን ጉዳይ ባለስልጣኑ እንዲያስተባብር ስልጣን ተሰጥቶታል።
የትምባሆ ቁጥጥር የተለያዩ አካላት በቅንጅት የሚሰሩት በመሆኑ ስራው ሲሰራ ቢቆይም ጠንካራ ሕግ ግን አልነበረም። አዋጅ ቁጥር 661 የትምባሆ ማዕቀፎች ቢኖሩትም ጠንካራ አይደሉም። ጥናቶች ተሰርተው፣ ነባራዊ ሁኔታውን ተመልክተናል የሌሎች አገራት ተሞክሮንም አይተናል።
እንደዩጋንዳ፣ ኬንያ ጠንካራ ሕግ አላቸው። ከአገሪቱ የአወቃቀር ሁኔታ አንጻር፣ ካለው የስልጣኔና የቴክኖሎጂ መስፋፋት ጋር በኢትዮጵያ ጠንካራ ሕግ መውጣት አለበት በሚል ሕጉ ወጥቷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እውቅና ተሰጥቶታል። አዋጁ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች 100 በመቶ ከትምባሆ ጭስ ነጻ መሆን አለባቸው ይላል። አጫሾች በማገገሚያ ቦታዎች በመታገዝ ጭምር ከሱሱ እንዲወጡ ማድረግም ያስፈልጋል። ዋናው ጉዳይ ግን የአዋጁ ማዕቀፍ አጠቃላይ ዓላማው የማያጨሱ ሰዎች እንዳይጎዱ ማድረግና ሰዎች ወደማጨስ እንዳይገቡ ማድረግ ስለሆነ ድሮ የማጨሻ ቦታ ተከልሎ ይፈቀድ ነበር በአሁን አዋጅ አይፈቀድም።
የትምባሆ ፓኬቱ 70 በመቶ ስእላዊ በሆነ የጤና ማስጠንቀቂያ እንዲታሸግ አድርጓል። ሺሻን ጨምሮ የተለየ ጣዕም /ፍሊቨር/ ያላቸው ምርቶች መጠቀም ሙሉ ለሙሉ የተከለከለ ነው። ኤሌክትሮኒክስ ሲጋራም በአዋጁ ክልክል ነው። ከ21 ዓመት በታች ላለ ወጣት ወይም ሕጻን ትምባሆ አይሸጥም፣ በነጠላ ትምባሆ መሸጥ የተከለከለ ነው። እነዚህ ክልከላዎች በህጉ ላይ ተቀምጠዋል። ይሄ ዝም ብሎ የጸደቀ አዋጅ አይደለም። ብዙ ፈተናዎች ነበሩበት።
በማስፈጸም ሂደቱ ላይ በተለያየ ጊዜ በብዙሃን መገናኛና በሌሎችም መንገዶች ግንዛቤ እንዲያዝ ተደርጓል። ወደ ትክክለኛው ትግበራም እየገባን እንገኛለን። የመንግስት ተቋማት ትራንስፖርት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና መሰል ሕዝብ የሚሰበሰብባቸው ተቋማትና ሌሎችም ነጻ ለማድረግ ተቆጣጣሪ በመመደብ ሊሆን አይችልም። ‹‹ትምባሆ እንዲጨስብኝ አልፈልግም በሕግ ተጠብቄያለሁ›› የሚል ማሕበረሰብ መፍጠር ይገባናል። በየተቋማቱ በየመዝናኛዎቹ፣ ሆቴሎች ላይ ሲጋራ ማጨስ የተከለከለ መሆኑን መለጠፍ አለባቸው፣ ማስተግበርም እንደዛው።
አዲስ አበባ ከተማ ትልልቆቹ ሆቴሎች ላይ ስንጀምር ክፍተቶች አይተናል። እንዲያስተካክሉ የአንድ ወር ጊዜ ተሰጥቶ ቁጥጥሩ እየተተገበረ ነው። ትልቅ ተግዳሮት ያለው ሺሻን ጨምሮ ማታ ማታ የሚፈጠሩ ጉዳዮች ላይ ነው። የማታ ስራ ያለፍትህ አካላት ድጋፍ የእኛም የክልል ተቆጣጣሪዎች መስራት አይችሉም።
በመሆኑም በሩብ አመቱ በርካታ የፍትህ አካላትን አሰልጥነናል። ለክልል የፍትህ አካላት ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ላይ እንገኛለን። የሌሊት የክትትል ስራ በአዲስ አበባና በክልሎች እየተሰራ ነው። በሂደቱ ደግሞ መልኩን ቀይሮ በተለይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመከራየት ሺሻ ማስጨሻና ሌሎች ነገሮች የሚደረጉበት ሁኔታ እየተስፋፋ ይገኛል። በመሆኑም ብዙ ፈተና ያለበትና በርካታ ስራ የሚጠይቀን ነው። የክልል ተቆጣጣሪ አካላትም የእለት ተዕለት ስራቸው አድርገው መተግበር ይገባቸዋል። ውጤት የምንለው ጠንካራ አዋጅ መውጣቱን ነው፣ አዋጁ ይደግፋል በፊት ሺሻ ዕቃ ተይዞ እንዴት እናስቀጣው? እንል ነበር አሁን ህግ አለ። የቅንጅት ስራ ግን ያስፈልጋል። ተቋማት በእቅዳቸው አካተው እንዲተገብሩት ማድረግ፣ ተቆጣጣሪ ማሕበረሰብ መፍጠርም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ የአልኮል መጠጥ እንዴት በምግብ ዘርፍ ተካተተ፣ ምንስ ሰርታችኋል?
ወ/ሪት ሔራን ፦ በመሰረታዊነት አልኮል በምግብ ዘርፍ ይመደባል። ግን ከማስታወቂያ አጠቃቀም አንጻር ላላስፈላጊ ነገር ሊውል ይችላል። አልኮል ሱስ ያስከትላል። በእዚህ ሱስ የተጠመዱ ሰዎች ደግሞ ለተለያየ ነገር ይጋለጣሉ። በጣም በከፍተኛ ደረጃ የትራፊክ አደጋ እየበዛ ያለው ሰው ራሱን ገዝቶ በመጠን መጠቀም ባለመቻሉ ነው። ከትምባሆና አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም ጋር ስናወራ አልኮል አብሮ የሚመጣ በመሆኑ ነው። የአልኮልን ጥራት፣ ደህንነት፣ ለአምራቹ ፍቃድ የመስጠትና መሰል ተግባራት ከምግብ ጋር አብሮ ይሰራል። ከ10 በመቶ በላይ የሆኑ የአልኮል መጠጦች በተለይ በብሮድካስት ማስታወቂያ ድሮም አይፈቀድም። ከ10 በታች ያሉት ግን በብሮድካስት ክልከላ አልነበረውም።
ስለዚህ በብሮድካስት በተለይ በጣም ብዙ አድማጭ ተመልካች ባለባቸው ሰዓቶች ከፍተኛ የሆነ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያዎች ይተላለፋ ነበር። ህጻናት ታሪካዊ የሆኑ ስፍራዎችን በታሪካቸው አያውቋቸውም ነበር። ስሞቹን በያዙ መጠጦች ተክተው እያወቋቸው በመሆኑ የቢራ መጠጦችን አውቀውታል፣ ከእዚህ ባሻገር መጠጦቹ የቤት፣ የመኪናና ሌሎች እጣዎችን በመያዛቸው ልጆች ወደ መዝናኛ ስፍራ ሲሄዱ ቤተሰቦቻቸውን ቢራ እንዲያዝዙ የሚያስገድዱበት ሁኔታ አለ። 18 ዓመት መቼ ደርሼ ብሎ የሚመኝ ልጅ እየተፈጠረ ይገኛል። ማስታወቂያ ልቅና የቁጥጥር ስርዓት ሲላላ የጠጪዎች ቁጥር ይጨምራል። ቁጥጥሩ ሲጠብቅም በተቃራኒው ይሆናል። ሌሎች አገሮችም ተግብረውት ውጤት አግኝተውበታል።
በመሆኑም አልኮል ማስታወቂያ ላይ ገደብ ተጥሏል። በየመንገዶች በቢልቦርድም ማስተዋወቅ ክልከላ ተደርጓል። የአልኮል መጠጦች ሎተሪ (ዕጣ) እንዳይኖራቸውም ሆኗል። 18 ዓመት የዕድሜ ገደብ ወደ 21 ዓመት ከፍ ብሏል። የብሮድካስት ማስታወቂያ በአዋጁ አብላጫ ድምጽ አጠቃላይ ክልከላ እንዲደረግ ምክር ቤቱ በመወሰኑ ለውጦች ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን፦ የእናንተ አንዳንድ ተቆጣጣሪ አካላት በቁጥጥር ስራቸው ችግሮችን እያዩ እንዳላዩ በማለፍ የሙስና ሁኔታ ለመፈጸም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ይነገራልና ለምን እነዚህን ወደትክክለኛው መስመር አታስገቧቸም?
ወ/ሪት ሔራን፦ እውነት ነው ይሄ በተቆጣጣሪዎች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የተቋሙ ስራ ለኪራይ ሰብሳቢነት በተለያየ መንገድ ተጋላጭ ያደርጋል። የተቋሙ ስራ የሚገናኘው በንግዱ ዘርፍ ከተሰማሩ ኣካላት ጋር ነው። አጠቃላይ ንብረት ላይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ውሳኔ የሚሰጥባቸው ስራዎች ናቸው። ይሄ ለተቆጣጣሪውም ለተቋሙም ስጋት አለው። በዛው ልክም በሁለቱም ወገን ለኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ተጋላጭ ነው። ይሄንን ልንቆጣጠር የምንችለው የሰራተኛውን አጠቃላይ ስነ ምግባርና አመለካከት ላይ በደንብ ሲሰራ ነው።
አጠቃላይ የተቋሙን ባህሪ ገጽታ በመቀየር ሰራተኛው በራሱ ፍቃድ ተነሳሽነት ኖሮት እንዲተገብር፣ ዕውቅና በመስጠት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ሌላው ስራችን ነው። ችግሩን ለመፍታት የብቃት ማረጋገጥ፣ ከመድሃኒትና ከምግብ ምዝገባ ጋር ተያይዞ ያሉ ስራዎች የኤሌክትሮኒክስ ስርዓት እንዲዘረጋ ተደርጓል። ተገልጋዩም ሃላፊውም ጉዳዩን ለመከታተል የሚያስችል ስርዓት እየተዘረጋ ይገኛል። ለሙስና የሚያጋልጡ ነገሮችን እየዘጋን የምንሄድበት ስርዓት ነው። በትግበራው ችግሩ እየቀነሰ ይሄዳል። የሕግና የአስተዳደር እርምጃ የምንወስድበት ይሆናል። አሁንም እያጣራናቸው ያሉና አስተዳደራዊና ሕጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ሰራተኞች አሉ።
አዲስ ዘመን ፦ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ወ/ሪት ሄራን፦እኔም አመሰግናለሁ
አዲስ ዘመን ጥር 20/ 2012
ዘላለም ግዛው