በአገሪቱ ያለው አቅም ውስን በመሆኑ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነውና መንግሥት የሌብነት ማዕከል ይሆናሉ ብሎ ያስቀመጣቸው ዘርፎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆኖ የደረጃ ሰንጠረዡን የሚይዘው ታዲያ መሬት ሲሆን፤ ይህንን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የተለያዩ አቅጣጫዎች ተቀይሰው በሥራ ላይ ውለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ብዙኃኑ የሀብቱ ተቋዳሽ መሆን ሲችል ተጠቃሚነታቸው እንደሚረጋገጥ ከማሰብ ይልቅ የግላቸውን ኑሮ ለማመቻት ሌት ተቀን የሚራወጡ ግለሰቦች እንዳሉና ለተጠያቂነታቸው ኅብረተሰቡ ከጎኑ እንዲቆም መንግሥት አበክሮ የሚያስተላልፈው መልዕክት ነው፡፡ ይህንን ያነሳንላችሁ ያለምክንያት አይደለም፤ ይልቁንም ከሰሞኑ በኅዳር ወር በሦስት ቤቶች ላይ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ያወጣው ጨረታ መንግሥትንና ሕዝብን በሚጎዳ መልኩ ተከናውኗል በሚል ለተቋማችን የደረሰውን ጥቆማ ይዘንላችሁ ስለቀረብን ነው፡፡
ጥቆማው
ጥቆማ አቅራቢዎቹ የከተማ አስተዳደሩ በሦስት ቤቶች ላይ ጨረታ እንዳወጣ በመግለጽ፤ ለምንና እንዴት እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ ተጫራቾች ሳይጫረቱ ሰነድም ሳይገዙ እንደቆመ ይናገራሉ፡፡ በቢሮ ተጀምሮ በዚያው ውስጥ ለውስጥ ተጠናቋል የሚባለው ይኸው ጨረታ ታዲያ ተጫራቾች የማይመለስ 100 ብር ከፍለው ሰነድ እንዲገዙ የወጣ ቢሆንም ለጨረታ ከቀረቡት ሦስት ቤቶች መካከል አንዱና በ 643 የቤት ቁጥር ላይ ያለው ግን ሰነዱ አልቋል መባሉን ይገልፃሉ፡፡ ‹‹ለምን አይሸጥልንም፣ እንዴትስ ሊያልቅ ቻለ?›› በሚል ላቀረቡት ጥያቄም አይሸጥም የሚል ድፍን ያለ ምላሽ ለተጫራቾች እንደተሰጠ ነው የሚናገሩት፡፡
ጨረታው ለሕዝብ ክፍት ከሆነና ማስታወቂያ ከወጣበት በኋላ ሰነድ መግዛት ክልከላ የተደረገበት የቤት ቁጥር 643 መጠሪያው ‘ፋሚሊ ሆቴል’ የሚሰኝ ሲሆን፤ በዚህ ላይ የተጫረቱት አንድ ግለሰብ መሆናቸውን በማንሳት ጥቆማ አቅራቢዎቹ ሁኔታውን ያብራራሉ፡፡ ግለሰቧ የራሳቸውን አምስት ሰዎች የጨረታውን ሰነድ በማስገዛት ስለተወዳደሩ ለእርሳቸው ጥቅም ሲባል ብቻ በጨረታው ሌሎች ተሳታፊ እንዳይሆኑ ‹‹ሰነድ የለም›› በሚል መከልከሉ ፍጹም ተገቢነት የጎደለው ተግባር ነው በማለትም ድርጊቱን ይኮንናሉ፡፡ በወቅቱ አስተዳደሩ ግርግር በመነሳቱ ወዲያው ጨረታው እንደተሰረዘ መስማታቸውን ይናገራሉ፡፡
ቤቱ የመንግሥት ንብረት መሆኑን የሚናገሩት ጥቆማ ሰጪዎቹ፤ ለጨረታ የቀረበው የቤቱ መነሻ ዋጋ 200 ሺህ ብር ቢሆንም የመንግሥትንና ሕዝብ ጥቅም ከግምት ያላስገባው የአስተዳደሩ ድርጊት ግን ይህንን ጥቅም እንዳሳጣው ይገልፃሉ፡፡ ጨረታው በዚህ መልኩ ባልታወቀ ሁኔታ ተደፋፍኖ በማለፉ በርካቶች በጨረታው ተሳታፊ ሆነው መንግሥት ሊያገኝ ይችል የነበረውን ጥቅም በአምስት ሰዎች ዘግተውታልም ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ጨረታው ከተዘጋ በኋላ ቤቱ ታሽጎ መቀመጥ ሲገባው ግለሰቧ ሰብረው ገብተውበታል፡፡ በአጠቃላይም የጨረታው ሒደት ሕጋዊ እንዳልነበር በመተቸት በኋላም ቤቱ እንዴት እንደሆነ ሳይታወቅ መተላለፉ ከተማ አስተዳደሩ ዓይን ያወጣ ሙስና መፈፀሙን አጠራጣሪ አያደርገውም ሲሉ ጥቆማ ሰጪዎቻችን አቅርበዋል፡፡ እኛም ወደ ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ቢሾፍቱ ከተማ ጉዳዩን ለማጣራት ተጉዘን ነበር፡፡
የጨረታ ኮሚቴው
ጥቆማ በቀረበበት ጨረታ ላይ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዳኛቸው ለገሰ፤ የጨረታ ማስታወቂያው ድርጅቱ የተሻለ አማራጭ ሲያገኝ በከፊልም ሆነ በሙሉ የመሰረዝ መብቱ የተጠበቀ እንደሆነ ይገልጽ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በዚህ መሠረት ጨረታው ለጊዜው እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ለጨረታው መቋረጥ ደግሞ ጊዜው አጥሯል የሚልና ለሕዝብ ዕይታ አመቺ ባልሆነ ቦታ ተለጥፏል የሚሉ ቅሬታዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ቅሬታዎቹን በደንብ ለመመልከት በመወሰኑ ጨረታው እንደቆመ ያስረዳሉ፡፡
ጨረታው ቢወጣም እንዳልተከፈተ የሚናገሩት ሰብሳቢው፤ በአንዳንዱ ቤቶች ላይ ብዙ ተወዳዳሪዎች ባልተሳተፉበት ሁኔታ ጥሩ ዋጋ ላይገኝ ይችላል በሚል ቅሬታዎቹን መነሻ በማድረግ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ያብራራሉ፡፡ በሕጉ መሠረት መሥሪያ ቤቱ ካላመነበት ይህን መሰል እርምጃ መውሰድ እንደሚቻል በመግለጽ፤ ጨረታው ግልጽ እንዳልነበርና የከተማው ነዋሪ ለመጥቀም በሚል የወጣ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ቀኑ ከደረሰ ግዴታ መከፈት ስላለበት በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ሰዎች ሰነድ እንዳላገኙ ቅሬታቸውን ስላቀረቡ በቀጣይ የጨረታ ማስታወቂያ ለማውጣት ተስማምተው መራዘሙን ይገልጻሉ፡፡
ከአስተዳደሩ ‹‹ቤቶቹ በጨረታ ተላልፈው ቁልፍ ይሸጥ›› በሚል በቀረበው ጥያቄ መሠረት መውጣቱን የሚናገሩት ሰብሳቢው፤ ብዙ ቅሬታዎች በመቅረባቸው መቆሙን ያስታውሳሉ፡፡ በጨረታ ሕግ ይህን መሰል አቤቱታ ሲቀርብ ቆም ብሎ ነገሩን ማጤንና መመልከት ተገቢ ስለሚሆን ተወያይተው ማራዘማቸውን ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን አንደኛው ቤት ሰው ገብቶበታል የሚለውን ቅሬታ እንደማያውቁ ነው የሚናገሩት፡፡ የተላለፈለት ግለሰብ ካለ መጀመሪያውኑ ጨረታ ማውጣት ተገቢ አይደለም የሚሉት ሰብሳቢው፤ በዚህ ላይ ከአስተዳደሩ የደረሳቸውና የሚያውቁት መረጃ እንዳሌለ ይናገራሉ፡፡
ቤቱን ማን ወሰደው? እንዴት?
የደረሰንን ጥቆማና የጨረታ ኮሚቴ ሰብሳቢው የሰጡንን ምላሽ ይዘን የቤት ቁጥር 643 ወደሆነው ፋሚሊ ሆቴል አመራን፡፡ በስፍራው እንደደረስን አቶ ሥዩም ተካ የተባሉ ግለሰብ አግኝተናል፡፡ ከዚህ ቀደም የመጠጥ ማከፋፈያ (ግሮሰሪ) ከፍተው ይሠሩ እንደነበር በመግለጽ፤ ኪራዩ እየተወደደ በመቸገራቸውና የመክፈል አቅም በማጣታቸው የከተማው ሽማግሌዎች ችግራቸውን ተረድተው ቤት እንዲሰጣቸው ለመንግሥት ባቀረቡት ጥያቄ ለ16 ዓመታት ተዘግቶ የኖረው ይህ ቤት እንደተሰጣቸው ይገልፃሉ፡፡
በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የሚያስረዱት አቶ ሥዩም፤ የመኖሪያ ቤት እንዳሌላቸውም ይናገራሉ፡፡ ችግራውን የተመለከቱ የአገሬው ሽማግሌዎችም የመንግሥት ቤት ቢኖራቸው የተሻለ ሥራ ሊሠሩ እንደሚችሉ ገልፀው በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎችን በር በማንኳኳት መጠየቃቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም ከ200 ሽማግሌዎች መካከል 17 ሽማግሌዎች ተመርጠው ከከተማው ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እስከ ማዘጋጃ ቤት በመሄድ ጥያቄውን ያነሳሉ፡፡ ለጥያቄያቸውም ቤቱን እንዲያገኙ በአስተዳደር እንደተወሰነላቸውና ቤቱ በባለቤታቸው በወይዘሮ አስቴር እንዳለ ሥም በመዞሩ ማደስ እንደሚችሉ ይረጋገጥላቸዋል፡፡
ውሳኔውን ያገኙት ነሐሴ 2011 ዓ.ም እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ስዩም፤ ቤቱን በተባሉት መሠረት አድሰው ቢጨርሱም የተሰጣቸው የሥምምነት ሰነድ አለመኖሩን ግን ይናገራሉ፡፡ ሥምምነት ወረቀቱ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁም ቀስ በሉ የሚል ምላሽ እንዳገኙና በቅርቡ እንደሚሰጣቸው ቃል እንደተገባላቸው ይናገራሉ፡፡ እድሳቱን ካጠናቀቁ በኋላ ቤቱ ውስጥ ጠቅልለው ከገቡ ሁለት ወራት እንደሞላቸው ይገልፃሉ፡፡
‹‹አድሱት ችግር የለም›› በሚል አስተዳደሩ እንደመለሰላቸው የሚናገሩት አቶ ሥዩም ዋስትናቸውም ሆኑ ማስረጃዎቻቸው ሽማግሌዎቹ እንደሆኑ ይናገራሉ። በዚሁ ቤት ላይ ስለወጣው ጨረታ ያውቁ ይሆን? ለአቶ ሥዩም ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር፡፡ እርሳቸው ግን በምላሻው እንደማያውቁ ነው የገለጹት፡፡ እንደተወሰነላቸውና ወረቀቱ እንደሚሰጣቸው ቢገለጽም በእንጥልጥል መቅረቱን በኀዘን ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም እነርሱን ጨምሮ ለ31 ዓመታት ቤቱን ሲጠብቁ የነበሩ ግለሰብ አንድ ክፍል የያዙ ሲሆን፤ ሌሎች ሦስት ወጣቶችም እንዲሁ ሰርቪሱ ውስጥ ይገኛሉ ይላሉ፡፡
ስለእነርሱ ቤት ብዙ ወሬ ሲናፈስ እንደሚሰሙ የሚናገሩት አቶ ሥዩም፤ በተቃራኒው ግን ሌሎች በርካታ የመንግሥት ቤቶች ሲሸጡ እንደሚመለከቱና አስተዳደሩ ውስጥ ብልሹ አሠራርን በሚከተሉ አካላት የቤቶች ሥም እንዴት እንደዞረ ሳይታወቅ እንደሚፈፀም ይናገራሉ። በተቃራኒው እነርሱ የሚገኙበትን ቤት ሽማግሌዎች በአግባቡ በመጠየቃቸው የሚናፈስ ወሬ እንደሆነ በመናገር ቅሬታው ተገቢ አለመሆኑን ውድቅ ያደርጋሉ፡፡
በመቀጠልም ቤቱ በሥማቸው ዞሯል የተባሉት ወይዘሮ አስቴር እንዳለን አግኝተን ያነጋርናቸው ሲሆን፤ ቤቱን ሽማግሌዎች ጠይቀው ያገኙት እንደሆነ ነው የነገሩን፡፡ ጨረታ እንደወጣ እንደማያውቁም ነው የሚገልጹት፡፡ ነገር ግን በዚህ ጨረታ እንደወጣበት የማያውቁት በአገር ሽማግሌዎች ጥየቃ ከተሰጣቸው ቤት ውጪ ሌላ አንደኛው ጨረታ ወጣበት የተባለው ቤት ጨምሮ ተዘግተው የነበሩ መሆናቸውን ለአስተዳደሩ ጥቆማውን የሰጡት እርሳቸው እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ በዚህ መልኩ ጥቆማ ከሰጡ በኋላ በአንደኛው ቤት ላይ እንዲጫረቱ ቢነገራቸውም እርሳቸው ግን በሽማግሌዎች ጥያቄ በአሁኑ ወቅት እየኖሩበት ያለውን ሆቴል በማግኘታቸው ሌላ ትርፍ እንዳላስፈለጋቸው ይገልፃሉ፡፡
በርካታ ቤት ተዘግቶ በሌላ በኩል ደግሞ ሥራ አጥ መኖሩ ተገቢ አይደለም የሚሉት ወይዘሮ አስቴር፤ በተቻለ መጠን ያለው ሀብት ውስን በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም ይገባል በማለት ቤቶቹ ተዘግተው ከሚቀመጡ ለከተማዋ ሥራ አጥ እንዲሰጥ መጠየቃቸውን ይናገራሉ፡፡ ቤቱ እንዲሰጣቸው መነሻ ሆነዋል ያሏቸውን ሠርተፊኬቶችንም አሳይተውናል፡፡ በተጨማሪም የከተማው ሽማግሌዎች ፊርማ ያረፈባቸው ሰነዶች በእጃቸው የሚገኙ ሲሆን፤ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር አካላት የተፃፃፏቸው ደብዳቤዎችንም ለመመልከት ችለናል፡፡
በከተማዋ የዋጋ ግሽበትን በማረጋጋትና የተለያዩ ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ ሥራዎችን በመሥራታቸው ከመንግሥት ይህንኑ ተግባራቸውን ለማመስገን በተለያዩ ጊዜያት የተሰጧቸው የምስክር ማረጋገጫ ወረቀቶች እንዳሉ የሚናገሩት ወይዘሮ አስቴር፤ የአገር ሽማግሌዎቹም ለእርሳቸው ቤት እንዲሰጥ ጥያቄ ያቀረቡበት ዋነኛ ምክንያት ይኸው መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይሁን እንጂ የከተማ አስተዳደሩ ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ግለሰቦች ለሕዝብና ለመንግሥት ሳይሆን የግል ኪሳቸውን ለማደለብ ከማሰብ የተነሳ ጉዳይን በብር ብቻ ማስፈፀም ይፈልጋሉ ይላሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ቤቱን ክልሉ እንዲሁም የከተማው ከንቲባ የተለያዩ ሰነዶችን አገላብጠው እንዲሰጣቸው የፈቀዱላቸው ቢሆንም የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ግን ለ16 ዓመታት የረሳውንና እንዳለም የማያውቀውን ይህንኑ ቤት አድሰው እንዲገቡ ካደረጋቸው በኋላ እስካሁን ምንም ዓይነት ማረጋገጫ እንዳልሰጣቸው በኀዘን ይገልፃሉ፡፡
ሆቴሉን ለማደስ ከፍተኛ ወጪ ማውጣታቸውን የሚገልጹት ወይዘሮ አስቴር፤ ለዓመታት የተጠራቀመ የውሃና የመብራት ሳይቀር ከ36 ሺህ ብር በላይ ክፍያ መፈፀማቸውን ይናራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አስፈላጊውን እድሳት ጨርሰው ቢገቡም ከአስተዳደሩ የተሰጣቸው
ፎቶ – ፀሐይ ንጉሤ
ፋሚሊ ሆቴል
«ቤቱ የከተማው ሽማግሌዎች በየደረጃው ለመንግሥት ባቀረቡት ጥያቄ ያገኘነው ነው፡፡ ጨረታ እንደወጣበትም አናውቅም፡፡ ነገር ግን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንድናድስና እንድንገባ በቃል ከነገሩን በኋላ ቤቱ በእኛ ሥም መሆኑን የሚያሳይና ሥራ መጀመር የሚያስችለን ምንም ዓይነት የሥምምነት ሰነድ ሊሰጠን አልቻለም»
ሥምምነት ባለመኖሩ ግን ሥራ መጀመር አልቻሉም። ይህንን ጥያቄ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ለአስተዳደሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ደበሌ በተደጋጋሚ እንዳቀረቡና እርሳቸውም እንዲያድሱ በቃል ከነገሯቸውና ያላቸውን ጥሪት ካፈሰሱ በኋላ የተባለውን ሥምምነት ሊሰጧቸው እንዳልቻሉና ለእንግልት እንደተዳረጉም ነው የሚናገሩት፡፡
እኛም በአሁኑ ወቅት በሆቴሉ የገቡትን ግለሰቦች እንዲህ ካነጋገርን በኋላ ‹‹ቤቱ የከተማው ሽማግሌዎች በየደረጃው ለመንግሥት ባቀረቡት ጥያቄ ያገኘነው ነው፡፡ ጨረታ እንደወጣበትም አናውቅም፡፡ ነገር ግን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንድናድስና እንድንገባ በቃል ከነገሩን በኋላ ቤቱ በእኛ ሥም መሆኑን የሚያሳይና ሥራ መጀመር የሚያስችለን ምንም ዓይነት የሥምምነት ሰነድ ሊሰጠን አልቻለም›› የሚለውን የግለሰቦቹን ምላሽ እንዲሁም ጥቆማውን በመያዝ ቤቱ በሽማግሌዎች ጥያቄ እንዴት ሊሰጥ ቻለ? ለግለሰብ ከተላለፈስ ለምን ጨረታ ማውጣት አስፈለገ? የሚሉና መሠል ጥያቄዎችን ይዘን ወደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ቢሮ አቀናን፡፡
የሚመለከተው አካል
በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ምክትል ሥራ አስኪያጅና የከተማ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከተማ ደበሌ፤ የመንግሥት ቤት የሚተላለፈው በጨረታ መሆኑን የሚያስቀምጥ መመሪያ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ በዚህ መመሪያ 2006 በተሰኘው የሕግ ማዕቀፍ መሠረት የቤቶች ማስተላለፍ ሁኔታው በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በመመሪያው መሠረት በአዋጅ 47/67 የተወረሱ ቤቶች በጨረታ ብቻ ይተላለፋሉ ይላል። ይህንን መነሻ በማድረግ በሦስት ቤቶች ላይ ጨረታ እንዲወጣ መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ተጫራቾች የማይመለስ 100 ብር በማስያዝ እንዲጫረቱ ቀርቦ ነበር፡፡
በ8/3/2012 ዓ.ም የወጣው የጨረታ ማስታወቂያ እያንዳንዱ ተጫራ ማሟላት የሚገባቸው መስፈርቶችንም ያካተተ እንደነበር አቶ ከተማ ይገልፃሉ፡፡ በዚህም በ22/3/2012 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 እንደሚከፈት የጨረታ ሰነዱ ተለጥፎ የነበረ ሲሆን፤ የተወሰኑ ሰዎች ተመዝግበው ነበር ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ መመሪያውን ተከትሎ ጨረታው ቢወጣም ‹‹ጨረታውን ብዙ ሰው አላየውም›› የሚል ቅሬታ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቀርቧል፡፡ በዚህም ጨረታው ሳይከፈት ወዲያው ሊቆም ችሏል፡፡ ሒደቱ እንዲቆም ቢደረግም ጨረታ ከወጣባቸው ቤቶች መካከል አንዱ በሆነው የቤት ቁጥር 643 ላይ ግን ሰው እንደገባበት ለአስተዳደሩ ጥቆማ ደርሷል፡፡ ነገር ግን ቤቱ ለግለሰቦቹ እንዲሰጥ የተወሰነ ውሳኔም ሆነ የተደረገ ሥምምነት የለም፡፡ ቤቱ ሆቴል ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የገቡት ሰዎች አስተዳደሩ ወስኖ አልሰጣቸውም፡፡ ከጨረታ ሒደቱ ከ15 ቀናት በኋላ ሰው እንደገባበት መረጃ ቢደርስም አስተዳደሩ በሕጋዊ መንገድ ሳያስተላልፍ ሆቴሉ ላይ ማን ገባበት? እንዴትስ ይህ ሊሆን ቻለ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያላገኘ በመሆኑ በቀጣይ ይጣራል፡፡ ጉዳዩን በሕግ ለመጠየቅም እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
እኛም ይህንን የኃላፊውን ምላሽ እንዳደመጥን ሁኔታው ከተከሰተና አስተዳደሩ ካወቀ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ድርጊቱም ከአስተዳደሩ ዕውቅናና ፈቃድ ውጪ ከሆነ በእነዚህ ጊዜያት ምን ዓይነት እርምጃን ወሰዳችሁ? የሚል ጥያቄን አንስተንላቸው ነበር፡፡ አቶ ከተማ፤ በምላሻቸው ለሕግ ክፍሉ ማሳወቃቸውንና በምን አግባብ ችግሩ እንደሚፈታ እየተወያዩ መሆናቸውን ገልፀውልናል፡፡ ኃላፊው በጉዳዩ ላይ እንደተወያዩ ቢገልጹም ለዚህ ማሳያ የሚሆን ችግሩን ለመፍታት በተደረገ ውይይት የተያዘ ቃለጉባዔ ስንጠይቃቸው ግን እንደሌለና በቃል ብቻ ተነጋግረው በሕግ እንደሚጠይቁ ምላሻቸውን ሰጥተውናል፡፡
ቤቱ ሰው ገብቶበታል ለዚህም የአስተዳደሩ የሕግ ክፍል ጉዳዩን ወደ ሕግ እንዲወስደው መነጋገራቸውን የሚናገሩት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፤ ቤቱ እንዲጠበቅ ለፖሊስ የተፃፈ ደብዳቤ እንዳለ ይገልፃሉ፡፡ ከዚህ በፊት ቤቱ ሆቴል የነበረ ቢሆንም ከ15 ዓመት በላይ ግን ተዘግቶ ቆይቷል፡፡ አስተዳደሩም በጥናት እንደደረሰበትና ከ30 ዓመት በላይ ግን አንድ ግለሰብ በጥበቃነት መቆየታቸውን እንደደረሰበትም ይናገራሉ፡፡
ቤቱ ለብዙ ዓመታት ተዘግቶ የቆየ በመሆኑ አስተዳደሩ በጨረታ አድርጎ ሊያከራየው አቅዶ ጨረታ ማውጣቱን ያስታውሳሉ፡፡ ቤቱ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ቢናገሩም እስከመቼ ለሚለው ጥያቄያችን ግን ደብዳቤ እየተፃፃፉ እንደሆነ ከመግለጽ የዘለለ ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ ቤቱን አስመልክቶ የሰነድ ማስረጃዎችንም ሊሰጡን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
ለተቋማችን የቀረበውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ባደረግነው ማጣራት በተጠቀሰው ቤት ያገኘናቸው ግለሰቦች ከአስተዳደሩ የእድሳት ፈቃድ ሳይቀር እንዳገኙ ቢገልጹም፤ የተባሉት የሥራ ኃላፊ ግን ግለሰቦቹ በምን አግባብ ቤቱ ውስጥ እንደገቡ እንደማያውቁ ነው የተናገሩት፡፡ እኛም በጉዳዩ ላይ የከተማው ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ምላሽ እንዲሰጥ ጥረት ብናደርግም ሊሳካ ግን አልቻለም፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 20/2012
ፍዮሪ ተወልደ