ምርጫው ቢተላለፍ ጥሩ ነው። ወደቀጣዩ ዓመት ሳይሆን ወደ ሌላ አገር። የፖለቲከኞች፣ የመራጩ ህዝቡና የአስመራጩ ሁኔታ አሳሳቢ ስለሆነ ምርጫው በገለልተኛ አገር ቢካሄድ አዋጭ ነው።
መራጩ ህዝብ ገና ምኑም ሳይያዝ የሚደግፋቸውን ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያለ መጥራት ጀምሯል። አንዳንድ ፖለቲከኞች ደግሞ የሚደግፏቸው ህዝብ ጩኸትና ጭብጨባ ስሜታዊ እያደረጋቸው ጸብ አጫሪ ንግግሮችን እያደረጉ ነው። ሀፍረት የሚባል ነገር አያውቁም። ያንሳፈፋቸው የስሜት ማዕበል ሲቀዘቅዝ በሰከንዶች ውስጥ የተነፈሱትን ለማስተባበል ሰዓታትን የወሰደ ማስተባበያ ሲሰጡ ይደመጣሉ። አስመራጩ አካልም ከፓርቲ ፕሮግራምና ከሃይማኖት መጽሐፍ እያጣቀሱ ፖለቲካን ወጥ፣ ሃይማኖትን እንጀራ አድርገው ለመራጩ ህዝብ ለማጉረስ የሚጥሩትን በዝምታ እየተመለከተ ነው።
ዘንድሮ እኛም ወግ ደርሶን ከ 130 የሚልቁት ፓርቲዎች በሁለት ጎራ ተከፍለዋል። እንደ አሜሪካኖቹ ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች ከሁለቱ ወገኖች አንዳቸውን ለመምረጥ እየተሰናዳን ነው። ፌዴራሊስቶች ነን የሚሉት ማንነትን መሰረት አድርገው የተደራጁ ፓርቲዎች ምርጫው ህዝቡ ከፌዴራሊስት ኃይሎችና አሃዳውያን አንዱን የሚመርጥበት ሪፈረንደም ነው ብለዋል። የአንድነት ኃይል እየተባሉ የሚጠሩት ወገኖችም እውነተኛ ፌዴራሊስቶች እኛ ነን መጪው ምርጫ ከህብረብሔራዊ ድርጅቶችና ከኮን ፌደራሎች አንዳቸው የሚመረጡበት ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ታዲያ ሁለቱም ወገኖች ታምር ካልተፈጠረ በቀር የየራሳቸው ጎራ እንደሚያሸንፍ በእርግጠኝነት እየተናገሩ ነው። እንዲህ ያለ አዝማሚያ የሚያመጣውን አደጋ ማስቀረት አሊያም ብዙ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር የሚቻለው ምርጫው በገለልተኛ አገር ሲካሄድ ነው።
ሪፈረንደሙ (ምርጫው) አገር ውስጥ የሚካሄድ ከሆነ ለየትኛውም ፓርቲ ውግንና የሌላቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ማግኘት አዳጋች ነው። በሌላ አገር ቢካሄድ ግን በቀላሉ ገለልተኛ ተሳታፊዎችን ማግኘት ይቻላል። ችግሩ ከ 130 በላይ የሆኑት ፓርቲዎች የሚስማሙበት ገለልተኛ አገር ማግኘት አይቻልም። ገዢው ፓርቲ ኤሪትሪያን ተቃዋሚዎች ደግሞ ግብጽን የሚመርጡ ይመስለኛል። ለሕዳሴው ግድብ ውዝግብ መፍትሄ የሆነችው አሜሪካ ተቃዋሚዎችንና ገዢውን ፓርቲ ማስማማት አያቅታትም። ዋናው ነገር በመርህ ደረጃ ምርጫው በገለልተኛ አገር እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱ ነው።
በዘንድሮ ምርጫ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በእኩል ደረጃ ከመራጩ ህዝብ ጋር መገናኘት የሚችሉት በማህበራዊ ድረ ገጾች ብቻ ነው። ሶሻል ሚዲያው ሁነኛ የቅስቀሳ ማድረጊያ ሜዳ መሆኑ አይቀሬ ነው። ተወዳዳሪዎቻቸው በማህበራዊ ድረ ገጾች አካውንት ከፍተው በግላቸው የምረጡኝ ዘመቻ ማካሄድ እንዲችሉ ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ፓርቲዎች በርካታ ናቸው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዲያ ባለቤት መሆን እንደማይችሉ ተደንግጓል። እንደሚታወቀው ሕግ የሚከበርበት አገር በመሆኑ የሚዲያ ተቋማት በቀጥታ በፖለቲካ ፓርቲዎች ባለቤትነት አልተያዙም። ነገር ግን የሚሰሩትን ስራ በመመልከት የትኛው ሚዲያ በማን እንደሚዘወር ማወቅ ቀላል ነው። አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በስውር እጅ የሚዘውራቸው ፓርቲ አፈ ቀላጤዎች መሆናቸውን ከወዲሁ እያሳዩ ነው።
እኔ የምለው … በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው እያንዳንዱ ፓርቲ ለምርጫ ቅስቀሳ ተመጣጣኝ የአየር ሰዓት የሚያገኘው ? ዛሬ እንደ ትናንቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብቸኛ አማራጭ አይደለም። ፖለቲካዊ አጀንዳን አንግበው የተቋቋሙ ሚዲያዎች በርክተዋል። ገዢው ፓርቲና አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዜና፣ በትንታኔ፣ በመዝናኛና በተለያዩ ፕሮግራሞቻቸው 24 ሰዓት የምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጉላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሏቸው። የተቀሩት ፓርቲዎች ግን ብሮድ ካስት ባለስልጣን ከሚመድብላቸው ሽርፍራፊ ሰዓት ውጭ አማራጭ የላቸውም። ምርጫው በገለልተኛ አገር ቢካሄድ ግን የአገሩን ሚዲያዎች የመጠቀም ተጨማሪ ዕድል ያገኛሉ።
ምርጫውን ውስብስብ የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በምርጫው የሚሳተፉት ዋነኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጫካ የገቡ በመሆናቸው ምናልባት ዱላ፣ ሜንጫ፣ ጠመንጃ፣ ቀስት፣ ወንጭፍና ድንጋይን የምርጫ ምልክት ሊያደርጉ ይችላሉ። የእነዚህ ፓርቲዎች ደጋፊዎች የምርጫ ምልክቶቻቸውን ይዘው ለድጋፍ ሰልፍ አደባባይ ሲወጡ ሊፈጠር የሚችለውን ነገር አስቡት። እንደኔ ገዢው ፓርቲ የምርጫ 2012 ምልክቱን ጋሻ ቢያደርግ የደጋፊዎቹን ህይወት ማትረፍ የሚችል ይመስለኛል። በቅርቡ ፓርላማው ያጸደቀው የጦር መሳሪያ ህግ መሰል መሳሪያዎች ለሽብር ተግባር እስካልዋሉ ድረስ ለሌላ ዓላማ ክልከላ እንደማይደረግባቸው ደንግጓል።
በምርጫ ዘመቻ ወቅት ተወዳዳሪዎች ቢያሸንፉ የሚወስዷቸውን እርምጃዎች እየዘረዘሩ ቃል የሚገቡት በሰለጠነው ዓለም ነው። በኛ አገር የፖለቲካ ባህል ግልጽ ከሆነ የፓርቲ ፕሮግራም ይልቅ “ይበላሃል ጅቦ” እየተባለ የሚዘፈን ማስፈራሪያ ውጤት ያመጣል።
ተወዳዳሪዎች በምርጫ ዘመቻ ወቅት ስለፓርቲያቸው ፖሊሲና ስለዕጩዎቻቸው ብቃት ለመራጩ ህዝብ የተሟላ መረጃ መስጠት ይጠበቅባቸዋል። ይህ አይነቱ አካሄድ ህዝቡ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ላይ ደርሶ ወካዩን እንዲመርጥ ያደርገዋል። እዚህ አገር ግን ይህ አይሰራም ከዚህ ቀደም በአንድ የምርጫ ክርክር ላይ የፓርቲያቸውን ፖሊሲ የተጠየቁ የፓርቲ ሊቀመንበር “ሳልመረጥ ፖሊሲዬን አልናገርም” ብለው እርፍ ብለዋል። በቅርቡም የአንድ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፕሮግራማችሁ ምንድን ነው ተብለው ሲጠየቁ። “ህዝባችን በትክክለኛ ሰዎች ስላልተወከለ መጀመሪያ ውክልናውን ማግኘት ነው የምንፈልገው ፕሮግራም ከዚያ በኋላ የምንቀርጽ ይሆናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ከዚህ ቀደም ቦርዱ ለፓርቲዎች የምርጫ ዘመቻ የሚውል ገንዘብ በሚሰጥበት ቀመር መሰረት 10 በመቶው ብቻ ለሁሉም ተሳታፊ ፓርቲዎች እኩል ይከፋፈላል። አስገራሚው ነገር 40 በመቶው ፓርቲዎቹ በፓርላማ ባላቸው መቀመጫ ብዛት የሚከፋፈል መሆኑ ነው። በሁለት የምርጫ ዘመን 99 ነጥብ ስድስት በመቶና መቶ በመቶ በአንድ ፓርቲ አባላት በተያዘ ፓርላማ እንዲህ ያለ ሕግ ስራ ላይ መዋሉ አስገራሚ ነው።
መቶ አይነት ፍላጎቶች ባሉባት አገር አንድ ፓርቲ መቶ በመቶ “እያሸነፈ” የዓለም ሪከርድን ሲሰባብር አሸናፊዎቹ በእንግሊዝኛ ተሸናፊዎቹ ደግሞ በአማርኛ “ጉድ” ብለዋል። በወቅቱ አንድ ባለስልጣን በአማርኛ “ጉድ” ላሉት ወገኖች ምላሽ ሲሰጡ ፣ “ገዢው ፓርቲ ሁሉንም ወንበሮች አልተቆጣጠረም የተወሰኑትን አጋሮች ናቸው የያዙት” ብለው ብዙዎች ሳያቅዱ እንዲስቁ አድርገው ነበር። በአዲስ መልክ የተቋቋመው ምርጭ ቦርድ የሚመሰገንበት አንዱ ምክንያት ቀመሩ ላይ ማስተካከያ ማድረጉ ነው።
በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ አሁን እንዳለው ስብስብ አመኔታን ያተረፈ ምርጫ ቦርድ የለም። እርግጥ ነው ባቀረበው ጊዜያዊ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅር ተሰኝተዋል። እኔ ግን የእስከዛሬውን ምርጫ ማካሄጃ ወር እንደ ዶግማ ሙጥኝ ማለት ትርጉም ያለው አይመስለኝም። ካሁን ቀደም ምርጫው በግንቦት ወር ሲካሄድ የቆየው በወቅቱ አመቺነት ሳይሆን በገዢው ፓርቲ አጉል እምነት ነው ባይ ነኝ። አሁን ማሊያ የቀየረው ገዢ ፓርቲ ደርግን አሸንፎ ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የቻለው በግንቦት ወር ነው።
በዚህ ምክንያት ግንቦት ወርን ገዱ አድርጎ የሚመለከተው ይመስለኛል። ምርጫው በግንቦት ወር ላይካሄድ እንደሚችል ስሰማ አንድ ዓመት ተራዝሞ ዕድሉ ለባለተራው መጋቢት ወር የሚሰጥ መስሎኝ ነበር። የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫው በያዝነው ዓመት እንዲካሄድ ግድ እንደሚል ስረዳ ገዢው ፓርቲ ሌላ ገዳም ቀን ከየት ያገኛል እያልኩ ስጨነቅ ነበር። በኋላ ነሐሴ 10 ተመረጠ። ነሐሴ አስር የጠቅላይ ሚኒስትሩ የልደት ቀን ነው። ገዢው ፓርቲ አሁንም ከአጉል እምነቱ የተላቀቀ አይመስልም።
በ1923 የተዘጋጀው ህገ መንግሥት “ህዝቡ ራሱ መምረጥ እስከሚችል ድረስ የምክር ቤቶቹ አባላት በንጉሡና በመኳንንቱ ይመረጣሉ” የሚል አንቀጽ ነበረው። ምርጫ ቦርድ ከዚህ አንቀጽ ትምህርት ወስዶ አገሪቷ ምርጫ ለማካሄድ አመቺ እስክትሆን ድረስ ምርጫው በሌላ አገር እንዲካሄድ ቢወስን መልካም ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 20/ 2012
የትናየት ፈሩ