ከጤና ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በኢትዮጵያ በየቀኑ ከሃያ እስከ ሰላሳ የሚሆኑ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡ይህም በየወሩ 100 እናቶች (ሁለት አገር አቋራጭ አውቶብስ ሙሉ) ህይወታቸውን ያጣሉ እንደማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በየወሩ 2 ሺ 400 እናቶች ለልዩ ልዩ የጤና ችግሮች የሚጋለጡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉን ማትረፍ እየተቻለ ነው ለሞት የሚዳረጉት፡፡የእናቶች ጤና አገልግሎት ሽፋን በሚፈለገው ልክ ተደራሽ ባለመሆኑም 50 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰ-ጡር እናቶች አሁንም በቤት ውስጥ ይወልዳሉ፡፡
እስካሁን በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ብቻ ያተኮሩ በመንግስት የተገነቡ ሆስፒታሎች ብዙም ባይኖሩም፣ አገልግሎቱ ከመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች አንስቶ እስከ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል ድረስ ከሌሎች ህክምናዎች ጋር ተካቶ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን የእናቶችና ህፃናት ጤና በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ በመደረጉ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎቶችን የማስፋት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡በቅርቡም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ በእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት ላይ ያተኮረ ራሱን የቻለ ሆስፒታል አስመርቆ ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር ወንድምአገኝ ገዛኸኝ እንደሚሉት፤ ሆስፒታሉ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎትን ለረጅም ጊዜ ተሸክሞ ቆይቷል፡፡ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ራሱን ችሎ የተገነባው የእናቶችና የህፃናት ልዩ ሆስፒታል በተለይ የጨቅላ ህፃናት ህክምናን ወደተሻለ ደረጃ ያደርሳል፡፡የእናቶች የጤና አገልግሎትንም በተሻለና ምቹ በሆነ መልኩ ለመስጠት ያስችላል፡፡
በ2 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ልዩ ሆስፒታሉ 453 በሚሆኑ አልጋዎች ፣ በ13 ክፍሎች የቀዶ ህክምና እና በስድስት አልጋዎች ልዩ የህፃናት እንክብካቤና የእናቶች ጤና አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ይህም ልዩ ሆስፒታሉ በተለይ በህፃናት ጤና ላይ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ይበልጥ ያሰፋዋል፡፡የህፃናት ቀዶ ህክምና አገልግሎቱንም በእጥፍ ያሳድጋል፡፡
እንደ ዋና ፕሮቮስቱ ገለፃ፤ በሃገሪቱ በርካታ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት ማእከላት ቢኖሩም፣ በጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው የእናቶችና ህፃናት ልዩ ሆስፒታል ራሱን ችሎ ከጨቅላ ህፃናት አንስቶ እስከ እናቶች ማዋለድ ህክምና ድረስ የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚችል በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡በቀን እስከ 1ሺ200 ለሚሆኑ እናቶች የማዋለድና እስከ 300 ለሚሆኑ ጨቅላ ህፃናት እስከ ልብ ቀዶ ህክምና ድረስ የዘለቀ የህክምና አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ተመሳሳይ የእናቶችና የህፃናት ጤና አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎችን ማስፋት የሚቻል ከሆነ የእናቶችና ህፃናትን የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋት፤ የአገልግሎት ጥራትንም ማሳደግ ይቻላል፡፡
ለቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ የቆዩት በቡፌት ፋውንዴሽን የአለም አቀፍ ፕሮግራም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሃ እንደሚሉት፤ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተጀመረውን ልዩ የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል አገልግሎት ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የማስፋት ስራዎች ይሰራሉ፡፡በተለይም አገልግሎቱ በቀጣይ በመቀሌ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ ሃሮማያ፣ ጅማ፣ አዳማና ሌሎችም ከተሞች እንዲስፋፋ ይደረጋል፡፡
በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያም የሚሰራ ማእከል ለመገንባት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የመሰረት ድንጋይ የተጣለ ሲሆን ፣ግንባታው በቀጣይ ሲጠናቀቅ የስነ ተዋልዶ ጤና ምርምርን፣ ስልጠናን ፣ፖሊሲንና ስርፀትን የሚሰራ ተቋም ይሆናል፡፡ማእከሉ እየጠነከረ ሲሄድ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ትልቅ የስነ ተዋልዶ ጤና የልህቀት ማእከል ሆኖ ያገለግላል፡፡
ዳይሬክተሯ በእናቶች ጤና በኩል ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ የካንሰር ህመም መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ የጡት ካንሰርና የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር ለእናቶች ሞት ምክንያት በመሆን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጠቀሱ ያብራራሉ፡፡ሴቶች የካንሰር ህመም ስር ከሰደደ በኋላ ሳይሆን አስቀድመው እንዲከላከሉት ለማድረግ በልዩ ሆስፒታሉ በመምጣት አስቀድመው ምርመራ አድርገው ራሳቸውን እንዲከላከሉ የማድረግ ስራ አስቀድሞ ይሰራል ብለዋል፡፡በሽታው ስር ሳይሰድ ቶሎ ሆስፒታል መምጣት ከቻሉ በቶሎ ማከም እንደሚቻል ያብራራሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ከወሊድ ጋር በተያያዘም በተለይ በስነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ ሴቶች ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል እንዲችሉ በርካታ ስራዎች የሚቀሩ በመሆናቸው ህብረተሰቡን በማሳተፍ በትኩረት መስራት ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ የጤና ስትራቴጂ የሚያተኩረው በገጠር እናቶች ላይ ከመሆኑ አኳያ በቅድመ መከላከል ላይ በስፋት መስራት ይገባል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ውስጥ የተገነባው የእናቶችና ህፃናት ሆስፒታል የእናቶችና ህፃናትን የጤና አገልግሎት ከማሻሻልና በተለይ ልዩ የሆኑ የህክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ፤ በዋናነት ደግሞ በወሊድ ወቅት የተለያዩ ችግሮች የሚገጥማቸውን እናቶች የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል፡፡
የፅኑ ህክምና አገልግሎትን ጨምሮ የእናቶች፣ የሴቶችና ህፃናት ህክምናና በርካታ አገልግሎቶችንም ለመስጠት ይጠቅማል፡፡ሆስፒታሉ ሪፈራል በመሆኑ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ዙሪያ ላሉና ከተለያዩ ክልሎች ለሚመጡም አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደሚሉት፤በርካታ ህዝብ በገጠር የሚኖር ከመሆኑ አኳያ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚቻለው ልዩ ሆስፒታሎችን በመገንባት ብቻ አይደለም፤ ከታች ጀምሮ ጤና ጣቢያዎችና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ጠንካራና የተሟላ የማዋለድ፣ የቀዶ ህክምናና ሌሎችንም አገልግሎቶችን እንዲሰጡ በማድረግ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ትልቁ ትኩረት መሆን ይኖርበታል፡፡
ለዚህም 400 የሚሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የእናቶችና የህፃናት ጤና አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ አስፈላጊውን ማቴሪያል የማሟላት ስራ ጤና ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ይህም በእናቶችና ህፃናት ጤንነት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ይሁን እንጂ የተለያዩ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎቶችን የሚሰጡ ልዩ ሆስፒታሎችን ደረጃ በደረጃ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ማስፋት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 19/2020
አስናቀ ፀጋዬ