የገና ወይም የእየሱስ ክርስቶስ ልደት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በልዩ ድምቀት የሚከበር ዓመታዊ በዓል ነው። ከሃይማኖታዊ በዓልነቱ በተጨማሪም ባህላዊ እሴቶች የሚንፀባረቁበት፤ ብዙሃኑ ዓመት በመጣ ቁጥር በተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶች እና መዝናኛዎች በድምቀት አክብረው የሚውሉበት ነው። የበዓሉ ማድመቂያዎች ከሆኑት ዝግጅቶች መካከል ደግሞ ባህላዊ ስፖርቶች በተለይም ደግሞ የገና ጨዋታ ይገኝበታል።
ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ እዚህ የደረሰው የገና ጨዋታ በሀገራችን ጥንታዊ ከሆኑ ባህላዊና ስፖርታዊ ውድድሮች ውስጥ ይመደባል። ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› በሚል ወጣቶች እና ህፃናት በየአካባቢያቸው ሰው በብዛት በሚሰበሰብበት ሜዳዎች ላይ አጓጊ ውድድር እና ስፖርታዊ ፍልሚያ ያደርጋሉ። ከዚህም ባለፈ በባህል ስፖርት ዘርፍ እውቅና ተሰጥቶት ከሌሎች መሰል ስፖርቶች ጋር በየዓመቱ በቋሚነት ውድድሮች ይዘጋጃሉ።
ዛሬ መላው ክርስቲያን በአንድነት በሚያከብረው የገና በዓል ዋዜማ ላይ እንገኛለን። ይህን ደማቅ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ ደግሞ በዚህ የዓመት የገና ጨዋታ እና ሌሎች የባህል ስፖርቶች በጋራ በማቀናጀት ለሳምንት የዘለቀ ውድድር በኢትዮጵያ ወጣቶች_ስፖርት አካዳሚ ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ረፋዱ ላይ ይጠናቀቃል።ውድድሩ በአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን የተዘጋጀ ነው። የገና ጨዋታ፣የፈረስ ጉግስ፣ ትግል፣ ቀስትን ጨምሮ 12 የባህል ስፖርቶች ህግና ደንብ ወጥቶላቸዋል። በዓሉን ምክንያት ያደረገው እና ለሳምንት የዘለቀው ጨዋታም እነዚህን የስፖርት አይነቶች ያካተተ ነው።
የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ የሚደረጉ የባህል ስፖርት ጨዋታዎች ለበዓል ድምቀት ይሁኑ እንጂ እንደ ከዚህ ቀደሙ ወግ እና ስርዓታቸውን ጠብቀው እንዲሁም ከዘመናዊው ስፖርት ጋር ተዋህደው በየጊዜው እድገት ሲያሳዩ አይስተዋሉም። ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ የነበራቸው ተቀባይነት እየደበዘዘና የመጥፋት አደጋ እየተጋረጠባቸው ይገኛል። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ከሚደረጉ የውድድር መርሃ ግብሮች ይልቅ ከአንድ እና ሁለት አጋጣሚዎች በዘለለ ትኩረት ተሰጥቷቸው አይዘጋጁም።
በአዲስ አበባ የሚደረጉ የባህል ስፖርቶች ውድድር የገና በዓል ሲመጣ ብቻ ሳይሆን በተለያየ ጊዜያት በስፋት መደረግ ይኖርበታል የሚል አስተያየት የሚሰነዝሩ በርካቶች ናቸው። እነዚህ ወገኖች «ዘመናዊ ስፖርቶች የሚስፋፉት መነሻቸውን ከባህላዊ ስፖርቶች መሰረት በማድረግ ነው» ሲሉ የባህል ስፖርቶች ላይ በትኩረት መስራት የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ለማሳየት ይሞክራሉ፤ በአገራችን በርካታ ባህላዊ ይዘት ያላቸውን ጨዋታዎች ከማስፋፋት ባለፈ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ማስቻል አስፈላጊ መሆኑን ነው የሚያሰምሩበት።
‹‹የባህል ስፖርታችን ተንቋል›› የሚል አመለካከት ያላቸው ወገኖችም አልጠፉም። ‹‹ለስፖርታዊ ወድድሮቹ በተዋረድ ሁሉም አካላት ትኩረት መስጠት አልቻሉም›› በማለት የሚሞግቱ ባለሙያዎች ከያአቅጣጫው ሃሳባቸው ሲሰነዝሩ ይደመጣል። በተለይ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳለበት ይነገራል።ውድድሮችን በተፈለገው መንገድ ለማዘጋጀት አቅም የለውም፤ ክፍለ ከተሞች ተወዳዳሪዎቻቸውን በተገቢው መንገድ በማስተባበር እና በማዘጋጀት፤ እንዲሁም የከተማው የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮው ለፌዴሬሽኑ እንደሌሎቹ ስፖርቶች ትኩረት በመስጠት ባህላዊ የስፖርት ውድድሮችን እስከነአካቴው ከመጥፋት ሊታደጓቸው እንደሚገባ ጥሪ የሚያስተላልፉ ወገኖች አልጠፉም። የዝግጅት ክፍላችን እነዚህ ጉዳዮች እንዴት ይታያሉ? በሚል ለአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስቶ ነበር።
አቶ ጌትሽ አስራት የአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን የፅህፈት ቤት ኃላፊ ነው። እርሱ እንደሚለው በዘንድሮው የገና ወቅት የባህል ስፖርት ውድድር በፈረስ ጉግስ፣ የገና ጨዋታ፣ በቱርቦ ድብልቅ እና በሌሎች ተጨማሪ ጨዋታዎች ለሳምንት የዘለቀ ውድድር እየተካሄደ ነው። የዘንድሮው ውድድር ከዚህ ቀደም ከተደረጉት ሻል ያለ እንቅስቃሴ ይታይበታል። አንፃራዊ በሆነ መልኩም አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት ሁሉም ክፍለ ከተሞች ስፖርተኞችን አቅርበው በመወዳደር ላይ ይገኛሉ።
የፅህፈት ቤት ኃላፊው የባህል ስፖርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን እና የሚነሱት ቅሬታዎች ትክክል መሆናቸውን ይናገራል። ይህ የሆነው ከበላይ የስፖርቱ አመራሮች ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ውስጥ የሚገኙት ባለድርሻ አካላት ልክ እንደ ዘመናዊው ስፖርት ሁሉ ለባህል ስፖርት ትኩረት አለመስጠታቸው የችግሩ መነሻ መሆኑን ያስረዳል። ከዚህ ባለፈ የመገናኛ ብዙሃን ለዚህ ዘርፍ በትኩረት በመስጠት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥረት አለማድረጋቸው እና በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ አለመስራታቸው አሁን የሚታየውን መዳከም እንደተፈጠረ ያስረዳል። በተለይ የገና በዓል ሲደርስ ብቻ ስለ ባህል ስፖርት መነሳቱ ተገቢ አለመሆኑን ነው የሚገልፀው።
ስፖርቱ አለመስፋፋቱን ተከትሎ መንስኤ ናቸው ተብለው ከሚነሱ እንቅፋቶች መካከል የበጀት እጥረት ዋናውና አንዱ ነው። በከተማው እና በሁሉም ክፍለ ከተሞች ውስጥ ለባህል ስፖርቶች በቂ አቅም ለመፍጠር የሚያስችል በጀት እንደማይመደብ ይነገራል።
‹‹ክፍለ ከተሞች ለዘመናዊ ስፖርቶች ከፍተኛ በጀት ቢመድቡም ነገር ግን ለባህል ስፖርቶች የሚሰጡት ትኩረት አነስተኛ ከመሆኑ በጀቱም በዛው ልክ ዝቅተኛ ነው›› የሚለው አቶ ጌትሽ ለእግር ኳስ እና መሰል ዘመናዊ ስፖርቶች ከሚመደበው ጋር ፍፁም እንደማይገናኝ ይገልፃል። አንዳንድ ጊዜ እንዲያውም በጀት የለንም በማለት ክፍለከተሞች በውድድሮች ላይ እንደማይሳተፉ ይናገራል። በውድ ድሩ ላይ የሚኙትም ክፍለከተሞች በውስን ስፖርቶች ላይ ብቻ የሚሳተፉ መሆኑን ያስረዳል። በተለይ ፌዴሬሽኑ ዓመታዊ ውድድር ሲያዘጋጅ ክፍለከተሞች በወረዳ ደረጃ አወዳድረው ስፖርተ ኞችን መርጠው ከተማ አቀፍ ውድደር ላይ መገኘት ሲገባቸው በበጀት እጥረት ምክንያት የሚታ ወቁ ስፖርተኞችን ብቻ መርጦ የማምጣት ችግር እንደሚታ ይባቸው ነው የሚያስረዳው።
አዲስ አበባ ውስጥ የባህል ስፖርቶች ፈተና እየገጠማቸው እንደሚገኝ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለዚህ መነሻ እንደ ምክንያት ከሚቀመጡት ችግሮች መካከል ደግሞ ዘመናዊነት እና የከተሜነት ጣጣው ነው። አቶ ጌትሽ ይህ ጉዳይ አንዱ እንቅፋት እንደሆነ በመግለፅ ‹‹የባህል ስፖርቶች ህዝባዊ መሰረት እንዲይዙ ተደራሽነታቸው ሊሰፋ ይገባል›› ይላል። በዚህም ተከታታይ ውድድሮች እና ስልጠናዎች ሲሰጡ ከዘመናዊው ስፖርት ባልተናነሰ በአዲስ አበባ ውስጥ የባህል ስፖርትን ማስፋት ያስችላል የሚል እምነት አለው። በተለይ የባህል ስፖርትን ሳይበረዝ ማሳደግ እንዲቻል እና በከተሜው ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነቱ እንዲሰፋ የመገናኛ ብዙሃን ሚና ሰፊ መሆኑን ያሰምርበታል።
የአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ብቻ ታህሳስ ላይ ውድድር ያዘጋጅ ነበር። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን በሌላ መርሃ ግብር መጋቢት ወር ላይ ተጨማሪ ውድድሮችን እያደረገ ይጋኛል። ለባህል ስፖርት መዳከም የውድድሮች ማነስ አንደኛው ምክንያት እንደሆነም ሲጠቀስ ቆይቷል። በዚህ ላይ አስተያየቱን የሚሰጠው የጽህፈት ቤት ኃላፊው ‹‹ስፖርቱን በማስፋት ህብረተሰባዊ መሰረት እንዲኖረው ውድድሮች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ከዚህም ባለፈ መሰናዶው በባለሙያ የተደገፈ ሊሆን ይገባል›› በማለት በተለይ በትምህርት ቤቶች አካባቢ አዲሱ ትውልድ ላይ ለማስረፅ በብቁ ባለሙያ የታገዘ ስራ ማከናወን አማራጭ የሌለው መሆኑን ያነሳል። በዋናነትም የባለሙያ እጥረቱን ለመቅረፍ ፌዴሬሽኑ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ያስረዳል።
‹‹የባህል ስፖርት ከተማው ላይ ያለው ወጣቱ ትውልድ አንዲያዘወትረው እንደ ኦሎምፒክ ስፖርቶች ፕሮጀክት ተቀርፆ ታዳጊዎችን ማፍራት ይኖርበታብል›› የሚለው የፅህፈት ቤት ኃላፊው አሁን ላይ ግን ከተማው ውስጥ ተወልደው የሚያድጉ ወጣቶች እና ማህበረሰቡ ዘመናዊ ስፖርቶች ላይ ብቻ ትኩረቱን እያደረገ መሆኑን ያነሳል። በአገር አቀፍ ደረጃም ፌዴሬሽኑ ይህ ነው የሚባል አመርቂ ውጤት እያገኘ አይደለም። በተለይ ውስን ውድድር በሚደረጉበት አዲስ አበባ ላይ የባህል ስፖርትን ወክለው የሚሳተፉ ወጣቶች በትምህርት እና ለኑሮ ከሌላ አካባቢዎች የመጡ ነበሩ፤ አሁን ግን የዋና ከተማው ነዋሪዎችን ብቻ ለማሳተፍ ሙከራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የባህል ስፖርት በብርቱ መዘንጋቱን የሚያመላክቱ መረጃዎችን ከያቅጣጫው አንስተናል። በዘንድሮው ዓመት ግን ትኩረት ሊያገኝ እንደሚገባ የተገነዘቡ አካላት እየተፈጠሩ መሆኑን አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ያስገነዝባሉ። ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት የሚካሄደው ውድድር አንድ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ብቻ ነበር። አሁን የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር ልክ እንደ ኦሎምፒክ ስፖርት ውድድሮች እንዲኖረው ለማድረግ እየተሰራ ነው። በተለይ አንዳንድ የባህል ስፖርቶች በትምህርት ቤት ውድድሮች እና በመላው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ እንዲካተቱ መደረጉ እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወሰድ ነው። ይሄ ሂደት በተለይ በገና ክብረ በዓል ላይ ብቻ የሚደምቀው የአዲስ አበባ የባህል ስፖርት ጨዋታ የተሻለ አጋጣሚ እንዲፈጠርለት ያደርጋል። ከዚህ ባለፈ ስፖርቱን የሚወድ፤ የባህል ስፖርቶች ምንነትን እንዲሁም ህጎቹን ጠንቅቆ የሚረዳ ዘመናዊ ማህበረሰብ የመፈጠር እድሉን ከፍ ያደርገዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2011
ዳግም ከበደ