
ኢትዮጵያ ስለአረንጓዴ ልማት ከሚዘምሩት አገራት መካከል በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች። አረንጓዴ ልማትን ተግባራዊ ለማድረግ ፖሊስና ስልት ነድፋለች። አገሪቱ ከነደፈቻቸው የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲዎች መካከል የደን ልማት አንዱ ነው። ባለፉት ዓመታት የደን ልማቱን ተግባራዊ ለማድረግ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ተክላለች። ይሁን እንጂ የተተከሉት ችግኞች ጸድቀው ውጤታማ ከመሆኑ አንጻር ችግር አለባቸው።
ከኢትዮጵያ የአካባቢና ደን ምርምር ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ከ2006 እስከ 2011 ዓ.ም 24 ነጥብ 1 ቢሊዮን ችግኝ ተክላለች። በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በተደረገው የጽድቀት የዳሰሳ ጥናት በአማካይ 54 ነጥብ 5 በመቶ ነው። ይህ ማለትም ከተተከለው ችግኝ 45 ነጥብ 5 በመቶ አልጸደቀም። በዚህም አገሪቱ ባለፉት ስድስት ዓመታት 65 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ከስራለች። ይህ ኪሳራ የደን ልማታችን አካሄድ ትክክል አለመሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።
የደን ልማቱ አካሄድ ከፖሊሲ እስከ አፈጻጸም ችግር ያለበት መሆኑንም የሚያሳይ ነው። የዘርፉ ምሁራንም የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው። በመሆኑም የደን ልማት ፖሊሲውን መቀየር ያስፈልጋል። ሲቀየርም የዘርፉን ባህሪ ታሳቢያ ያደረገ፣ የመሬት አጠቃቀም፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ የዘርፉ አልሚዎችን የሚበረታታ፣ በአገሪቱ ልማት ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ ከሌሎች የልማት ዘርፎች ጋር የተሳሰረ፣ በምርምር የሚደገፍ አካሄደን የሚከተል የፖሊሲ አቅጣጫን መሰረት ያደረገ አካሄድ መከተል ይገባዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ማስተካከያ ማድረግ የሚገባው ከፌዴራል እስከ ክልል ዘርፉን የሚመሩትን ተቋማት መዋቅር ማስተካከል ያስፈልጋል። በአሁኑ ሰዓት በፌዴራል ደረጃ የደን ዘርፍ የተለያዩ ተቋማት የሚያካሂዱት ሆኗል። በሀላፊነት የሚጠየቅና እስከ ታች የሚፈጽምና የሚያስፈጽም ተቋም የለም። ይህንን ታሳቢ ያደረገ አደረጃጃት መዘርጋት ሌላው የዘርፉ ማስተካካያ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። እንደ ሌሎቹ ልማቶች የግሉ ዘርፍ ደፍሮ የማይገባ ከሆነ መንግስት የግሉ ዘርፍ የሚሳተፍበት አቅጣጫ ማስቀመጥ አለበት።
ሌላው መስተካከል የሚገባው የሚተከሉ ችግኞች ለምን ጠቀሜታ እንደሚውሉ በዓላማ መትከል ነው። አለበለዚያ ከእንክብካቤ እስከ ተጠቃሚነት ዘልቆ የተፈለገውን ዓላማ ማሳካት አያስችልም። በመሆኑም ችግኝ ተከላ ከዝግጅት ጀምሮ እስከ እንክብካቤ ድረስ በእቅድ የሚመራ መሆን አለበት።
ከዚህ ውጭ መታሰብ ያለበት አገር በቀል እጽዋቶች መልማት አለባቸው። አሁን ከሚተከሉት 90 በመቶውን የሚሸፍነው ባህር ዛፍ ሲሆን ባህር ዛፍ የራሱ የሆነ ጠቀሜታና ጉዳት አለው። በመሆኑም በሁሉም መንገድ ተጠቃሚ ለመሆኑና የአገሪቱን ስነ ምህዳር ለማልማት የአገር በቀል እጽዋቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ማስተካከያ ማድረግም ያስፈልጋል።
የምርምር ተቋማትን መገንባትና ዘርፉን በባለሙያዎች መምራትም ሌላው ትኩረት መስጠት የሚገባው ነው። በዘርፉ ላይ የምርምር ተቋማትን ማጠናከር ለእያንዳንዱ የዘርፉ ችግር መፍትሄ ማመንጨት ይቻላል። አካሄዱ የረጅምና የአጭር ጊዜ ውጤት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማምጣት ያስችላል። የምርምር እና አስፈጻሚ ተቋማት በባለሙያዎች መምራትና ማስፈጸም የዘርፍ ዋና አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የደን ልማት በሳይንስና በእውቅት የሚመራ ስለሆነ ማንኛውም ሰው ስለተመደበ ብቻ የሚሰራው አይደለም። በመሆኑም ዘርፉን በእውቀት መምራት ይገባል።
መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በበጎ የሚነሳ ቢሆንም በውጤት ላይ መመስረት አለበት። አሁን እየሄደበት ያለው የደን ልማት ውጤቱ እምብዛም በመሆኑ አካሄዱን ፈትሾ ማስተካካያ ማድረግ የነገ ሳይሆን የዛሬ ስራ ሊሆን ይገባል። ለመትከል ብቻም ሳይሆን ጽድቀቱም ተገቢውን ትኩረት ሊደረግበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2012
ዘላለም ግዛው