የጌዲዮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ጌዲዮ ጥር 16 ቀን በባህላዊው መንገድ አዲስ ዓመት በደማቅ ሁኔታ ያከብራል ማለታቸው የሚታወስ ነው። ይህንን ተከትሎም ትናንት የዳራሮ አዲስ ዓመት ባህላዊ የዘመን መለወጫ በዞኑ እጅግ ውብ በሆነ መንገድ ተከብሮ አልፏል። በተለይ የዘንድሮውን በአል ልዩ የሚያደርገው የጌዲዮ ዞን ሰላም በማግኘቱም ተፈናቃዮች ወደየመኖሪያቸው መመለሳቸው እንዲሁም የእለት ተዕለት ኑሯቸውን መምራት በመቻላቸው መሆኑን አስተዳዳሪውና ልዩ ልዩ የዞኑ ሃላፊዎች በእለቱ ገልፀዋል።
የዳራሮ አዲስ ዓመት ጌዴኦ ቄዬ መንደሩን ሠላም ላደረገ፣ አዝመራና ሰብሉን ከተምች ለጠበቀ፣ ህዝቡንና ምድሩን ከመዓትና እርግማን ለታደገ ማጌኖ ወይም ፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ቀን ነው። ለአባ ገዳ ጉማታ ወይም ስጦታ የሚሰናዳበት በጋራ የሚከበር የምስጋናና የስጦታ በዓል ጭምር ነው። ትናንትም በጌዲዮ ይህንኑ ነበር የተመለከትነው። ዳራሮ ከወትሮው በተለየ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ጌዴኦ ሽር ጉድ ማለት ከጀመረ ሰነባብታ ነበር። በዚህም የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ለብሄረሰቡና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ‹‹እንኳን ለጌዴኦ ብሔር ዘመን መለወጫ የዳራሮ በዓል በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን›› በማለት ልዩ የደስታ መግለጫውን አስተላልፏል።
በጌዴኦ ብሄር ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የምስጋና የስጦታ በዓል ዳራሮ ዘንድሮም በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በቋንቋና ባህል ሲንፖዚየም እንዲሁም በተለያዩ ዝግጅቶቸ ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ በዲላ ከተማ በድምቀት ነው እየተከበረ የሚገኘው። የዘንድሮ የዳራሮ በዓል ‹‹ዳራሮ ለሰላማችን አንድነታችንና ለብልጽግናችን›› በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተከበረው። ከምንም በላይ ባህላዊ እሴቶች ለዘላቂ ሰላምና አንድነት ያላቸው የላቀ አስተዋፆ ልዩ እንደሆነው ተስተውሎበታል።
በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ የዞኑ ተወላጆችና ወዳጆችንም ‹‹ኑ ዳራሮን ከእኛ ጋር አክብሩ›› በማለት የጌዴኦ ዞን አስተዳደር የአክብሮት ጥሪውን አስተላልፎ ነው ከወትሮው በተለየ መንገድ ብሄራዊ የበዓል አከባበር ቅርፅ አስይዞ እያከበረው የሚገኘው። ዞኑ መስካሪ ሳያስፈልገው የካበተ የተፈጥሮ ጥበቃ ባህል ባለቤት፤ የትከል ድንጋዮች፤ የተለያዩ ተፈጥሮዓዊና ታሪካዊ ቅርሶች መገኛ፤ ልዩ ጣእም ያለው የይርጋጨፌ ቡና መፍለቂያ እንደሆነ ፀሀይ የሞቀው ነው። ለዚህም ነው ጌዴኦ እንደ ባህሉ ‹‹አሻማ ኑ ዳራሮን አብረን በጋራ እናክበር›› በሚል ጥሪ አድርጎ ከመላው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር በጋራ እያከበረው የሚገኘው።
በተለይ በዘንድሮው ክብረ በዓል ልዩ ሁኔታዎችም ተፈጥረዋል። ዞኑ የዳራሮ በዓልን ምክንያት በማድረግ በሆቴልና ቱሪዝም፤ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፤ በማኑፋክቸርና እንዲሁም መሰል ዘርፎች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶችን ለመቀበል በሩን ክፍት ማድረጉን ይፋ አድርጓል። ጥር 16 በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ አይቀርም ብሎ እንግዶቹን በመልካም ስነምግባር እና በፍፁም ባህላዊ ስነስርዓት ተቀብሎ አስተናግዷል።
ጥቂት ስለብሄረሰቡ
ጌዴኦ በኢትዮጵያ ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኝ ብሔር ነው። የጌዴኦ ብሔረሰብ በዋናነት በጌዴኦ ዞን ውስጥ ባሉ ስድስት ወረዳዎች በስፋት የሚኖር ሲሆን ከዞኑ ውጪም በሲዳማ ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል በቦረና እና በጉጂ ዞኖች በሚገኙ አጎራባች አካባቢዎች ወይንም ወረዳዎች በብዛት እንደሚገኙ ይገመታል። የጌዴኦ ብሔረሰብ በዋናነት በሚገኝባቸው የከተማና የገጠር አካባቢዎች ሌሎች የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የሲዳማ፣ የወላይታ በተለይም ደግሞ በከተሞች የጉራጌ እና የስልጤ ብሔረሰብ አባላት ከብሔረሰቡ ጋር በስብጥር ይኖራሉ። በሰሜን ከሲዳማ በደቡብ በምስራቅ እና በምዕራብ ከኦሮሞ ብሔረሰብ ጋር ይዋሰናል።
የጌዴኦ ብሔረሰብ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ጌዴኦኛ ሲሆን በብሔረሰቡ አባላት ጌዴኡፋ በመባል ይጠራል። በኩታ ገጠም ወይም አጎራባች ሥፍራዎች ያሉ የብሔረሰቡ አባላት ከጌዴኦኛ በተጨማሪ ሲዳምኛን እና ኦሮሚኛን እንዲሁም በከተሞች ያሉ ደግሞ አማርኛን በሁለተኛ ደረጃ ይጠቀማሉ።
ባህላዊ አስተዳደር
የጌዴኦ ብሔረሰብ አባላት ባህላዊውን የገዳ ስርዓት ከመመስረታቸው በፊት በእማዊ ዘመን ይተዳደር እንደነበር ይነገራል። ይህ ዘመን የሴቶች ፈላጭ ቆራጭነት የነገሠበት፣ በወንዶች ላይ የሴቶች የበላይነት የሚንፀባረቅበት በመሆኑ “የአኮማኖዬ” ዘመን ተብሎ ይጠራ ነበር። «አኮማኖዬ» የቤተመንግስት የማዕረግ ስም ሲሆን በዚህ ሥርዓት አንድ ንግስት ስትሞት ሌላኛዋ ሥርወመንግስቱን እየተካች ለረጅም ዓመታት ሕዝቡን እንዳስተዳደሩ በአፈታሪክ ይነገርላቸዋል። በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበረው ይኸው የአኮማኖዬ የአስተዳደር ስርዓት በነበረው አምባገነናዊ ባህርይ በወንዶች ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደሩ እና ሊከናወን የማይቻል ትዕዛዝ በመስጠቱ በአመጽ ከስልጣን እንደተወገደ አባቶች ያስረዳሉ። በአኮማኖዬ እግር የተተካው ባህላዊ አስተዳደር «የጐሣሎ» አስተዳደር እንደነበር ተያይዞ ይነገራል።
ይህ የጐሣሎ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት በባህሪይው አሀዳዊና አምባገነናዊ በመሆኑ እንደቀድሞው የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት የነገሰበት ነበር። በዚህ የተነሣ የአንድ ጐሣሎ አስተዳደር የሥልጣን መቆያ ጊዜው የተወሰነ ስላልነበር በዕድሜ መግፋት ወይንም በጤና መታወክ ምክንያት ለሚቀጥለው እስከሚያስተላልፍ ድረስ ሕዝቡን በፈላጭ ቆራጭነት ይመራ እንደነበር የብሔረሰቡ የሀገር ሽማግሌዎችና ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። በጐሣሎው አምባገነናዊ አስተዳደር እጅግ የተማረሩ የብሔረሰቡ አባላት የጎሣሎን መሪ በሀይል በማስወገድ የጌዴኦ ባህላዊ የገዳ አስተዳደር ሥርዓት ለመመስረት በቅተዋል።
በወቅቱ በአዲስ መልኩ የተመሠረተው የገዳ ሥርዓት የተለያየ የስልጣን እርከን ባላቸው ክፍሎች የተደለደለ፣ ሁሉም የየራሳቸውን የሥራ ድርሻ ሊያከናውኑ በሚችሉበት መልክ የተዋቀረ በመሆኑ ሥርዓቱ በባህሪው በጣም ዲሞክራሲያዊ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይነገራል። ይህ የጌዴኦ የገዳ ሥርዓት ዘጠኝ አባላት የሚገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ ያለው ሲሆን አመራር የሚሰጠው በጠቅላላ ጉባኤው በብሔረሰቡ ቋንቋ በ«ያኣው» ነው። የያኣው አባላት ልዩ ልዩ የስልጣን ደረጃዎች ያሏቸው ሲሆን እነዚህ የስልጣን እርከኖች በተዋረድ “አባገዳ”፣ “ጃላባ”፣ “ሮጋ”፣ “ጃልቃባ”፣ እና “ሀይቻ” በመባል ይታወቃሉ።
የሁሉም የበላይ የሆነው አባገዳ የሥርዓቱ የበላይ መሪ እና ለሕዝቡ ሰላምን፣ ብልጽግናን፣ ፍቅርን ጤናን የሚለምን በመሆኑ በሕዝቡ ዘንድ ከማንኛውም ሀጢያትና መጥፎ ሥራ የነፃነው ተብሎ ይታመናል። ሁለተኛው የስልጣን እርከን “ጃላባ” የሚባለው የአባገዳው ምክትል ሲሆን ዋና ተግባሩ ከአባገዳው መልዕክት እየተቀበለ”ሮጋ”ዎች የሚያቀብልና ከሌሎችም አካላት መልዕክት በመቀበል ለአባገዳው የማድረስ ስልጣን የተሰጠው ነው። ሌሎች እርከኖች እንደዚሁ የየራሣቸው ሀላፊነትና የሥራ ድርሻ ያላቸው ሲሆን በዚህ መልኩ የተዋቀረው የጌዴኦ የገዳ ሥርዓት በየስምንት ዓመቱ የስልጣን ርክክብ እንዲደረግ ያዛል። ወቅቱ ሲደርስ ይህን የስልጣን ርክክብ የሚያከናውኑ “ራባ” ዎች ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ስልጣን ተረካቢው “ሉባ”፣ ስልጣን አስረካቢው ደግሞ “ዮባ” በመባል ይታወቃሉ።
የጌዴኦ ብሔረሰብ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ “ማገኖ” ብሎ በሚጠራው አንድ አምላክ እንደሚያምን፤ ይኸው የሰማይ አምላክ ርህሩህ ከሁሉ የበላይ በተለይም የሁሉ ነገር ፈጣሪ በመሆኑ ሕዝቡ ተገቢ የሆነ ክብርና መስዋዕትን ያቀርባል። በጌዴኦ ባህላዊ እምነት” ወዮ” የሚባሉና ስርዓተ መስዋዕቱን የሚፈፅሙ ከሰባቱም የጌዴኦ ጎሣዎች የተወጣጡ የሀይማኖት መሪዎች አሉ። እያንዳንዳቸው የተለያዩ መንፈሣዊ ተግባራትን የመፈፀም፣ በእምነቱ መሠረት የመመረቅ እና የመርገም የሥራ ድርሻ ሲኖራቸው ከማገኖ ዘንድ ለዝናብ ለመብረቅ ለውሃ ሙላት …ወዘተ የተሰጣቸው የተለያየ “ቃሮ” ወይንም መንፈሣዊ ኃይል እንዳላቸው ይታመናል።
የጋብቻ ስነ ስርዓት
በጌዴኦ ብሔረሰቡ ዘንድ ተግባራዊ የሚደረጉ የተለያዩ የጋብቻ ዓይነቶች ያሉ ሲሆን እነዚህም “ካጃ” (ህጋዊ ወይንም የስምምነት ጋብቻ)፣ ቡታ” /የጠለፋ ጋብቻ/፣ጃላ፣ ኪንቾ፣” አደባና” ፣ሀዋዴ፣ ዋራዬ ኦልታ፣”ሰባ” እና “ጊንባላ” በመባል ይታወቃሉ። ከነዚህ መካከል “ካጃ” እና “ሀዋዴ” የተሰኙት የጋብቻ ዓይነቶች በብሔረሰቡ ውስጥ በስፋት ተቀባይነት ያላቸው ሲሆን “ቡታ” እና “ዋራዬ ኦልታ” የተሰኙት በአፈፃፀማቸው በህገወጥነት ይፈረጃሉ። እንደነዚህ ያሉ የጋብቻ ዓይነቶች ሕገወጥ በሆነ መልኩ ቢፈፀሙም በመጨረሻ ውስጥ ለውስጥ በሚደረግ ስምምነት እና ባህላዊ አስተዳደርና እምነት ፍራቻ ሕጋዊነታቸው ይፀድቃል። “ሰባ” የሚባለው ጋብቻ በወንዱና በሴቷ ወላጆች ይሁንታ ወይንም መፈቃቀድ የሚከናወን ሲሆን “ሀዋዴ” የሚባለው ደግሞ በሌላ ሶስተኛ ሰው አግባቢነት ወንዱና ሴቷ ስምምነት ላይ የሚደርሱበት ከዚህም በኋላ ወደ ሴቷ ቤተሰቦች ሽማግሌ በመላክ የሚፈፀም የጋብቻ ዓይነት ነው።
ብሔረሰቡ በሕጋዊነት የተቀበላቸው የጋብቻ ዓይነቶች ከመፈፀማቸው በፊት ከጥንት ጀምሮ በዓይነት የሚተገበር የጥሎሽ ሥርዓት ይኖራል። በጥንታዊ የጋብቻ ሥርዓት ጥሎሽ ይሰጥ የነበረው ለአባትና እናት ሲሆን ከሚቀርቡ ስጦታዎች መካከል ለአባት ጠገራ፣ ድርብቡልኮ፣ ሂቶ (መቀነት) በዋናነት የሚሰጡ ሲሆን ለእናት ደግሞ ነጠላ ቡልኮ (ዱዳ) ይሰጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባህላዊ የጥሎሽ ስጦታ ወደ ገንዘብ ተለውጦ ከፍተኛ የገንዘብ ክፍያ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። የጥሎሽ ገንዘብ ከፍ ማለት በብሔረሰቡ ዘንድ ሕጋዊ ጋብቻን እያመነመነ በመምጣቱ በገዳ ሥርዓት ጠቅላላ ጉባኤው (ያኣ) ለአባት ቡልኮ መግዣ ስድሣ ብር፣ ለእናት ደግሞ ሃያ ብር በድምሩ ብር ሰማኒያ እንዲሰጥ ቢወሰንም አንዳንድ የብሔረሰቡ አባላት በገዳ ስርዓቱ የተወሰነውን የጥሎሽ መጠን በመተላለፍ ከብር 1 ሺህ ጀምሮ የጥሎሽ ገንዘብ ሲሰጡ ይስተዋላሉ።
በቤተሰብ ስምምነት በሚፈፀመው ሕጋዊ ጋብቻ ወቅት ተጋቢዎች በተጋቡ በሶስተኛው ቀን የሙሽራው ወላጆችና ቤተዘመድ በወንዱ ቤት ተሰባስበው የጉርሻ /ጊጫ/ ሥነ ሥርዓት በማከናወን ለሙሽሪት የተለያዩ ስጦታዎችን የሚሰጥበት ሥርዓት አለ። በዚህን ዕለት የሙሽራው ዘመድ አዝማድ በተገኘበት ሙሽራዎች (ወንዱ በስተቀኝ ሴቷ በስተግራ በመሆን) ከተሰብሳቢዎች ፊት ለፊት ቁጢጥ ብለው የሚከናወነውን የጉርሻ (የስጦታ) ሥነ ሥርዓት ለመፈፀም ይጠባበቃሉ። ጉርሻው /ስጦታው/ የሚጀመረው ከሙሽራው አባት ወይንም አባት ከሌለ ከተሰብሳቢዎች መካከል አንጋፋ ከሆነው ሰው ስለሆነ ሙሽሪት ቀደም ብላ በተዘጋጀችበት መሠረት ጉርሻውን (ስጦታውን) ለመቀበል ወደ አባት ወይንም አንጋፋው ሰው ተጠርታ ትሄዳለች።
በዚህ ሥነሥርዓት ወቅት ሙሽሪት ከወንዱ ቤተሰብ የምትፈልገውንና የምትጠብቀውን ስጦታ እስከምታገኝ ድረስ የሚሰጣትን ጉርሻ አትቀበልም። ስለዚህ በጥሪው መሠረት የልጁ አባት ወይንም አንጋፋው ቤተዘመድ አጉራሽ” ይህን ያህል ብር ሰጠሁሽ ይላታል።” እሷም” አይበቃኝም” ትላለች። በመቀጠል” ይህን ያህል መሬት ሰጠሁሽ” ይላል። አሁንም መልሳ “አይበቃኝም” ትላለች። ከዚያም “ይህንን ያህል ከብት ሰጠሁሽ” ሲላት አይበቃኝም አይበቃኝም “ እያለች ከቆየች በኋላ ከአጉራሹ (ከስጦታ ሰጪ) ዘንድ የምትፈልገውን ያህል ስጦታ ስታገኝ ጉርሻውን ትቀበላለች። በዚህ መልኩ የተሰበሰበውን ቤተዘመድ በሙሉ በማዳረስ ለጎጆ መውጫ የሚሆናትን በቂ ሀብትና ንብረት ታገኛለች።
አዲስ ዘመን ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም
ዳግም ከበደ