‹‹ከእኛው የወጣ ጠማማ ነው ጉድ የሠራን›› የሚለው የዛፎች አባባል የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ነባራዊ ሁኔታ ይገልጻል። ሌሎች የአፍሪካ አገራት ምን እንደሚሉ መደምደም ባይቻልም የኢትዮጵያ ምሁራንና ፖለቲከኞች የሚሉትን ግን ሁላችንም እናውቃለን። የፖለቲካም ሆነ የታሪክ ተንታኝ ነኝ የሚሉት ሁሉ ‹‹አይ የአፍሪካ ፖለቲካ!›› እያሉ ነው የሚሳለቁት። አፍሪካ የጦርነት አህጉር ብቻ መሆኗን ነው የሚናገሩት።
ከአፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ እንምጣ። የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችም ሆኑ ምሁራን አገሪቱን በግጭት የተመሰረተች አድርገው ነው የሚስሏት። በተለይም አሁን አሁን ደግሞ ብሶበታል። ‹‹የጋራ ታሪክ የለንም›› እስከማለት ተደርሷል። መቶ እና ሺህ ዓመታት ወደኋላ እየሄዱ ገዥዎች ዴሞክራሲያዊ አይደሉም እየተባለ ነው። ሺህ ዓመታት ወደኋላ በመሄድም ታሪክ መናቆሪያ እየሆነ ነው። ‹‹የጋራ ታሪክ የለንም›› የሚለው ሀሳብ አሁን ላይ የጋራ አገራዊ አንድነት እንዳይኖረን እያደረገ ነው። ለመሆኑ በዚህ ላይ የታሪክ ምሁራን ምን ይሉ ይሆን?
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ወርሃዊ የገለጻና ውይይት መድረክ አለው። ወር በገባ የመጨረሻው ሐሙስ የሚደረገው የአካዳሚው የገለጻና ውይይት መድረክ የታህሳስ ወር መጨረሻ ርዕሰ ጉዳዩ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ፤ ዕድገቱና ተግዳሮቱ›› የሚል ነበር። አቅራቢው ደግሞ የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ናቸው። በገለጻና ውይይቱ የተገኙ ታዳሚዎች የዕድሜ ባለጸጎች፣ ምሁራንና ወጣቶች ናቸው። ከመድረኩ ድባብ እንጀምር።
ቦታው አራት ኪሎ የሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ አዳራሽ ነው። በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የገለጻና ውይይት ፕሮግራም ከአንዴም ሁለቴ ታድሚያለሁ። አዳራሹ በጣም ሰፊ በመሆኑ ሞልቶ አይቸው አላውቅም። በዚያ ላይ ደግሞ እንዲህ አይነት የገለጻና ውይይት መድረኮች ብዙም ታዳሚ የላቸውም። በዚህ ቀን ያየሁት ግን ከወትሮው የተለየ ነበር። አዳራሹ ሰፊ ስለሆነ መቀመጫ ባይጠፋም እንደበፊቱ ግን ካሜራዎች ባዶ ወንበር አልቀረጹም።
ምክንያቱ ብዙ ነበር። አንደኛ በመገናኛ ብዙኃን (በተለይም በማህበራዊ ገጾች) ሰፊ የማስተዋዋቅ ሽፋን አግኝቷል። አቅራቢው ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ናቸው። የኢትዮጵያን ታሪክ የጻፉና የተመራመሩ ናቸው። ሦስተኛው ምክንያት ግን ርዕሰ ጉዳዩ ነው። ለዚህም ይመስላል ብዙ የቴሌቭዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች ነበሩ። አሁን ያለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የታሪክ ክርክር የበዛበት ነው። በሂደት ላይ ያለው የታሪክ ትምህርት ፍኖተ ካርታ ደግሞ አንዱ ጉዳይ ነው። የፍኖተ ካርታው ጉዳይ ግን ከታዳሚዎች ተደጋግሞ ቢነሳም ፕሮፌሰሩ በሂደት ላይ ስለሆነ ብዙም አላሉበትም። አሁን ወደ ገለጻና ውይይቱ እንግባ።
አንድ የዕድሜ ባለጸጋ ከተናገሩት ልጀምር። ‹‹የትኛዋ ሀገር ናት ግን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው በውይይት የተመሰረተች?›› ብለው ሲጀምሩ ነበር ታዳሚውን ያነቃቁት። ምክንያታቸው በመግቢያ ላይ ያልኩት ነው። ሁልጊዜም የሚባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ስምምነት የሌለበት ነው የሚል ነው። ከታሪክ እንደምናየው ግን የትኛዋም የዓለም አገር በስምምነት አልተመሰረተችም። ‹‹አፍሪካ የጦርነት አህጉር ናት›› ይባላል። ይሄን የሚሉት አውሮፓውያን ቢሆኑ እኮ ደግ ነበር፤ እንዲህ የሚሉት ግን ራሳቸው አፍሪካውያን ናቸው። እውነት ከአውሮፓውያን የበለጠ ጦርነትን የዋኘበት አህጉር አለ? ከአውሮፓውያን በበለጠ አገሮች እርስበርስ የተዋጋ አለ? የአውሮፓውያን አገራት እንዴት ነው የተመሰረቱት?
ልዩነቱ እነርሱ ቀድመው መሰልጠናቸው ነው። አሁን የአፍሪካ አገራትን መሳለቂያ እያደረጉ ነው። እነርሱ የጦርነት ታሪክ የሌላቸው ይመስል የጦርነት ምሳሌዎቻቸው የአፍሪካ አገራት ናቸው። ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣው ደግሞ ከአውሮፓና ከሌሎች አገራት ወራሪን ድል አድርጋ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ የኖረች አገርን፤ እኛ የጭቅጭቅና የክርክር አደረግናት፤ በዚህም ጉዟችን ወደፊት ሳይሆን ወደኋላ ሆነ። ለመሆኑ ስለታሪካችን ፕሮፌሰር ባህሩ ምን አሉ?
ዕድገቱ
የታሪክ አጻጻፍ በእነ ጀርመንና ፈረንሳይ አገራት ነው ያዳበረው። የትኛዋም የዓለም አገር በስምምነት እንዳልተመሰረተች ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴም ያሰምሩበታል። የሰው ልጅ ሥልጣኔ ደረጃ በደረጃ እያደገ ሲመጣ የአስተዳደር ሥርዓቶችም በዚያው ልክ ይቀያየራሉ። እንደየ አገራቱ ልማድና ባህሪም የአገራት አመሰራረት ታሪክ ተጽፏል። ቀጥሎም የአገራቱ ሁነት እየተሰነደ ይቀመጣል። ‹‹ታሪክ ማለት ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ የተከናወነ ሁነት ሰነድ ነው›› ይላሉ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ።
የታሪክ አጻጻፍ ዕድገት በኢትዮጵያ ከ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እየዳበረ እንደመጣ ያብራራሉ ፕሮፌሰር ባህሩ። የታሪክ ምንጭ የሆኑትን ደብዳቤዎች፣ ውሎች፣ ዜና መዋዕሎች እየተጠቀሙ ነው ታሪክ የተጻፈው። ለዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ መጻፍ ምክንያት የሆኑት ደግሞ እንደነ ተክለጻድቅ መኩሪያ ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች መምጣታቸው፣ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም መቋቋምና የታሪክ ትምህርት ክፍል መከፈት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። በሌላ በኩል እንደ ጀርመን፣ ፈረንሳይና አሜሪካ የመሳሰሉ የውጭ አገራት የኢትዮጵያን ታሪክ አጥንተዋል። በታሪክ ትምህርት ክፍልም ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ እየተሰጠ ነው። በዚህም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አውደ ጥናቶችና ምርምሮች እየተደረጉ ነው።
የዘመናዊ ታሪክ ጸሐፊዎች መምጣትና የታሪክ ትምህርት ክፍል መስፋፋት አመርቂ ውጤት አስገኝቷል ይላሉ የታሪክ ምሁሩ። ይሄውም፤ ታሪክ ከሰሜን ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ እንዲሄድ አድርጓል። ፖለቲካ ላይ ያተኩር የነበረው የታሪክ አጻጻፍ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችንም መጻፍ ጀምሯል። የጥንት ደብዳቤዎችን፣ ውሎችንና ዜና መዋዕልን ተጠቅሞ የጥንትና የመካከለኛው ዘመን ታሪክ ላይ ብቻ ከመንጠልጠል አልፎ ዘመናዊ የታሪክ አጻጻፍ ተጀምሯል። አሁን ላይ ያሉ ሁነቶች የሚሰነዱበት ብዙ ምቹ ሆኔታም ተፈጥሯል። ዓመታዊ ውይይቶችና ጥናቶች ይደረጋሉ።
ድክመቱ
የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም አገራት ላይ የታሪክ አጻጻፍ ዕድገት ገለጻ ያደረጉት ፕሮፌሰር ባህሩ ድክመቶችንም ተናግረዋል። ድክመቶቹ እንግዲህ ትኩረታቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ነው። በመድረኩ ላይ ብዙ ተወያዮች ሀሳብ አስተያየት የሰጡትም በድክመቶቹ ላይ ነው። ምክንያቱ ይታወቃል፤ ካለንበት ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ነው። ለማንኛውም ፕሮፌሰሩ ድክመት ብለው የጠቃቀሷቸው እነዚህ ናቸው።
የታሪክ መጽሐፎችና የጥናት ውጤቶች ላይ ሥርዐት አለመኖር። ይሄውም በየጊዜው ይጻፋሉ አይታተሙም። ጥናትና ምርምሮች ይደረጋሉ ታዳሚ ጋ አይደርሱም፤ የመደርደሪያ ማድመቂያ ሆነው ይቀራሉ።
ሌላው ችግር ደግሞ የፀሐፊዎች ዘመናዊ ታሪክ ላይ ብቻ መረባረባቸው ነው። ይሄ እንግዲህ ሁላችንም የምናየው ነው። በአንድ ጀንበር የሚጻፉ መጽሐፎችን በየአዟሪዎች እጅ እያየን ነው። ልክ እንደ ጋዜጣ ትናንት ማታ የነበረን ክስተት መጽሐፍ ሆኖ እያየነው ነው። መጽሐፍ ረጅም ጊዜ የሚወስድ፤ ብዙ ጥናትና ምርምር የሚደረግበት እንጂ የአንድ ሰሞን ጫጫታ ተሰብስቦ የሚጻፍበት አይደለም። ይህ አይነት ርብርብ ዓላማው ሁሉም የየራሱን ፖለቲካዊ እሳቤ ለማራመድ ነው። እነዚህ የአንድ ጀንበር መጽሐፎች ለዘመናት ተሰንደው ሲቀመጡ የተዛባ ታሪክ ሊያስተላልፉ ነው ማለት ነው። ከዘመናት በኋላ የሚኖረው ትውልድ የተዘበራረቀ ታሪክ ያገኛል ማለት ነው። አንደኛው መጽሐፍ ‹‹ነጭ ነው›› ያለውን ሌላኛው ‹‹ጥቁር ነው›› ይለዋል። አንዱ ‹‹አጭር ነው›› ያለውን ‹ሌላው ‹‹ረጅም ነው›› ይለዋል። እንዲህ አይነት መጽሐፎች ናቸው እንግዲህ እየተሰነዱ ያሉት።
የአርኪዮሎጂ ትምህርት ክፍል ለማቋቋም ረጅም ጊዜ መውሰዱም እንደ አንድ ችግር ተጠቅሷል። አርኪዮሎጂ የቆዩ የታሪክ ቅሪቶችን ለማወቅ የሚያስችል ዘመናዊ ዘዴ ነው። ቴክኖሎጂን በመጠቀም የድሮውን ዛሬ ለማወቅ ያስችላል።
በታሪክ አጻጻፍ ላይ የሚስተዋሉ ድክመቶችን ‹‹ውስጣዊ እና ውጫዊ›› ሲሉ በሁለት ይከፍሏቸዋል ፕሮፌሰር ባህሩ። ውስጣዊ ችግር የተባለው ራሳቸው የታሪክ ምሁራንን እና የታሪክ ትምህርት ክፍልን የሚመለከት ነው። እንደ ችግር ከተጠቀሱት አንዱ ቋንቋ ነው። ለብዙዎች ተደራሽ በሆነ ቋንቋ አልተጻፈም። በየዩኒቨርሲቲዎች እንደምናየው የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችም በእንግሊዘኛ ቋንቋ ነው። ሌላው ውስጣዊ ችግር የተባለው ተተኪዎችን የማፍራት ችግር መኖሩ ነው። አንጋፋ የታሪክ ምሁራንን የሚተኩ ወጣቶች አልተፈጠሩም። ይሄ አሁን ያሉትን ምሁራንና የታሪክ ትምህርት ክፍል ሰዎችን ይመለከታል።
ውጫዊ ድክመት የተባለው ከመንግስት ይጀምራል። ለሁሉም እንቅስቃሴዎች የመንግስት ደጋፍ የግድ ነው። በተደጋጋሚ እንደሚባለው መንግስት ደግሞ ያለፈን ታሪክ ሲወቅስና ሲያስወቅስ እንጂ ሲያበረታታ አይታይም። አንዱን ረጋጭ አንዱን ተረጋጭ እያደረገ እንዲናቆሩ እንጂ የጋራ አገርና ታሪክ እንዲኖራቸው አልሰራም። የብሄር ብሄረሰቦችን ቀን ሲያከብር እንደ ዓድዋ ያሉ የድል በዓላትን አዳክሟል። በነገራችን ላይ ዓድዋ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ ግን በድምቀት እየተከበረ ነው። ምናልባት ፕሮፌሰር ባህሩ ቀደም ባሉት ዓመታት የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን አለማግኘቱ ስላስገረማቸው ይሆናል። ቢሆንም ግን አሁንም የአገራዊ አንድነት ስሜት ያለው ዓድዋ የሚገባውን ያህል ተከብሯል ማለት ደግሞ አይቻልም።
ሌላው በድክመት የተጠቀሰው 70/30 የትምህርት ፖሊሲ ነው። ይሄውም 70 በመቶ ለተፈጥሮ ሳይንስና 30 በመቶ ለማህበራዊ ሳይንስ መሆኑ ነው። በነገራችን ላይ በቅርቡ በ‹‹ኢትዮጵያን ሄራልድ›› እና አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በወጣ ዜና ሊሻሻል እንደሆነ አንብበናል። ተፈጻሚነቱን ወደፊት የምናየው ይሁንና የችግሩን መኖር ግን መንግስትም እንዳመነበት ያሳያል። ከታች ያሉ ተማሪዎች ወደ ማህበራዊ ትምህርት ክፍሎች ትኩረት እንዳያደርጉ ስጋት የሚፈጥር ነው።
ሌላው ትኩረት ተሰጥቶት ሲያከራክር የነበረው ድክመት ደግሞ ‹‹ታሪክን የፖለቲካ መሳሪያ ማድረግ›› የሚለው ነው። ይሄ እንግዲህ ቀደም ሲል ያልነው አይነት ማለት ነው። የራስን ፖለቲካዊ አመለካከት ለማስረጽ የፈጠራ ታሪኮችን መጻፍ፣ የአክራሪ ፖለቲከኞች የቁርሾ ታሪክ መጻፍ ይጠቀሳሉ። ‹‹የጋራ ታሪክ የለንም›› በሚል የራስን አካባቢ ከሌላው መነጠል የተጠቀሱ ድክመቶች ናቸው።
ፕሮፌሰር ባህሩ የጠቀሱት አንድ ነገር አለ። ይሄውም አጼ ምኒልክ ጡት ቆርጠዋል በሚል የሚቀነቀነው ትርክት ሆን ተብሎ ለመከፋፈል ጥቅም ላይ የዋለ መሆኑን ነው። በሁለት መንገድ ነው ያዩት። የጀመሪያው ታሪኩ የፈጠራ ታሪክ መሆኑን። ሁለተኛው ደግሞ የዘመኑን ዓውድ የሳተ መሆኑን። ‹‹በዚያን ዘመን ማነው ያልቆረጠ? ማነው ያልተቆረጠ?›› ሲሉ ነው የገለጹት። አጼ ቴዎድሮስ እጅ ሲቆርጡ እንደነበርም ምሳሌ ጠቅሰዋል። ልብ በሉ! ነገሩ የፖለቲከኞች የመከፋፈል ሴራ መሆኑን የምናውቀው እዚህ ላይ ነው። ምንም እንኳን እርሳቸው አገራዊ ሰው ቢሆኑም አጼ ቴዎድሮስን በአሁኑ ዘመን እንያቸውና አማራ ናቸው። አጼ ቴዎድሮስ እጅ ሲቆርጡ የነበረው ግን የአማራን ነው። ይባስ ብሎም የራሳቸው አካባቢ የሆነውን ጎንደርን ነው። አጼ ቴዎድሮስ በቤተ ክርስቲያን ላይም ከፍተኛ ቁጥጥር አድርገው ነበር። ቄሶችን ሁሉ ሲያስወጡ ነበር። ዳሩ ግን የአማራን እጅ ቆረጡ ተብሎ አቧራ ተነስቶ አያውቅም። የአጼ ምኒልክ አገዛዝም ይሄው ነው። ግዛት ሲያስፋፉ ‹‹ልጅህን ለልጄ›› በሚል አይነት ሽምግልና አይደለም። ‹‹አንተ ትብስ አንተ ትብስ›› ተባብለው በመተሳሰብ አይደለም። የዘመኑ ባህሪ ነበርና በግጭትና በጦርነት ነው። ይሄንን ግን የዘመኑ ባህሪ ከማድረግ ይልቅ አንድን ብሄር ለይተው ያጠቁ የሚያስመስል ትርክት ቀረበ። የቀደም መሪዎችን አሉታዊ ጎን እየፈለግን በማራገብ ውለታቸው ግን ተረሳ። ይሄ ደግሞ በአገሩ የሚኮራና ታሪክ የሚሰራ ትውልድ እንዳይፈጠር ያደርጋል ማለት ነው።
የመፍትሔ አቅጣጫዎች
ፕሮፌሰር ባህሩ ለመፍትሔ ይሆኑ ዘንድ ‹‹አቅጣጫዎች›› ብለው ያስቀመጧቸው አሉ። አንደኛው መዛግብትን ማጠናከር ነው። ይሄውም በፈጠራ ታሪኮች ከመነታረክ ያድነናል። ሌላው ንቁ አንባቢ መፍጠር ነው። ንቁ አንባቢ ተፈጠረ ማለት አንዱን ከአንዱ ያነጻጽራል፣ ያገናዝባል። የፈጠራ ታሪክ ቢጻፍለት እንኳን ሰነዶችን እያጣቀሰ ያረጋግጣል። በወቅቱ የነበሩ ሁነቶች የተዘገቡበትንና የቀረቡ ሪፖርቶችን ያነባል።
ታሪክን ከፖለቲካ ጥገኝነት ማላቀቅ ሌላው መፍትሔ ተብሎ የተቀመጠ ነው። ይሄ ማለት ሚዛናዊ ሆኖ መጻፍ ማለት ነው። አሁን በምናየው ሁኔታ ይሄንን ነው ያጣነው። አማራው አማራ ውስጥ የተሰራ ጥፋት አይጽፍም፤ ኦሮሞው ኦሮሞ ውስጥ የተሰራ ጥፋት አይጽፍም፤ ትግሬው ትግራይ ውስጥ የተሰራ ጥፋት አይጽፍም። ሁሉም የሌላውን ጥፋት ሲያራግብ የራሱን ግን በመሸፋፈን ነው፤ ሌላው እንኳን ሲናገርበት ለምን ተነገረ በሚል ይደነፋል። ይሄ ነው የታሪክ መዛባት የሚፈጥረው። ከዚህም ሲብስ ደግሞ አንዱ በሌላው ላይ የፈጠራ ትርክት ያራግባል።
‹‹የሐያሲዎች መኖር›› ተብሎ የተጠቀሰው መፍትሔ በዚህ ወቅት በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ለመጽሐፍነት የማይበቁ መጽሐፎች እየታተሙ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በአንድ ወቅት ዘገባ ሰርቼ ነበር። መጽሃፎች በዚህ መልኩ መጻፍ አለባቸው ብሎ ብያኔ መስጠቱ የሀሳብ ነፃነትን ሊያፍን እንደሚችል ስጋት መኖሩን ከአንድ ደራሲ ጋር ባደረግኩት ቆይታ ለመገንዘብ ችያለሁ። በስመ የሀሳብ ነፃነት ግን ታሪክ እየተዛባ ነው። አንዱ ብድግ ብሎ ያለምንም ምንጭ የራሱን ስሜት ብቻ መጽሐፍ አድርጎ ያወጣል፤ የሚገርመው ደግሞ ብዙ ገዥና አንባቢ ያለው እንዲህ አይነቱ መጽሐፍ ነው። እንዲያውም ከፖለቲካ ንግድ አልፎ የቢዝነስ ንግድ ሆኗል። ምን ቢጽፍ እንደሚያዋጣው ያውቃል። ይሄ ሰው ብር ያስገኝለት እንጂ የአገሪቱ ታሪክ መዛባት ጉዳዩ አይደለም። ስለዚህ የጠነከረ ሐያሲ ያስፈልገናል።
ይሄ ወቅታዊ ብሽሽቅ ያልፋል፤ ታረክ ሆኖም ይሰነዳል። እኛ ያለፉ መሪዎችን ስንወቀስ ግን እኛም የሚያስወቅስ ሥራ እየሰራን ነው። የመጭው ዘመን ትውልድ ምን ይለን ይሆን ብለን እናስብ። በአገራችን ታሪክም እንኩራ። ከሰለጠኑ አገራት መማር ያለብን ነገር ይሄው ነው። እነርሱ እዚህ የደረሱ ወደኋላ ሳይሆን ወደፊት ስላሰቡ ነው። በአመሰራረት በልጠውን አይደለም። ለመሆኑ በስምምነት የተመሰረተች አገር አለች ይሆን ?
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 16/2012
ዋለልኝ አየለ